ለመብታችሁ ብቁ ሁኑ
የክህነት ስርዓቶች እና የቃል ኪዳኖች ተስፋ እንዴት የእግዚአብሔርን ኃይል በህይወታቸው ውስጥ እንድገባ እንደሚፈቅ ተማሩ።
በቅርቡ ባለቤቴ ግሬግ ከባድ ቀዶ ጥገና እና የኬሞቴራፒ ሕክምናን የሚጠይቅ ምርመራ አደረገ። ልክ እንደ ብዙዎቻችሁ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳጋጠማችሁ ሁሉ እኛም ወዲያውኑ የሰማይ እርዳታና የአምላክን ኃይል ለማግኘት መጸለይ ጀመርን። ከግሬግ ቀዶ ጥገና በኋላ በነበረው የሰንበት ቀን፣ ቅዱስ ቁርባን ወደ ሆስፒታል ክፍላችን ተላከልን።
በዚህ ጊዜ፣ ቅዱስ ቁርባንን የወሰድኩት እኔ ብቻ ነበርኩ። አንድ ቁራሽ ዳቦ። አንድ ስኒ ውሃ። በቤተክርስቲያን ውስጥ፣ አእምሮዬ ብዙውን ጊዜ የሚያተኩረው በቅዱስ ቁርባን አሰጣጥ ሥርዓት ላይ ነው—በመዘጋጀቱ፣ በበረከቱ እና በሚተላለፍበት ላይ። ነገር ግን በዚያ ከሰአት በኋላ፣ ያንን ቁራሽ ዳቦ እና ያንን ጽዋ ውሃ ስወስድ በቅዱስ ስርአት እራሱ እና በገባሁት የቃል ኪዳን የተስፋ ቃል እኔ ልጠቀመው ስለምችለው የእግዚአብሔር ሀይል ስጦታ አሰላስልኩ። ይህ ወቅት እኔ ከሰማይ ኃይል የሚያስፈልኝ ወቅት ነበር። በጥልቅ ሃዘን፣ ድካም እና እርግጠኛ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ፣ በጣም የምፈልገውን ከእርሱ ኃይል እንድወስድ ስለሚያስችለኝ ስለዚህ ስጦታ አሰብኩ። ቅዱስ ቁርባንን መካፈሌ ከጌታ መንፈስ ጋር ያለኝን ወዳጅነት ይጨምራል፤ በዚህም የመላእክትን አገልግሎት እና ለመቋቋም የሚያስችለውን የአዳኙን ጥንካሬ ጨምሮ የእግዚአብሔርን ኃይል ስጦታ የበለጠ ለማግኘት እንድችል ያደርጋል።
አስፈላጊው ነገር ስርዓቱን የሚያስፈፅመው ማነው የሚለው ብቻ ሣይሆን—ስርዓቱ እና የቃል ኪዳኖቹ የተስፋ ቃላት የሚከፍቱት ነገሮችም የእኔን ትኩረት ማግኘት እንደሚገባቸው ከዚህ በፊት በዚህን ያህል ግልጽነት የተገነዘብኩ አይመስለኝም። በክህነት ስርዓቶች እና በቃል ኪዳን ተስፋዎች እግዚአብሔር እንዲቀድሰን እና ከዚያም በኋላ በህይወታችን ድንቅ ስራዎችን እንዲሰራ ያስችለዋል። ነገር ግን ይህ የሚሆነው እንዴት ነው?
በመጀመሪያ፣ አንድ ሥርዓት የእግዚአብሔርን ኃይል በሕይወታችን እንዲገልጥ፣ ከእግዚአብሔር ልጅ በተሰጠ ሥልጣን መከናወን አለበት። የአሠጣጥ ስርዓቱ አስፈላጊ ነው። አብ የክህነት ስርአቶቹን ቁልፎች እና እነርሡን በበላይነት የመቆጣጠር ስልጣንን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጠው። በእሱ አመራር፣ በክህነቱ ስርአት፣ የእግዚአብሔር ወንድ ልጆች በእግዚአብሔር ወንድ ልጅ ምትክ እንዲቆሙ ተሹመዋል።
ሁለተኛ፣ የቃል ኪዳን ተስፋዎችን መግባት ብቻ አይደለም—ልንጠብቃቸው ይገባል። በብዙ የወንጌል ስርዓቶች፣ ከእግዚአብሔር ጋር ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን እንገባለን፤ እነዚያን ቃል ኪዳኖች ስንጠብቅ እንደሚባርከን ቃል ገብቷል። የእግዚአብሔርን ኃይል እንድንጠቀም የሚያስችለን የክህነት ሥርዓቶችን ከቃል ኪዳኑ ተስፋዎች ጋር በማጣመር መጠበቅ እንደሆነ ተገንዝበናልን?
የዛን ከሰዓት በኋላ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሴት ልጅ የሆንኩት እኔ፣ በክህነት ስርዓቶች አማካኝነት የእግዚአብሔርን ሀይል ስጦታ እንዴት ማግኘት እንደምችል እና የእግዚአብሔር ሀይል በውስጤ እንደሚሰራ በእውነት ተረድቼ ይሆን ስል አሰብኩ።
በ2019 (እ.አ.አ) የአዳኙን ኃይል በህይወታችን እንዴት መጠቀም እንደምንችል በማስተማር ለቤተክርስቲያኗ ሴቶች ትንቢታዊ ግብዣ ቀርቦ ነበረ። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን በሃርመኒ ፔንስልቬንያ ለኤማ ስሚዝ የተሰጠን ራዕይ በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 25ውስጥ እንድናጠና ጋብዘውናል። ያን ግብዣ መቀበል ህይወቴን ቀይሮታል።
ባለፈው ወር ሃርመኒን የመጎብኘት ያልተጠበቀ እድል አግኝቼ ነበረ። እዚያ፣ በሜፕል ዛፎች ስር፣ ክህነት ለጆሴፍ ስሚዝ እና ለኦሊቨር ካውድሪ ተመልሷል። የጆሴፍ እና የኤማ ቤት መግቢያ በር የሚገኘው በእነዚያ ዛፎች አቅራቢያ ነበር። በዚያ ቤት ውስጥ ካለው ምድጃ ማዶ አንድ መስኮት አለ። ከዚያ መስኮት አጠገብ ቆሜ፣ ኤማ በዛፎቹ ላይ አሻግራ ስትመለከት ምን አስባ ሊሆን እንደሚችል አሰብኩ።
በሐምሌ 1830 (እ.አ.አ) ውስጥ፣ ኤማ 26 ዓመቷ ነበር፤ እሷም በጣም ወጣት ነበረች። በትዳር ውስጥ ሦስት ዓመት ተኩል አሳልፋለች። የመጀመሪያ ወንድ ልጇን በሞት አጥታለች። የእሱ ትንሽ መቃብር ከቤቷ ቁልቁል በሚያስወርደውመንገድ ላይ ነው። በዚህ መስኮት ላይ ስቆም አዕምሮዋ ምን እያሰበ እንደነበረ መገመት ለእኔ ከባድ አልነበረም። በእርግጠኝነት ስለ ገንዘባቸው፣ ለደህንነታቸው ስለሚያሰጋው ስደት እና ስለወደፊት ህይወታቸው አሳስቧታል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ሥራ በዙሪያዋ በሁሉም ቦታ ነበር። በእቅዱ ውስጥ ያላት ቦታ፣ በመንግሥቱ ውስጥ ያላት ዓላማና በእግዚአብሔር ፊት ያላት አቅምስ አሳስቧት ይሆን?
ምናልባት ያሳሰባት ይመስለኛል።
ልክ ከመንገዱ ተሻግሮ፣ የእግዚአብሔር ክህነት ስልጣን እና ቁልፎች ስጦታ ወደ ምድር ተመልሷል። ይህ ወቅት ኤማ ከሰማይ ኃይል የሚያስፈልጋት ወቅት ነበር። በጥልቅ ሃዘን፣ ድካም፣ እና ጥርጣሬ ውስጥበነበረችበት በዚያ ወቅት፣ ኤማ ስለዚህ በጣም ስለሚያስፈልጋት፣ ከእርሱ ሀይልን ሊከፍት ስለሚችለው ስለእግዚአብሔር የክህነት ስጦታ፣ ተደንቃለችለች ብዬ እገምታለሁ።
ግን ኤማ በዚያ መስኮት ላይ ቆማ ከመደነቅ ያለፈ ነገርን አድርጋለች።
ነቢዩ ጆሴፍ በቁልፎች፣ ስለክህነት ክፍሎች፣ ስለስርዓቶች፣ እና በክህነት አገልግሎት እንዴት መርዳት እንደሚችል እየተማረ ሳለ፣ ጌታ ራሱ በነብዩ በኩል ለኤማ ራእይ ሰጣት። ይህ መገለጥ የተሠጠው ናቩ ለነበረችው የሴቶች መረዳጃ ማህበር ፕሬዘዳንት ኤማ ሳይሆን ሃርመኒ ለነበረችው የ26 አመቷ ኤማ ነበር። በራዕይ አማካኝነት፣ ኤማ እነዚያ የክህነት ስርዓቶች በህይወቷ ውስጥ ለመስራት ያላቸውን ችሎታ ስለሚያሳድግ ውስጣዊ መቀደስ እና የቃል ኪዳን ግንኙነት ተምራለች።
በመጀመሪያ፣ ጌታ ኤማ በእቅዱ ውስጥ ያላትን ቦታ፣ ማን እና የማን እንደነበረች—በመንግስቱ ውስጥ ሴት ልጅ እንደነበረች አስታውሷታል። እርሷም ቃል ኪዳኖቿን ከጠበቀች፣ የእግዚአብሔርን ኃይል የሚከፍቱ ሥርዓቶችን በሚያካትተው “በጥሩነት ጎዳና ላይ እንድትሄድ” ተጋብዛለች።
ሁለተኛ፣ በጥልቅ ሀዘንዋ ወቅት፣ ጌታ አላማ ሰጣት። ኤማ በዳግም መመለሡ የነበራት ሚና የተመልካችነት ሚና ብቻ አልነበረም፤ በመካሄድ ላይ ባለው ሥራ ውስጥ ወሳኝ ተሳታፊ ነበረች። “ቅዱሳት መጻህፍትን ለማብራራትና ቤተ ክርስቲያንን ለማበረታት” ተለይታለች። ጊዜዋ “ለመጻፍ እና ብዙ ለመማር የተሰጠ” ይሆናል። ኤማ፣ ቅዱሳን ለማምለክ እንዲያዘጋጁ የመርዳት ቅዱስ ሚና ተሰጥቷት ነበር ፤ መዝሙሮቻቸው ጌታ እንደ ጸሎት ይቀበላቸዋል እንዲሁም “በረከትን በራሳቸው ላይ በማድረግ ይመልስላቸዋል።”
በመጨረሻም፣ ጌታ ኤማን በዘለዓለማዊ ሕይወት ከፍ ከፍ እንድትል የሚያዘጋጃትን የውስጣዊ መቀደስ ሂደት ዘርዝሯል። ጌታም “ይህንን ባታደርጊ፣ እኔ ወዳለሁበት ስፍራ መምጣት አትችዪምና” ብሎ ገለፀላት።
ክፍል 25ን በጥንቃቄ ካነበብን ወደ አንድአስፈላጊ የሆነ የእድገት ደረጃ እየሄደች እንደነበረ እናውቃለን። ኤማ በመንግሥቱ ውስጥ ሴት ልጅ ከመሆን “የተመረጠች ሴት” ንግስት ወደ መሆን ትሸጋገራለች። የአሮናዊ እና የመልከ ጼዴቅ የክህነት ስርዓቶች ቃል ኪዳኗም ከመጠበቋ ጋር ተዳምሮ ከመንፈሱ እና ከመላእክት ጋር ያላትን ጓደኝነት ያሳድጋል፣ ህይወቷን በመለኮታዊ ምሪት እንድትመራ ሀይል ይሰጣታል። እግዚአብሔር በመለኮታዊ ኃይሉ ልቧን ይፈውሳል፣ አቅሟን ያሰፋል፣ እንዲሁም ወደፊት ልትሆን እንደምትችል ወደሚያውቀው ወደራሷ ማንነት ይለውጣታል። በመልከ ጼዴቅ ክህነት ስርዓትም፣ በሕይወቷ ውስጥ “የአምላክ ዓይነት ሀይል ይታያል” እንዲሁም ጌታ ከእሱ መረዳትን እንድታገኝ መጋረጃውን ይከፍላል። ይህ የእግዚአብሔር ኃይል በውስጣችን ሲሠራ ምን እንደሚመስል ያሳያል።
ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩት፦
በሃርሞኒ ውስጥ የተፈጸሙት ነገሮች ሁሉ በሕይወታችሁ ውስጥ ትልቅ አንደምታዎች አሏቸው፡፡ የክህነት ስልጣን መመለስ እና ጌታ ለኤማ የሰጠው ምክር እያንዳንዳችሁን መምራት እና መባረክ ይችላል። …
የእግዚአብሔርን ሀይል በህይወታችሁ ለማግኘት፣ ጌታ ኤማን እና እያንዳንዳችን እንድናደርግ ያዘዘንን ተመሳሳይ ነገሮች ማድረግን ይጠይቅብናል።”
በሃርመኒ በዚያ መስኮት በሁለቱም በኩል አስፈላጊ ነገሮች እየተከናወኑ ነበር፣ ጌታ ለጠራት ለተመረጠችው ሴት የተሰጠውን መገለጥ ጨምሮ—የእግዚአብሔር ሴት ልጅ ኤማ ስሚዝን የሚያበረታ፣ የሚያበረታታ እና የሚያስተምር ራዕይ ተሰጥታል።
የልጅ ልጃችን ኢዛቤል ስም እና በረከት በተሰጣት ጊዜ አባቷ ስለ ክህነት ግንዛቤ እንዲኖራት፣ ይኸውም ማደግ እንደምትቀጥል እና በህይወቷ ስለሚያስገኘው በረከት እንደምትማር፤ እና በመረዳት ማደጉን ስትቀጥል በክህነት ላይ ያላት እምነት እንደሚያድግ ባርኳታል።
ክህነትን ለመረዳት እና እነዚያን የክህነት ስርዓቶች እና የቃል ኪዳኖች ተስፋ እንዴት የእግዚአብሔርን ኃይል ለማግኘት እንደሚረዷት ለመማር ብዙ ጊዜ ትንሽ ልጅ እንደዚህ አይነት በረከት አልተለመደም። ነገር ግን ኤማን አስታወስኩኝ እና ለራሴ ለምን? ብዬ አሰብኩኝ። ይህች ትንሽ ሴት ልጅ በመንግስቱ ውስጥ የተመረጠች ሴት እና በመጨረሻም ንግሥት የመሆን አቅም አላት። በእሱ የክህነት ስርዓቶች እና የቃል ኪዳን ተስፋዎቿን በመጠበቋአማካካኝነት፣ ህይወት የሚያመጣውን ምንም አይነት ችግር እንድታሸንፍ እና እግዚአብሔር ልትሆን እንደምትችል የሚያውቀው ሴት እንድትሆን ለመርዳት የእግዚአብሔር ሀይል በእሷ በኩል ይሰራል። ይህ በመንግሥቱ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ልጃገረድ እንዲረዳው የምፈልገው ነገር ነው።
የክህነት ስርዓቶች እና የቃል ኪዳን ተስፋዎች የእግዚአብሄር ሃይል ወደ ህይወታችሁ በተሻለ ብቃት እንዲፈስ፣ በእናንተ ላይ እና በእናንተ በኩል ለመስራት፣ ወደ ሙሉ አላማችሁ እና እምቅ ችሎታችሁ ላይ እንድትደርሱ ሀይልን ለመስጠት እና ለማስታጠቅ እንደሚያስችሉ ተማሩ።
ስለአሮናዊ እና የመልከ ጼዴቅ የክህነት ስርዓቶች፣ ከእያንዳንዳቸው ጋር ስለምንገባው የቃል ኪዳን ተስፋዎች እና በእነዚያ ስርዓቶች አማካኝነት ስለምናገኘው የእግዚአብሔር ሃይል በጥንቃቄ ተማሩ እንዲሁም አሰላስሉ።
አስፈላጊ የሆነው ስርዓቱን የሚያከናውነው ማን ነው የሚለው ብቻ እንዳልሆነ አስታውሱ፤ ስርዓቱ እና የቃል ኪዳን ተስፋ የሚከፍተውም ትኩረታችሁ ያስፈልገዋል።
ከዳቦው እና ከውሃው መካፈል ችግርንለማሸነፍ ይረዳችሁ ዘንድ ሃይሉ በእናንተ ውስጥ እንደሚሰራ የሚያሳይ ሳምንታዊ አስታዋሽ ነው። የቅዱስ ክህነትን ልብስ መልበስ እናንተ እንድትሆኑ እንዲረዳችሁ በእናንተ ውስጥ የሚሰራው የእርሱ ኃይል ስጦታ የዕለት ተዕለት አስታዋሽ ነው።
ሁላችንም የእግዚአብሔርን ኃይል ስጦታን ለማግኘት እንችላለን።
ቅዱስ ቁርባንን በተቀበልን ቁጥርም።
ይህም የሰንበት ቀኔ የጎላ ድርጊት ነው። የቤተመቅደስ መግቢያ ፈቃዴን የምወደው ለዚህ ነው።
“በዚህም ስርዓት ውስጥ፣ የአምላክ አይነት ሀይል ይታያል።”
ስለዚህ ስጦታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እመሰክራለሁ፣ አሜን።