አጠቃላይ ጉባኤ
የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ቀላል ነው
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


16:6

የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ቀላል ነው

የሰማይ አባት ልጆችን ቀላሉን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት የማስተማር ቅዱስ ስራ ምስክርነቴን እሰጣለው።

ሁሉንም የእግዚአብሔር ልጆች ለማሳዘን በሚፈልገው በአፍራሹ በሰይጣን የማያቋርጥ በሚመስሉ ኃይሎች እየተፈተኑ ያሉ የምንወዳቸው የቤተሰብ አባላት ሁላችንም አሉን። ብዙዎቻችን እንቅልፍ ያልተኛንባቸው ሌሊቶች አሉ። አደጋ ያንዣበበባቸውን ሰዎች ባለው መልካም ሃይል ሁሉ ለመክበብ ሞክረናል። ስለእነርሱ በፀሎት ተማፅነናል። ወድደናቸዋል። የቻልነውን ያህል ከሁሉም የተሻለ ዓርአያ ሆነናል።

በጥንት ጊዜ የነበረው ብልሁ ነቢይ አልማ ተመሳሳይ ፈተናዎች ገጥመውታል። የሚመራቸው እና የሚወዳቸው ሠዎች በጨካኝ ጠላት ተደጋጋሚ ጥቃት ይደርስባቸው ነበር፣ ሆኖም በክፋት በተሞላው ዓለም ውስጥ እያሉም ጻድቅ ልጆችን ለማሳደግ እየሞከሩ ነበር። አልማ ብቸኛ የድል ተስፋው አንዳንድ ጊዜ ዝቅ አድርገን ልንገምተው የምንችለው እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ ያን ያህል የማንጠቀምበት ኃይል እንደሆነ ተሰማው። እርሱም እግዚአብሔር እንዲረዳው ጸለየ።

አልማ፣ እግዚአብሔር እንዲረዳው፣ የሚመራቸው ሰዎች እና ጠላቶቹ ንስሐ መግባት ይጠበቅባቸው እንደነበር አወቀ። ስለዚህም፣ ለመዋጋት የተለየ አካሄድን መረጠ።

መፅሐፈ ሞርሞን በዚህ መንገድ ይገልፀዋል፦ “እናም አሁን፣ የቃሉ መሰበክ ህዝቡ ትክክለኛውን እንዲሰራ የሚመራ ታላቅ ዝንባሌ ስላለው—አዎን፣ ይህም ከጎራዴ፣ ወይም ከሚሆንባቸው ማንኛውም ነገር፣ የበለጠ በአዕምሮአቸው ላይ ውጤት ይኖረዋል—ስለዚህ አልማ ኃያል ውጤት ያለውን የእግዚአብሔር ቃል በጎነት መሞከራቸው አስፈላጊነቱን አሰበ።”

የእግዚአብሔር ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ እና በሐዋሪያቱ የተሠጠ ትምህርት ነው። አልማ፣ የትምህርት ቃላት ታላቅ ኃይል እንዳላቸው ያውቅ ነበር።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ውስጥ ጌታ የእርሡን የትምህርት መሠረት ገልጿል፦

“ስለሆነም፣ እነሆ፣ በሁሉም ስፍራ ሁሉም ሰዎች ንስሀ እንዲገቡ አዝዛለሁና። …

“ስለሆነም፣ እነሆ ጌታ አዳኛችሁ የስጋ ሞትን ሞተ፤ ስለዚህ ሰዎች ንስሀ ገብተው ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ የሰዎችን ሁሉ ህመም ተሰቃየ።

“እናም በንስሀ ብቻ ሰዎችን ሁሉ ወደ እርሱ ያመጣ ዘንድ፣ ከሞት ዳግም ተነሳ።”

“እናም ትሰግዳላችሁ እናም አባቴን በስሜ ታመልካላችሁ።

“… በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ንስሃ መግባት እና መጠመቅም አለባችሁ።”

“እንደምትቀበሉ በማመን በእምነት አባቴን በስሜ ጠይቁ እናም መንፈስ ቅዱስ ይኖራችኋል።”

“እናም፣ አሁን፣ ይህንን ከተቀበላችሁ በኋላ፣ በሁሉም ነገሮች ትእዛዛቴን መጠበቅ አለባችሁ።”

“የክርስቶስ[ን] ስም በላያችሁ ላይ ውሰዱ እናም እውነትን በቅንነት ተናገሩ።

“እናም ስሜ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ ንስሀ የሚገቡና የሚጠመቁ እናም እስከመጨረሻው ድረስ የሚጸኑ፣ እንዲሁ ይድናሉ።”

በእነዚያ ጥቂት ምንባቦች ውስጥ፣ አዳኙ የእርሱን ትምህርት እንዴት ማስተማር እንዳለብን ፍጹም የሆነ ምሳሌ ሰጥቶናል። ይህም ትምህርት በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን፣ ንስሀ መግባት፣ መጠመቅ፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን መቀበል፣ እና እስከመጨረሻ መፅናት ሲሆን የእግዚአብሔርን ልጆች ሁሉ ይባርካል።

እነዚህን መርሆች ለምንወዳቸው ስናሥተምር፣ መንፈስ ቅዱስ እውነትን እንድናገኝ ይረዳናል። የመንፈስ ቅዱስ ማነሳሳት ስለሚያስፈልገን፣ እውነተኛውን ትምህርት ከማስተማር ባለፈ ግምትን ወይም የግል ትርጓሜን ማስወገድ አለብን።

ተጽዕኖ ልታሣድሩበት እየሞከራችሁ ያለው ሰው የምትወዱት ከሆነ ይህን ማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል። እሱ ወይም እሷ የተማረውን/ችውን ትምህርት ችላ ብሎት/ላው ሊሆን ይችላል። አንድን አዲስ ወይም በጣም የሚያስደስት ነገርን ለመሞከር ፈታኝ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የእውነትን መንፈስ የሚገልጠው እኛ እውነተኛውን ትምህርት ከማስተማር ላለማለፍ ጥንቃቄ የምናደርግ ሲሆን ብቻ ነው። ወደ ሐሰት ትምህርቶች መጠጋትን ከምናስወግድባቸው በጣም አስተማማኝ መንገዶች አንዱ በቀላል መንገድ ለማስተማር መምረጥ ነው። ደህንነት የሚገኘው በቀላልነት ነው፣ የሚጠፋውም ትንሽ ነው።

በቀላሉ ማስተማር የደህንነት ትምህርትን ገና ከማለዳው፣ ህጻናት በኋላ ላይ በሚገጥማቸው የአታላዩ ፈተና ሳይነኩ፣ መማር የሚያስፈልጓቸው እውነቶች በማህበራዊ ሚዲያ፣ በእኩዮቻቸው እና በራሳቸው የግል ችግር አዋኪ ነገሮች ከመዋጣቸው ከብዙ ጊዜ በፊት ቀድመን እንድናካፍል ያስችለናል። የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ለልጆች ለማካፈል የምናገኘውን እያንዳንዱን አጋጣሚ ልንጠቀምበት ይገባል። እነዚህ የማስተማሪያ ጊዜያት ውድ ናቸው እንዲሁም ከተቃዋሚ ኃይሎች የማያቋርጡ ጥረቶች ጋር ሲወዳደሩ በጣም ትንሽ ናቸው። አንድን ትምህርት በህጻን ህይወት ውስጥ ቀስ በቀስ ለማስረጽ ለሚጠፋው ለእያንዳንዱ ሰዓት፣ እነዛን የሚያድኑ እውነቶች ጥያቄ ውስጥ በሚያስገቡ ወይም ችላ በሚሉ መልዕክቶች እና ምስሎች የተሞሉ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የተቃዋሚ ሰዓታት አሉ።

አንዳንዶቻችሁ ልጆቻችሁን መዝናኛ ወደ እናንተ ለመሳብ ይረዳ ይሆን ብላችሁ ልታስቡ ትችላላችሁ ወይም ልጃችሁ በምታስተምሩት ትምህርት ይጨናነቅ ይሆን ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ከዚያ ይልቅ፣ “ያለው ጊዜ በጣም አጭር በመሆኑ እንዲሁም ያሉት ዕድሎች በጣም ጥቂት በመሆናቸው፣ በእምነታቸው ላይ መምጣታቸው የማይቀሩት ፈተናዎች ሲመጡባቸው የሚያጠነክሯቸውን ምን ዓይነት የትምህርት እውነቶችን ላካፍላቸው እችላለሁ?” የሚለውን ማሠብ አለብን። ዛሬ የምታካፍሏቸው እውነቶች የሚያስታውሷቸው ሊሆኑ ይችላሉ፣ እንዲሁም የዛሬው ቀን ወዲያው ያልፋል።

የሴት ቅድመ አያቴ የሆነችው ሜሪ ቦምሜሊ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ለማካፈል ያላትን ቅንዓት ሁልጊዜ አደንቃለሁ። የ 24 ዓመት ልጅ እያለች ሚስዮናውያን ቤተሰቦቿን በስዊዘርላንድ አስተማሯቸው።

ከተጠመቀች በኋላ፣ ሜሪ በአሜሪካ ያሉ ቅዱሳንን መቀላቀል ፈለገች፣ ስለዚህም ከስዊዘርላንድ ወደ በርሊን ሄደች በዚያም ለአንዲት ሴት የቤተሰብ ልብስ በመሥራት ሥራ ተቀጠረች። ሜሪ የምትኖረው በሠራተኛ ክፍል ውስጥ ነበር እንዲሁም መሸመኛ ማሽኗን በቤቱ ሣሎን ውስጥ አደረገች።

በዚያን ጊዜ፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሣን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ትምህርት በርሊን ውስጥ ማስተማር ህገወጥ ነበር። ሜሪ ግን የተማረቻችውን ነገሮች ከማካፈል መታቀብ እንደማትችል አወቀች። የቤቱ ባለቤት የሆነችው ሴት እና ጓደኞቿ ሜሪ ስታስተምር ለመስማት በመሸመኛ ማሽኗ ዙሪያ ይሰበሰቡ ነበር። የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ ለጆሴፍ ስሚዝ ስለመገለጣቸው፣ ስለመልዓክት ጉብኝት እና ስለመፅሐፈ ሞርሞን ተናገረች። የአልማን መዝገቦች በማስታወስ ስለትንሣኤ ትምህርት አስተማረች። ቤተሰቦች በሠለስቲያል መንግሥት ውስጥ አንድ ላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ መሠከረች።

ሜሪ ዳግም የተመለሰውን ወንጌል ትምህርት ለማካፈል የነበራት ትጋት ወዲያው ችግር አስከተለ። ወዲያውኑ ፖሊሶች ሜሪን ወደ ወህኒ ቤት ወሰዷት። በመንገድ ላይ ሣሉም፣ በማግስቱ ጠዋት የምትቀርብበትን ዳኛ ስም ፖሊሱን ጠየቀችው። በተጨማሪም፣ ስለቤተሰቡ እንዲሁም ጥሩ አባት እና ጥሩ ባል ስለመሆኑ ጠየቀች። ፖሊሱ፣ ዳኛው ዓለማዊ ሠው እንደሆነ ገለፀ።

ሜሪ በወህኒ ቤት ውስጥ እርሳስ እና ወረቀት ጠየቀች። በመፅሐፈ ሞርሞን ላይ በተገለጸው መሠረት ስለኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሣት በመመሥከር፣ ስለመንፈሳዊው ዓለም በማብራራት እና ስለንስሀ በመግለጽ ለዳኛው ደብዳቤ ስትጽፍ አደረች። ለመጨረሻው ፍርድ ከመቅረቡ በፊት ዳኛው ስለሕይወቱ ማሠላሠል እንደሚያስፈልገው ጠቆመችው። ንሰሃ ሊገባባቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች እንዳሉት እንደምታውቅ፣ ይህም ቤተሰሠቡን በእጅጉ እንደሚያሳዝን እና ታላቅ ሀዘንን እንደሚያመጣበት ጻፈች። በነጋታው ጠዋት ደብዳቤዋን ፅፋ ስትጨርስ፣ ለፖሊሱ በመስጠት ለዳኛው እንዲሠጥላት ጠየቀችው እርሱም እንዲሁ ለማድረግ ተሥማማ።

በኋላም ዳኛው ፖሊሡን ወደ ቢሮው አስጠራው። ሜሪ የጻፈችው ደብዳቤ ዳግም የተመለሠውን ወንጌል ትምህርት እያስተማረች እና በዚህም ሕግን እየጣሰች ስለመሆኑ የማይካድ ማስረጃ ነበር። ይሁን እንጂ ፖሊሱ ወዲያው ወደ ሜሪ የወህኒ ቤት ክፍል ተመለሠ። ክሶቹ ሁሉ እንደተሠረዙ እና በነፃ መሄድ እንደምትችል ነገራት። ዳግም የተመለሰውን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ትምህርት ማስተማር ወደ ወህኒ ቤት እንድትጣል ምክንያት ሆኗት ነበር። እንዲሁም የንስሐን ትምህርት ለዳኛው መናገሯ ከወህኒ ቤት እንድትወጣ አደረጋት።

ሜሪ ቦምሜሊ ከተፈታች በኋላም ማስተማሯን አላቆመችም። የቃላቶቿ መዝገብ እውነተኛውን ትምህርት ገና ወዳልተወለዱት ትውልዶች አስተላልፏል። አዲስ የተለወጠ ሰው እንኳን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ማስተማር ይችላል የሚለው እምነቷ ዘሮቿ ፈተናን ለመቋቋም በሚያደርጉት ትግል እንደሚጠናከሩ አረጋግጧል።

የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ለምንወዳቸው ሠዎች ለማስተማር የተቻለንን ስናደርግ፣ አንዳንዶች አሁንም ላይቀበሉ ይችላሉ። ጥርጣሬ ወደ አዕምሯችሁ ሊገባ ይችላል። የአዳኙን ትምህርት በብቃት ለማስተማር በበቂ ሁኔታ ስለማወቃችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ። እናም እሱን ለማስተማር አስቀድማችሁ ሙከራዎችን አድርጋችሁ የነበረ ከሆነ አዎንታዊ ውጤቶች ለምን የበለጠ እንደማይታዩ ልታስቡ ትችላላችሁ። ለእነዚያ ጥርጣሬዎች እጃችሁን አትስጡ። እርዳታ ለማግኘት እግዚአብሔርን ጠይቁ።

“አዎን፣ እናም ለድጋፍህ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጩህ … የልብህ ዝንባሌ ለዘለዓለም በጌታ ላይ ይሁን።”

“እናም አሁን ትሁትና፣ ጨዋና ታዛዥ፣ ሁሉን የምትቀበሉ፣ ታላቅ ፅናት የበዛባችሁና ታጋሽ የሆናችሁ፤ በሁሉም ነገር ራሳችሁን የምትገዙ፣ በሁሉም ጊዜ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ለመጠበቅ ትጉህ፤ የፈለጋችሁትን ነገር በመንፈስም ሆነ በስጋ የምትጠይቁ፣ ለተቀበላችሁትም ማንኛውም ነገር ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር ምስጋና የምትሰጡ እንድትሆኑ እፈልጋለሁ።”

ከጸለያችሁ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ከተነጋገራችሁ እና የምትወዱትን ሰው እንዲረዳ ከለመናችሁት፣ እንዲሁም ላገኛችሁት እርዳታ ብቻ ሳይሆን የምትፈልጓቸውን ሁሉ ወዲያው ወይም በጭራሽ ባለመቀበላችሁ ለሚገኘው ትዕግስት እና ገርነት ካመሰገናችሁት ወደ እርሱ እንደምትቀርቡ ቃል እገባላችኋለሁ። ትጉህ እና ታጋሽ ትሆናላናችሁ። ከዚያም ሰይጣን የምትወዷቸውን እና የምትጸልዩላቸውን ሠዎች ዕድገት ለመግታት የሚያደርገውን ሙከራ እንዲያልፉ ለመርዳት የምትችሉትን ሁሉ እንዳደረጋችሁ ማወቅ ትችላላችሁ።

“ጌታን የሚጠብቁ ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ አይደክሙም።”

ስለቤተሠቦች በሚናገረው የቅዱሳት መፃሕፍት ዘገባ ውስጥ ተስፋ ማግኘት ትችላላችሁ። ተምረውት የነበረውን ነገር ችላ ስላሉት ወይም ከእግዚአብሔር ይቅርታ ለማግኘት ሲቸገሩ ስለነበሩት እንደ ታናሹ አልማ፣ የሞዛያ ልጆች እና ሄኖስ ስላሉ ሠዎች እናነባለን። ቀውስ ውስጥ በገቡበት ወቅት፣ ወላጆቻቸው የነገሯቸውን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት አስታውሰዋል። ማስታወሳቸው አድኗቸዋል። ያንን የተቀደሰ ትምህርት ማስተማራችሁ ይታወሳል።

በመንፈስ እንድንነጻ እንዲሁም በመጨረሻ በእግዚአብሔር ፊት መልካም አቀባበል እንዲደረግልን ስለሚያስችለን፣ ከእግዚአብሔር እና ከልጁ ጋር እንደ ቤተሰቦች ለዘላለም በክብር እንድንኖር ስለሚያስችለን ቀላል የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ለሰማይ አባት ልጆች ስለማስተማር ቅዱስ ሥራ እመሰክራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።