ሥሩን ተንከባከቡት፣ ከዚያም ቅርንጫፎቹ ያድጋሉ
የምስክርነታችሁ ቅርንጫፎች በሰማይ አባት እና በተወደደው ልጁ ካላችሁ ጥልቅ እምነት የተነሳ ጥንካሬ ያገኛል።
በዝዊካው የሚገኝ አንድ አሮጌ የጸሎት ቤት
2024 (እ.አ.አ) ለእኔ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ወሳኝ ዓመት ነው። በዝዊካው፣ ጀርመን ውስጥ ተጠምቄ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል ሆኜ ማረጋገጫ ከተሠጠኝ 75 አመት ይሆነዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባልነቴ ለእኔ ዕንቁ ነው። ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ መካከል፣ ከእናንተ ከወንድሞቼ እና ከእህቶቼ ጋር እንደ አንዱ አብሮ፣ መቆጠር፣ የሕይወቴ ታላቁ ክብር ከሆኑት ውስጥ አንዱ ነው።
ስለ የግል የደቀመዝሙርነት ጉዞዬ ሳስብ፣ አእምሮዬ ብዙ ጊዜ በልጅነቴ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስትያን የቅዱስ ቁርባን ስብሰባዎች ላይ አስደሳች ትዝታዎችን አሳልፌ ስለነበረበት ቦታ፣በዝዊካው ውስጥ ስለሚገኘው አሮጌ ቪላ ያስባል። የምሥክርነቴ ችግኝ የመጀመሪያውን እንክብካቤ ያገኘበት ስፍራ በዚያ ነበር።
ይህ የአምልኮ ቤት በአየር የሚሰራ አሮጌ ኦርጋን/የሙዚቃ መሳሪያ ነበረው። በየሰንበቱ ኦርጋኑ እንዲሰራ የሚያደርገውን የመንፊያን ጠንካራ ማንሺያ ወደላይ እና ወደታች እንዲገፋ አንድ ወጣት ሰው ሀላፊነት ይሰጠው ነበር። አንዳንድ ጊዜ በዚህ አስፈላጊ ተግባር ውስጥ የማገዝ እድል ተሠጥቶኝ ነበር።
ጉባኤው የምንወዳቸውን መዝሙሮች ይዘምር በነበረበት ወቅት፣ ኦርጋኑ ውስጥ ያለው አየር እንዳያልቅ በሙሉ ኃይሌ እነፋ ነበር። መንፊያውን ከሚቆጣጠረው መቀመጫ ሆኜ፣ አንዳንድ አስገራሚ ባለቀለም መስታወት መስኮቶችን መመልከት የምችልበት ግሩም እይታ ነበረኝ፣ አንደኛው አዳኙን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያሳይ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ጆሴፍ ስሚዝ በቅዱስ ጫካ ውስጥ ሆኖ ያሳያል።
እነዚያን የፀሐይ ብርሃን የሚያርፍባቸውን መስኮቶች ስመለከት፣ የቅዱሳንን ምስክርነት እያዳመጥኩ የጽዮንን መዝሙር ስዘምር የነበረኝን ቅዱስ ስሜት እስከ አሁን ድረስ አስታውሳለሁ።
በዚያ ቅዱስ ስፍራ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ለአእምሮዬ እና ለልቤ ወንጌሉ እውነት እንደሆነ መሰከረልኝ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የአለም አዳኝ ነው። ይህ የእርሱ ቤተክርስቲያን ነው። ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እግዚአብሔር አብን እና ኢየሱስ ክርስቶስን አይቷል እንዲሁም ድምፃቸውን ሰምቷል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ፣ በአውሮፓ ተመድቤ ሳለሁ ወደ ዝዊካው የመመለስ ዕድል አግኝቼ ነበር። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ያ ተወዳጅ የድሮው የጸሎት ቤት በዚያ አልነበረም። ለትልቅ የመኖሪያ ሕንፃ የግንባታ ቦታን ለማመቻቸት ከብዙ አመታት በፊት ፈርሷል።
ዘላለማዊ የሆነ ምንድን ነው? ያልሆነውስ ምንድን ነው?
ከልጅነቴ ጀምሮ ይህ ተወዳጅ የሆነው ሕንፃ አሁን ትውስታ ብቻ ሆኖ መቅረቱ በጣም አሳዛኝ እንደሆነ አምናለሁ። ለእኔ የተቀደሰ ሕንፃ ነበር። ነገር ግን ሕንፃ ብቻ ነበር።
በአንጻሩ፣ ከብዙ ዓመታት በፊት ከመንፈስ ቅዱስ ያገኘሁት መንፈሳዊ ምስክርነት አልጠፋም። እንዲያውም እየጠነከረ መጥቷል። በወጣትነቴ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መሰረታዊ መርሆች የተማርኳቸው ነገሮች በህይወቴ ሙሉ ጽኑ መሰረት ሆነውኛል። የዝዊካው የጸሎት ቤት እና ያጌጠው መስታወት ፈራርሶ ከጠፋ በኋላም እንኳን— ከሰማይ አባቴ እና ከተወዳጅ ልጁ ጋር የፈጠርኩት የቃል ኪዳን ግንኙነት ከእኔ ጋር ጸንቶ ቆይቷል።
ኢየሱስም እንዲህ አለ፣ “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ “ቃሌ ግን አያልፍም።”
“ተራሮች ይፈልሳሉ፥ ኮረብቶችም ይወገዳሉ፤ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አይፈልስም የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም፥ ይላል መሐሪሽ እግዚአብሔር።”
በዚህ ሕይወት ልንማራቸው ከምንችላቸው በጣም አስፈላጊ ነገሮች አንዱ በዘላለማዊና ባልሆነ መካከል ያለው ልዩነት ነው ። አንድ ጊዜ ያንን መረዳት ከቻልን፣ ሁሉም ነገር ይለወጣል፤ ይኸውም ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት፣ የምናደርጋቸው ምርጫዎች ፣ ከሰዎች የምናስተናግድበት መንገድ።
ዘላለማዊ የሆነውን እና ያልሆነውን ማወቅ የኢየሱስ ክርስቶስን እና የቤተክርስቲያኑን ምስክርነት ለማሳደግ ቁልፍ ነገር ነው።
ቅርንጫፎቹ ስሮች እንዳይመስሏችሁ
ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንዳስተማረው፣ ዳግም የተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል፣ “ሁሉን[ም] እንዲሁም እያንዳንዱን እውነት ይቀበላል።” ይህ ማለት ግን ሁሉም እውነት እኩል ዋጋ አለው ማለት አይደለም። አንዳንድ እውነቶች ወሳኝ እና አስፈላጊ እንዲሁም የእምነታችን ሥር ናቸው። ሌሎች ደግሞ ቅጥያዎች ወይም ቅርንጫፎች ሲሆኑ ዋጋ የሚኖራቸው ከመሠረታዊ ነገሮች ጋር ሲጣበቁ ብቻ ነው።
ነቢዩ ጆሴፍም ሲናገር፣ “የሐይማኖታችን መሰረታዊ መርሆች ሐዋርያት እና ነቢያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸው ምስክርነቶች ሲሆን፣ ያም እርሱ እንደሞተ፣ እንደተቀበረ፣ እና በሶስተኛውም ቀን እንደተነሳ፣ እንዲሁም ወደ ሰማይ እንዳረገ የሚመሰክሩት ናቸው፤ ሌሎች ከሐይማኖታችን ጋር የሚያያዙ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ለሐይማኖታችን መሰረታዊ መርሆች ቅጥያ ብቻ ነው።”
በሌላ አነጋገር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እና የኃጢያት ክፍያው የምስክርነታችን ሥር ናቸው። ሌሎች ነገሮች ሁሉ ቅርንጫፎች ናቸው።
ይህ ማለት ቅርንጫፎቹ አስፈላጊ አይደሉም ማለት አይደለም። ዛፍ ቅርንጫፎች ያስፈልጉታል።. ነገር ግን አዳኙ ለደቀ መዛሙርቱ እንደነገራቸው፣ “ቅርንጫፉ በወይኑ ግንድ ውስጥ ከሌለ በራሱ ፍሬ ማፍራት አይችልም።” ከአዳኙ፣ በሥሮቹ ውስጥ ከሚገኘው ምግብ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ከሌለው፣ ቅርንጫፉ ይጠወልጋል እንዲሁም ይሞታል።
ስለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ምስክርነት ስናሳድግ፣ አንዳንድ ጊዜ ቅርንጫፎቹ ስሮች ይመስሉን ይሆን ብዬ አስባለው። ኢየሱስ በዘመኑ በነበሩት ፈሪሳውያን ላይ ያየው ስሕተት ይህ ነበር። በአንፃራዊነት ጥቃቅን ለሆኑት የሕግ ዝርዝር ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረትን በመስጠታቸው አዳኙ እንደ “ፍርድንና ምህረት እና ታማኝነት” ያሉ መሰረታዊ መርሆችን— “በሕግ ያለውን ዋና ነገር”ብሎ የጠራውን ችላ ብለዋል።
ዛፍን መከባከብ ከፈለጋችሁ ውሃ የምታጠጡት ቅርንጫፎቹን አይደልም። የምታፈሱት ሥሩ ላይ ነው። በተመሳሳዩ ሁኔታ፣ የምስክርነታችሁ ቅርንጫፎች እንዲያድጉ እና ፍሬ እዲያፈሩ ከፈለጋችሁ፣ ሥሩን ተንከባከቡ። ስለ አንድ የተወሰነ ትምህርት ወይም ልምምድ ወይም ስለ አንድ የቤተክርስቲያን ታሪክ እርግጠኛ ካልሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማመን መገንዘቢይን ፈልጉ። ለእናንተ የከፈለውን መሥዋዕትነት፣ ለእናንተ ያለውን ፍቅርእና ለእናንተ ያለውን ፈቃድ ለመረዳት ጥረት አድርጉ። በትሕትና ተከተሉት። የምስክርነታችሁ ቅርንጫፎፍ በሰማይ አባት እና በተወደደው ልጁ ካላችሁ ጥልቅ እምነት የተነሳ ጥንካሬ ያገኛል።
ለምሳሌ፣ ስለ መፅሐፈ ሞርሞን ጠንካራ ምስክርነት እንዲኖራችሁ ከፈለጋችሁ፣ ውስጡ በያዘው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ላይ አተኩሩ። መፅሐፈ ሞርሞን ስለእርሱ ምን እንደሚያስተምር ፣ እና ወደ እርሱ እንድትመጡ እንዴት እንደሚጋብዛችሁ እና እንደሚያነሳሳችሁ እንዲሁም እንዴት እንደሚመሰክር ልብ በሉ።
በቤተክርስቲያን ስብሰባዎች ወይም በቤተመቅደስ ውስጥ የበለጠ ትርጉም ያለው ተሞክሮ የምትፈልጉ ከሆነ፣ እዚያ በምንቀበላቸው ቅዱስ ስርዓቶች ውስጥ አዳኙን ለመፈለግ ሞክሩ። ጌታን በተቀደሰ ቤቱ ውስጥ ፈልጉት።
በቤተክርስቲያን ጥሪዎቻችሁ ድካም ወይም የመሰላቸት ስሜት ከተሰማችሁ፣ አገልግሎታችሁን እንደገና መልሳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ለማድረግ ሞክሩ። ለእርሱ ያላችሁ ፍቅር መገለጫ እንዲሆን አድርጉት።
ሥሮቹን ተንከባከቡ ከዚያም፤ ቅርንጫፎቹ ያድጋሉ። ውሎ አድሮ ደግሞ ፍሬ ያፈራሉ።
ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ጠንካራ እምነት በአጋጣሚ የሚሆን ነገር አይደለም። አይደለም በዚህ ምድራዊ ህይወት ውስጥ፣ በአጋጣሚ የሚያድጉ እሾህ እና አሜኬላ ብቻ ነው። ጤናማና ፍሬያማ የሆነ የእምነት ዛፍ ሆን ብሎ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። የዚህ ጥረት አንዱ ዓቢይ ክፍል በክርስቶስ ላይ ሥር የሰደደ መሰረት እንዲኖረን ማስቻል ነው።
ለምሳሌ ፥ በመጀመሪያ፣ ተግባቢ በሆኑ አባላት፣ ደግ በሆነው ኤጲስ ቆጶስ ወይም በተዋበ መልኩ ስለተገነባው የፀሎት ቤት ስለተደነቅን ወደ አዳኙ ወንጌል እና ወደ ቤተክርስቲያኗ ልንሳብ እንችላለን። ቤተክርስቲያኑን ለማሳደግ እነዚህ ሁኔታዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው።
ይሁን እንጂ፣ የምሥክርነታችን ሥሮች ከዚያ ይበልጥ የጠነከሩ ካልሆኑ፣ ወደ አጥቢያ ህንጻዎች ስንሄድ እንደጠበቅነው ያማሩ ባይሆኑ፣ አባላቱም ደግሞ እንደለመድነው ተግባቢዎች ሳይሆኑ ቢቀሩ ኤጲስ ቆጶሱ መልካም ያልሆነ ነገር ቢናገረንና፣ ቢያሳዝነን በመጨረሻ ምን ይፈጠራል?
ሌላ ምሳሌ፦ ትእዛዛቱን ብንጠብቅ እና በቤተመቅደስ ውስጥ ብንታተም፣ በትልቅ ደስተኛ ቤተሰብ፣ ብሩህ እና ታዛዥ በሆኑ ልጆች እንደምንባረክ፣ ሁሉም ደግሞ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ንቁ ሆነው እንደሚቆዩ፣ ምስዮን እንደሚያገለግሉ፣ በአጥቢያ መዘምራን ውስጥ እንደሚዘምሩ እና ቅዳሜ ጥዋት በፈቃደኝነት ቤተክርስቷኑን ለማጽዳት እንደሚረዱ ተስፋ ማድረግ ምክንይታዊ አይሆንም?
ይህንን ሁላችንም በህይወታችን ውስጥ እንደምንመለከተው በእርግጠኝነት ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን ባይከሰትስ? በስራው እና በጊዜው በመተማመን፣ ሁኔታዎች ምንም ያህል የተወሳሰቡና ከባድ ቢመስሉን ከአዳኙ ጋር እንቆያለን?
ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ አለብን:- ምስክርነቴ በሕይወቴ ውስጥ ይሆናል ብዬ ተስፋ ባደረኩት ነገር ላይ የተመሠረተ ነው? በሌሎች ሰዎች ድርጊት ወይም አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው? ወይስ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፅኑ መሰረት ያለው ”ሥር የሰደ[ደ] እና የታነ[ጸ]” ነው?
ወጎች፣ ልማዶች እና እምነት
መፅሐፈ ሞርሞን “የእግዚአብሔርን ስርዓቶች በመጠበቅ ትጉ ስለነበሩ” ህዝቦች ይናገራል። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ቆሪሆር የሚባል ተጠራጣሪ መጣ፣ የአዳኙን ወንጌል እና “የአባቶቻቸውን ወጎች”፣ “ሞኝ” ከንቱ ነገርች እያለ በመጥራት ያሾፍ ነበር። ኮሪሆር “የብዙዎችን ልብ በመማረክ በክፋታቸው ራሳቸውን ቀና እንዲያደርጉ’ አድርጓቸዋል።” ነገር ግን፣ ለሌሎች የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ከወግ ይልቅ ታላቅ ስለ ነበረ ሊያታልላቸው አልቻለም።
እምነት በግል ልምድ ሲመጣ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ባለን የግል ቁርጠኛነት ሲሆን፣ ሌሎች ከሚናገሩት ወይም ከሚያደርጉት ነገር ውጭ ሲሆን፥ ጥልቅ የሆነ ሥር ያለውና ጠንካራ ይሆናል።
ምስክርነታችን ይፈተናል እንዲሁም በብዙ ይፈተሻል። ያልተፈተነ እምነት፣ እምነት ሊባል አይችልም። ያልተፈተነ እምነት ጠንካራ አይሆንም። ስለዚህ የእምነት ፈተና ወይም መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች ካሉዋችሁ ተስፋ አትቁረጡ።
እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ሁሉንም ነገር እንረዳለን ብለን መጠበቅ የለብንም። ያ እምነት አይደለም። አልማ እንዳስተማረው፣ “እምነት ስለ ነገሮች ፍፁም የሆነ እውቀት አለ ማለት አይደለም።” ጥያቄዎቻችን በሙሉ ከተመለሱልን በኋላ ለመስራት የምንጠብቅ ከሆነ፣ ልናከናውነው የምንችለውን መልካም ነገር እንገታለን፣ የእምነታችንንም ኃይል እንገድብላን።
እምነት ውብ ነገር ነው ፤ ምክንያቱም በተስፋ የሚጠበቁ በረከቶች ቢዘገዩም እንኳን ጸንቶ ይቆያል። የወደፊቱን ማየት አንችልም፣ ሁሉንም መልሶች አናውቅም፣ ነገር ግን ወደ ፊት ጉዞ ከቀጠልን እና ቀና ብለን ከተጓዝን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እና ቤዛችን ስለሆነ በእርሱ መተማመን እንችላለን።
እምነት በክርስቶስና በአስተምሮቱ ውስጥ ያለ ሥር የሰደደ መሠረተ ስላለው ፈተናዎች እና የሕይወት ጥርጣሬዎችን ይቋቋማል። ኢየሱስ ክርስቶስ እና እርሱን የላከው የሰማይ አባታችን አንድ ላይ ሆነው የማይቀያየሩ እና ፍጹም ልብ የሚጣልባቸው ናቸው።
ምስክርነት በአንድ ጊዜ ገንብታችሁ ለዘላለምም የሚቆም አይነት ነገር አይደልም። ይልቅ ያለማቋረጥ እንደምትከባከቡት አይነት ዛፍ ነው ። የእግዚአብሔርን ቃል በልብ ውስጥ መትከል ብቻ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ምሥክርነታችሁ ማደግ ሲጀምር፣ ዋናው ሥራ ይጀምራል! “እንዲያድግ፣ ፍሬም እንዲያፈራ፣ ሥር እንዲሰድድ፣ በታላቅ ጥንቃቄ የምትንከባከቡት የዚያን ጊዜ ነው።” “ታላቅ ትጋት” እና “በቃሉ ላይ ትዕግሥትን” ይጠይቃል። ነገር ግን እግዚአብሔር “ከዚያም ወንድሞቼ፣ ዛፉ ፍሬ እንዲያስገኝላችሁ በመጠበቃችሁ ለእምነታችሁ፣ ለትጋታችሁና፣ ለፅናታችሁ፣ እናም ለታጋሽነታችሁ ደመወዝን ታገኛላችሁ”በማለ ቃል ገብቷል።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ወድ ጓደኞቼ፣ ውስጤ የድሮውን የዙዊክ የጸሎት ቤት እና በቀለም የተቀቡ የመስታወት መስኮቶቹን የሚናፍቀው የእኔ ክፍል አለ። ይሁን እንጂ ባለፉት 75 ዓመታት ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ካሰብኩት በላይ እጅግ አስደሳች የሆነ የሕይወት ጉዞ እንድጓዝ ረድቶኛል። በመከራዬ ወቅት አጽናንቶኛል፣ ድክመቶቼን እንዳውቅ ረድቶኛል፣ መንፈሳዊ ቁስሎቼን ፈውሷል እንዲሁም እያደገ በመጣው እምነቴ ተንከባክቦኛል።
በአዳኙ፣ በትምህርቱ፣ እንዲሁም በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የእምነታችንን ሥር ሁልጊዜ እንድንመግብ ልባዊ ጸሎቴ እና በረከቴ ነው። ስለዚህም የምመሰክረው በመድኃኒታችን፣ በቤዛችን፣ በመምህራችን በተቀደሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።