የእግዚአብሔር ወንዶች እና ሴት ልጆች
እኛ ሁላችንም ቃል በቃል የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆንን በእውነት እናምናለን፣ በዚያም ምክንያት እንደ እርሱ የመሆን አቅም አለን።
ዛሬ፣ እግዚአብሔር ከገለጠላቸው በጣም የከበሩ፣ የሚያስደስቱ እና ሃያል የሆኑ የወንጌል እውነቶች መካከል ስለአንዱ ለመናገር እወዳለሁ። በተመሳሳይ ሰዓትም፣ ይህ በሚገርም ሁኔታ በብዛት የምንተችበት አንድ ነገር ነው። ከጥቂት አመታት በፊት ያጋጠመኝ ነገር ለዚህ የወንጌል እውነት ያለኝን አድናቆት ጥልቅ አድርጎታል።
እንደ ቤተክርስቲያኗ ተወካይ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የሚደረጉ ጥምቀቶች ሁሉ ሥርዓታቸው በውኃ እንዲሁም በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እስከተደረገ ድረስ ትክክለኛ እንደሆኑ እውቅና እንደሚሰጡ በተነገረበት ሃይማኖታዊ ጉባኤ ላይ እንድገኝ ተጋብዤ ነበር። ከዚያም፣ ይህ ፖሊሲ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የሚደረጉ ጥምቀቶችን እንደማይመለከት ተብራራ።
ከጉባኤው በኋላ ማስታወቂያውን የሚመራው መሪ እንደዚህ የለየበትን ምክንያቶች በጥልቀት መረመርኩ። አስደናቂ እና እንድናስተውል ያደረገንን ውይይት አደረግን።
በአጭሩ፣ መለየት ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት ሌሎች የክርስቲያን እምነቶች ብዙውን ጊዜ ሥላሴ ብለው ስለሚጠሩት ስለአምላክ ካለን እምነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስረዳኝ። ጊዜ ወስዶ ስለ እሱ እምነት እና ቤተክርስቲያን ፖሊሲ ስላስረዳኝ ያለኝን አድናቆት ገለጽኩለት። በውይይታችን መጨረሻ ተቃቅፈንና ተሰነባበትን።
ኋላ ላይ ስለ ውይይታችን ሳሰላስል፣ ይህ ጓደኛዬ “ምስጢረ ሥላሴ” ብሎ የጠራውን ነገር የኋለኛው ቀን ቅዱሳን አይረዱም በማለት የተናገረው ነገር አሳሰበኝ። ስለምን እየተናገረ ነበር? ስለ እግዚአብሔር ተፈጥሮ ካለን መረዳት ጋር የተያያዘ ነበር። እግዚአብሔር አብ “ከፍ ከፍ ያለ” የከበረ “እንደ ሰው የሚዳሰስ ሥጋና የአጥንት አካል እዳለው፣ ወልድም እንዲሁ” እንደሆነ እናምናለን። በዚህም፣ ስለ እግዚአብሔር ተፈጥሮ ባወራን ቁጥር፣ በሆነ መንገድ ስለራሳችንም ተፈጥሮ እየተናገርን ነን።
ይህ እውነት የሆነው ሁላችንም “በመል[ኩ] እንደ በአምሳ[ሉ]” ስለተፈጠርን ብቻ ሳይሆን፣ ዘማሪው እንደዘገበው፣ እግዚአብሔር “አማልክት ናችሁ፤ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ” ስላለን ነው። ይህ ለእኛ በዳግም መመለስ እንደገና የተገኘ ውድ ትምህርት ነው። በአጭሩ የእኛ ሚስዮናውያን እንደ መጀመሪያው ትምህርት፣ አንደኛ አንቀጽ፣ መጀመሪያ መስመር ከሚያስተምሩት ጋር አንድ ነው፦“እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን ነው…[፤] እኛም ልጆቹ ነን።”
አሁን፣ “ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ነን ብለው ያምናሉ” ልትሉ ትችላላችሁ። አዎን፣ ያም እውነት ነው፣ ነገር ግን መረዳታቸው እኛ ከምንናገረው ጥልቅ ትርጉም አንደምታ በጥቂቱ የተለየ ሊሆን ይችላል። ለኋለኛው ቀን ቅዱሳን ይህ ትምህርት ዘይቤያዊ አይደለም። ይልቁንስ፣ እኛ በእርግጥ የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆንን በእውነት እናምናለን። እርሱ “[የመንፈሳችን] አባት” ነው፣ በዚህም ምክንያት ለአንዳንዶች የማይታሰብ ቢመስልም እርሱን የመምሰል አቅም አለን።
የመጀመሪያው ራዕይ የዳግም መመለስ በሮችን ከከፈተ አሁን ከ200 ዓመታት በላይ አልፏል። በጊዜው፣ ወጣቱ ጆሴፍ ስሚዝ የትኛውን ቤተክርስቲያን መቀላቀል እንዳለበት ለማወቅ ከሰማይ ምሪትን ፈለገ። በዚያ ቀን በተቀበለው መገለጥ፣ እንዲሁም በኋላ በተሰጡት መገለጦች አማካኝነት ነቢዩ ዮሴፍ ስለ እግዚአብሔር ተፈጥሮ እና እንደ ልጆቹ ከእርሱ ጋር ስላለን ግንኙነት እውቀትን አግኝቷል።
በዚህም ምክንያት፣ የሰማይ አባታችን ይህን ውድ ትምህርት ከመጀመሪያ ጀምሮ እንዳስተማረ ይበልጥ በግልፅ እንማራለን። ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት ከቅዱሳት መጻህፍት ቢያንስ ሁለት ጥቅሶችን እንድጠቅስ ፍቀዱልኝ።
በታላቅ ዋጋ ዕንቁ ውስጥ የተጠቀሰውን እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን መመሪያ ታስታውሱ ይሆናል።
“እግዚአብሔርም ለሙሴ እንዲህ አለው፥ እነሆ፣ እኔ ሁሉን የሚገዛ ጌታ እግዚአብሔር ነኝ፣ እናም መጨረሻ የሌለውም ስሜ ነው” የሚለውን እናነባለን። በሌላ አገላለጽ፣ ሙሴ፣ እኔ ማን እንደ ሆንኩ እንድታውቅ እፈልጋለሁ። ከዚያም “እናም እነሆ፣ አንተ ልጄ ነህ” ሲል ጨመረ። በኋላም፣ “ለአንተ አንድ ሥራ አለኝ፣ ሙሴ፣ ልጄ እናም አንተ በአንድያው ልጄ ምሳሌ ነህ” አለው። ከዚያም በመጨረሻ፣ “አሁንም እነሆ፣ ልጄ ሙሴ፣ይህን አንድ ነገር አሳይሃለሁ”በማለት ያበቃል።
እግዚአብሔር ለሙሴ “አንተ ልጄ ነህ” የሚለውን አንድ እውነት ቢያንስ ሦስት ጊዜ በመደጋገም ለሙሴ ለማስተማር የቆረጠ ይመስል ነበር። የሙሴን ስም ሲጠቅስ ልጁ መሆኑን ወዲያው ያክል ነበር።
ነገር ግን፣ ሙሴ ብቻውን ከቀረ በኋላ በእግዚአብሔር መገኘት ወስጥ ስላልነበረ ደካማ እንደሆነ ተሰማው። ያኔ ሰይጣን ሊፈትነው መጣ። ንድፉን በዚህ ለማየት ትችላላችሁን? እርሱ የተናገረው የመጀመሪያው ነገር፣ “የሰው ልጅ ሙሴ ሆይ ፣ ስገድልኝ” የሚል ነበር።
በዚህ አውድ፣ ሰይጣን እርሱ እንዲሰግድለት ያቀረበው ጥያቄ ትኩረቱን ለመስረቅ ብቻ ሊሆን ይችላል። ለሙሴ በዚያ የድካም ጊዜ ትልቅ ፈተና የነበረው ግራ መጋባት እና የእግዚአብሔር ልጅ ሳይሆን “የሰው ልጅ” እንደሆነ ማመን ነበር።
“እናም እንዲህ ሆነ፣ ሙሴም ሰይጣንን ተመለከተው እና አለ፤ ማን ነህ? እነሆ፣ እኔ በአንድያ ልጅ አምሳል የሆንኩት የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ።” ደስ የሚለው ነገር፣ ሙሴ ግራ አልተጋባም እንዲሁም ትኩረቱ እንዲወሰድ አልፈቀደም። በእውነት እሱ ማን እንደሆነ ተምሮ ነበር።
ቀጣዩ ዘገባ በማቴዎስ 4 ላይ ይገኛል። ሊቃውንት ይህንን፣ ጌታችን የተፈተነው ሦስት ጊዜ ብቻ ይመስል፣ ነገሩ እንደዚያ ባይሆንም፣ “ሦስቱ የኢየሱስ ፈተናዎች” ይሉታል።
የእነዚህን ፈተናዎች ትርጉም እና ይዘት ለማብራራት በመቶዎች የሚቆጠር ሊትር ቀለም ጥቅም ላይ ውሏል። እንደምናውቀው፣ ምዕራፉ ኢየሱስ ወደ ምድረ በዳ እንደሄደ እንዲሁም “አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጾመ በኋላ ተራበ” በማለት ይጀምራል።
የሰይጣን የመጀመሪያ ፈተና የጌታን ሥጋዊ ፍላጎት ከማርካት ጋር የተያያዘ እንደበረ ይታያል። “እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል” በማለት አዳኙን ፈተነው።
ሁለተኛው ፈተና እግዚአብሔርን ከመፈታተን ጋር የተያያዘ ነበር፥ “መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል … ተብሎ ተጽፎአልና ወደ ታች ራስህን ወርውር።”
በመጨረሻም፣ ሦስተኛው የሰይጣን ፈተና የዓለምን ምኞት እና ክብር ያመለክታል። ኢየሱስን “የአለምን መንግስታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው፣ [ሰይጣን] ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።”
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የሰይጣን የመጨረሻ ፈተና ከሦስቱ ልዩ ትንኮሳዎች ጋር ያለው ግንኙነት አነስተኛ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ተፈጥሮውን እንዲጠራጠር ከመፈተን ጋር ይበልጥ ተያያዥነት ያለው ነው። ቢያንስ ሁለት ጊዜ፣ ከመፈተኑ በፊት “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ”፣ በእውነት ካመንክ ይህን ወይም ያንን አድርግ የሚል ፈታኝ ክስ ከሰይጣን ቀርቧል።
እባካችሁ ኢየሱስ ሊጾምና ሊጸልይ ወደ ምድረ በዳ ከመግባቱ በፊት ወዲያው የሆነውን ነገር አስተውሉ፦ የክርስቶስን ጥምቀት ታሪክ እናገኛለን። ከውኃውም በወጣ ጊዜ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ነበር።
ግንኙነቱን ልብ እንላለን? የሚመሳሰል ነገር መለየት እንችላለን?
ስለ መለኮታዊ ተፈጥሮአችን እና እጣ ፈንታችን በተማርን ቁጥር፣ የፅድቅ ሁሉ ጠላት የሆነው እንድንጠራጠር መፈተኑ ምንም አያስደንቅም።
በእውነት ማን እንደሆንን በትክክል ብናውቅ ውሳኔያችን ምን ያህል የተለየ ይሆን ነበር።
በምንኖረው ሁከት እየበዛ ባለበት ፈታኝ ዓለም ውስጥ፣ የቤተክርስቲያን አባል ስንሆን እና ራእያችንን የሚያነሳ እና ወደ መለኮታዊነት የሚጋብዘንን ወንጌል ስንቀበል የተከበሩ ሰዎች ቢያንስ ሰብአዊ ክብራችንን ለማጉላት ይጥራሉ።
የኢየሱስ “የሰማይ አባታ[ችን] ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ” የሚለው ትእዛዝ ከኛ የሚጠብቀው ከፍ ያለ እንደሆነ እንዲሁም ስለ ዘላለማዊ ችሎታችን በግልጽ ያሳያል። አሁን፣ ይህ ሁሉ በአንድ ጀምበር የሚሆን አይደለም። በፕሬዚዳንት ጄፍሪ አር. ሆላንድ አባባል፣ “በስተመጨረሻ” ይሆናል። ነገር ግን የተስፋው ቃል “ወደ ክርስቶስ [ከመጣን]” “በእርሱ ፍጹማን [እንደምንሆን]” ነው። ያም ብዙ ስራ ያስፈልገዋል—ምንም ያልሆነ ስራ ሳይሆን፣ መለኮታዊ ስራ። የእርሱን ስራ!
አሁን፣ መልካሙ ዜና የሰማይ አባታችን በግልጽ “እነሆ፣ የሰውን ህያውነት እና ዘለአለማዊ ህይወት ማምጣት ስራዬ እና ክብሬ ይህ ነው”በማለት ማወጁ ነው።
የፕሬዚዳንት ኔልሰን፣ “ሰለስቲያል አስቡ”የሚለው ግብዣ ስለ መለኮታዊ ተፈጥሮአችን፣ ስለመነሻችን እና ወደ መድረሻችን ለመድረስ ስላለን አቅም አስደናቂ ማስታወሻ ያመለክታል። ሰለስቲያልን ማግኘት የምንችለው በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕት አማካኝነት ብቻ ነው።
ምናልባት ሰይጣን ኢየሱስን ከምድራዊ አገልግሎቱ መጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ በዚሁ ተመሳሳይ ፈተና ለማሳት የሞከረው ለዚህ ነው። ማቴዎስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ፣ “የሚያልፉትም፣ … የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ” እያሉ ይሰድቡት እንደነበር ጽፏል። እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና እርሱ አላዳመጣቸውም ይልቁንም ሰማያዊ በረከቶችን ሁሉ የምንቀበልበትን መንገድ አዘጋጀልን።
ለደስታችን ትልቅ ዋጋ እንደተከፈለ ሁሌም እናስታውስ።
ከሃዋርያው ጳውሎስ ጋር እንዲህ እመሰክራለሁ፥ “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።