አጠቃላይ ጉባኤ
ኃያሉ፣ የስነ-ምግባር ዑደት የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


14:8

ኃያሉ፣ የስነ-ምግባር ዑደት የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት

የክርስቶስን ትምህርት በድግግሞሽ፣ በተደጋጋሚ እና ሆን ብላችሁ እንድትኖሩት እና በዚያ መንገድ ላይ ያሉትን ሌሎችንም እንድትረዱ እጋብዛችኋለሁ።

ከብዙ አመታት በፊት፣ ባለቤቴ ሩት፣ ልጃችን አሽሊ እና እኔ በሁዋዪ ስቴት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሌሎች ቱሪቶች እያደረጉት በነበረው የካያክ ቀዘፋ ሽርሽር ላይ ተቀላቀልን። ካያክ ወደ ውሃ ዝቅ ያለ፣ ቀዛፊው ወደ ፊት በመመልከት የሚቀመጥበት ታንኳ የሚመስል ጀልባ ነው፣ እናም ይህም ሁለት-ምላጭ ያለው መቅዘፊያ በመጠቀም ውሀውን ከወደፊት ወደኋላ በአንድ በኩል የሚስብና በሌላውም በኩል እንዲሁ በመድገም የሚደረግ ነው። እቅዱ ከኦዋሁ የባህር ዳርቻ ተነስቶ ወደ ሁለት ትናንሽ ደሴቶች መቅዘፍ እና መመለስ ነበር። ወጣት እያለሁ በተራራው ባሕሮች ዙሪያ ካያኮችን ቀዘፌ ስለነበር በራሴ ተማምኜ ነበር። ከመጠን ያለፈ በራስ መተማመን በፍጹም ጥሩ ውጤት አያመጣም፣ ያመጣል እንዴ?

አስጎብኛችን መመሪያ ሰጠን እንዲሁም የምንጠቀማቸውን የውቅያኖስ ካያኮች አሳየን። ከዚህ በፊት ቀዝፊያቸው ከማውቃቸው የተለዩ ነበሩ። በካያኩ ውስጡ ከመቀመጥ ይልቅ አናቱ ላይ መቀመጥ ነበረብኝ። ካያኩ ላይ ስወጣ የስህበት ማእከሉ እኔ አውቀው ከነበረው የበለጠ ነበር ስለዚህም በውሃ ውስጥ ብዙም ሚዛኔን አልጠበኩም ነበር።

ስንጀምር፣ ከሩት እና ከአሽሊ በፍጥነት እየቀዘፍኩኝ ነበር። ከትንሽ ጊዜ በኋላ፣ በጣም ጥያቸው ሄጄ ነበር። ድፍረት በተሞላበት ፍጥነቴ ኩራት ቢሠማኝም፣ መቅዘፌን አቆምኩኝና እንዲደርሱብኝ ጠበቅኳቸው። ወደ13 ሴንቲ ሜትር የሚሆን ትልቅ ማዕበል የካያኬን ጎን መታው እና ወደ ውሃው ውስጥ ገለበጠኝ። ካያኩን ወደ ላይ ከገለበጥኩትና እንደገና ከላይ ለመውጣት ስታገል በነበረበት ጊዜ፣ ሩት እና አሽሊ አልፈውኝ ሄዱ፣ ነገር ግን እጅግ በጣም ትንፋሽ አጥሮኝ ስለነበር መቅዘፍ መቀጠል አልቻልኩም ነበር። ትንፋሼ መለስ ሳይልልኝ ይህን 20 ሴንቲ ሜትር የሚሆን ሌላ ትልቅ የሆነ ማዕበል ካያኬን በድጋሜ ገለበጠው። ካያኩን ማስተካከል በቻልኩኝ ጊዜ፣ ትንፋሽ አጥሮኝ ስለነበር ወደ ካያኩ ተመልሼ መውጣት የምችል ስላልመሰለኝ ፈራሁ።

አስጎብኚው ሁኔታዬን በማየት ወደ እኔ በመቅዘፍ መጥቶ፣ ካያኬ ውስጥ ለመግባት እንዲቀለኝ ካያኬ እንዳይነቃነቅ አደረገው። በራሴ ለመቅዘፍ በጣም ትንፋሽ እንዳጠረኝ ባያ ጊዜ ካያኬን በገመድ በማሰር እኔን እየጎተተ መቅዘፍ ጀመረ። ወዲያውኑ ትንፋሼን በመስብሰብ በበቂ ሁኔታ በራሴ መቅዘፍ ጀመርኩኝ። ገመዱን ፈታው ከዚያም የመጀመሪያው ደሴት ላይ ካለምንም ተጨማሪ እርዳታ ደረስኩኝ። እዚያ ስደርስ ስለደከመኝ በአሸዋው ላይ ተዘረርኩኝ።

ቡድኑ እረፍት ከወሰደ በኋላ፣ አስጎብኚው በዝግታ እንዲህ አለ፣ “አቶ ረንለንድ፣ እንድርድሪቶን በመጠበቅ መቅዘፎን ከቀጠሉ፣ ደህና እንደሚሆኑ አስባለሁ።” ወደ ሁለተኛው ደሴት እና ወደ መነሻ ቦታው ስንቀዝፍ የሱን ምክር ተከተልኩኝ። ሁለቴ አስጎብኚው ከአጠገቤ እየቀዘፈ መልካም እያደረግኩኝ እንደሆንኩኝ ነገረኝ። ትልቅ ማዕበሎች ካያኬን በጎን በኩል ቢመቱትም እንኳን አልተገለበጥኩኝም ነበር።

ካያኩን ያለማቋረጥ በመቅዘፍ ከጎን የሚመቱኝን የማዕበሎች ተጽዕኖ በመቀነስ እንድርድሪቴን እና ወደፊት መሄዴን ቀጠልኩኝ። በመንፈሳዊ ህይወታችን ውስጥም ተመሳሳይ መርህ ተግባራዊ ይሆናል። ፍጥነታችንን ስንቀንስ በተለይም ስንቆም ለአደጋ ተጋላጭ እንሆናለን። ያለማቋረጥ ወደ አዳኙ “በመቅዘፍ” መንፈሳዊ እንድርድሪታችንን ከጠበቅን፣ የዘለአለም ህይወታችን በእርሱ ላይ ባለን እምነት ላይ ስለሚመሰረት ደህንነታችን ይበልጥ የተጠበቀ እና የበለጠ የማንሰጋ እንሆናለን።

“የክርስቶስ ትምህርትን በመላ ህይወታችን በተደጋጋሚ ስንቀበል” መንፈሳዊ እንድርድሪት ይፈጠራል። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩት ይህን ማድረግ “ሃያል የስነ-ምግባር ዑደትን” ይፈጥራል። በእርግጥ፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን፣ ንስሃ መግባት፣ በጥምቀት አማካኝነት ከጌታ ጋር የቃል ኪዳን ግንኙነት መፍጠር፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን መቀበል እና እስከ መጨረሻው መጽናት የሆኑት የክርስቶስ ትምህርት መሰረታዊ ነገሮች ለአንድ ጊዜ የሚከናወኑ ክስተቶች እንዲሆኑ የታሰቡ አይደሉም። በተለይም፣ “እስከ መጨረሻ መፅናት” በክርስቶስ ትምህርት ውስጥ የተነጠለ ደረጃ አይደለም፣ —ማለትም፣ የመጀመሪያዎቹን አራቱን ነገሮች ጨርሰን፣ ከአደጋ ለመጠበቅ አንድ ጥግ ይዘን ለመሞት መጠባበቅ አይደለም። አይደለም፣ እስከ መጨረሻ መጽናት ማለት ፕሬዚዳንት ኔልሰን የገለጹትን “ሃያል የስነ-ምግባር ዑደት” ለመፍጠር የክርስቶስ ትህምርትን ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን በድግግሞሽ እና በተደጋጋሚ ተግባራዊ ማድረግ ነው።

በድግግሞሽ ማለት የክርስቶስ ትህምርትን መሰረታዊ ነገሮች በመላ ህይወታችን ውስጥ ደግመን ደጋግመን እንለማመዳለን ማለት ነው። በተደጋጋሚ ማለት በእያንዳንዱ ድግግሞሽ ላይ እንገነባለን እናም እናሻሽላልን ማለት ነው። መሰረታዊ ነገሮችን ብንደጋግምም እንኳን ወደፊት በሌለው ዑደት ውስጥ እንሽከረከራለን ማለት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ በእያንዳንዱ ጊዜ በዑደቱ ውስጥ ስናልፍ ይበልጥ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንቀርባለን ማለት ነው።

እንድርድሪት ፍጥነትንም አቅጣጫንም ያካትታል። ካያኩን በተሳሳተ አቅጣጫ በሃይል ብቀዝፈው ኖሮ፣ ከፍተኛ ፍጥነትን እፈጥር ነበር ነገር ግን ወደ ተፈለገው መዳረሻ አልደርስም ነበር። በህይወት ውስጥ፣ ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ወደ እርሱ ለመምጣት ወደ አዳኙ ”መቅዘፍ” ይኖርብናል።

በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት በየቀኑ መመገብ ይኖርበታል። በየቀኑ ስንጸልይ፣ በየቀኑ ቅዱሳት መጽሐፍትን ስናነብ፣ የእግዚአብሔርን መልካምነት በየቀኑ በጥልቀት ስናስብ፣ በየቀኑ ንስሃ ስንገባ እና በየቀኑ የመንፈስ ቅዱስ መነሳሳቶችን ስንከተል ይገነባል። ሁሉንም ምግባችንን ለመመገብ እሁድን መጠበቅ እና ሳምንታዊ የአመጋገብ ድርሻን ማጨናነቅ ጤናማ እንዳልሆነ ሁሉ፣ ምስክርነታችንን የመመገብ ባህሪን በሳምንት አንድ ቀን ውስጥ መገደብ በመንፈሣዊ ጤናማ አይደለም።

ለግል ምስክርነቶቻችን ሃላፊነትን ስንወስድ፣ መንፈሳዊ እንድርድሪትን እናገኛለን እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ጠንካራ እምነትን ቀስ በቀስ እናዳብራለን ከዚያም የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የህይወት ዋና አላማ ይሆናል። በተመሳሳይ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ህጎች ስንጠብቅ እና ንስሃ ስንገባ እንድርድሪት ይገነባል። ንስሃ መግባት ያስደስታል ከጥፋቶቻችን እንድንማር ይፈቅድልናል፤ ለዘላለም የምናድገውም እንደዚህ ነው። ከካያካችን ውስጥ የምንገለበጥበት እና እራሳችንን በጥልቅ ውሃ ውስጥ የምናገኝበት ጊዜዎች ያለ ምንም ጥርጥር ይመጣሉ። ብዙ ጊዜ ብንወድቅም እንኳን በንስሃ አማካኝነት ወደ ላይ ተመልሰን መውጣት እና መቀጠል እንችላለን። አስፈላጊው ነገር ተስፋ አለመቁረጣችን ነው።

የክርስቶስ ትምህርት ቀጣዩ መሰረታዊ ነገር ጥምቀት ነው እሱም የውሃ ጥምቀትን እና ማረጋገጫ በመቀበል የሚገኘውን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ያካትታል። ጥምቀት አንድ ጊዜ የሚከናወን ክስተት ሲሆን ቅዱስ ቁርባንን ስንወስድ የጥምቀት ቃል ኪዳናችንን ደጋግመን እናድሳለን። ቅዱስ ቁርባን ጥምቀትን አይተካም፣ ነገር ግን በክርስቶስ ትምህርት ውስጥ የመጀመሪያ መሠረታዊ ነገሮች የሆኑትን እምነትን እና ንሰሃን መንፈስ ቅዱስን ከመቀበል ጋር ያገናኛል። ቅዱስ ቁርባንን በትጋት ስንካፈል፣ መንፈስ ቅዱስን ወደ ህይወታችን እንጋብዛለን፣ ልክ ስንጠመቅ እና ማረጋገጫን ስንቀበል እንዳደረግነው። በቅዱስ ቁርባን ጸሎቶች ውስጥ የተገለጸውን ቃል ኪዳን ስንጠብቅ፣ መንፈስ ቅዱስ አጋራችን ይሆናል።

መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን ውስጥ ታላቅ ተጽእኖ ሲያደርግ፣ ቀጣይነት ባለው መልኩ ክርስቶስ መሰል ባህርያትን እናዳብራለን። ልቦቻችን ይቀየራሉ። ክፉ ነገሮችን የማድረግ ዝንባሌያችን ይቀንሳል። “ጥሩ ነገርን ያለማቋረጥ ማድረግን ” ብቻ እስከምንፈልግ ድረስ ጥሩ ነገርን የማድረግ ፍላጎታችን ይጨምራል። እናም እስከ መጨረሻው ለመጽናት የሚያስፈልገንን የሰማይ ሃይል እናገኛለን። እምነታችን ጨምሯል፣ እናም ሃያሉን የስነ-ምግባር ዑደት ለመድገም ዝግጁ ነን።

ወደፊት የሚሄድ መንፈሳዊ እንድርድሪት በጌታ ቤት ውስጥ ተጨማሪ ቃል ኪዳኖችን ከእግዚአብሔር ጋር ለማድረግም ያነሳሳናል። ብዙ ቃል ኪዳኖች ወደ ክርስቶስ ያቀርቡናል እንዲሁም በበለጠ በጠነከረ መልኩ ከእርሱ ጋር ያገናኙናል። በእነዚህ ቃል ኪዳኖች አማካኝነት የእርሱን ሃይል በላቀ ሁኔታ እናገኛለን። ግልጽ ለማደረግ ያህል፣ የጥምቀት እና የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች በራሳቸው የኃይል ምንጭ አይደሉም። የኃይል ምንጭ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እና የሰማይ አባታችን ናቸው። ቃል ኪዳኖችን መፈጸም እና ማክበር በህይወታችን ውስጥ ኃይላቸው የሚተላለፍበት መተላለፊያ ይፈጥራሉ። በእነዚህ ቃል ኪዳኖቻችን መሰረት ስንኖር መጨረሻ ላይ የሰማይ አባት ያለውን ነገሮች ሁሉ ወራሾች እንሆናለን። የክርስቶስን ትምህርት በመኖር የሚፈጠረው እንድርድሪት መለኮታዊ ተፈጥሯችንን ወደ ዘላለማዊ እጣ ፈንታችን ለመቀየር የሚያስፈልገውን ሃይል መሥጠት ብቻ ሳይሆን፣ ተገቢ በሆነ መልኩ ሌሎችን እንድንረዳ ያበረታታናል።

በካያኩ ውስጥ እንዳለሁ ከተገለበጥኩኝ በኋላ አስጎብኚው እንዴት እንደረዳኝ አስቡ። ከሩቅ ሆኖ ፣ “አቶ ረንለንድ፣ በውሃው ውስጥ ምን እያደረጉ ነው?” የሚል የማያግዝ ጥያቄን አልጠየቀም። ወደ እኔ በመቅዘፍ፣ “አቶ ረንለንድ፣ ጠንካራ ቢሆኑ ኖሮ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ አይገቡም ነበር።” ሲልም አልገስጸኝም ወደ ላይ ለመውጣት እየጣርኩኝ በነበረበት ወቅትም ካያኬን መጎተት አልጀመረም። እንዲሁም በቡድኑ ፊት እርማት አልሰጠኝም ነበር። ከዚያ ይልቅ፣ እርዳታን በምፈልግበት ወቅት የሚያስፈልገኝን እርዳታ ሰጠኝ። ምክሩን ለመቀበል ዝግጁ በሆንኩበት ወቅት ምክር ሰጠኝ። እንዲሁም ሊያበረታታኝም ከሚጠበቅበት የበለጠ ነገርን አደረገ።

ሌሎችን ስናገለግል፣ የማይረዱ ጥያቄዎችን መጠየቅ ወይም የሚታወቅን ነገር መጠቆም የለብንም። ብዙ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ችግር ውስጥ መሆናቸውን ያውቃሉ። ፈራጆች መሆን የለብንም፣ ፍርዳችን አያግዝም ወይም ተቀባይነትን አያገኝም እንዲሁም ብዙ ጊዜ የተሳሳተ መረጃን የያዘ ነው።

በተለይም እራሳችንን በችግር ውስጥ ካሉ ሰዎች የበለጠ ጻድቅ አድርገን ከደመደምን፣ እራሳችንን ከሌሎች ጋር ማነፃፀር ከፍተኛ ስህተቶችን ወደመሥራት ሊመራን ይችላል ። እንዲህ ያለው ንፅፅርም፣ እራሳችሁ ያለተስፋ በ3 ሜትር ውሃ ውስጥ እየሰመጣችሁ እያላችሁ፣ ሌላ ሰው በ4 ሜትር ውሃ ውስጥ በመሥመጥ ላይ ያለውን ስታዩ፣ እርሱ ከባድ ሃጢያተኛ እንደሆነ አድርጋችሁ እየፈረዳችሁበት እና ስለራሳችሁ ጥሩ ስሜት እየተሠማችሁ ከሚሆነው ጋር አንድ አይነት ነው። ቢሆንም፣ ሁላችንም በራሳችን መንገድ እየታገልን ነን። ማንኛችንም ደህንነትን በጸጋው እንጂ በራሳችን አናገኝም ። በፍጹም አንችልም። ያዕቆብ በመጽሐፈ ሞርሞን ውስጥ፣ “ከእግዚአብሔር ጋር ከታረ[ቅን] በኋላ የም[ንድነው] በእግዚአብሔር ፀጋ ውስጥና በእርሱ በኩል ብቻ እንደሆነ [እናስታውስ]” በማለት አስተምሯል። ከፊሉን ብቻ ሳይሆን፣ የአዳኙ ማለቂያ የሌለው የሃጢያት ክፍያ ሁላችንም ያስፈልገናል።

በዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር መስተጋብር ስንፈጥር ርህራሄያችን፣ የሌሎችን ሥሜት መረዳታችን እና ፍቅራችን ሁሉ ያስፈልገናል። በችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ “በቃላችን እና በድርጊታችን ውስጥ የሚታየው የኢየሱስ ክርስቶስ ንጹህ ፍቅር ሊሰማቸው ይገባል።” ስናገለግል፣ ሌሎችን በተደጋጋሚ እናበረታታለን እንዲሁም እንረዳለን። አንዳንድ ሰዎች ባይቀበሉንም እንኳን፣ ሲፈቅዱ ማገልገላችንን እንቀጥላለን። አዳኙ እንዳስተማረው፣ “ለእነዚህ አይነት ለማገልገል መቀጠል አለባችሁ፤ ምክንያቱም አንድ ቀን እንደሚለወጡና ንሰሃ እንደሚገቡ እናም በልባቸው ሙሉ አላማ ወደ እኔ እንደሚመጡ አታውቁምና፣ እናም እፈውሳቸዋለሁ፤ እናንተም ደህንነትን ወደ እነርሱ ለማምጣት መሳሪያ ትሆናላችሁ።” የአዳኙ ስራ መፈወሥ ነው። የእኛ ስራ መውደድ ነው፣ ይኸውም ሌሎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሳቡ በሚረዳ መልኩ መውደድ እና ማገልገል ማለት ነው። ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ኃያል የስነ-ምግባር ዑደት ፍሬዎች ከሆኑት አንዱ ነው።

የክርስቶስን ትምህርት በድግግሞሽ፣ በተደጋጋሚ እና ሆን ብላችሁ እንድትኖሩት እና በዚያ መንገድ ላይ ያሉትን ሌሎችንም እንድትረዱ እጋብዛችኋለሁ። የክርስቶስ ትምህርት የሰማይ አባት እቅድ እምብርት እንደሆነ እመሰክራለው፣ ይህም የእርሱ ትምህርት ነውና። በኢየሱስ ክርስቶስ እና በሃጢያት ክፍያው እምነትን ስንለማመድ፣ በቃል ኪዳን መንገድ ላይ ወደፊት እንገፋለን እንዲሁም ሌሎች የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት እንነሳሳለን። የሰማይ አባትን መንግስት ወራሾች መሆን እንችላለን፣ ይህም የክርስቶስን ትምህርት በእምነት የመኖር መደምደሚያ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. 5 ኢንች ብቻ የሆነ።

  2. 8 ኢንች ብቻ የሆነ።

  3. በፊዚክስ፣ እንድርድሪት = ቁስ x ፍጥነት ስንቆም፣ ፍጥነት ዜሮ ነው። ስለሆነም፣ የቀድሞ እንድርድሪታችን ወይም ቁሳችን ምንም ይሁን ምን የቁስ እና የፍጥነት ውጤት ዜሮ ይሆናል።

  4. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “የመንፈሳዊ ፍጥነት ሃይል፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2022 (እ.አ.አ)፣ 98ን ይመልከቱ። ፕሬዚዳንት ኔልሰን ፣ “አወንታዊ መንፈሳዊ እንድርድሪት አሁን ከሚያስፈልገን ይልቅ መቼም ፈልገነው አናውቅም” ሲሉ መክረዋል። ያ “በፍርሃት እና ባለመረጋጋት ውስጥ ወደ ፊት” ለመሄድ ጥሩ መንገድ ነው። እንዲሁም 2 ኔፊ 2፥6–79፥23–24ን ይመልከቱ።

  5. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “አለምን ማሸነፍ እና እረፍትን ማግኘት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2022 (እ.አ.አ)፣ 97።

  6. ራስል ኤም. ኔልሰን “አለምን ማሸነፍ፣” 97

  7. “የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት” የሚለው ሃረግ ከ“የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል” ሃረግ ጋር ተመሳሳይ ነው። 2 ኔፊ 31፥2–213 ኔፊ 9፥14–2211፥7–4127፥1–21ን ይመልከቱ።

  8. በክርስቶስ ትምህርት ውስጥ ማንኛውንም መሰረታዊ ነገሮች መተው መንፈሳዊ እንድርድሪታችንን ያዘገየዋል ወይም ያቆመዋል። 2 ኔፊ 28፥30አልማ 12፥10–11ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፥31–3450፥24ን ይመልከቱ።

  9. በፊዚክስ፣ እንድርድሪት = ቁስ x ፍጥነት ፍጥነት የእንቅስቃሴ እና የአንድ እቃ የፍልሰት አቅጣጫ ፍጥነት ጥምረት ነው። ፍጥነት ቬክተር ነው እና በተፈጥሮ አቅጣጫዊ ነው።

  10. 2 ኔፊ 2፥6–79፥23–24ን ይመልከቱ።

  11. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “የመንፈሳዊ ፍጥነት ሃይል፣” 99ን ይመልከቱ።

  12. ቆላስያስ 2፥6–7 ይመልከቱ።

  13. ራስል ኤም. ኔልሰን “አለምን ማሸነፍ፣” 97 መንፈሳዊ እንድርድሪትን በመጠበቅ የምስክረነታችን ጥቅም ላይ በማተኮር፣ የምስክርነታችን ሃላፊነትን ስለመውሰድ የፕሬዝዳንት ኔልሰን ንግግር በፕሬዚዳንት ኤም. ረስል ባላርድም ተጠቅሷል [“በእምነት የእግር አሻራ ኢየሱስ ክርስቶስን ተከተሉት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2022 (እ.አ.አ)፣ 35] እና ሽማግሌ ክውንተን ኤል. ኩክ [“ለእግዚአብሔር እና ለስራው ታመኑ፣” ሊያሆና፣ ህዳር፣ 2022 (እ.አ.አ)፣ 120]።

  14. የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሙላት በዳግም መመለስ፥ የሁለት መቶ አመተኛው ለአለም የተላለፈ አዋጅ፣” የወንጌል ቤተመጽሐፍት፤ በረስልኤም. ኔልሰን፣ “A Plea to My Sisters [ለእህቶቼ የሚቀርብ ልመና]፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2015 (እ.አ.አ) 97ን ይመልከቱ።

  15. ሞዛያ 26፥30አልማ 34፥31ሞሮኒ 6፥8ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 58፥42ን ይመልከቱ።

  16. 2 ኔፊ 31፥13ን ይመልከቱ።

  17. ሽማግሌ ጄምስ ኢ. ታልሜጅ እንዲህ ጻፉ፣ “በወንጌል መርሆዎች እና ስነ-ስርዓቶች ጥናታችን ሂደት ውስጥ፣ በአራተኛው የእምነት አንቀጽ ውስጥ እንደተጠቀሰው፣ የጌታ እራት የቅዱስ ቁርባን ርእስ ትኩረትን ይስባል፣ አስፈላጊ የሆነውን ይህን ስነ-ስርአት መካፈል የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት ለሆኑት ሁሉ የእምነት፣ የንስሃ እና በውሃ እና በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቅ ስምምነትን ይጠይቃል።” (The Articles of Faith [የእምነት አንቀጾች] 12ተኛ እትም፣ [1924 (እ.አ.አ)]፣ 171)።

  18. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 59፥9ን፣ ይመልከቱ።

  19. ዳለን ኤች ኦክስ፣ “የክርስቶስ ሉይ ምስክሮች፣” ኤንዛይን፣ ሚያዝያ 2001 (እ.አ.አ)፣ 23፤ ሊያሆና፣ ሚያዚያ 2001 (እ.አ.አ)፣ 14ን ይመልከቱ።

  20. ሞዛያ 5፥2

  21. ለምሳሌ 2 ኔፊ 31፥2–213 ኔፊ 11፥23–3127፥13–21ሞሮኒ 4፥35፥26፥6ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፥77፣ 7959፥8–9ን ይመልከቱ።

  22. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 14፥784፥33–38ን ይመልከቱ።

  23. 3 ሜትር የሚሆን

  24. 4 ሜትር የሚሆን

  25. ኤፌሶን 2፥8–9ን ይመልከቱ።

  26. 2 ኔፊ 10፥24

  27. ፕሬዚዳንት ጀፍሪ አር. ሆላንድ እንዲህ አስተማሩ፣ “አንድ የተጎሳቆለ፣ የደከመ ዋናተኛ ወደ ባህር ዳርቻ ለመድረስ ጨክኖ ሲጥር፣ ሲጀመር ሊያጋጥሙት ያልበረባቸውን ጠንካራ ንፋሶችን እና ከባድ ማዕበሎችን ከታገለ በኋላ፣ የተሻለ ፍርድ ያገኘነው ወይም ምናልባት እድለኞች የነበርነው፣ ወደ ጎኑ በመቅዘፍ በመቅዘፊያችን ልንመታው እና ጭንቅላቱን ውሃ ውስጥ ልንዘፍቀው አይገባንም። ጀልባዎች ለዛ አይደለም የተሰሩት። ነገር ግን፣ አንድ አንዶቻችን ያንን እርስ በእርስ እናደርጋለን” (“ገመድ፣ ቀለበት እና የደለበ ጥጃ [A Robe, a Ring, and a Fatted Calf]” [የብሬገም ያንግ ዩኒቭርሲቲ መንፈሳዊ ስብሰባ፣ ጥር 31፣ 1984 (እ.አ.አ)፣ speeches.byu.edu]።

  28. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “አስታራቂዎች ይፈለጋሉ፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2023 (እ.አ.አ.)፣ 100።

  29. 3 ኔፊ 18፥32