ምዕራፍ ፳፮
ክርስቶስ ለኔፋውያን ያገለግላል—ኔፊ የህዝቡን መጥፋት አስቀድሞ አየ—ከምድር ውስጥ ይናገራሉ—አህዛብም ሀሰተኛ ቤተክርስቲያንን እናም ሚስጥራዊ ሴራዎችን ይሰራሉ—ጌታ በክህነት የሚደረገውን ተንኮል ይከለክላል። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም ልጆቼና የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳ በኋላ እራሱን ለእናንተ ያሳያል፤ ለእናንተ የሚናገራችሁ ቃልም ለእናንተ ህግ ይሆንላችኋል።
፪ እነሆም እላችኋለሁ፣ ብዙ ትውልድ እንደሚያልፉ፣ እናም በህዝቦቼ መካከል ታላቅ ጦርነትና ፀብ እንድሚኖር ተመልክቻለሁ።
፫ እናም መሲሁ ከመጣም በኋላ ስለውልደቱ፣ እንዲሁም ስለሞቱና ትንሳኤው፤ ለህዝቦቼ ምልክቶች ይሰጣል፤ እናም ለኃጢአተኞች ያ ቀን ታላቅና የሚያስፈራ ይሆናል፣ ምክንያቱም እነርሱ ይጠፋሉና፤ እናም የሚጠፉትም እነርሱ ነቢያትንና፣ ፃድቃንን፣ ስለአወጡአቸውና፣ በድንጋይ ስለወገሩአቸው፣ ስለገደሉአቸውም ነው። ስለዚህ የቅዱሳን ደም ጩኸት በእነርሱ ላይ ከምድር ወደ እግዚአብሔር ይወጣል።
፬ ስለዚህ፣ ኩራተኞችና፣ አመፅን የሚያደርጉ ሁሉ፣ የሚመጣው ቀንም ያቃጥላቸዋል፣ ይላል የሰራዊት ጌታ፣ እንደገለባ ይሆናሉና።
፭ እናም ነቢያትንና፣ ፃድቃንን፣ የሚገድሉ የምድር ጥልቅ ይውጧቸዋል፣ ይላል የሰራዊት ጌታ፤ እናም ተራሮች ይጫኗቸዋል፣ አውሎ ነፋስም ይወስዳቸዋል፣ ህንፃዎችም በላያቸው ላይ ይወድቃሉ፣ እናም ይሰባብሩአቸዋል እንዲሁም ወደ ዱቄትነት ይለውጡአቸዋል።
፮ እናም በነጎድጓድና፣ በመብረቅ፣ በመሬት መናወጥና፣ በሁሉም አይነት ጥፋት፣ ይቀጣሉ፣ የጌታም የቁጣ እሳት በእነርሱ ላይ ይነዳልና፣ እናም እነርሱ እንደገለባ ይሆናሉ፣ የሚመጣውም ቀን እነርሱን ይበላል፣ ይላል የሰራዊት ጌታ።
፯ አቤቱ በህዝቤ ጥፋትና ሞት የተነሳ፣ የነፍሴ ስቃይ! እኔ ኔፊ አይቼዋለሁ፣ እና ይህም በጌታ ፊት ሊያጠፋኝ ደርሷልና፤ ነገር ግን መንገድህ ጻድቅ ነው ብዬ ወደ አምላኬ መጮህ አለብኝ።
፰ ነገር ግን እነሆ፣ የስደት መከራ ቢደርስባቸውም የነቢያትን ቃል የሚሰሙ እናም የማያጠፏቸው፣ ነገር ግን የተሰጠውን ምልክት በመጠባበቅ በእምነት ፀንተው ክርስቶስን ወደ ፊት የሚመለከቱ ጻድቃኖች—እነሆ፣ እነርሱም የማይጠፉት ናቸው።
፱ ነገር ግን የፅድቅ ልጅ ይገለፅላቸዋል፤ ይፈውሳቸዋልም፣ እናም ሶስት ትውልድ እስከሚያልፍ ድረስ በእርሱ ሰላም ይኖራቸዋል፣ ከአራተኛው ትውልድም ብዙዎች በፅድቅ ያልፋሉ።
፲ እናም እነዚህ ነገሮች በሚያልፉበት ጊዜ ፈጣን ጥፋት በህዝቤ ላይ ይመጣል፤ ምክንያቱም በነፍሴ ስቃይ ቢኖርም፣ ይህን አይቼዋለሁ፤ ስለዚህ፣ እንደሚሆንም አውቃለሁ፤ እናም እራሳቸውን ያለ ዋጋ ይሸጣሉ፤ ለኩራታቸውና ለሞኝነታቸው ጥፋትን ዋጋ ይቀበላሉና፤ ለዲያብሎስ እጃቸውን ስለሰጡ፣ እናም ከብርሃን ይልቅ የጨለማን ስራ ስለመረጡ፣ ስለዚህ ወደ ሲኦል ሊወርዱ ይገባቸዋል።
፲፩ የጌታ መንፈስ ሁል ጊዜ ከሰው ጋር አይቆይም። እናም መንፈስ ከሰው ጋር መስራት ሲያቆም ፈጣን ጥፋት ይመጣል፣ እናም ይህ ነፍሴን ያሳዝነዋል።
፲፪ እናም እኔ አይሁዶችን ኢየሱስ፣ እንዲሁም ያው ክርስቶስ፣ መሆኑን ለማሳመን ስናገር፣ አህዛቦችም ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘለዓለማዊ አምላክ መሆኑን ሊረዱት ይገባቸዋል፤
፲፫ እናም እሱ በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ እራሱን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይገልፃል፤ አዎን፣ ለሁሉም ሀገሮች፣ ነገዶች፣ ቋንቋና ህዝብ እንደ እምነታቸው በሰው ልጆች መካከል አስደናቂ ተአምራትን፣ ምልክትን፣ እና ድንቅ ነገርን ይሰራል።
፲፬ ነገር ግን እነሆ፣ እኔ የመጨረሻ ቀናትን በተመለከተ ጌታ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች እነዚህን ነገሮች የሚያመጣባቸውን ቀናትም በተመለከተ እተነብይላችኋለሁ።
፲፭ ዘሮቼና የወንድሞቼ ዘሮች ባለማመን ከመነመኑና፣ በአህዛብ ከተመቱ በኋላ፤ አዎን፣ እግዚአብሔር በሰራዊቱ ከከበባቸውና፣ የግንብ ከለላ ካደረገላቸው በኋላ፣ ከሚዋጉአቸውም ከከለላቸው፤ እናም እስከሚጠፉም እንኳን፣ በትቢያም ዝቅ ካደረጋቸው በኋላ፣ ሆኖም የፃድቃን ቃል ይፃፋል፣ የታማኞች ፀሎትም ይሰማል፣ እናም ባለማመን የመነመኑትም ሁሉ አይረሱም።
፲፮ እነዚያ የሚጠፉት ከመሬት ይናገራሉ ቃላቸውም ዝቅ ብሎ ከአፈር ይወጣል፣ ድምጻቸውም ከመሬት እንደሚወጣ እንደመናፍስት ጠሪ ድምፅ ይሆናል፤ ጌታ እግዚአብሔር እነርሱን በተመለከተ፣ ከመሬት ውስጥ እንደሆኑ ሁሉ፣ ያንሾካሽክ ዘንድ ኃይልን ይሰጠዋል፤ ቃላታቸውም ከአፈር ወጥተው ያንሾካሽካሉ።
፲፯ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና—በእነርሱ መካከል ስለሚደረጉት ነገሮች ይፅፋሉ፣ እናም ተፅፈውም በመጽሐፍ ይታተማሉ፣ እናም ባለማመን የመነመኑት አያገኟቸውም፣ ምክንያቱም እነርሱ የእግዚአብሔርን ነገሮች ለማጥፋት ይሻሉና።
፲፰ ስለሆነም፣ እነዚያ የሚጠፉት በፍጥነት ጠፍተዋል፤ እናም የጨካኞችም ብዛታቸው እንደሚያልፍ ገለባ ይሆናል—አዎን፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ይህም ፈጥኖ፣ በድንገትም ይሆናል—
፲፱ እናም እንዲህ ይሆናል፣ ባለማመን የመነመኑት በአህዛብ እጅ ይመታሉ።
፳ እናም አህዛብ በአይናቸው ኩራት ምክንያት ተሰናክለዋል፣ እናም በእንቅፋታቸው ትልቅነት የተነሳ ተሰናክለዋል፣ በዚህም ብዙ ቤተክርስቲያንን ሰርተዋል፤ ይሁን እንጂ፣ ጥቅም ያገኙበትና የድሆችን ፊት ይፈጩ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ኃይልና ተአምራት ንቀዋል፣ እናም የራሳቸውን ጥበብና ትምህርት ለራሳቸው ሰብከዋል።
፳፩ እናም ምቀኝነት፣ ጭቅጭቅና ጥላቻ የሚያመጡ ብዙ ቤተክርስቲያኖች ተሰርተዋል።
፳፪ እናም እንደ ጥንቱም እንኳን ቢሆን፣ እንደ ዲያብሎስ ውህደት መሰረት አሁንም ደግሞ ሚስጥራዊ ሴራዎች አለ፣ የነዚህ ሁሉ ነገሮች መስራች እርሱ ነውና፤ አዎን፣ የግድያ እና የጨለማ ስራ መስራች፤ አዎን፣ ለዘለዓለም በጠንካራው ገመድ እስከሚያስራቸው፣ በተልባ ገመድ አንገታቸውን ይስባል።
፳፫ እነሆም፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ጌታ እግዚአብሔር በጨለማ አይሰራም እላችኋለሁ።
፳፬ እርሱም ለዓለም ጥቅም ካልሆነ በስተቀር ማንኛውንም አያደርግም፤ ምክንያቱም ሰዎችን ሁሉ ወደ እርሱ ይስብ ዘንድም ሕይወቱን አሳልፎ እስከመስጠት ዓለምን ይወዳል። ስለዚህ፣ ማንንም ደህንነቱን እንዳይካፈሉ አያዝም።
፳፭ እነሆ፣ ለሰው ከእኔ ራቁ ብሎ ተናግሯልን? እነሆ፣ እኔ እላችኋለሁ፣ አይደለም፤ ነገር ግን እርሱ እንዲህ ይላል—እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ ያለገንዘብም ያለዋጋም ወተትና ማር ግዙ።
፳፮ እነሆ፣ ከምኩራብ ወይም ከማምለኪያ ቤቶች ውጪ መውጣት እንዳለባቸው እርሱ አዟልን? እነሆ፣ እላችኋለሁ አላለም።
፳፯ ደህንነቱን እንዳይካፈሉ እርሱ አዝዟቸዋልን? እነሆ እኔ እላችኋለሁ—አላዘዛቸውም፤ ነገር ግን እርሱ ለሰዎች ሁሉ በነፃ ሰጥቶታል፤ እናም እርሱ ህዝቡን ሁሉንም ሰዎች ንስሀ ለመግባት እንዲያሳምኑአቸው አዟል።
፳፰ እነሆ፣ ጌታ ከቸርነቱ እንዳይካፈሉ ያዘዘው አለ? እነሆ እኔ እላችኋለሁ—የለም፤ ነገር ግን ሁሉም ሰው እንደሌላው ታድሏል፤ እናም ማንም አልተከለከለም።
፳፱ የክህነት ተንኮል እንዳይኖር አዟል፣ እነሆም፣ የክህነት ተንኮሎችም ጥቅምና ሙገሳን ከአለም ያገኙ ዘንድ ሰዎች የሚሰብኳቸውና እራሳቸውን በዓለም ውስጥ በብርሃን የሚያስቀምጡበት ነው፤ ነገር ግን እነርሱ የፅዮንን ደህንነት አይሹም።
፴ እነሆ፣ ጌታ ይህንን ነገር ይከለክላል፤ ስለዚህ፣ ጌታ እግዚአብሔር ሰው ሁሉ ለጋስ መሆን እንዳለበት ትዕዛዝን ሰጥቷል፣ ይህም ልግስና ፍቅር ነው። እናም ለጋስነት ከሌላቸው ከንቱ ናቸው። ስለሆነም፣ ልግስና ቢኖራቸው የፅዮን ሰራተኞች እንዲጠፉ አይፈቅዱም ነበር።
፴፩ ነገር ግን በፅዮን ያሉ ሰራተኞች ለፅዮን ይሰራሉ፤ ምክንያቱም ለገንዘብ ከሰሩ ይጠፋሉና።
፴፪ እናም ጌታ እግዚአብሔር እንደገና ሰዎች መግደል እንደሌለባቸው፤ መዋሸት እንደሌለባቸው፤ መስረቅ እንደሌለባቸው፤ የጌታን ስም በከንቱ መጥራት እንደሌለባቸው፤ እንዳይመቀኙ፤ ጥላቻ እንዳይኖራቸው፤ አንዱ ከሌላው እንዳይጣላ፤ ዝሙትን እንዳይፈፅሙ፤ እናም ከእነዚህ ውስጥ ማንኛውንም ማድረግ እንደሌለባቸው አዝዞአል፤ እነዚህን የሚፈፅሙ ይጠፋሉና።
፴፫ ከእነዚህ ማናቸውም ክፋቶች በጌታ አይመጡምና፤ እርሱ በሰው ልጆች መካከል መልካም የሆነውን ያደርጋልና፤ እናም ለሰዎች ልጆች ግልፅ ከሆነው በስተቀር ምንም አያደርግም፤ እርሱም ከቸርነቱ ይካፈሉ ዘንድ ሁሉም ወደ እርሱ እንዲመጡ ይጋብዛል፤ እናም ወደ እርሱ የሚመጡትን ማንንም፣ ጥቁርም ነጭም፣ ባሪያውንና ነፃውን፤ ሴትና ወንድን አይክድም፤ እምነተቢሶችንም ያስታውሳል፤ እናም አይሁድም ሆኑ አህዛብ፣ ሁሉም ለእግዚአብሔር አንድ ናቸው።