ቅዱሳት መጻህፍት_የእምነት መሰረት
ቅዱሳት መጻህፍት ለመለወጥ እና በወንጌል ታማኝ ሆነን እንድንቆይ ስላላቸው ጠቀሜታ አቅልለን ልንመለከት አይገባም።
እኔና ባለቤቴ፣ ሜሪ፣ በቅርቡ የመጽሐፍ ፎቶ እና ከፊት ለፊት የሚነበብ መልእክት የያዘ ቲ ሸርት ተመለከትን፥ “መጻህፍት፦ የመጀመሪያው በእጅ የሚያዝ መሳሪያ።”
ስለዚህ አስደሳች መልእክት እና ሁሉም አይነት በእጅ የሚያዙ መሣሪያዎች ምን ያህል ትልቅ ትርጉም እንዳላቸው አሰብኩ። በተጨማሪ ማሰላሰል ስጀምር፣ ማንኛውም መሣሪያ ወይም ሰው ሠራሽ የማሰብ ችሎታ ያለው ነገር ከመለኮታዊ መገለጥ የሚመጣውን መንፈሳዊ መመሪያ ያህል አስፈላጊ ወይም ታላቅ እንደማይሆን ተገነዘብኩ።
በእጅም ይሁን በዲጂታል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እና መፅሐፈ ሞርሞን፥ ሌላኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ከአለም አዳኝ ከኢየሱስ ክርስቶስ መንፈሳዊ መመሪያ እና ትምህርት ይዘጋጃል። እነዚህ መጻሕፍት፣ እግዚአብሄር ለጥንት ነቢያትና ለሰዎች የሰጠውን መመሪያ እንዲሁም ለግል ሕይወታችን የሚሰጡትን መመሪያ በጽሑፍ በማስፈር ረገድ ላበረከታቸው ከፍተኛ አስተዋጾ እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንመለከታቸዋለን።
እነዚህ የተቀደሱ ቅዱሳት መጻህፍት ሕያው ነቢያት ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር ተጣምረው በዛሬው ዓለም ውስጥ ለእኛ የትምህርት መመሪያ ይሰጡናል። እነዚህ ቅዱሳት መጻህፍት ከጌታ ምሪትን ለሚሹ ግለሰቦች እና ቤተሰቦች መመሪያ፣ እርማት፣ መጽናናትን እና ማጽናኛ ሲሰጡ ትልቅ ኃይል አላቸው።
ቅዱሳት መፅሀፍት፣ ከመንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ መነሳሳት ጋር ተደምሮ፣ የተሰበረ ልብ እና የተዋረደ መንፈስ ላላቸው እና ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ለሚፈልጉ ሰዎች ለመለወጥ የሚያመቻች ዋነኛ ምንጭ ሆነው ይቀጥላሉ። ቅዱሳት መጻህፍት ጠላት እምነትን ለማዳከም የሚያደርገው የማያቋርጥ ጥረት ለመቋቋም የሚያስችል መሰረት ለመገንባት ይረዳሉ።
አዲስ የተለወጡ ሰዎች በዘመናት ሁሉ በቤተክርስቲያኗ ታሪክ አስፈላጊ በመሆን ባርከዋል። አንድ ምሳሌ በተለይ ለእኔ ውድ ነው። ወጣት ኤጲስ ቆጶስ በነበርኩበት ጊዜ፣ ሁለት ድንቅ እህት ሚስዮናውያን የዊልያም ኤድዋርድ ሙስማን ቤተሰብን ያስተምሩ ነበር። አባትየው፣ በጣም ጥሩ ጠበቃ ሲሆን የአንድ ትልቅ ማህበር ዋና አማካሪ ነበር። ታማኝ ሚስቱ ጃኔት ቤተሰቡ ይበልጥ ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት ለመኖር እንዲጣጣር ትረዳ ነበር።
በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኙት ልዩ የሆኑት ወንድና ሴት ልጆቻቸውም እየተማሩ ነበር። አራቱም ትምህርት ያገኙ ሲሆን ወደ ቤተ ክርስቲያንም ይሄዱ ነበር ። እህት ሚስዮናውያን መፅሀፈ ሞርሞንን በማንበብ እና በመጸለይ የዚያን ቅዱስ መፅሀፍ ምስክርነት እንዲያገኙ አጽንኦት ሰጥተው ነበር። በሚገርም ሁኔታ፣ ቤተሰቡ ሙሉ መፅሀፈ ሞርሞንን በአጭር ጊዜ ውስጥ በጸሎት አነበበው።
ቀደም ሲል የአጥቢያ የሴቶች መረዳጃ ማህበር ፕሬዚዳንቶች የነበሩት የካስማ ሚስዮናውያን ወደ ቅዱስ ቁርባን ስብሰባዎች አብረዋቸው ይሄዱ ነበር።
ቤተሰቡ ወደ ጥምቀት እየተቃረበ ሳለ ቤተክርስቲያኑን የሚነቅፍ ትልቅ ጽሑፍ ደረሳቸው። ይህ የሆነው ከኢንተርኔት በፊት ሲሆን ጽሑፉ አንድ ትልቅ ካርቶን ሞልቶ ነበር።
እህት ሚስዮናውያን በቅርቡ በ34 አመቴ ኤጲስ ቆጶስ በመሆን እንደመጠራቴ፣ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንድረዳቸው ጋበዙኝ። በሳሎናቸው ተሰብስበን ሳለ ቤተክርስቲያኑን የሚተቹ ትልልቅ በራሪ ወረቀቶች በክፍሉ መሃል ተቀምጠው ነበር። ይህን ኃላፊነት በጸሎት ጠየኩ። በመክፈቻው ጸሎት ወቅት፣ መንፈስ “እውነት መሆኑን አስቀድሞ ያውቃል” በማለት በሹክሹክታ ነገረኝ። ይህ በጣም አስፈላጊ ነበር። እህቶችም የቀሩት የቤተሰቡ አባላት ምስክርነት እንዳላቸው ያምኑ ነበር ። ስለ አባትየው እርግጠኞች አልነበሩም ።
ወዲያው እንዲህ ብዬ ነገርኩት መንፈስ አስቀድሞ ምስክርነት እንዳለው አሳውቆኝ ነበር። “ይህ እውነት ነው?” በትኩረት ተመለከተኝ እና መንፈስ የመፅሐፈ ሞርሞንን እና የቤተክርስቲያኗን እውነት መሆን እንዳረጋገጠለት ተናገረ።
ከዚያም መንፈሳዊ ማረጋገጫ ካገኙ በራሪ ወረቀቶቹን መከለስ ያስፈልግ እንደሆነ ጠየቅሁት።
አባትየው አስፈላጊ እንዳልሆነ ገለጸልኝ። የቀሩት የቤተሰቡ አባላት በምላሹ ተስማምተው ነበር።
አንድ ትልቅ ጥያቄ እንዳላቸው ተናግረ፡ ቤተክርስቲያንን የሚቃወሙ ብዙ ጽሑፎች የተቀበሉበት አንዱ ምክንያት፣ የሌላ እምነት አባላት በመሆናቸው ነበር። በተጨማሪም፣ ለዚያ እምነት አዲስ የጸሎት ቤት ለመገንባት ትልቅ ስጦታ ለመስጠት ቃል ገብቶ ነበር። እህት ሚስዮናውያን የአስራትን አስፈላጊነት አስተምረውት እንደነበር ነገረኝ፣ ይህንንም በአመስጋኝነት ተቀበለው፣ ነገር ግን ቀደም ሲል የገባውን ቃል ማክበርም ስህተት ይሆን ብሎ አሰበ። ቃል የገባውን የስጦታ መክፈሉ የተከበረ እና ተገቢ እንደሚሆን አረጋገጥኩለት።
መላው ቤተሰብ ተጠመቀ ። ከአንድ አመት በኋላ በኦክላንድ ካሊፎርኒያ ቤተመቅደስ ውስጥ እንደ ቤተሰብ ታተሙ። በቦታው የመገኘት እድል አግኝቼ ነበር። ልጁ የህግ ትምህርትን አጠናቀቀ፣ የካሊፎርኒያ ባር ፈተናን አለፈ እና ወዲያውኑ በጃፓን ታማኝ ሚስዮኑን አገለገለ። ተተኪዎቹ ትውልዶች ለወንጌል ታማኝ ሆነው ሲቀጥሉ ባለፉት አመታት ተመልክቻለው። በአንደኛው የልጅ ልጃቸው መታተም ላይ የመካፈል እድል አግኝቼ ነበር።
በዘመናችን እየታዩ ያሉ ለውጦችም አስደናቂ ናቸው። ባለፈው ሰኔ ወር አሰልጣኝ አንዲ ሬይድ፣ የካንሳስ ከተማ ዋና የእግር ኳስ አሰልጣኝ እና እኔ፣ ከሌሎች ጋር በመሆን እምነታችንን እና የሌሎችን እምነቶች ወክለው፣ በኒውዮርክ ከተማ በሪቨርሳይድ ቤተክርስቲያን በተካሄደ የባለብዙ እምነት ዝግጅት ላይ ንግግር አድርገን ነበር። አሰልጣኝ ሬይድ ለግብዣዎች እና እድሎች ምላሽ ስለሚሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ማዕከል ስለሆነው ስለ ሁለተኛ እድል አፅንዖት ሰጥተዋል። በማግስቱ ጥዋት፣ ከሚስቶቻችን ታሚ ሪድ እና ሜሪ ጋር፣ በማንሃታን ሁለተኛ አጥቢያ በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ ተገኘን። መንፈሳዊ አገልግሎት ነበር። በጉባኤው ውስጥ ብዙ አዳዲስ አማኞች ነበሩ። አምስት በቅርብ የተጠመቁ አባላት፣ አራት ወንዶች እና አንዱ ወጣት፣ ቅዱስ ቁርባንን ከሚያሳልፉ የአሮናዊ ክህነት አባላት መካከል ነበሩ። ተመሳሳይ የአዳዲስ አባላት ፍልሰት በመላው ቤተክርስቲያኑ እየተከሰተ መሆኑን ስገልጽ ደስተኛ ይሰማኛል።
ለቅዱስ ግብዣዎች ምላሽ ለሚሰጡ፣ ሕይወታቸውን ለሚለውጡ እና ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል እድሉን የሚቀበሉ ሰዎች ላይ ለሚታየው ጉልህ እድገት አመስጋኞች ነን። በመጽሐፍ ቅዱስ እና በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ እንደተማሩት በእምነት፣ በንስሃ፣ በጥምቀት እና በማረጋገጫ ወደ ቃል ኪዳኑ መንገድ ይገባሉ።
ቅዱሳት መጻህፍት ለመለወጥ እና በወንጌል ታማኝ ሆነን እንድንቆይ ስላላቸው ጠቀሜታ አቅልለን ልንመለከት አይገባም። በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የነበሩት ነቢያት ስለአዳኙ ተልዕኮ ያውቁና ወንጌሉንም ያስተምሩ ነበር። መፅሐፈ ሞርሞንን ስንማር፣ ስንረዳ እና ትምህርቶቹን በተግባር ላይ ስናውል ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ይረዳናል። ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ “አንድ ወንድ [ወይም ሴት] ከማንኛውም መጽሐፍ ይልቅ [የመጽሐፉን] መመሪያዎችን በማክበር ወደ እግዚአብሔር ይቀርባሉ”በማለት አስተምሯል።
መፅሐፈ ሞርሞን የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለማወቅ፣ ማንበብ፣ ማሰላሰል እና መጸለይ ከዚያም ደግሞ በመመሪያዎቹ መሰረት መመላለስ ያስፈልገናል። ነብዩ ሞሮኒ በቅን ልብ፣ በእውነተኛ ሀሳብ እና በክርስቶስ በማመን ስንጸልይ እግዚአብሔር የመጽሐፉን እውነተኛነት እንደሚገልጥልን ቃል ገብቷል። መጽሐፈ ሞርሞንን ማጥናት ዘላቂ ለሆነ መለወጥ አስፈላጊ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ እና በመፅሐፈ ሞርሞን መካከል ያለውን ግንኙነት፣ በእጅ እንደሚያዙ መሳሪያዎች ስናሰላስል፣ አንድ ሰው ጥያቄ ሊጠይቅ ይችላል። ጌታ ሁለቱ መጽሃፎች “በአንድነት” እንደሚጣመሩ እና “በእጅህም ውስጥ አንድ ይሁኑ” ብሎ ቢያውጅ ምን ያህል ጠቃሚ እና አጋዥ ይሆናል ብላችሁ ታስባላችሁ? ስለ “ይሁዳ በትር”፣ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ እንዲሁም ስለ “ዮሴፍ በትር”፣ በመጽሐፈ ሞርሞን ጌታ የተናገረው ይህ ነው።
በብዙ ጉልህ ጉዳዮች፣ መፅሐፈ ሞርሞን መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጎላ እና የሚያንጽ መሠረታዊ ትምህርት ይሰጣል። የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ትምህርት ጥልቅ ምሳሌ ነው።
መፅሃፍ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት እና ትንሳኤ ጨምሮ ምድራዊ አገልግሎቱ ትክክለኛ ዘገባ ይሰጣል። መፅሐፈ ሞርሞን ከመሞቱ በፊት ነቢያት በዝርዝር ስላብራሩትን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሀጢያት ክፍያ ይበልጥ በግልጽ ያስቀምጣል።
የአልማ ምዕራፍ 42 ርዕስ የኢየሱስ ክርስቶስ የሀጢያት ክፍያ ትምህርት ያለውን አስፈላጊነት ያንጸባርቃል ።
እንዲህ ይላል፦ “ሟችነት ሰዎችን ንስሃ እንዲገቡ እናም እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ የሚያስችል የሙከራ ጊዜ ነው—የአዳም መውደቅ በሰው ዘር ሁሉ ላይ ጊዜያዊ እናም መንፈሳዊ ሞትን አመጣ—ቤዛነት በንስሃ አማካይነት ይመጣል—እግዚአብሔር እራሱ ለዓለም ኃጢያት ክፍያን ይከፍላል—ንሰሃ የሚገቡ ምህረትን ያገኛሉ—ሌሎች በሙሉ በእግዚአብሔር ፍትህ ስር ናቸው—ምህረት በኃጢያት ክፍያው አማካኝነት ይመጣል—እውነተኛ ንስሃ ገቢዎች ብቻ ይድናሉ።”
ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን “መፅሐፈ ሞርሞንን በጸሎት መንፈስ በየቀኑስታጠኑበየቀኑየተሻሉ ውሳኔዎችን እንደምትወስኑ ቃል እገባለሁ” በማለት ተናግረዋል በተጨማሪም “በየቀኑ ራስችሁን በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ስታጠልቁ፣ በየእለቱ ክፋን መከላከያ እንደሚኖራችሁ ቃል እገባለሁ”ብለዋል።
እንደገለጽኩት፣ አዲስ በእጅ የሚያዝ መሣሪያ-መጽሐፍ ጽንሰ ሐሳብ አስደንቆኝ ነበር ነገር ግን፣ ዛሬ በአለም ላይ ያለውን የኢንተርኔት አስደናቂ አስፈላጊነት እገነዘባለሁ። አንድ ዘመናዊ በእጅ የሚያዝ መሣሪያ በታሪክ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት የሚሞላ መረጃ ሊሰጥ ይችላል። በዚህ ዘመን ውስጥ በመኖራችን አመስጋኞች ነን ። በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍት እና የቤተክርስቲያን መሳሪያዎች በዲጂታል መልክ እንዲገኙ ስለሚያስችሉ አመስጋኝ ነኝ። ኢንተርኔት ወንጌልን ለማጥናት ኃይል ያለው መሳሪያ ነው። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በቴክኖሎጂ ተጠቅመው ለጓደኞቻቸው ጥቅሶችን ያካፍላሉ ። ለምሳሌ፣ የመፅሐፈ ሞርሞን መተግበሪያ ለጓደኞቻችሁ መፅሐፈ ሞርሞን ለማስተዋወቅ የሚያስችል ግሩም መንገድ ነው፤ እንዲሁም በየትኛውም ቦታ ብትሆኑ በቀላሉ በተለመደ እና ተፈጥሮዊ በሆነ መንገድ ልታካፍሉ ትችላላችሁ።
ኢንተርኔት ብዙ በረከቶችን ቢቢኖሩትም፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ቀደም ሲል የገለጽኳቸውን አይነት ቤተክርስቲያን የሚተቹ ጽሁፎች ጥርጣሬን ለመፍጠር እና ክቡር የወንጌል መርሆች ላይ እምነትን ለማዳከምም ጥቅም ላይ ውሏል። ፕሬዚዳንት ኔልሰን የጠቀሱት “የዘመኑ ክፉቶች” አካል ሊሆን ይችላል።
ጠላት እና እርሱን የሚረዱት፣ አውቀውም ሆነ ሳያውቁት፣ ቀደም ሲል የገለጽኩትን ቤተክርስቲያን የሚተች ጽሑፍ የሞላበትን ሳጥን ከእግዚአብሔር እውነት ለማራቅ በማሰብ በኢንተርኔት ፈጥረዋል።
ባለፉት ዓመታት ጥርጣሬ ለመፍጠር የተነሱት አከራካሪ ጉዳዮችም በሚያስደንቅ ሁኔታ ተመሳሳይ ናቸው። በተለይ በ20ዎቹ እድሜ ላይ ከነበርኩበት ከ1960ዎቹ ጋር የእኛን ዘመን ስታወዳድሩ ይህ እውነት ነው።
ቅዱሳት መጻህፍት በሁሉም ነገር እንድንዳኝ እና ጥበበኞች እንድንሆን ያስተምሩናል። ኢንተርኔትን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ወይም ጎጂ በሆነ መንገድ መጠቀም ይቻላል።
የረጅም ጊዜ አባላትም ሆኑ ወንጌልን የሚያጠኑት ስለሚመለከቷቸው ነገር አስበው መሆን አለበት። ሥነ ምግባር የጎደለው ፣ ሐቀኝነት የጎደለው ወይም ዓመጽ ባለበት ነገር አትዝናኑ ። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ፣ እነዚህ ስልቶች እምነትን ወደሚያጠፋ እና ዘላለማዊ እድገትህን ወደሚያሳጣ መንገድ ሊመሩ ይችላሉ። አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድርባችሁ ይችላል። ጽድቅን ፈልጉ፤ እንዲሁም በኢንተርኔት ላይ ለመተው የሚከብዱ ተስፋ የሚይሳቆርጡ ነገሮችን እና ብዙ ሰዓት በመጠቀም ራሳችሁን ማስጨነቅ ተው። ሕይወታችሁን በአዎንታዊና በጽድቅ ሐሳቦች ሙሉ፣ ደስተኛ ሁኑ፣ ተዝናኑ፣ ነገር ግን ከስንፍና ራቁ። እዚህ ላይ ልዩነት አለ። 13ኛው የእምነት አንቀጽ ድንቅ መመሪያ ነው። ከሁሉም በላይ፣ መንፈስን ወደ ህይወታችሁ በሚስበው እና እውነትን ከስህተት ለመለየት በሚረዳው መፅሀፈ ሞርሞን ውስጥ ዘወትር ተጠመቁ።
በምንም መንገድ ከቃል ኪዳን መንገድ ለራቁት፣ ምክሬ ወደ ቅዱሳት መጻህፍት፣ ትንቢታዊ መመሪያ፣ በቤት ውስጥ ሃይማኖታዊ አከባበር፣ እና የእምነት ሙዚቃ መመለስን ነው። እያንዳንዱ ነፍስ ለእግዚአብሔር ውድ ነው። እንፈልጋችኋለን! ጌታ ይፈልጋችኋል፣ እናንተም እርሱ ያስፈልጋችኋል። ሁሌም ተቀባይነት አላችሁ። በብዙ አመት የቤተክርስቲያን አገልግሎቴ፣ ወደ ቃል ኪዳን መንገድ የተመለሱትን እና ያገለገሉትን እና ሁሉንም የባረኩትን፣ እና ያገኟቸውን ሁሉ የወደዱትን ድንቅ ሰዎች ከፍ አድርጌ እመለከታለሁ።
የተቀደሱ ቅዱሳት መጻህፍት እና ህያው ነቢያት፣ አፍቃሪ የሰማይ አባት የደስታ እቅዱን ለልጆቹ በሙሉ የሚያቀርብበት ዋነኛ መንገድ ናቸው።
ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮት እና ስለ ሀጢያት ክፍያው እውነታ እርግጠኛ ምስክርነቴን እሰጣለሁ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።