እግዚአብሔር ሁሉንም ልጆቹን ይወዳል
ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ወደእኛ ይጣራል እና ልጆቹን ወደእርሱ ለማምጣት እንረዳው ዘንድ እኛን ይጠቀማል።
የሰማይ አባታችን ከእናንተ የሚሻው ምንድነው? በቅድመ ምድራዊ ህይወት እያላችሁ የሰማይ አባት ለምድር ህይወታችሁ እናንተን ያዘጋጅ እንደነበር ትረዳላችሁን? ፕሬዘዳንት ራስል ኤም ኔልሰን ለታዳጊዎች ሲናገሩ እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፣ “የሰማይ አባታችን ብዙዎችን ክቡር መንፈስቶቹን—ምናልባትም … ምርጦቹን ቡድን—ለዚህ መጨረሻ ደረጃ በማዘጋጀት አስቀምጦ ነበር።” ለእነዚህ የኋለኞቹ ቀናት የተጠበቅን በመሆናችን ምክንያት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙር ለመሆን መማር ለእኛ እጅግ አስፈላጊ ነው።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እረኛ ነው እና መንጋዎቹንም ያውቃቸዋል እናም መንጎቹም እረኛውን ያውቃሉ ምክንያቱም “የራሱንም በጎች በየስማቸው [ይጠራቸዋል]።” እርሱ ዘወትር ወደእኛ ይጣራል እና ልጆቹን ወደእርሱ ለማምጣት እንረዳው ዘንድ እኛን ይጠቀማል።
ከተወሰነ ጊዜ በፊት በአቅራቢያችን አጎራባች በሆኑ አካባቢዎች የካስማ ፕሬዘዳንቱ እና እኔ የቤተክርስቲያን አባላትን እየጎበኘን ነበር። በመርሃ ግብራችን መሰረት ጉብኝታችንን ካጠናቀቅን በኋላ የካስማ ፕሬዘዳንቱ አንድ ተጨማሪ ቤተሰብን መጎብኘት እንችል እንደሆነ ጠየቀኝ። እነርሱን ማነጋገር እንዳለብን ጥልቅ ስሜት አደረበት።
በሩን አንኳኳን እናም አንዲት እህት ከፈተችልን። ወደ እኔ ተመለከተች ነገር ግን ማን እንደሆንኩ ባለማወቋ ብዙም ትኩረት አላደረገችም። በስሟ ጠርቶ ሰላምታ ወደሰጣት ወደካስማ ፕሬዘዳንቱ እጄን ጠቆምኩኝ። እርሱን በሰማችው እና ባየችው ጊዘ፣ በጣም ተደሰተች። እዚያው በበሩ አጠገብ እንደቆሙ ሁለቱም ተቃቀፉ እናም አለቀሱ። ይህ ለጉብኝታችን ድምቀትን ሰጥቶታል። ይህች እህት ከአንድ ቀን በፊት ለካንሰር ህመም ማስታገሻ ሽክምና የተቀበለች መሆኗን አላወቅንም ነበር። ጎልማሳ የሆነ ልጇንም ለመንከባከብ እጅግ አቅም አንሷት ነበር። ስለዚህ የካስማ ፕሬዘዳንቱ ልጇን ሲያለብሰው ረዳሁት እናም በተሽከርካሪ ወንበሩ ላይ አስቀመጥነው። አስቀድሞ ሌላ የተወደደች እህት ከአጥቢያው ያመጣችውን ምግብ መገብነው እና በሌሎችም ስራዎች እገዛ አደረግን። ከቤታቸው ከመውጣታችን በፊት ልንባርካቸው ቻልን።
በዚህ ጉብኝት ወቅት በሙሉ በአእምሮዬ ሲመላለስ የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ እንደሚወዳቸው ማረጋገጫ ነበር። እርሱ ይረዳቸዋል የእነርሱንም ልዩ የህመም ሁኔታ ያውቃል። ሁሉም ጊዜ በሚባል ደረጃ ጉብኝታችን የተከናወነው በዝምታ ነበር። በዚህ ወቅት ትልቅ ስብከት አልሰጠንም ወይም የምንወደውን ጥቅስ አላካፈልንም ነገር ግን ጌታ በመንፈሱ በብዙ ባርኮናል።
የሰማይ አባታችሁ እናንተን ከላከበት ታላላቅ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ሙሉ አቅማችሁን ታውቁ ዘነድ ነው። ወንጌሉን ስበኩ የሚለው መጽሐፍ የሚያስተምረን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማነጻጸርን ማስወገድ እንዳለብን ነው። መንፈሳዊ ችሎታዎቻችሁ ልዩ፣ ግላዊ፣ እና ተፈጥሮአዊ ናቸው፣ እንዲሁም የሰማይ አባታችሁ እነዚህን እንድታጎለብቱ ሊረዳችሁ ይፈልጋል። ሁልጊዜም የሰማይ አባታችሁን ፍቅር እንዲሰማው ልታደርጉት የምትችሉት አንድ ሰው ይኖራል። አቅማችሁ መለኮታዊ ነው። በዚህ ውድድር በበዛበት አለም ውስጥ ስኬታማ ለመሆን ራሳችሁን ማዘጋጀት እስፈላጊ ቢሆንም፣ በህይወት ዘመናችሁ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዝሙር ለመሆን እና የመንፈስን ጥልቅ ስሜት ለመከተል መጣር ነው። ይህን ባደረጋችሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ህይወታችሁን ይባርካል፣ እርሱ የአሁን ወይም የወደፊት ቤተሰባችሁን ይባርካል እናም የምታገኟቸውን የእርሱን ልጆች ህይወት ይባርካቸዋል።
ታላቅ እድል ባለበት ጊዜ እየኖርን ነው። ምንም እንኳ አያሌ ችግሮች ቢገጥሙንም፣ ሌሎች የሰማይ አባታችንን ፍቅር እንዲሰማቸው እንድንረዳቸው በከፊል እዚያ እንዳሉ አውቃለሁ። ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዳስተምሩት፣ “በመጪዎቹ ቀናት ከዚህ ቀደም አለም በምንም አይቶት ከማያውቀው በላይ የሆኑ ታላቅ የጌታን ሀይል መገለጫዎች እናያለን።” የሚረዱ እጆችን፣ መታቀፍን፣ የመጽናናት ስሜትን ወይም በቀላሉ ከእነርሱ ጋር በዝምታ እንድንሆን የሚፈልጉ ሰዎችን ለማየት እድሉን አግኝተናል። ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ሸክሞቻቸውን ለማቅለል ለመርዳት ከቻልን፣ ከዚያም በህይወታቸው ውስጥ የአዳኙን ሀይል ታላቅ መገለጥ ለማየት እንችላለን።
እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን በአለም ላይ በጎ ተጽእኖን ማድረግ ይችላሉ። በፊታችን ላይ የሚንጸባረቅን የሀሴት ስሜት፣ ከፍቅር ቃላት እና ከደግነት ተግባራት ጋር የምናካፍለውን ሀሴት ልናቀርብ እንችላእን። መልካም ባልንጀሮች፣ መልካም ቀጣሪዎች፣ መልካም ሰራተኞች እንሁን። በሁሉም ጊዜያት መልካም ክርስቲያኖች ለመሆን እንጣር።
የሰማይ አባት ልጆች ከእርሱ ጋር የሚያስተሳስራቸውን ቃል ኪዳኖች ለማግኘት ይችሉ ዘንድ ጌታ ወንጌሉን ከአስፈላጊ ስርዓቶች ጋር መልሷል። በዕለት ተዕለት ተግዳሮቶቻቸው እህቶቻችንን እና ወንድሞቻችንን በመርዳት፣ እርሱም በበኩሉ በዚህ አለም እና በዘለአለም ታላላቅ በረከቶቹን ቃል ይገባላቸው ዘንድ ከሰማዩ አባታቸው ጋር እነዚህን የተቀደሱ ኪዳኖችን እንዲያደርጉ እና እንዲጠብቁ ለመርዳት እናስታውስ። እነዚህ ቃል ኪዳኖች ሊከናወኑ የሚችሉት በዳግም በተመለሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና በክህነት ቁልፎች ብቻ ነው።
በሌላ አባባል ሌሎችን በቃል ኪዳን መንገድ እንዲቆዩ መርዳት እንችላለን። አንዳንዶቻችን ከጊዜ ወደጊዜ ከመንገዱ እናፈነግጣለን፣ እና በዚህም ምክንያት በሰማዩ አባታችን አማካይነት ሁልጊዜ ለመመለስ የሚቻል መሆኑን ማስታወስ ይገባናል። ምንም እንኳ አካሄዳችን ፍጹም የሆነ ባይሆንም፣ ጌታ ዘወትር የሚያስታውሰን፣ “በእውነተኛ ፍላጎት ንሰሃ ሁል ጊዜም ከገ[ባን]፣ እናም ይቅርታን ከፈለ[ግን] ይቅር [እንባላለን]።”
ዛሬ ከጠላት ዘዴዎች አንዱ ለመቀየር ምንም መንገድ እንደሌለን ወይም ከዚህ ወዲያ ምንም ተስፋ እንደሌለን እንድናስብ እና እንድናምን ለማድረግ ነው። ይህ አጥፊ አስተሳሰብ ብዙዎቻችንን ከመሞከር እንድንታቀብ ያደርገናል። እና በዚህ ጊዜ ነው ፍቅራችን፣ የማበረታቻ ቃላቶቻችን እና ድጋፋችን፣ ጊዜያችን፣ እና እርዳታችን የሆነ ግለሰብ ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሞክር ተስፋ የሚሰጠው።
ምናልባትም፣ “አዎን፣ ነገር ግን ማን ያገለግለኛል?” በማለት እያሰባችሁ ይሆናል። ሄደን የወንድም እና የእህቶቻችንን ህይወት በምንባርክበት ጊዜ፣ ህይወታችንን በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት የሚሞላ ምስክርነቶችን እንሰበስባለን። እነዚህ ምስክርነቶች አንዴ በድጋሚ ሙከራ እንድናደርግ የሚያበረቱን ናቸው። መንፈስ ቅዱስ ያበረታናል እና በችግሮቻችን እና በግል ፈተናዎቻችን መሀል እንድንቀጥል በታደሰ ምስክርነት ይረዳናል። የሌሎችን ህይወት ለመባረክ በፈለግን ጊዜ ሁሉ ጌታ በተጨማሪ ምህረት ይጎበኘናል፤ በህይወታችን ውስጥ ያጠነክረናል እናም ይረዳናል።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችሁ እና በግል የሚረዳችሁ መሆኑን እባካችሁ አስታውሱ። ጥሪን ማከናወን እና የእግዚአብሔርን ልጆች ለመርዳት ነገሮችን ወደጎን መተው ምን እንደሆነ እርሱ ያውቃል። በእርሱ ካመናችሁ እና ባትጠራጠሩ ፣ በሁሉም ነገር ሊባርካችሁ እርሱ ሀይል አለው።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በአጀንዳችን ውስጥ ያልነበሩትን እናትና ልጅ እንድንጎበኝ የክህነት መሪው በተነሳሳበት በዚያ ቀን፣ እነርሱ እኛን የሚፈልጉ መሆናቸውን እግዚአብሔር ያውቅ እንደነበር አውጃለሁ። እና በመጨረሻም የተገለገልኩት እኔው እራሴ ነበርኩ። በዚያ ቀን አዳኙ ለእኛ ካለው ፍቅር ታላቅ የሆነን ትምህርት ተቀብያለሁ።
ኢየሱስ ክርስቶስ የአለም አዳኝ መሆኑን፣ እርሱ ህያው እንደሆነ፣ በምድር ኖሮ ለእናንተ እና ለእኔ እንደሞተ፣ ከመጋረጃው በስተጀርባ ካሉት ጋር በሀሴት በመሞላት በሰለስቲያል ግንኙነት ለመገናኘት ተስፋ እንድናደርግ ለእናንተ እና ለእኔ ከሞት እንደተነሳ እመሰክራለሁ። እናንተን እና እኔን ፍጹም እንደሚረዳን አውቃለሁ። እያንዳንዱን አስቸጋሪ ጊዜያቶቻችንን እርሱ የሚረዳ መሆኑን፣ እና በጣም በዛልንባቸው በእነዚያ ጊዜያት ሁሉ ሊረዳን ሀይል እንዳለው አውቃለሁ። በእነዚህ ቀናት ወንጌሉን ዳግም ለመመለስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እና የሰማይ አባታችን ለጆሴፍ ስሚዝ እንደተገለጠ አውቃለሁ። ውድ ነቢያችን ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን የጌታ ነቢይ እንደሆኑ አውቃለሁ፣ እናም ይህንን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እመሰክራለሁ፣ አሜን።