የተስፋ ድል
ተስፋ ሕያው ስጦታ ነው፣በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ስንጨምር የሚያድግ ስጦታ ነው።
በአለም ዙሪያ የምትገኙ ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ይህን “የአጠቃላይ ጉባኤ” ልዩ ጊዜ ስንጀምር የሰማይ አይኖች በእርግጠኝነት በእኛ ላይ ያተኩራሉ። በአገልጋዮቹ በኩል “የጌታን ድምፅ” እንሰማለን፤ የመንፈስ ቅዱስ “ምሪት፣ አቅጣጫ ማሳየት እና ማጽናናት” ይሰማናል፣ እናም እምነታችን ይጠነክራል።
ከሶስት አመታት በፊት፣ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን አጠቃላይ ጉባኤን በሚከተሉት ቃላት ጀምረው ነበር፦ “በልባችሁ ለሚመላለሱ ጥያቄዎች የሚመጣው ንጹህ መገለጥ ይህንን ጉባዔ አብዝቶ የሚሸልም እና የማይረሳ ያደርገዋል።” በእነዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ጌታ እንድትሠሙት የሚፈልገውን እንድትሠሙ የሚረዳችሁን የመንፈስ ቅዱስን አገልግሎት ገና እየለመናችሁ ካልሆናችሁ፣ አሁን እንድታደርጉት እጋብዛችኋለሁ። እባካችሁ ይህንን ጉባኤ በአገልጋዮቹ በኩል ከጌታ የሚመጡ መልዕክቶችን የመመገቢያ ጊዜ አድርጉት።”
ቅዱሳት መጻህፍት ሶስት ቃላትን ሃያል በሆነ መልኩ በአንድ ላይ ያገናኛሉ፡ እምነት፣ ተስፋ፣ ልግስና። የተስፋ ስጦታ በዋጋ ሊተመን የማይቻል የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።
ተስፋ የሚለው ቃል እኛ እንዲከናወኑ ስለምንፈልጋቸው ብዙ ነገሮች ጥቅም ላይ ይውላል። ለምሳሌ፣ “ባይዘንብ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ወይም “ቡድናችን እንደሚያሸንፍ ተስፋ አደርጋለሁ።” አላማዬ በኢየሱስ ክርስቶስ እና ዳግም በተመለሠው ወንጌል ላይ ያተኮረውን ቅዱስ እና ዘለአለማዊ ተስፋችንን እና “በራስ በመተማመን ስለምንጠባበቀው[ቃቸው] … ቃል ስለተገባላቸው የፅድቅ በረከቶች” መናገር ነው።
ለዘለአለም ህይወት ያለን ተስፋ
የዘለአለም ሕይወት ተስፋችን በክርስቶስ ጸጋ እና በራሳችን ምርጫዎች የተረጋገጠ ነው፣ ይህም ወደ ሰማያዊ ቤታችን እንድንመለስ እና ከሰማይ አባታችን፣ ከተወዳጅ ከልጁ፣ ከታማኝ ቤተሰባችን እና ውድ ጓደኞቻችን ጋር፣ እናም ጻድቃን ወንዶች እና ሴቶች ከሁሉም አህጉር እና በእያንዳንዱ ክፍለ ዘመን ካሉት ጋር በሰላም እና በደስታ ለዘለአለም እንድንኖር የሚያስችለን አስደናቂ በረከት ነው።
በምድር ላይ ስንፈተን እና ማለፋችን ሲረጋገጥ ደስታ እና ሀዘን እናገኛለን። ድላችን የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን በኃጢአታችን፣ በችግሮቻችን፣ በፈተናዎቻችን፣ በፍትሃዊ ባለመሆን እና በዚህ የሟች ህይወት ፈተናዎች ላይ ድል ስንቀዳጅ ነው።
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ስናጠናክር፣ ከትግላችን ባሻገር የዘለአለምን በረከቶች እና ተስፋዎች እንመለከታለን። ብሩህነቱ እንደሚጨምር ብርሃን፣ ተስፋ የጨለመውን ዓለም ያበራል፣ እናም የወደፊቱን የተከበረ ጊዜያችንን እናያለን።
ተስፋ የሚመጣው ከእግዚአብሔር ነው
ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ፣ የሰማይ አባታችን እና የተወደደው ልጁ ጻድቃንን ውድ በሆነው የተስፋ ስጦታ በጉጉት ባርከዋቸዋል።
አዳምና ሔዋን ከገነት ከወጡ በኋላ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተስፋ ቃል በመልአክ ተምረዋል። የተስፋ ስጦታ ሕይወታቸውን አበራላቸው። አዳምም ይህን በማለት አወጀ፣ “አይኖቼ ተከፍተዋልና፣ እና በዚህ ህይወትም ደስታ ይኖረኛል፣” ሔዋንም ይህንን ተናግራለች “የመዳ[ናች]ንን ደስታ፣ እናም ለታዛዡ ሁሉ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ዘለአለማዊ ህይወትን አናውቅም ነበር።”
ልክ መንፈስ ቅዱስ ለአዳም ተስፋን እንዳመጣ ሁሉ፣ የዘለአለም ህይወትን እውነታ በመግለጽ፣ የጌታ መንፈስ ሃይል ዛሬ ታማኞችን ያስረዳቸዋል።
አዳኝ አጽናኝን፣ መንፈስ ቅዱስን፣ “አለም [እንደሚሰጠው]” አይነት ሳይሆን፣ እምነትን እና ተስፋን እና ሰላምን የሚያመጣ አጋርን ይልክልናል።
“በዓለም ሳላችሁ” ይላል አዳኙ፣ “መከራ አለባችሁ፥ ነገር ግን አይዞአችሁ [የተስፋ ብርሃንን ያዙ]፤ አለምን አሸንፌዋለሁ።”
በአስቸጋሪ ጊዜ፣ በእምነት ጌታን መታመንን እንመርጣለን። በጸጥታም ጸሎት እንዲህ እንላለን፣ “የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ።” በየዋህነት በመፍቀዳችን ጌታ እንደሚያጸድቅልን ይሰማናል፣ እናም ጌታ በመረጠው ጊዜ የሚልክልንን ቃል የተገባለትን ሰላም እንጠብቃለን።
ሐዋርያውጳውሎስ እንዳስተማረው፣ “የተስፋ አምላክም … በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ ደስታንና ሰላምን ሁሉ [ይሞላባችኋል]፣” “በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፣” ”
የተስፋ ትምህርት
ነቢዩ ሞሮኒ በመከራ ጊዜ በክርስቶስ ላይ ተስፋ ስለመኖሩ ከተሞክሮው ያውቅ ነበር። አስጨናቂ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጿል።
በሚያስደንቅ ሁኔታ፣ በዚህ ጨለማ እና ብቸኝነት በተሞላበት ሰአት፣ ሞሮኒ የአባቱን የተስፋ ቃል መዝግቧል።
“ስለሆነም፣ አንድ ሰው እምነት ካለው ተስፋ ሊኖረው ይገባል፤ ያለ እምነት ምንም ዓይነት ተስፋ ሊኖር አይችልም።”
“እናም ተስፋ የምታደርጉበት ምንድን ነው? … በክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ እናም በትንሳኤው ኃይል ለዘለዓለም ህይወት እንዲኖራችሁ ተስፋ ይኑራችሁ።”
ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ተስፋ ሕያው ስጦታ ነው፣በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ስንጨምር የሚያድግ ስጦታ ነው። “ምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ … ነው።” በጸሎት፣ በቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች፣ ትእዛዛትን በመጠበቅ፣ ቅዱሳት መጻህፍትን እና የዘመናችን ነቢያትን ቃል ባለማቋረጥ በመመገብ፣ ቅዱስ ቁርባንን በመውሰድ፣ ሌሎችን በማገልገል፣ እና በየሳምንቱ ከቅዱሳን ጋር በማምለክ፣ የእምነታችንን ማስረጃ የሆነውን እንገነባለን።
የተስፋ ቤት
ክፋት እየጨመረ በሄደበት ጊዜ ተስፋችንን ለማጠናከር፣ ጌታ ነቢዩን በቤተመቅደሶቹ ምድርን እንዲሞላ አዘዘው።
ወደ ጌታ ቤት ስንገባ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ተስፋችንን ሲያረጋግጥልን ይሰማናል።
ቤተመቅደስ ስለ ባዶው መቃብር እና ከመጋረጃው ባሻገር ያለው ህይወት ለሁሉም እንደሚቀጥል ይመሰክራል።
ዘለአለማዊ የትዳር አጋር ለሌላቸው፣ ሁሉም ጻድቅ ሰው እያንዳንዱን ቃል የተገባለትን በረከት እንደሚቀበል ስርአቶቹ በኃይል ያረጋግጣሉ።
ወጣት ጥንዶች ለጊዜ ብቻ ሳይሆን ለዘለአለም ለመታተም በመሠዊያው ላይ ሲንበረከኩ ታላቅ ተስፋ አለ።
አሁን ያሉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ለትውልዶቻችን በተሰጡ ተስፋዎች ውስጥ ለእኛ ትልቅ ተስፋ አለ።
አምነን በጌታ ቤት ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን ቃል ኪዳን አጥብቀን ስንይዝ ምንም አይነት ህመም፣ ምንም በሽታ፣ ምንም ኢ-ፍትሃዊነት፣ ምንም መከራ፣ ተስፋችንን ሊያጨልምብን የሚችል ነገር የለም። የብርሃን ቤት፣ የተስፋ ቤት ነው።
ተስፋ በሚጣልበት ጊዜ
በክርስቶስ ላይ ተስፋ የሌላቸው ሰዎችን ሀዘን እና ተስፋ መቁረጥ ስናይ የሃዘን እንባዎችን እናፈስሳለን።
በቅርብ ጊዜ በክርስቶስ ላይ እምነት ነበራቸው ነገር ግን እምነታቸውን ለመተው የወሰኑ ባልና ሚስት ከሩቅ ሆኜ ተመልክቻለሁ። በአለም ውስጥ ስኬታማ ነበሩ፣ እና በበአዕምሮ እውቀታቸው እና እምነታቸውን በመካዳቸው ደስታ ይሰማቸው ነበር።
ገና ወጣት እና ብርቱ የነበረው ባልየው ድንገት ታሞ እስኪሞት ድረስ ሁሉም ነገር መልካም የሆነ መስለው ነበር። ልክ እንደ ፀሐይ ግርዶሽ የወልድን ብርሃን ዘግተው ነበር፣ ውጤቱም የተስፋ ግርዶሽ ሆነ። ሚስትየው፣ ባለማመንዋ፣ አሁን ግራ በመጋባት፣ በሚጎዳ ሁኔታ ባለመዘጋጀቷ፣ ልጆቿን ማጽናናት አልቻለችም። በድንገት ነገን ማየት እስኪያቅታት ድረስ ህይወቷ በፍጹም ሥርዓት እንደተቀናጀ የአዕምሮ እውቀቷ ነገራት። የእሷ ተስፋ መቁረጥ ጨለማ እና ግራ መጋባትን አመጣ።
ልብ በሚሰብር አደጋ ጊዜ የሚገኝ ተስፋ
የእሷን አሰቃቂ ተስፋ መቁረጥ በሃዘን ጊዜ ውስጥ በክርስቶስ ተስፋ ካላቸው ከሌላ ቤተሰብ ጋር ላነጻጽር።
ከሃያ አንድ አመት በፊት የወንድሜ ልጅ ቤን አንደርሰን እና የባለቤቱ ሮቢ አዲስ የተወለደው ልጅ ከአይዳሆ የእርሻ ማህበረሰባቸው ወደ ሶልት ሌክ ሲቲ ለህክምና በድንገተኛ በረራ ተወሠደ። ሆስፒታል ደረስኩ፣ እና ቤን በልጃቸው ልብ ላይ ያለውን ከባድና ለሕይወት አስጊ የሆኑ ችግሮችን ገለጸ። እጃችንን በትሬይ ትንሽ ጭንቅላት ላይ ጫንን። ጌታ በቀጣይ ህይወት ባረከው።
ትሬይ በህይወቱ የመጀመሪያ ሳምንት የልብ ቀዶ ጥገና ተደረገለት እና ተጨማሪ ቀዶ ጥገናዎች ተከተሉ። ዓመታት በገፉ ቁጥር ትሬይ የልብ መቀየር እንደሚያስፈልገው ግልጽ ሆነ። አካላዊ እንቅስቃሴው ውስን ቢሆንም እምነቱ እየሰፋ ሄደ። እንዲህ ሲል ጽፏል፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ የማመንን አስፈላጊነት እና የመዳንን እቅድ ምስክርነት ሁልጊዜ ስለማውቅ ለራሴ ሃዘን አይሰማኝም።
ትሬይ ይህን በደንብ የሚታወቀውን የፕሬዚዳንት ኔልሰንን ጥቅስ በስልኩ ውስጥ አስቀመጠ፦ “የሚሰማን ደስታ ካሉን የህይወታችን ሁኔታዎች ጋር ያለው ግንኘነት አነስተኛ ነው እንዲሁም በህይወታችን ትኩረት ከምንሰጠው ነገር ጋር ያላቸው ተዛምዶ ታላቅ ነው።”
ትሬይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሁልጊዜ የሙሉ ጊዜ ተልእኮ ለማገልገል በጉጉት እጠባበቃለሁ፣ ነገር ግን … ዶክተሮቼ ልብ ከተቀየረልኝ ቢያንስ ከአንድ አመት በኋላ እንጂ በሚስዮን እንዳገለግል አይፈቅዱልኝም። … በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነቴን እጥላለው።”
ትሬ ከዚህ ሴሚስተር ጀምሮ በቢዋዩ አካውንቲንግ ትምህርት ተቀባይነት በማግኘቱ ተደስቶ ነበር፣ ነገር ግን በሃምሌ መገባደጃ ላይ ለልብ መቀየር ወደ ሆስፒታል ለመምጣት የሚጠበቀውን የስልክ ጥሪ በተደወለለት ወቅት የበለጠ ተደስቶ ነበር።
“አንድ አመት፣” ትሬይ እንዲህ አለ፣ “እና በተልዕኮዬ ላይ እሆናለሁ።”
ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል ሲገባ ብዙ ጉጉቶች ነበሩ። ሆኖም ግን፣ በቀዶ ጥገናው ወቅት አስከፊ ችግሮች ነበሩ፣ እና ትሬ ወደ ንቃተ ህሊና አልተመለሰም።
እናቱ ሮቢ እንዲህ አለች፦ “አርብ በጣም ልብ የሚሰብር ቀን ነበር … በአእምሮአችን ለመረዳት ለመሞከር። … ሁሉንም ነገር ለመገንዘብ ለመሞከር ያለ እንቅልፍ ቆየሁ። … ቅዳሜ ግን በፍጹም የደስታ ስሜት ተነሳሁ። ሰላም ብቻ አልነበረም፣ ሁኔታውን መካድም አልነበረም። ለልጄ ደስታ ተሰማኝ እና እንደ እናቱ ደስታ ተሰማኝ። … ቤን ከእኔ በጣም ቀደም ብሎ ተነስቶ ነበር፣ እና በመጨረሻም የመናገር እድል ስናገኝ፣ ቤንም ከእንቅልፉ ሲነሳ በእርግጠኝነት ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶት ነበር።”
ቤን እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “እግዚአብሔር በቅዱስ መንፈሱ እንዳስተማረኝ ግልጽነት ወደ ነፍሴ መጣ። ከለሊቱ 10 ሰአት ላይ ከእንቅልፌ ነቃሁ እና በቃላት ሊገለጽ በማይችል ሰላም እና ደስታ ተሞላሁ። ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? … የትሬይ ማለፍ በጣም ያሳምማል፣ እና በጣም እናፍቀዋለሁ። ጌታ ግን ያለ መጽናናት አይተወንም። … አስደሳች በሆነው ዳግም መገናኘትን በጉጉት እጠባበቃለሁ።”
የተስፋ ቃል ኪዳን
ትሬይ በማስታወሻው ላይ ከፕሬዚዳንት ኔልሰን አጠቃላይ የጉባኤ ንግግር የተገኙትን ቃላት ጽፏል፦ “ልጆቻችሁ ሊዳን በማይቻል ህመም ሲሰቃዩ፣ ወይም ስራችሁን ስታጡ ወይም ባለቤታችሁ ሲከዳችሁ ደስታ የሚሰማ አይመስልም። ሆኖም በእርግጠኝነት አዳኝ የሚሰጠው ደስታ ይሄ ነው። የእሱ ደስታ የማያቋርጥ ነው፣ ይህም የእኛ ‘ችግሮቻን ለተወሰነች ጊዜ እንደሆነ’ [ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥7]እናም ይህም ለእኛው በጎነት እንደሚውል ያረጋግጥልናል።”
ወንድሞች እና እህቶች፣ የምትፈልጉት ሰላም እንደፈለጋችሁት በፍጥነት ላይመጣ ይችላል፣ ነገር ግን በጌታ ስትታመኑ፣ ሰላሙ እንደሚመጣ ቃል እገባላችኋለሁ።
በፍፁም የተስፋ ብርሃን እየገፋን ውድ እምነታችንን እንንከባከብ። ተስፋችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እመሰክራለሁ። በእርሱ በኩል፣ የጽድቅ ሕልማችን ሁሉ እውን ይሆናሉ። እርሱ የተስፋ እግዚአብሔር—የተስፋ ድል ነው። እሱ ህያው ነው እና ይወዳችኋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።