አጠቃላይ ጉባኤ
ብዙ ዓመት ባልሆነ ጊዜ ውስጥ
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


16:16

ብዙ ዓመት ባልሆነ ጊዜ ውስጥ

ታማኝ እና ታዛዥ ካልሆንን፣ እግዚአብሔር የሰጠንን የብልጽግና በረከት ወደሚሠርቅ የኩራት እርግማን ልንለውጠው እንችላለን።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ዛሬ በመድረክ ላይ ቆሜ፣ ከኮቪድ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሶስት ጊዜ ሲሞላ አይቻለሁ። እናንተ ለመማር የምትጓጉ የኢየሱስ ክርስቶስ ቆራጥ ደቀመዛሙርት ናችሁ። ስለታማኝነታችሁ አደንቃችኋለሁ። እንዲሁም እወዳችኋለሁ።

ዕዝራ ታፍት ቤንሰን ከሕዳር 1985 (እ.አ.አ) እስከ ግንቦት 1994 (እ.አ.አ) ድረሥ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል። ፕሬዚዳንት ቤንሰን የቤተክርስቲያኗ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ 33 ዓመቴ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩ ጊዜ 42 ዓመቴ ነበር። ትምህርቶቻቸው እና ምስክርነቶቻቸው ጥልቅ እና ኃይለኛ በሆኑ መንገዶች ተጽዕኖ አሳድረውብኛል።

ከፕሬዚዳንት ቤንሰን አገልግሎት ልዩ ገፅታዎች አንዱ በመፅሐፈ ሞርሞን ዓላማ እና አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ነበር። “መፅሐፈ ሞርሞን የሐይማኖታችን የማዕዘን ድንጋይ—የምስክርነታችን የማዕዘን ድንጋይ፣ የትምህርታችን የማዕዘን ድንጋይ እንዲሁም በጌታችን እና በአዳኛችን ምስክርነት ውስጥ የማዕዘን ድንጋይ ነው” በማለት በተደጋጋሚ ትኩረት ሰጥተዋል። በተጨማሪም፣ በዚህ በኋለኛው ቀን የኢየሱስ ክርስቶስ ኪዳን ውስጥ ስለሚገኘው የኩራት ኃጢአት የሚያወሱ ትምህርቶች እና ማስጠንቀቂያዎች ላይ በተደጋጋሚ ትኩረት አድርገዋል።

በፕሬዚዳንት ቤንሰን የተሰጠ አንድ የተለየ ትምህርት ታላቅ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል እንዲሁም በመፅሐፈ ሞርሞን ጥናቴ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን እንደቀጠለ ነው። እንዲህም ነበር ያሉት፦

“መፅሐፈ ሞርሞን… የተፃፈው ለእኛ ዘመን ነው። ኔፋውያን መጽሐፉ አልነበራቸውም፤ የጥንት ላማናውያንም እንዲሁ አልነበራቸውም። ለእኛ ታሥቦ የተዘጋጀ ነበር፡፡ ሞርሞን የጻፈው በኔፋውያን ስልጣኔ መጨረሻ ገደማ ነበር። ነገሮችን ሁሉ ከመጀመሪያው ጀምሮ በሚያየው በእግዚአብሔር አነሳሽነት፣ [ሞርሞን] ለእኛ እጅግ ጠቃሚ የሚሆኑትን ታሪኮች፣ ንግግሮች እና ድርጊቶች በመምረጥ ለክፍለ ዘመናት የተፃፉ መዝገቦችን አሳጥሮ ፃፈ።”

ፕሬዝዳንት ቤንሰን እንዲህ ቀጠሉ፦ “የመጽሐፈ ሞርሞን ዋና ዋና ፀሐፊዎች እያንዳንዳቸው ለወደፊቱ ትውልዶች እንደጻፉ መስክረዋል። … የእኛን ዘመን ተመልክተው ለእኛ እጅግ ትላቅ ዋጋ የሚኖራቸውን ነገሮች ከመረጡ፣ መጽሐፈ ሞርሞንን ማጥናት ያለብን በዚያ መንፈሥ አይደለምን? እራሳችንን በተደጋጋሚ እንዲህ ብለን መጠየቅ አለብን፣ ‘ሞርሞንን [ይህንን ታሪክ] በመዝገቡ ውስጥ … እንዲያካትት ጌታ ያነሳሳው ለምንድን ነው? [ከዚህ ምክር] በአሁኑ ጊዜ እንድኖር የሚረዳኝ ምን ትምህርት ማግኘት እችላለሁ?’ ብለን ራሳችንን ያለማቋረጥ መጠየቅ አለብን።”

የፕሬዚዳንት ቤንሰን ቃላት እንድንገነዘብ የሚረዱን መጽሐፈ ሞርሞን በዋነኛነት ስላለፈው የሚያትት ታሪካዊ መዝገብ አለመሆኑን ነው። ከዚያ ይልቅ ይህ የቅዱሣት መፃህፍት ቅፅ የወደፊቱን ጊዜ ይመለከታል እንዲሁም በዘመናችን ላሉ ሁኔታዎች እና ችግሮች የተዘጋጁ ጠቃሚ መርሆችን፣ ማስጠንቀቂያዎችን እና ትምህርቶችን ይዟል። ስለዚህ፣ መፅሐፈ ሞርሞን ስለወደፊታችን እና አሁን ስለምንኖርበት እንዲሁም ገና ስለምንኖርበት ጊዜ የሚናገር መጽሐፍ ነው።

በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ካለው የሔለማን መጽሐፍ ለእኛ ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን አሁን በምንመረምርበት ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ እርዳታን እናገኝ ዘንድ እጸልያለሁ።

ኔፋውያን እና ላማናውያን

የሔለማን እና የልጆቹ መዝገብ የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ሲጠባበቁ ስለነበሩት ሰዎች ይገልጻል። በቅዱሳት መፃሕፍት ዘገባ ውስጥ የተነገረው ግማሽ ክፍለ ዘመን የላማናውያንን መለወጥ እና ጽድቅ መሆን፣ እንዲሁም የኔፋውያንን ክፋት፣ ክህደት እና አስጸያፊ ድርጊቶች አጉልቶ ያሳያል።

በዚህ ጥንታዊ መዝገብ ውስጥ የሚገኙት በኔፋውያን እና በላማውያን መካከል ያሉት ተከታታይ ንጽጽሮች ዛሬ ለእኛ በጣም አስተማሪ ናቸው።

“አብዛኞቹ ላማናውያን ፃድቃኖች ሆነው በእምነታቸው ብርታት እንዲሁም ፅኑነት ፅድቃቸው ከኔፋውያን ይበልጥ ነበር።

“እናም አብዛኞቹ ላማናውያን ፃድቃኖች ሆነው በእምነታቸው ብርታት እንዲሁም ፅኑነት ፅድቃቸው ከኔፋውያን ይበልጥ ነበር።”

“እናም ላማናውያን በአምላካቸው እውቀት ማደግ፣ አዎን እነርሱ ስርዓቶችንና ትዕዛዛቱን መጠበቅ፣ እናም በፊቱም በእምነት እንዲሁም በቀጥታ መራመድ በጀመሩበት ጊዜ፣ ኔፋውያን እምነት አጥተው መመንመን እንዲሁም በክፋትና በእርኩሰት ማደግ መጀመራቸውን እንደዚህ እንመለከታለን።

“እናም በኃጢአታቸውና ልባቸውን በማጠጠራቸው የተነሳ የጌታ መንፈስ ከኔፋውያን መለየት እንደጀመረ እንመለከታለን።

“እናም ላማናውያን የማያስቸግሩና ቃሉን ለማመን ፈቃደኞች በመሆናቸው ጌታ ከመንፈሱ በላያቸው ላይ ማፍሰስ መጀመሩን ተመለከትን።”

ምናልባት በኔፋውያን ወደዚህ ክህደት መውደቅ ውስጥ በጣም አስደናቂው እና የሚያሣስብ ገጽታ ቢኖር “እነዚህ ሁሉ ክፋቶች በእነርሱ ላይ የመጡት በረጅም ጊዜ ውስጥ [አለመሆኑ] ነው።”

ኔፋውያን ከእግዚአብሔር ራቁ።

በአንድ ወቅት ጻድቅ የነበረው ሕዝብ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግትር እና ክፉ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ሰዎች አብዝቶ ባርኳቸው የነበረውን እግዚአብሔርን እንዴት እንደዚህ በፍጥነት ሊረሱት ቻሉ?

ዛሬ፣ የኔፋውያን አሉታዊ ምሣሌ ኃይለኛ እና ጥልቅ በሆነ መንገድ እኛን የሚያስተምር ነው።

“የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ተብለው ራሳቸውን በሚጠሩት ሠዎች ልብ ውስጥ ኩራት መግባት የጀመረው በምድሪቱ በነበራቸው እጅግ ታላቅ ሃብትና ብልፅግና ምክንያት ነበር።”

“ልባቸውን በሀብት እንዲሁም በዚህ በዓለም ከንቱ ነገሮች ላይ አድርገዋል” “እጅግ ሀብታም በመሆና[ቸው]፣ ከመልካሙም ባሻገር ከፍ እንዲያደርጋ[ቸው] ወደ ልባ[ቸው] እንዲገባ ባደረ[ጉት] ኩራት የተነሳ ዋይታ በእ[ነርሱ] ላይ ይመጣል!”

ጥንት የኖሩ ሠዎች ዛሬ ከመቃብር የሚያሠሙት ድምፆች ይህንን ዘለአለማዊ ትምህርት እንድንማር ይማፀኑናል፦ ብልጽግና፣ ንብረት እና ምቾት በጻድቃን ላይ እንኳን ሳይቀር ኩራትን በማምጣት መንፈሣዊ ጉዳት ወይንም መንፈሣዊ ሞትን ያስከትላሉ።

ኩራት ወደ ልባችን እንዲገባ መፍቀድ ቅዱሥ በሆነውም እንድንሳለቅ፣ በትንቢት መንፈሥ እና በራዕይ መንፈሥ እምነት እንድናጣ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በእግራችን ሥር እንድንረግጥ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንድንክድ፣ ነቢያትን እንድናባርር እና እንድንሣለቅባቸው፣ ከፍቃዳቸው የሚቃረን ነገር እንድንጠይቃቸው፣ አምላካችንን እንድንረሣ፣ እንዲሁም “[እኛን] የፈጠረው ጌታ አምላካ[ችን] [በእኛ] ላይ እንዲገዛና እንዲነግሥ [እንዳንፈልግ] ያደርገናል።”

ስለዚህ፣ ታማኝ እና ታዛዥ ካልሆንን፣ እግዚአብሔር የሰጠንን የብልጽግና በረከት ከዘለአለማዊ እውነቶች እና ወሳኝ ከሆኑ በመንፈሳዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ላይ ትኩረታችንን ገለል ወደሚያደርግ እና ትኩረታችንን ወደሚሠርቅ የኩራት እርግማን ልንለውጠው እንችላለን። ሁልጊዜ በኩራት ከተነሳሳ እና ከተጋነነ ለራስ ከሚሠጥ ከፍ ያለ ግምት፣ ከተሳሳተ ለራሴ ብቁ ነኝ ከሚል የግል ግምገማ እንዲሁም ሌሎችን ከማገልገል ይልቅ የራስን ከመፈለግ መጠንቀቅ አለብን።

በኩራት በመወጠር በራሳችን ላይ ስናተኩር፣ በመንፈሳዊ እንታወራለን እንዲሁም ብዙ፣ ከሁሉም የላቀ ወይም ምናልባትም በውስጣችን እና በዙሪያችን እየመጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ እናጣለን። ራሳችንን ብቻ የምንመለከት ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ “[ማተኮሪያ]” ልንመለከተውና ልናተኩርበት አንችልም።

እንዲህ ያለው መንፈሳዊ መታወር ደግሞ ከጽድቅ ጎዳና እንድንርቅ ሊያደርገን ወደተከለከለውም መንገድ ሊያስገባን ይችላል። “[በራሣችን] አመለካከት” በእውርነት ስንሄድ እና አፍራሽ መንገድን ስንከተል፣ በራሳችን ማስተዋል እየተደገፍን በጉልበታችን እየኮራን፣ በጥበባችን እየተመካን ነው።

ላማናዊቱ ሳሙኤል የኔፋውያኖችን ከእግዚአብሔር ፊታቸውን ማዞር እንዲህ ደመደመ፦ “የህይወት ዘመናችሁን በሙሉ ልታገኙት በማትችሉት ተመኝታችኋል፤ እናም ታላቅና ዘለዓለማዊው ራስ በሆነው ውስጥ ባለው የፅድቅ ተፈጥሮ ተቃራኒ በሆነው ነገር ክፋትን በመስራት ደስታን ተመኝታችኋል።”

ነቢዩ ሞርሞን እንዳስተዋለው፣ “እናም አብዛኞቹ ሰዎችም ከነኩራታቸው እንዲሁም ኃጢአታቸው [ሲቀሩ]፣ እናም ጥቂቶቹ ክፍሎች በእግዚአብሔር ፊት በጥንቃቄ [ይራመዳሉ]፣”

ኔፋውያን ወደ እግዚአብሔር ቀረቡ።

በሔለማን መጽሐፍ ውስጥ፣ እያደገ የመጣው የላማናውያን ጽድቅ ከኔፋውያን ፈጣን መንፈሳዊ ውድቀት ጋር ግልፅ ተቃርኖ ያሣያል።

ላማናውያን በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እና በነቢያት ትምህርቶች በማመን፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነታቸውን በመለማመድ፣ ለኃጢአታቸው ንስሐ በመግባት እና ታላቅ የልብ ለውጥ በማሳየት ወደ እግዚአብሔር ቀረቡ፣ እንዲሁም እውነትን ወደማወቅ መጡ።

“ስለዚህ፣ ይህንን እንደሚያውቁ የመጡ ሁሉ፣ በእምነታቸውና ነፃ በተደረጉበትም ነገር ፅኑ እናም የማይነቃነቁ መሆናቸውን በራሳችሁ አውቃችኋል።”

“እናም አብዛኞቹ [የላማናውያን] ክፍሎች በተወሰነላቸው ጎዳና እንደሚንቀሳቀሱ ልብ እንድትሉ እፈልጋለሁ፣ በእግዚአብሔርም ፊት በጥንቃቄ ይራመዳሉ፤ እናም በሙሴ ህግ መሰረትም ትዕዛዛቱንና ህግጋቱን እንዲሁም ፍርዱን ያከብራሉ። …

“… እንዲህ እላችኋለሁ፣ አብዛኞቹ ይህንን ያደርጋሉ፤ እናም የተቀሩት ወንድሞቻቸውን ወደ እውነት ያመጡ ዘንድም ያለማቋረጥ ትጋትን ያደርጋሉ።”

በዚህም ምክንያት፣ “በእምነታቸው ብርታት እንዲሁም ፅኑነት [የላማናውያን] ፅድቅ ከኔፋውያን ይበልጥ ነበር።”

ማስጠንቀቂያ እና ተስፋ

ሞሮኒ እንዲህ ብሏል፦ “እነሆ፣ ጌታ በዚያን ቀን እነዚህ ነገሮች በመካከላችሁ በሚመጡበት ጊዜ በቅርቡ መምጣት ስላለባቸው ታላቅ እና አስገራሚ ነገሮች ለእኔ አሳይቶኛል።

“እነሆ፣ እናንተ እዚህ እንዳላችሁ አድርጌ እናገራችኋለሁ፣ እናም እናንተ ግን የላችሁም። ነገር ግን እነሆ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተን አሳይቶኛል፣ እናም እኔም ስራችሁን አውቃለሁ።”

እባካችሁ መፅሐፈ ሞርሞን የወደፊቱን ጊዜ እንደሚመለከት እንዲሁም በዘመናችን ላሉ ሁኔታዎች እና ችግሮች የተዘጋጁ ለእኔ እና ለእናንተ የሚሆኑ ጠቃሚ መርሆችን፣ ማስጠንቀቂያዎችን እና ትምህርቶችን እንደያዘ አስታውሱ።

ክሕደት በሁለት ደረጃዎች ሊከሠት ይችላል፦ በተቋም ደረጃ እና በግለሠብ ደረጃ። በተቋም ደረጃ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በክሕደት ሣቢያ አትጠፋም ወይም ከምድር አትወሠድም።

ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ ዘገበ፦ “የእውነት ደንብ ተቋቋመ፣ ያልተቀደሰ ማንም እጅ የስራውን እድገት ማቆም አይችልም፤ … ነገር ግን የእግዚአብሔር እውነት በድፍረት፣ በግርማ፣ በገለልተኝነት፣ በሁሉም አህጉራት ዘልቆ እስኪገባ፣ ሁሉንም ድንበር እስኪጎበኝ፣ ሁሉንም አገራት እስኪጠርግ፣ እናም እያንዳንዷ ጆሮ እስክትሰማ፣ የእግዚአብሔርም ዓላማ እስኪሳካ እናም ታላቁ ያህዌ ሥራው ተጠናቋል እስኪል ድረስ ይጓዛል።”

በግለሠብ ደረጃ፣ እያንዳንዳችን “ከኩራት [እንጠበቅ]፣ አለበለዚያም እንደ ጥንቶቹ ኔፋውያን እንሆናለን።”

እናንተ ወይም እኔ የኩራትን ትዕቢት ለማስወገድ በበቂ ሁኔታ ጠንካራ እና ታማኝ እንደሆንን የምናምን ከሆነ ምናልባት አሁን በዚህ ገዳይ መንፈሳዊ በሽታ የተጠቃን እንደሆነ ልጠቁማችሁ። በቀላል አነጋገር፣ እናንተ ወይም እኔ በኩራት በሽታ ልንጠቃ እንደምንችል የማናምን ከሆነ፣ ለጥቃት የተጋለጥን እንዲሁም በመንፈሳዊ አደጋ ውስጥ ነን። ብዛት በሌላቸው ቀናት፣ ሣምንታት፣ ወራት ወይም ዓመታት የመንፈሳዊ ብኩርና መብታችንን ከምስር ወጥ ባነሰ ነገር ልናጣው እንችላለን።

ነገር ግን፣ እናንተ ወይም እኔ በኩራት ልንጠቃ እንደምንችል ካመንን፣ ትናንሽ እና ቀላል ነገሮችን፣ እንዲሁም “እንደ ልጅ ሁሉን የሚቀበል፣ የዋህ፣ ትሁት፣ ትዕግሥተኛ፣ በፍቅር የተሞላ … ጌታ ብቁ ነው ብሎ የሚያደርስበትን ሁሉንም ነገሮች ለመቀበል ፈቃደኛ” እንድንሆን የሚጠብቁንን እና የሚረዱንን ያለማቋረጥ እናደርጋለን። “ራሣቸውን ዝቅ እንዲያደርጉ ሳይገደዱ ራሳቸውን ዝቅ ያደረጉ የተባረኩ ናቸው።”

የፕሬዝዳንት ቤንሰንን ምክር ስንከተል እና ሞርሞን በሔለማን መጽሃፍ አሣጥሮ በፃፈው ውስጥ ያስቀመጣቸውን ዘገባዎች፣ ምክሮች እና ማስጠንቀቂያዎች ጌታ ለምን እንዲያካትት እንዳነሳሳው እራሳችንን ስንጠይቅ፣ እነዚህ ትምህርቶች ዛሬ ለግላችን እና ለቤተሰባችን ሕይወት የተለዩ ሁኔታዎች እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርጋቸው እንደምንገነዘብ ቃል እገባለሁ። ይህን በመንፈስ የተነሣሣ መዝገብ ስናጠና እና ስናሰላስል፣ ልንማራቸው የሚገቡንን ትምሕርቶች በሚያዩ ዓይኖች፣ በሚሰሙ ጆሮዎች፣ በተከፈቱ አዕምሮዎች እና በሚረዱ ልቦች መማር ያለብንን ትምህርቶች እንድንማር “ወደ ፈተና እንዳንገባ ከኩራት እንድንጠበቅ” ይባርኩናል።

ዘለዓለማዊ አባት እግዚአብሔር አባታችን እንደሆነ በደስታ ምስክርነቴን እሰጣለሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሡ ብቸኛ እና የተወደደ ልጁ ነው። አዳኛችን ነው። እንዲሁም፣ በጌታ የየዋህነት መንፈስ ስንራመድ፣ ኩራትን እንደምናስወግድ እና እንደምናሸንፍ እንዲሁም በእርሱ ሰላምን እንደምናገኝ እመሠክራለሁ። እንዲህ የምመሰክረውም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።