“ይህ የእኔ ወንጌል ነው”—“ይህች የእኔ ቤተክርስቲያን ናት”
ይህ የአዳኝ ወንጌል ነው፣ እንዲሁም ይህች የእርሱ ቤተክርስቲያን ናት (3 ኔፊ 27፥21፤ ሞዛያ 26፥22፤ 27፥13 ተመልከቱ)። የሁለቱ ነገሮች ውህደት ሀይለኛ እና ለውጥ ለማምጣት የሚችል ነው።
ለብዙ ክፍለ ዘመናት በጣም ኃይለኛ ፈንጂ በመሆን ይታወቅ የነበረው ባሩድ ነው። የመድፍ ኳሶችን መተኮስ ይችል ነበር፣ ሆኖም በአብዛኞቹ የማዕድን እና የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ውጤታማ አልነበረም። ዓለትን የመሠባበር ሃይል አልነበረውም።
በ1846 (እ.አ.አ) አስካኒዮ ሶብሬሮ የተባለ ጣልያናዊ የኬሚስትሪ ባለሙያ ናይትሮግሊስሪን የተሠኘ አዲስ ፈንጂ ቀመመ። ይህ ቅባታማ ፈሣሽ ከባሩድ ቢያንስ አንድ ሺህ እጥፍ ሃይል ነበረው። ዓለትን በቀላሉ ለመስበር ይችል ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ናይትሮግሊስሪን በቀላሉ ይፈነዳ ነበር። ከትንሽ ከፍታ ላይ ብትለቁት ይፈነዳል። በጣም ከጋለ ይፈነዳል። በጣም ከቀዘቀዘም ይፈነዳል። በቀዝቃዛ፣ ጨለማ ክፍል ውስጥ ቢቀመጥ እና እዚያው ቢተው እንኳን መጨረሻ ላይ ይፈነዳል። አብዛኛዊቹ አገራት እንዳይጓጓዝ እንዲሁም ብዙዎቹ እንዳይመረት እገዳ ጣሉ።
በ1860 (እ.አ.አ) አልፍሬድ ኖቤል የተባለ ስዊድናዊ ሣይንቲስት ናይትሮግሊስሪን ሣይፈለግ እንዳይፈነዳ የማድረግ ሙከራውን ጀመረ። ከሰባት ዓመታት ምርምር በኋላም ናይትሮግሊስሪንን ዳይአቶሜሸስ ኧርዝ ወይም ኪሴልጉር በመባል ወደሚታወቅ ብዙ ዋጋ ወደሌለው ነገር ውስጥ በመሳብ ግቡን እውን አድርጓል። ኪሴልጉር ወደ ዱቄትነት ሊፈጭ የሚችል ቀዳዳዎች ያሉት ዓለት ነው። ኪሴልጉር ከናይትሮግሊስሪን ጋር ሲደባለቅ ናይትሮግሊስሪንን ስለሚስብ የሚፈጠረው ጭቃ “የዱላ” ቅርፅ እንዲይዝ ሊደረግ ይችላል። በዚህ መልክ ሲሆን ናይትሮግሊስሪን በተሻለ ሁኔታ በቀላሉ አይፈነዳም ነበር። የመፈንዳት ሃይሉ ሳይቀንስ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ሊከማች፣ ሊጓጓዝ እና ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። ኖቤል፣ የናይትሮግሊስሪንን እና የኪሴልጉርን ውሁድ ድማሚት ብሎ ሰይሞታል።
ድማሚት ዓለምን ቀየረ። ኖቤልንም ሃብታም አደረገው። አስካኒዮ ሶብሬሮ እንዳገኘው፣ በቀላሉ እንዳይፈነዳ የሚያደርገው ነገር ባይኖር ኖሮ ናይትሮግሊስሪንን ለንግድ መጠቀም በጣም አደገኛ ነበር። ቀድሜ እንዳልኩት፣ ብቻውን ኪሴልጉር ውስን ዋጋ ነበረው። ነገር ግን የሁለቱ ነገሮች ውህደት ድማሚት ለውጥ የሚያስገኝ እና ውድ ሆኗል።
በተመሳሳይ መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውህደት ሀይለኛ እና ለውጥ የሚያመጣ ጥቅሞችን ያስገኝልናል። ወንጌሉ ፍጹም ነው፣ ሆኖም ይህን ለማስተማር፣ ንፅህናውን ለመጠበቅ እና በአዳኙ ሀይል እና ሥልጣን መሠረት ቅዱስ ሥርአቶቹን ለማከናወን መለኮታዊ ሥልጣን የተሰጣት ቤተክርስቲያን ታስፈልጋለች።
በአዳኙ ወንጌል እና የመጽሐፈ ሞርሞን ነቢይ በሆነው በአልማ የተቋቋመችውን የቤተክርስቲያኑን ውህደት አስቡ። ቤተክርስቲያኗ “ህዝቡን [በሚያዳነው] ጌታ ንስሃንና እምነትን ካልሆነ በቀር ምንም እንዳ[ትሰብክ]” ሃላፊነት ነበረባት። ቤተክርስቲያኗ የእግዚአብሔርን ስልጣን በመጠቀም “እርሱን [በማገልገል] እናም ትዕዛዛቱን [በመጠበቅ … እንደ ምስክርነት ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት በጌታ ስም [በ]መጠመቅ …” የጥምቀትን ሥርዓት እንዲከናወን የማድረግ ሃላፊነት ነበረባት። የተጠመቁት ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳቸው ላይ ወሰዱ፣ ወደ እርሱ ቤተክርስቲያን ተቀላቀሉ፣ እንዲሁም መንፈሱን በብዛት በእነርሱ ላይ እንደሚያፈስላቸው ቃል ተገባላችው።
አልማ ወንጌልን ሲያስተምር ለመስማት ሕዝቡ ወደ ሞርሞን ውሃ ሄዱ። ምንም እንኳን እነዚያን ውሀዎች እና የከበቧቸውን ቃካዎች ቢያከብሯቸውም፣ የጌታ ቤተክርስቲያን ቦታ ወይም ህንጻ አልነበረም፣ ወይም አሁንም አይደለም። በቀላሉ ቤተክርስቲያኗ፣ ጌታ አላማዎቹን እንዲያስፈጽም የምትረዳ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ ተራ ሰዎች በመለኮት በተዘጋጀ መዋቅር የተሰበሰቡባት እና የተደራጁባት ናት። ቤተክርስቲያኗ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ አባት እቅድ ውስጥ ያላቸውን ማዕከላዊ ሚና የምንማርባት መሳሪያ ናት። ቤተክርስቲያኗ ግለሠቦች በሥርዓቶች ውስጥ እንዲሳተፉ እና ከእግዚአብሔር ጋር ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳኖችን እንዲገቡ የሚያደርግ ሥልጣን ያለው መንገድን አቅርባለች። እነዚያን ቃል ኪዳኖች መጠበቅ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ያደርገናል፣ ኃይሉንም እንድንጠቀም ፈቃድ ይሠጠናል፣ እንዲሁም እርሱ እንድንሆን ወደሚፈልገው ዓይነት ሠው ይለውጠናል።
ልክ ድማሚት ያለ ናይትሮግሊስሪን የተለየ እንዳልሆነ ሁሉ፣ የአዳኙ ቤተክርስቲያንም በእርሱ ወንጌል ላይ ከተገነባች ብቻ ነው ልዩ የምትሆነው። አዳኝ ወንጌል እና በዚህ የሚገኙትን ስርዓቶችን ለማስተዳደር ስልጣን ባይኖር ኖሮ፣ ቤተክርስቲያኗ በጣል ልዩ አትሆንም ነበር።
የኪሴልጉር ሣይፈለግ እንዳይፈነዳ የማድረግ ተፅዕኖ ባይኖር ኖሮ ናይትሮግሊስሪን እንደ ፈንጂ የሚኖረው ዋጋ ውስን ይሆን ነበር። በታሪክ እንደታየው፣ የጌታ ቤተክርስቲያን ባትኖር ኖሮ፣ የሰው ልጅ ስለወንጌሉ ያለው ግንዛቤ ወጥነት የጎደለው ይሆን ነበር—ይኸውም፣ ትምህርቶች በጊዜ ሂደት ይለወጡ ነበር እንዲሁም ለተለያዩ ሀይማኖቶች፣ ባህሎች እና ፍልስፍናዎች ተፅእኖ የተጋለጠ ይሆን ነበር። የእነዚያ ተፅዕኖዎች ውህደት እስከዚህ የመጨረሻው ዘመን ድረሥ በእያንዳንዱ ዘመን ታይቷል። ምንም እንኳን በመጀመሪያ ንፁሕ ወንጌል የተገለጠ ቢሆንም፣ መለኮታዊ ስልጣን ያለው ማዕቀፍ ስላልነበረ የዚያ ወንጌል አተረጓጎም እና አተገባበር ቀስ በቀስ ኃይሉን የካደ የአምልኮት መልክ ያዘ።
የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ የክርስቶስን ትምህርት ለማስተማር እንዲሁም የወንጌልን የደህንነት እና በዘለዓለማዊ ሕይወት ከፍ ከፍ የማድረግ ሥርዓቶች ለማከናወን በእግዚአብሔር ሥልጣን ስለተሰጣት የእርሱን ሀይል መጠቀምን ታስችላለች። አዳኙ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ኃይሉን መጠቀም እንድንችል ሊረዳን እንዲሁም ሊለውጠን ይፈልጋል። ስለኃጢአታችን መከራን ተቀብሏል እንዲሁም ከሚገባን ቅጣት ይቅር ሊለን ይፈልጋል። ቅዱሣን እንድንሆን እንዲሁም በእርሱ ፍፁማን እንድንሆን ይፈልጋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን የማድረግ ኃይል አለው። እርሱ ጉድለት ስላለብን የሚራራ እንዲሁም በኃጢአት ምክንያት ለሚመጣብን የዘለዓለም ፍርድ እንዲያው ዝም ብሎ የሚያዝንልን ብቻ አይደለም። አይደለም፣ ከዚያ በላይ አድርጓል፣ እንዲሁም ቤተክርስቲያኑ ሀይሉን ለማግኘት እንድትችል አድርጓል።
ቤተክርስቲያኗ የምታስተምረው የወንጌል ዋና ጭብጥ ኢየሱስ ክርስቶስ “ስቃያችንን ተቀበለ፤ እናም ሀዘናችንን ተሸከመ”። እርሱም “የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።” እርሱም “በመስቀል ታግሶ፣” “የሞትን እሥር” በጠሰ፣ “ወደ ሠማይ [አረገ]፣ እናም በሰዎች ልጆች ላይ ያለውን ምህረት ለመጠየቅ በእግዚአብሔር ቀኝ እጅ በኩል [ተቀመጠ]።” ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ ያደረገው አባቱን እንዲሁም እኛን ስለሚወድ ነው። ሥፍር ቁጥር የሌለውን ዋጋ ከፍሏል፣ በዚህም “እርሱ እምነት ያላቸውን በሙሉ የእርሱ አድርጓል [እናም ጠበቃ] ይሆናል” ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማፅደቅ እና ለመቀደስ ይችል ዘንድ ንስሐ እንድንገባና ወደ እርሱ እንድንቀርብ ከመፈለግ ያለፈ ሌላ ምንም አይሻም። ይህን ፍላጎቱን ለማሣካት አይታክትም እንዲሁም አያወላውልም።
የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ሀይል እና የቃል ኪዳን ፍቅሩ የሚገኝውው በቤተክርስቲያኑ በኩል ነው። የአዳኙ ወንጌል እና የቤተክርስቲያኑ ውህደት ህይወታችንን ይለውጧል። ይህም የእናቴን አያታት ለውጧል። የወንድ አያቴ ኦስካር አንደርሰን በስቶክሆልም ደሴቶች ውስጥ በምትገኘው ሁግማርሰ ደሴት ላይ በመርከብ መሥሪያ ውስጥ ይሠራ ነበር። ሚስቱ አልበርቲና እና ልጆቻቸው በስዊድን ዋናው መሬት ላይ ይኖሩ ነበር። በየሁለት ሳምንቱ ቅዳሜ ቅዳሜ፣ ኦስካር እሁድ ምሽት ወደ ሁግማርሰ ከመመለሱ በፊት በሣምንቱ መጨረሻ ቀናት ጀልባውን እየቀዘፈ ወደቤት ይመጣል። አንድ ቀን ፣ በሁግማርሰ ሳለ፣ ሁለት አሜሪካዊ ሚስዮናውያን ዳግም የተመለሰውን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሲያስተምሩ አደመጠ። ኦስካር የሰማው ነገር ንጹህ እውነት እንደሆነ ተሰማው፣ እንዲሁም ለመናገር በሚያዳግት ደስታ ተሞላ።
በሚቀጥለው ጊዜ ወደ ቤት በተመለሰ ጊዜ ኦስካር ስለሚስዮናውያን ሁሉንም ነገር ለአልበርቲና በደስታ ነገራት። ያስተማሩትን እንዳመነበት ገለፀ። እነርሱ የሰጡትን ፓምፍሌቶች እንድታነባቸው ጠየቃት። እንዲሁም ወደፊት የሚወለዱ ልጆቻቸው አንዳቸውም በጨቅላነታቸው መጠመቅ አለባቸው ብሎ እንደማያስብ ነገራት። አልበርቲና ተናደደችና ፓምፍሌቶቹን በቆሻሻው ክምር ላይ ወረወረቻቸው። ኦስካር እሁድ ምሽት ለስራ ከመመለሱ በፊት በመካከላቸው ብዙም ንግግር አልነበረም።
ልክ እንደሄደ አልበርቲና እነዚያን ፓምፍሌቶች አነሣቻቸው። የእነርሱን ትምህርት ከመጠቀም ብዛት ባረጀው መጽሐፍ ቅዱሷ ውስጥ ካሉት ትምህርቶች ጋር በጥንቃቄ አነፃፀረቻቸው። ያነበበችው ነገር እውነት እንደሆነ በተሠማት ጊዜ ተደነቀች። በሚቀጥለው ጊዜ ኦስካር ወደ ቤት ሲመለሥ፣ ልክ ይዞት የመጣውን መፅሐፈ ሞርሞንን ቅጂ እንደተቀበለችው ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገለት። አልበርቲና አሁንም ትምህርቱን በመጽሐፍ ቅዱሷ ውስጥ ካለው ትምህርት ጋር እያነፃፀረች በጉጉት አነበበች። እንደ ኦስካር ሁሉ ንጹህ እውነት እንደሆነ አወቀች፣ እንዲሁም ለመግለፅ በሚያዳግት ደስታ ተሞላች።
ኦስካር፣ አልበርቲና እና ልጆቻቸው እዚያ ወዳሉት ጥቂት የቤተክርስቲያን አባላት ቀረብ ለማለት ወደ ሁግማርሰ ተዛወሩ። ኦስካር እና አልበርቲና በ1916 (እ.አ.አ) ከተጠመቁ ከአንድ ሣምንት በኋላ፣ ኦስካር የእነዚያ በሁግማርሰ የሚኖሩ ቡድን መሪ እንዲሆን ጥሪ ተሠጠው። ልክ እንደብዙዎቹ ተለዋጮች፣ ኦስካር እና አልበርቲና በአዲሱ እምነታቸው ምክንያት ትችት ገጠማቸው። የአካባቢው ገበሬዎች ለእነርሱ ወተት ሊሸጡላቸው ፍቃደኛ አልሆኑም። ስለዚህም ኦስካር በየዕለቱ ውሃውን እየቀዘፈ በመሄድ መቻቻልን ከሚያውቅ ገበሬ ወተት ይገዛ ነበር።
ሆኖም በቀጣዮቹ ዓመታት፣ በከፊል በአልበርቲና ጠንካራ ምስክርነት እና በጥልቅ የሚስዮናዊ ቅንነት የተነሳ በሁግማርሰ የቤተክርስቲያኗ አባልነት ጨመረ። ቡድኑ ቅርንጫፍ ሲሆን ኦስካር የቅርንጫፍ ፕሬዘዳንት በመሆን እንዲያገለግል ጥሪ ተሠጠው።
የሁግማርሰ ቅርንጫፍ አባላት ለዚያ ደሴት ጥልቅ አክብሮት ነበራቸው። ይህ የእነርሱ የሞርሞን ውሀ ነበር። ስለቤዛቸው ቀስ በቀስ ዕውቀትን ያገኙበት ቦታ ይህ ነበር።
በዓመታት ውስጥ፣ ኦስካር እና አልበርቲና የጥምቀት ቃል ኪዳናቸውን ሲጠብቁ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተለውጠዋል። ተጨማሪ ቃል ኪዳኖች ለመግባት እና የቤተመቅደስ በረከቶችን ለመቀበል በጉጉት ፈለጉ። እነዚያን በረከቶች ለማግኘት፣ ስዊድን ከሚገኘው ቤታቸው ወደ ሶልት ሌክ ሲቲ በ1949 (እ.አ.አ) ለዘለቄታው ተሰደዱ። ኦስካር በሁግማርሰ የሚገኙ አባላት ለ33 አመት መሪ ሆኖ አገለገለ።
የናይትሮግሊስሪን እና የኪሴልጉር ውህደት ድማሚት ዋጋ ያለው እንዲሆን አድርጎታል፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና የእርሱ ቤተክርስቲያን ውህደት በዋጋ የማይተመን ነው። ኦስካር እና አልበርቲና ዳግም ስለተመለሠው ወንጌል የሰሙት የእግዚአብሔር ነቢይ ሚስዮናውያንን ወደ ስዊድን ስለጠራ፣ ስለመደበ እና ስለላከ ነበር። በመለኮት በተሠጣቸው ሥልጣን መሠረት፣ ሚስዮናውያን ኦስካርን እና አልበርቲናን የክርስቶስን ትምህርት አስተምረዋል እንዲሁም በክህነት ስልጣን አጥምቀዋቸዋል። እንደ አባላት፣ ኦስካር እና አልበርቲና መማራቸውን፣ ማደጋቸውን እና ሌሎችን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። የገቧቸውን ቃል ኪዳኖች በመጠበቃቸው የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ሆነዋል።
አዳኙ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን “ቤተክርስቲያኔ” ሲል ይጠራታል ምክንያቱም ወንጌሉን የመስበክ፣ ሥርዓቶቹን እና ቃል ኪዳኖቹን የማከናወን እና በዚህም ኃይሉ ያፀድቀን እና ይቀድሠን ዘንድ መለኮታዊ ዓላማውን ለማስፈፀም ሥልጣን ስለሰጣት ነው። የለቤተክርስቲያኑ፣ ምንም ስልጣን የለው፣ በዝሙ የተገለጹትን እውነቶችን መስበክ የለም፣ ምንም ቃል ኪዳኖች ወይም ስርዓቶች የሉም፣ የአምላክነት አይነት ሀይል ማሳየት አይቻለም፣ ምንም እግዚአብሔር እንድንሆን ወደሚፈልገን ለመለወጥ አይቻለም፣ እንዲሁም እግዚአብሔል ለልጆቹ ያለው እቅድም በከንቱ ይሆናል። በዚህ የዘመን ፍጻሚ ያለችው ቤተክርስቲያን ለእቅዱ ዋና ክፍል ናት።
ራሳችሁን ለአዳኙ፣ ለወንጌሉ እና ለቤተክርስቲያኑ ይበልጥ እንድትሰጡ እጋብዛችኋለሁ። ይህን ስታደርጉ የአዳኙ ወንጌል እና የቤተክርስቲያኗ ውህደት ሃይልን ወደህይወታችሁ እንደሚያመጣ ታውቃላችሁ። ይህ ኃይል ከድማሚት እጅግ የላቀ ነው። በመንገዳችሁ ላይ ያሉትን ዓለቶች ይሰባብራል፣ የእግዚአብሔርን መንግስት ወራሽ ወደመሆን ይለውጣችኋል። እናም እናንተም ለመናገር በሚያዳግት እንዲሁም “በክብር በተሞላ ደስታ የተሞላችሁ” ትሆናላችሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።