በሙሉ ልባችሁ እርሱን እሹ
ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት እና በእርሱ ለመጠናከር ጸጥ ያለ ጊዜ ከፈለገ፣ እኛም እንዲህ ማድረጉ ጥበብ ነው።
ከብዙ አመታት በፊት፣ ባለቤቴ እና እኔ በቶኪዮ፣ ጃፓን እንደ ሚስዮን መሪዎች አገልግለናል። በዚያ ጊዜ ሽማግሌ የነበሩት ራስል ኤም. ኔልሰን የሚስዮን አካባቢያችንን በጎበኙበት አንድ ጊዜ፣ ከሚስዮናውያን አንዱ፣ አንድ ሰው እነርሱን ለማዳመጥ በጣም ሥራ እንደበዛበት ቢነግራቸው እንዴት መልስ መስጠት እንዳለባቸው ጠየቃቸው። ምንም ሳይጠራጠሩ፣ ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዲህ አሉ፣ “በዚያ ቀን ምሳ ለመብላት ሥራ ይበዛባቸው እንደሆነ እጠይቃቸዋለሁ፤ ከዚያም ሰውነት እና መንፈስ እንዳላቸው አስተምራቸዋለሁ፣ እናም ልክ ሰውነታቸው ምግብ ሳይመገብ እንደሚሞት፣ መንፈሳቸውም የእግዚአብሔር መልካም ቃል ካልተመገበ እንዲሁ እንደሚሆን አስተምራቸዋለሁ።”
“የሥራ መብዛት” የሚል ፍቺ ያለው የጃፓንኛ ቃል ኢሶጋሺ ሁለት ምልክቶች (忙) ያሉት ፊደል መሆኑን ልብ ማለት ትኩረትን የሚስብ ነው። በግራ በኩል ያለው “ልብ” ወይም “መንፈስ”፣ እንዲሁም በቀኝ በኩል ያለው “ሞት” ማለት ነው—ይህም ምናልባት፣ ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ መንፈሳችንን ለመመገብ እስከማንችል ድረሥ ስራ ሲበዛብን በመንፈሳዊ ወደመሞት ሊመራን እንደሚችል ይጠቁማል።
ጌታ በዚህ ትኩረትን በሚከፋፍል እና ግርግር በተሞላበት ፈጣን ዓለም ውስጥ፣ ለእርሱ ጥራት ያለው ጊዜን መስጠት ከዘመናችን ዋና ፈተናዎች አንዱ እንደሆነ ያውቃል። በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል በመናገር፣ ከምንኖርበት ውዥንብር ቀናት ጋር ሊመሳሰሉ የሚችሉትን የምክር እና የጥንቃቄ ቃላት አቅርቧል፦
“በመመለስ እና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ እናንተም እንቢ አላችሁ።
“ነገር ግን፣ በፈረስ ላይ ተቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም አላችሁ፤ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ደግሞም፣ በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን አላችሁ፤ ስለዚህም የሚያሳድዱአችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ።”
በሌላ አባባልም፣ ምንም እንኳን ደህንነታችን በብዙ ጊዜ ወደ እርሱ በመመለስ ላይ እና ከአለም ጭንቀት በማረፍ የተመካ ቢሆንም፣ የኛ አናደርጋቸውም። ምንም እንኳ በራስ መተማመናችን የሚመጣው ከጌታ ጋር በጸጥተኛ የማሰላሰሊያ እና የማስተዋል ጊዜ በምናገኘው የጥንካሬ እድገት በኩል ቢሆንም፣ አናደርገውም። ለምን? ምክንያቱም፣ እንደሚባለው፣ በፈረሳችን እየሸሸን—“እምቢ፣ በሌሎች ነገሮች ስራ በዝቶብናል” ስለምንል ነው። ስለዚህ፣ ከእግዚአብሔር እየራቅን እንሄዳለን፤ በፍጥነት ለመሄድ አጥብቀን እንጠይቃለን፤ እናም በፍጥነት ስንሄድም፣ ሰይጣን በፍጥነት ይከተላል።
ምናልባት በህይወትችን ውስጥ “በእያንዳንዷ ቀን” ለጌታ ጊዜ እንድንሰጥ ፕሬዚዳንት ኔልሰን በተደጋጋሚ የተማፀኑን በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። “ጸጥተኛ ጊዜ ቅዱስ ጊዜ–የግል ራዕይን እና ውስጣዊ ሰላምን የሚያመቻች ጊዜ”፣ እንደሆነ አስታውሰውናል። ነገር ግን የጌታን ድምፅ ለመስማት፣ እንደመከሩን፣ “እናንተም የተረጋጋ መሆን አለባችሁ።”
መረጋጋት ግን ለጌታ ጊዜ ከመስጠት በላይ ነው—ይህም ጥርጣሬአችንን እና የፍርሀት ሀሳቦቻችንን መተው እና ልባችንን እና አዕምሮአችንን በእርሱ ላይ ማተኮርን ያስፈልገዋል። ሽማግሌ ዴቪድ ኤ. ቤድናር እንዳስተማሩት፣ “ጌታ‘ዕረፉ’ ሲል የሠጠው ማሳሰቢያ፣ ካለመናገር ወይም ካለመንቀሳቀስ የበለጠ ነገርን [ያካትታል]።7 ሀሳብ እንዳቀረቡበትም፣ ማረፍ “[በ]አዳኙ ላይ ያለማቋረጥ እንድናተኩ የሚያስታውሰን መንገድ ሊሆን ይችላል።”
ማረፍ ጥረትን የሚጠይቅ የእምነት ስራ ነው። Lectures on Faith [የእምነት ትምህርታዊ መግለጫ] እንደሚጠቁመው፣ “ሰው በእምነት ሲሰራ በአዕሮአዊ ጥረት ይሰራል።” ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዳወጁት፣ “ትኩረታችን መሆን ያለበት በአዳኛችን እና በወንጌሉ ላይ ነው። በሁሉም አስተሳሰባችን ወደ እርሱ እንድንመለከት ማድረግ አእምሮአዊ ጥረትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ነገር ግን እንደዛ ስናደርግ፣ ጥርጣሬያችን እና ፍርሀታችን ይጠፋሉ።” አዕምሮአችን ትኩረት እንዲኖረው ስለማድረግ አስፈላጊነት በመናገር፣ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ኦ. መኬይ እንዲህ ብለዋል፦ “እኔ እንደማስበው ለአምልኮ መርህ ለሆነው ስለማሰላሰል የምንሰጠው ትኩረት በጣም ትንሽ ነው። … ማሰላሰል ወደ ጌታ ፊት ከምናልፍባቸው በጣም የተቀደሱ በሮች አንዱ ነው።”
ለእኔ በእምነት የተሞላ፣ ማረፍ ምን ማለት እንደሆነ የሚያሰላስል ስሜትን የሚያዝል በጃፓን ቋንቋ mui [ሙይ]፣ የሚባል ቃል አለ። ይህም ሁለት ፊደላትን የያዘ ነው (無為)። በግራ በኩል ያለው ፊደል “ምንም” ወይም “ምንምነት” ማለት ነው፣ እንዲሁም በቀኝ ያለውም “ማድረግ” ማለት ነው። አብረው እነዚህም “ምንም ማድረግ” ማለት ናቸው። ቃል በቃል በመውሰድ፣ ይህ ቃል ሲነጻጸር “ምንም አለማድረግ” የሚል የተሳሳተ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። ይህም፣ “ማረፍ” “ከአለመናገር ወይም ከአለመነቃነቅ” ከሚለው ቃል ጋር የተሳሳተ ትርጉም እንደሚሰጠው ሁሉ። ሆኖም ግን፣ “ማረፍ” እንደሚለው ሀረግ፣ ከፍተኛ ትርጉም አለው፤ ለእኔ ይህም እንድንረጋጋ እና በታላቅ መንፈሳዊ እይታ እንድንኖር የሚያስታውሰን ነው።
በእስያ ሰሜን እንደ የአካባቢ አመራር ከሽማግሌ ታካሺ ዋዳ ጋር በማገለግልበት ጊዜ፣ ባለቤታቸው፣ እህት ናኦሚ ዋዳ፣ ታዋቂ የጃፓን ቋንቋ የእጅ ጸሀፊ እንደነበሩ አወቅኩኝ። እህት ዋዳ የ mui፣ ቃልን የጃፓን ቅርፅ እንዲፅፉልኝ ጠየኳቸው። ይህን የእጅ ፅሁፍ በቤቴ ግድግዳ ላይ በማስቀመጥ እንዳርፍ እና በአዳኝ ላይ እንዳተኩር የማስታውስበት እንዲሆን ፈልጌ ነበር። ቀላል ለሚመስለው ጥያቄ ወደያው ባለመቀበላቸው ተደንቄ ነበር።
በሚቀጥለው ቀን፣ ማመንታታቸውን በስህተት መንገድ እንደተረዳሁ በመገንዘብ፣ ሽማግሌ ዋዳ እነዚህን ቃላት መጻፍ ታላቅ ጥረት እንደሚያስፈልገው ገለጹለኝ። የቃላቱን ትርጉም በነፍሳቸው በጥልቅ እስከሚረዱ እና በልባቸው የሚሰማቸውን ለመግለጽ እስከሚችሉ ድረስ የቃሉን ፅንሰ-ሀሳብ እና ገጸ-ባህሪያት ላይ ማተኮር እና ማሰላሰል ያስፈልጋቸው ነበር። በጣም ብዙ ጊዜ የሚፈጀውን እንደ ቀላል አድርጌ በመጠየቄ አፍሬ ነበር። ይህንን ባለማወቄ ይቅርታ መጠየቄን እንዲነግሩልኝ እና እንዲያደርጉ የጠየኩትን እንደሰረዝኩኝ እንዲነግሯቸው ጠየኳቸው።
ከጃፓን ልለቅ ስል፣ እኔ ሳልጠይቃቸው እህት ዋዳ የጃፓን ቃል muiን በሚያምር ሁኔታ የተጻፈ የእጅ ፅሁፍ እንደስጦታ በመስጠት አስደነቁኝ። አሁን ይህም በቤሮዌ ውስጥ በተከበረ ቦታ ላይ ይገኛል፣ ይህም ጌታን በየዕለቱ በሙሉ ልቤ፣ ሀይሌ፣ አዕምሮዬ፣ እና ጉልበቴ፣ እንድፈልገው እና እንዳገለግለው እንዳስታውስ ያደርገኛል። በዚህ ራስ ወዳጅ ባለሆነ ስራ፣ የmui፣ ወይም የመረጋጋት ትርጉምን ሌላ ቃላት ለመግለጽ ከሚችሉት በላይ አደረጉ። ባለማሰብ፣ ወይም በሀላፊነት ስሜት ምክንያት እነዚህን ቅርጾች ከመጻፍ ይልቅ፣ እርሳቸው ይህን የእጅ ጽሁፍ በልብ ሙሉ አላማ እና በእውነት ፍላጎት ለመቅረጽ ጣሩ።
በተመሳሳይ ሁኔታም፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያለንን ጊዜ በእንደዚህ አይነት በልብ የተሞላ አምልኮ እንድናሳልፈው ይፈልጋል። ይህን ስናደርግም፣ አምልኮአችን ለእርሱ ያለን ፍቅር በግለጫ ይሆናል።
ከእርሱ ጋር እንድንነጋገር ይመኛል። አንድ ጊዜ፣ ከቀዳሚ አመራር ጋር በነበረ ስብሰባ ላይ የመዝጊያ ጸሎት ካቀረብኩኝ በኋላ፣ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ወደእኔ ዞር ብለው፣ “ስትጸልይ፣ ስራ በበዛብን ሰዓት እሱ መኖሩን ለማረጋገጥ ጊዜ ስንወስድ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያስደስተው እያሰብኩኝ ነበር” አሉኝ። ይህም ቀላል ቢሆንም እኛ ከጌታ ጋር ለመነጋገርቆም ማለታችን ምን ያህል እንደሚያስደስተው እንድናስታውስ የሚያደርገን ነው።
ምንም እንኳን ትኩረታችንን ቢፈልግም፣ ወደ እርሱ እንድንመጣ አያስገድደንም። ለኔፋውያን፣ ከሞት የተነሳው ጌታ እንዲህ አለ፡ “ዶሮ ጫጩቶችዋን እንደምትሰበስብ ሁሉ እሰበስባችሁ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ፣ እናም እናንተ ግን አልወደዳችሁም።” ይህንንም ለእኛም በአሁን ጊዜ በሚጠቅም በዚህ ተስፋ በሚሰጥ ግብዣ አስከተለ፦ “[ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ ስር እንደምትሰበስብ ስንት ጊዜ እሰበስባችኋለሁ] [ንሰሃ ከገባችሁ እናም በልባችሁ ሙሉ አላማ ወደ እኔ ከተመለሳችሁ]።”
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ወደ እርሱ እንድንመለስ ብዙ ጊዜ እድሎች ይሰጠናል። እነዚህ እድሎች የእለት ጽሎቶችን፣ የቅዱሳት መጻህፍት ጥናቶችን፣ የቅዱስ ቁርባን ስርዓቶችን፣ የሰንበት ቀንን፣ እና የቤተመቅደስ አምልኮን ያካትታሉ። እነዚህን ቅዱስ እድሎች “ከምናደርጋቸው” ዝርዝሮች ውስጥ አውጥተን ወደ “ምንም ማድረግ” ዝርዝራችን ውስጥ ብናስገባቸውስ፤ ይህም ማለት፣ ልክ እህት ዋዳ ለእጅ ፅሁፋቸው እንዳደረጉት እኛው እነዚህ በአንድ አይነት ሀሳባዊነት እና ትኩርት ብናደርጋቸውስ?
“ለዚያ ጊዜ የለኝም” በማለ ታስቡ ይሆናል። እኔም ብዙ ጊዜ እዲህ ተሰምቶኛል። ነገር ግን የሚያስፈልገው ተጨማሪ ጊዜ ሳይሆን፣ ለእግዚአብሔር ባስቀመጥናቸው ጊዜያት ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ እና ትኩረት ማድረግን እንደሆነ ሀሳብ አቀርባለሁ።
ለምሳሌ፣ በመናገር ትንሽ ጊዜ በማሳለፍ እና ከእግዚአብሔር ጋር ብዙ ጊዜ ብናሳለፍስ፤ እንዲሁም ስንናገር፣ በልብ የተሰማ እና ልዩ የምስጋናና ፍቅር መግለጫዎች ብንጠቀምስ?
ፕሬዚዳንት ኔልሰን ቅዱሳት መጻህፍትን ከማንበብ ይልቅ እንድናጣጥማቸው መክረውናል። በትንሹ በማንበብ እና አብዝተን ብናጣጥም ምን አይነት ለውጥ ያመጣል?
ቅዱስ ቁርባንን ለመውሰድ እና የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያን በዚህ ቅዱስ ስራአት ላይ በደስታ ለማሰላሰል አዕምሮአችንን ለማዘጋጀት ተጨማሪ ጥረት ብናደርግስ?
በእብራውያን “እረፍት” የሚል ትርጉም ባለው በሰንበት ቀን፣ ከሌሎች ሀሳቦች ብናርፍ እና ከጌታ ጋር ለእርሱ ያለንን አምልኮት ለማቅረብ በጸጥታ ለመቀመጥ ጊዜ ብንወስድስ?
በቤተመቅደስ አምልኮአችን፣ መመሪያ እንደተሰጠን፣ ትኩረት ለመስጠት ወይም በሰለስቲያል ክፍል ውስጥ በጸጥታ ማሰላሰል ስነስርዓታዊ እና የተተኮረ ጥረት ለማድረግ የምንችል ብንሆንስ?
ትኩረታችን በማድረግ ላይ ያነሰ እና ከሰማይ አባትና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን የቃል ኪዳን ግንኙነት ለማጠናከር የጨመረ ከሆነ፣ እነዚህ እያንዳንዱ ቅዱስ ጊዜያት የሚያበለፅግ፣ እንዲሁም በግል ህይወቶቻችን ውስጥ የሚያስፈልገንን መመሪያዎች እንደምንቀበል እመሰክራለሁ። በሉቃስ ታሪክ ውስጥ እንደነበረችው ማርታ፣ እኛ፣ በአብዣኛው ተጠንቃቂ እና በብዙ ነገሮች የምረበሽ ነን። ሆኖም ግን፣ ከጌታ ጋር በየዕለቱ ስንገናኝ፣ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ያሳውቀናል።
አዳኝም ለማረፍ እና ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ከአገልግሎቱ ጊዜ ወስዷል። ጌታ ጸጥ ወዳለ ቦታ፣ ወደ ተራራ፣ ወደ ምድረበዳ፣ ወደ በረሃ ወይም “ትንሽ ራቅ” ወዳለ ቦታ ለአብ ለመጸለይ እንደሄደ ቅዱሳት መጻህፍት በታሪክ ተሞልተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት እና በእርሱ ለመጠናከር ጸጥ ያለ ቦታ ከፈለገ፣ እኛም እንዲህ ማድረጉ ጥበብ ነው።
ልባችንን እና አዕምሮአችንን በሰማይ አባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስናተኩር እና የመንፈስ ቅዱስን የረጋ ድምጽ ስንሰማ፣ ምን አስፈላጊ እንደሆነ የጠራ አስተያየት ይኖረናል፣ ጥልቅ የሆነ ርህራሄ እናገኛለን፣ እንዲሁም በእርሱም እርፍት እና ጥንካሬ እናገኛለን። ተጻራሪ በሆነ ሁኔታ፣ በመዳን እና ከፍ ከፍ በማድረግ ስራው እግዚአብሔርን ለመርዳት እኛ ረጋ ያለ እንቅስቃሴ እንዲኖረን ያስፈልገን ይሆናል። ሁልጊዜ “በእንቅስቃሴ” ላይ መሆን በህይወታችን ውስጥ ያለውን “ግርግር” ይጨምርበታል እንዲሁም የምንፈልገውን ሰላም ይሰርቀዋል።
ወደ ጌታ በሙሉ ልብ አላማ ስንመለስ፣ በጸጥታ እና በመተማመን እርሱን ልናውቅ እና እርሱ ለእኛ ያለውን መጨረሻ የሌለውን ፍቅር ሊሰማን እንችላለን።
ጌታ እንዲህ ሲል ያጽናናል፦
ጌታ እንዲህ ቃል ገብቷል፣ “ወደ እኔ ቅረቡ እና እኔም ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ ተግታችሁም ፈልጉኝ እናም ታገኙኝማላችሁ።”
እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ካሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ።”
ይህም እውነት እንደሆነ እመሰክራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።