አጠቃላይ ጉባኤ
ወደ ደሥታ ቤተክርስቲያን እንኳን በደህና መጣችሁ።
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


13:2

ወደ ደሥታ ቤተክርስቲያን እንኳን በደህና መጣችሁ።

በአዳኛች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የሚያድን ህይወት እና ተልዕኮ ምክንያት፣ በምድር ላይ ከሚገኙት ሁሉ ደስተኛ የሆንን ሰዎች ለመሆን—እንዲሁም የሚገባን—ለመሆን እንችላለን።

በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል ለመሆን የተጠመቅኩት በ1987 (እ.አ.አ) የገና ዋዜማ ወደ 37 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ነበር። ያ በህይወቴ እና በዘለዓለማዊ ጉዞዬ ውስጥ በእውነት አስደናቂ ቀን ነበር፤ ስለዚህም መንገዱን ያዘጋጁ እና ወደዚያ ወደ አዲስ ውልደት ውሃ ያመጡኝን ጓደኞቼን በጥልቅ አመሰግናቸዋለሁ።

ጥምቀታችሁ ትናንትም ይሁን ከዓመታት በፊት፣ የምትሠበሠቡት በትልቅ ብዙ አጥቢያ ባለው ቤተክርስቲያን ህንጻ ውስጥም ሆነ የሳር ክዳን ባለው መጠለያ፣ አዳኙን ለማሰብ ቅዱስ ቁርባንን የምትቀበሉት በታይኛም ይሁን በስዋሂሊኛ፣ ወደ ደሥታ ቤተክርስቲያን እንኳን ደህና መጣችሁ ልላችሁ እወዳለሁ! ወደ ደሥታ ቤተክርስቲያን እንኳን በደህና መጣችሁ!

የደሥታ ቤተክርስቲያን

የሰማይ አባታችን ለእያንዳንዱ ልጆቹ ባለው የፍቅር ዕቅድ እንዲሁም በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ህይወት እና ተልዕኮ የተነሣ በምድር ላይ እጅግ ደስተኞቹ ሰዎች ለመሆን እንችላለን —እንዲሁም መሆን— አለብን! ብዙ ጊዜ መከራ በበዛበት ዓለም ውስጥ ያሉ አስቸጋሪ የህይወት ፈተናዎች ጥልቅ ተፅዕኖ ሲያሳድሩብንም እንኳን፣ በክርስቶስ ምክንያት ባለን ተስፋ እና መልካም በሆነው የደሥታ ዕቅድ ውስጥ ያለንን የራሣችንን ቦታ በማወቃችን ምክንያት እያደገ የሚሄድ እንዲሁም ዘላቂ የሆነ የደስታ ሥሜትን እና ውስጣዊ ሠላምን ማዳበር እንችላለን።

የጌታ የመጀመሪያው ሐዋርያ የሆኑት ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን፣ የቤተክርስቲያኗ ፕሬዚዳንት ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በተናገሩት በእያንዳንዱ ንግግር በሚባል ደረጃ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከል ካደረገ ሕይወት ስለሚመጣ ደስታ ተናግረዋል። ነገሩን በአጭሩ እንዲህ ገልፀዋል፦ “ደሥታ ከእርሱና በእርሱ ምክንያት ይመጣል።… ለኋለኛው ቀን ቅዱሳን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ደሥታ ነው!”

እኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት ነን። እኛ የደሥታ ቤተክርስቲያን አባላት ነን። ስለዚህም፣ የደሥታ ሁሉ ምንጭ የሆነውን ለማምለክ በእያንዳንዱ የሰንበት ዕለት በቅዱስ ቁርባን ስብሰባዎች አንድ ላይ ከምንሰባሰብበት የበለጠ እንደ ህዝብ ያለን ደስታ የሚገለጥበት አንድም ቦታ ሊኖር አይገባም! እዚህ የጌታ እራት የሆነውን ቅዱስ ቁርባንን፣ ከኃጢአት ኩነኔ እና ከሞት መዳናችንን እንዲሁም የአዳኙን ኃያል ፀጋ ለማስታወስ ከአጥቢያችን እና ከቅርንጫፍ ቤተሰቦቻችን ጋር እንሰበሰባለን። እዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘውን የደስታ፣ የመሸሸጊያ፣ የይቅርታ፣ የምስጋና እና የአባልነት ተሞክሮን ለማግኘት እንመጣለን!

ይህ በክርስቶስ በጋራ የምታገኙት የመደሰት መንፈስ ነው? የምታመጡት ይህንን ነው? ምናልባት ይህ ከእናንተ ጋር እምብዛም ግንኙነት እንደሌለው ታስቡ ይሆናል፤ ወይም ምናልባት ነገሮች ሁልጊዜ የሚደረጉበትን መንገድ ለምዳችሁት ይሆናል። ነገር ግን፣ ዕድሜያችን እና ጥሪያችን ምንም ይሁን ምን የቅዱስ ቁርባን ስብሰባዎቻችን በደስታ የተሞሉ፣ በክርስቶስ ላይ ያተኮሩ፣ ሊሆኑ የሚችሉትን ያህል መልካም አቀባበል የሚደረግባቸው ጊዜያት፣ የደስታ ጥልቅ የአክብሮት መንፈስ ያለው ለማድረግ ሁላችንም አስተዋፅዖ ልናደርግ እንችላለን።

የደስታ ጥልቅ አክብሮት

የደስታ ጥልቅ አክብሮት? “ይህ እውነት ነው?” ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ። በእርግጥም፣ አዎ፣ ነው! አምላካችንን በጥልቅ እንወደዋለን፣ በነገሮች ሁሉ እናከብረዋለን እንዲሁም ክብር እንሠጠዋለን፣ ጥልቅ አክብሮታችን የሚፈሥሠውም በክርስቶስ የተትረፈረፈ ፍቅር፣ ምህረት እና ደኅንነት ከምትደሰት ነፍስ ነው! ይህ ለጌታ የሚሠጠው የደስታ አክብሮት የቅዱስ ቁርባን ስብሰባዎቻችን መለያ ሊሆን ይገባል።

ይሁን እንጂ ለብዙዎች ጥልቅ አክብሮት የሚባለው በጣም ለረዥም ሰዓት አጥብቀን እጅ በደረት ማድረግ፣ አንገታችንን መድፋት፣ ዓይኖቻችንን መጨፈን እና አለመንቀሣቀስ ማለት ብቻ ነው! ይህ ምናልባት ኃይለኛ ልጆችን ለማስተማር የሚረዳ መንገድ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም፣ እያደግን እና እያወቅን ስንሄድ ጥልቅ አክብሮት ከዚህ እጅግ የላቀ መሆኑን እንመልከት። አዳኙ ከእኛ ጋር ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ነበር የምንሆነው? አይደለም፣ ምክንያቱም “[በእርሱ] ዘንድ የደስታ ሙላት [አለ]”!

መልካም፣ ለብዙዎቻችን ይህ በቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ላይ ሊደረግ የሚገባው ለውጥ ልምምድ ይጠይቃል።

መሣተፍ ከማምለክ ጋር ሲነጻጸር

በሰንበት ዕለተ የምንሰበሰበው በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ ከተገኘን በኋላ ልናደርጋቸው ከሚገቡን ዝርዝሮች ውስጥ ልንሠርዘው ብቻ አይደለም። የምንሠበሠበው ለአምልኮ ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ጉልህ ልዩነት ይህ ነው። መሣተፍ ማለት በቦታው መገኘት ማለት ነው። አምልኮ ማለት ግን በታሠበበት እኛን በሚለውጠን መንገድ አምላካችንን ማመስገን እና መውደድ ማለት ነው!

በመድረክ ላይ እና በተሰብሣቢዎች መካከል

አዳኙን እና እርሱ እንዲሆን ያስቻለውን ቤዛ ለማስታወስ የምንሰበሰብ ከሆነ፣ ፊታችን ደሥታችንን እና ምስጋናችንን የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት! ሽማግሌ ኤፍ.ኤንዚዮ ቡሼ የቅርንጫፍ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ፣ በአንድ ወቅት ከተሠብሣቢዎች መካከል የነበረ አንድ ልጅ በመድረክ ላይ ሣሉ ተመልክቷቸው ጮክ ብሎ፣ “እንዲህ አይነት ጨካኝ ፊት ያለው ሰው እዚያ ምን ይሠራል?” ብሎ ስለጠየቀበት ታሪክ ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ የሚቀመጡት—ተናጋሪዎች፣ መሪዎች፣ መዘምራን—እና የስብሠባው ታዳሚዎች ፊታቸው ላይ በሚያሣዩት ገፅታ አማካኝነት “ወደ ደስታ ቤተክርስቲያን እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚለውን መልዕክት አንዳቸው ለሌላቸው ያስተላልፋሉ!

መዝሙር መዘመር

በሚዘመርበት ጊዜ የድምፃችን ጥራት የቱንም ያህል ቢሆን አምላካችንን እና ንጉሣችንን ለማመስገን አብረን እንዘምራለን ወይስ ቃላቶቹን እናጉረመርማለን ወይም አንዘምርም? “የጻድቃን መዝሙር [በእግዚአብሔር] ዘንድ ጸሎት” እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ዘግበዋል። ስለዚህ እንዘምር! እናመስግነው!

ንግግሮች እና ምሥክርነቶች

ንግግሮቻችንን እና ምስክርነቶቻችንን በሰማይ አባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ወንጌላቸውን በትህትና በመኖር ፍሬዎች፣ ይኸውም “ከጣፋጮች በላይ ጣፋጭ” በሆኑት ፍሬዎች ላይ እናተኩር። ከዚያም በእውነት “ … እርሃባ[ችን] እስከሚጠፋና ጥማታች[ን] እስኪቆረጥ ድረሥ እንኳን … [እንመገባለን]” በልጁም ደሥታ አማካኝነት ሸክማች[ንን] [ያቀልልናል]።

ቅዱስ ቁርባን

የአገልግሎቶቻችን ታላቅ የትኩረት ነጥብ ቅዱስ ቁርባኑን ራሱን መባረክ እና መውሰድ ነው፤ ዳቦ እና ውሃው የጌታችንን የኃጢያት ክፍያ ሥጦታ እና አጠቃላይ የመሰብሰባችንን ዓላማ ይወክላል። ይህም “የመንፈሣዊ መታደሥ ቅዱስ ጊዜ”፣ እንዲሁም ሁል ጊዜ አዳኙን እንድናስታውስ፣ ትዕዛዛቱን እንድንጠብቅ እና ስሙን በእኛ ላይ እንድንወስድ ቃል ኪዳን እንደገና የምንገባበት ጊዜ ነው።

በሕይወታችን የተለያዩ ጊዜያት፣ በሃዘን ውስጥ ሆነን እና ብዙ ሸክሞችን ተሸክመን ወደ ቅዱስ ቁርባን ልንመጣ እንችላለን። በሌሎች ጊዜያት፣ ከጭንቀት እና ከችግር ነፃ ሆነን እና ሸክም ሳይኖርብን እንመጣለን። ዳቦው እና ውሃው በሚባረክበት ጊዜ በትኩረት ስናዳምጥ እንዲሁም እነዚያን የተቀደሱ ምልክቶች ስንወሥድ፣ የአዳኙን መስዋዕትነት፣ ይኸውም በጌቴሴማኒ ስለመሠቃየቱ፣ በመስቀል ላይ ስላሣለፈው ጭንቀት እና ለእኛ ሲል ስላሳለፈው ሀዘን እና ስቃይ ለማሰላስል እንፈልጋለን። የእኛን መከራ ከእርሱ መከራ ጋር ስናገናኝ፣ ያ ነው ለነፍሳችን እፎይታን የሚሠጠው። በሌላ ጊዜያት ደግሞ፣ የኢየሱስ ድንቅ ስጦታ በዚህ እና በዘለዓለማዊ ሕይወታችን እንዲሳካ ስላደረገው ግሩም እና ጣፋጭ ደስታበአመስጋኝነት እንደነቃለን! ወደፊት ለሚመጣውን እንደሰታለን—ከውድ አባታችን እና ከተነሳው አዳኛችን ጋር ለሚሆነው ተወዳጅ ዳግም ግንኙነት።

የቅዱስ ቁርባን ዓላማ በሳምንቱ ውስጥ ሁሉንም ጥፋት የፈፀምንባቸውን መንገዶች ብቻ እያሠብን አግዳሚው ላይ መቀመጥ ነው ብለን መገመትን ተለማምደን ይሆናል። ሆኖም የዚህን ተቃራኒ እናድርግ። በፀጥታው ውስጥ፣ ጌታ በዚያ ሣምንት በሚያስደንቅ ፍቅሩ ከእኛ ጋር ሲሆን ያየንባቸውን ብዙ መንገዶች ማሰላሰል እንችላለን! “በየዕለቱ ንስሀ በመግባት የሚገኘውን ደስታ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማሠብ እንችላለን። አዳኙ በችግሮቻችን እና በአሸናፊነታችን ውስጥ ለገባባቸው ጊዜያት እንዲሁም ለፀጋው፣ ለይቅርታው እና ችግሮቻችንን ለማሸነፍ እና ሸክማችንን በትዕግስት እና በደስታ ለመሸከም ሃይሉ ለተሰማን አጋጣሚዎች ምስጋናችንን ልናቀርብ እንችላለን።

አዎን፣ ስለኃጢአታችን በአዳኛችን ላይ ስለደረሱበት መከራዎች እና ፍትሕ መጓደሎች እናሰላስላለን፣ በርግጥ ያ በጥሞና ማሰብን ያስከትላል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እዚያው እንቆማለን—በአትክልቱ ስፍራ፣ በመስቀሉ ላይ፣ በመቃብሩ ውስጥ። ወደ መቃብሩ መከፈት፣ ወደ ሞት መሸነፍ እንዲሁም ሰላም ከማግኘት እና ወደ ሠማያዊ ቤታችን ከመመለስ በሚያግዱንን ነገሮች ሁሉ ላይ ክርስቶስ ወዳገኘው ድል ከፍ ወዳለው ደሥታ መሄድ አንችልም። በቅዱስ ቁርባን ጊዜ የምናፈሠው እንባ የሀዘንም ይሁን የምስጋና፣ አብ በሠጠው በልጁ ስጦታ ምሥራች ምክንያት በሚያስደሥት መገረም ይሁን!

ትናንሽ ወይም ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ያሏቸው ወላጆች

እንግዲህ ትናንሽ ወይም ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ላሏቸው ወላጆች፣ በቅዱስ ቁርባን ጊዜ እንቅሥቃሴ የሌለበት እና ፀጥ ያለ የማሰላሰያ ጊዜ የሚባል ነገር የለም። ሆኖም ትናንሽ ልጆቹን ያለማቋረጥ ስትንከባከቡ ከአዳኙ እና በአዳኙ ምክንያት የሚሰማችሁን ፍቅር፣ ምስጋና እና ደስታ ምሳሌ በመሆን ሣምንቱን ሙሉ በአጫጭር ጊዜዎች ማስተማር ትችላላችሁ። ይህን ለማሣካት የሚደረግ ምንም ዓይነት ጥረት ከንቱ አይሆንም። እግዚአብሔር እናንተን በደንብ ያውቃል።

የቤተሰብ፣ የአጥቢያ እና የቅርንጫፍ ምክር ቤቶች

በቤት እንደምናደርገው፣ በቤተክርስቲያን ለሚኖረን ጊዜ ተስፋችንን እና የምንጠብቃቸውን ነገሮች ማሳደግን ልንጀምር እንችላለን። በቤተሰብ ሸንጎዎች ውስጥ፣ ሠዎች የደሥታ ቤተክርስቲያንን እንዲቀላቀሉ እያንዳንዱ ግለሠብ እንዴት ትርጉም ባለው መንገድ የአቀባበል አስተዋፅዖ ማድረግ እንደሚችል ለመወያየት እንችላለን! በቤተክርስቲያን አስደሳች ተሞክሮ እንዲኖረን ልናቅድ እና ልንጠብቅ እንችላለን።

የአጥቢያ ምክር ቤቱ ለቅዱስ ቁርባን ጊዜያችን የደሥታ ጥልቅ አክብሮት ባህልን ሊያስብ እና ሊፈጥር እንዲሁም ይህንን ለማገዝ ተግባራዊ እርምጃዎችን እና የዕይታ ምልክቶችን መለየት ይችላል።

ደሥታ

ደሥታ ለተለያዩ ሰዎች የተለየ መልክ አለው። ለአንዳንዶች መግቢያ በሩ ላይ የሚቀርብ ሞቅ ያለ ሠላምታ ሊሆን ይችላል። ለሌሎች ደግሞ፣ ሰዎችን በፈገግታ እና በደግነት እንዲሁም ለመርዳት ዝግጁ በመሆን አጠገባቸው በመቀመጥ ምቾት እንዲሰማቸው በፀጥታ መርዳት ሊሆን ይችላል። የተገለሉ ወይም በዳርቻ ላይ እንዳሉ ለሚሰማቸው ሰዎች፣ የዚህ አቀባበል ሙቀት ወሳኝ ይሆናል። በመጨረሻም፣ አዳኙ የቅዱስ ቁርባን ጊዜያችን እንዴት እንዲሆን እንደሚፈልግ እራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። እያንዳንዱ ልጆቹ አቀባበል እንዲደረግላቸው፣ እንክብካቤ እንዲያገኙ፣ እንዲማሩ እና እንዲወደዱ የሚፈልገው እንዴት ነው? እርሱን በማስታወስ እና በማምለክ ለመታደስ ስንመጣ እንዴት እንዲሰማን ይፈልጋል?

መደምደሚያ

በእምነት ጉዞዬ መጀመሪያ ላይ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘው ደሥታ የመጀመሪያው ታላቅ ግኝቴ ነበር፣ በሕይወቴ ላይም ጉልህ ተፅዕኖ አሣድሯል። ይህንን ደሥታ ገና ያላገኛችት ከሆነ፣ ፍለጋውን ጀምሩት። ይህ የአዳኙን የሰላም፣ የብርሃን እና የደሥታ ሥጦታ ለመቀበል የቀረበ ግብዣ ነው—የቀረበውም በየሠንበቱ በእርሡ ራሥን ለማስደሠት፣ በእርሡ ለመደነቅ እና በእርሡ ሐሴት ለማድረግ ነው።

አሞን በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ እንዲህ ሲል በተናገረ ጊዜ የልቤን ሥሜት ገልጿል፦

“አሁን ለመደሰት ምክንያት የለንምን? አዎን፣ እንዲህ እላችኋለሁ ከዓለም መፈጠር ጀምሮ እንደ እኛ ለመደሰት ታላቅ ምክንያት ያላቸው ሰዎች በጭራሽ የሉም፤ አዎን፣ እናም ደስታዬ በአምላኬ እስከምኮራም እንኳን ደርሷል፤ ምክንያቱም እርሱ ሁሉም ስልጣን፣ ሁሉም ጥበብ፣ እናም ሁሉም ግንዛቤ አለውና፤ ሁሉንም ነገር ያውቃልና፣ እርሱ እስከ ደህንነትም እንኳን ንስሃ ለሚገቡትና በስሙ ለሚያምኑት መሀሪ ነውና።

“እናም ይህ ኩራት ከሆነ፣ እኔም እንደዛው እኮራለሁ፤ ምክንያቱም ይህ የእኔ ህይወትና ብርሃን፣ … የእኔ ደስታና ታላቁ ምስጋናዬ ነው።”

ወደ ደሥታ ቤተክርስቲያን እንኳን በደህና መጣችሁ! በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ፕሬዚዳንት ራስል አኤም. ኔልሰን እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፦ “ደስታ ሃያል ነው፣ እናም በደስታ ላይ ማተኮር የእግዚአብሄርን ሃይል ወደ ህይወታችን ያመጣል። በሁሉም ነገሮች እንደሚሆነው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻ አርያችን ነው፣ እርሱም ‘በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታገሰ’” [እብራውያን 12፥2]። ያንን አስቡት! በምድር ላይ ካሉ የሚያሳቅቁ ተሞክሮዎችን ለመጽናት፣ አዳኛችን ያተኮረው በደስታ ላይ ነው።! በፊቱ ያለው ደስታ ምንድን ነበር? እርግጥም እኛን የማጽዳት፣የመፈወስ፣ እናም የማጠንከር ደስታ፤ ንስሃን ለሚገቡ የሚከፈለው የሃጢያት ክፍያ ደስታ፤ ለእኔና ለእናንተ ወደቤታችን—በንጽህና እና በብቁነት—ከሰማያዊ ወላጆቻችን እና ቤተሰቦቻችን ጋር ለመኖር እንድንመለስ የሚያስችል ደስታ ነው። ወደ እኛ፣ ወይም ወደምንወዳቸው፣ ስለሚመጡት ደስታዎች ትኩረት ካደረግን፣ በዚህ ጊዜ አጥለቅላቂ፣ አሰቃይ፣ አስፈሪ፣ ፍትሃዊ ያልሆነ፣ ወይም በቀላሉ የማይፈጸም የሆኑትን ምን መጽናት እንችላለን?” (“ደስታ እና መንፈሳዊ ደህንነት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2016 (እ.አ.አ)፣ 82–83)።

  2. መዝሙር 16፥11

  3. ኤፍ. ኤንዚዮ ቡቼ፣ “Lessons from the Lamb of God [ከእግዚአብሔር በግ የመጣ ትምህርት]፣” Religious Educator 9፣ ቁ.2 (2008[እ.አ.አ])።

  4. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 25፥12

  5. መዝሙር 100፥1 ይመልከቱ።

  6. አልማ 32፥42

  7. አልማ 33፥23 ይመልከቱ።

  8. አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ፦ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል29.2.1.1፣ የወንጌል ቤተ መፃህፍት ውስጥ ይመልከቱ።

  9. ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን፣ mission leadership seminar [የሚስዮን መሪዎች ሴሚናር፣ ሰኔ 2019 (እ.አ.አ)፤ በዴል ጂ. ረንለንድ “Unwavering Commitment to Jesus Christ [ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለ የማይናወጥ የልብ ውሳኔ]፣” ሊያሆና፣ ሕዳር. 2019 (እ.አ.አ) ውስጥ የተጠቀሰ።

  10. ፕሬዚዳንት ጎርደን ቢ. ሂንክሊ እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፦ “እንደ ካህን በቅዱስ ቁርባን ጠረጴዛ ሥር ስትንበረከኩ እና በራዕይ የመጣውን ጸሎት ስታቀርቡ፣ መላውን ጉባኤ ከጌታ ጋር በቃል ኪዳን ሥር ታደርጋላችሁ። ይህ ትንሽ ነገር ነው? ይህም ከሁሉም በላይ አስፈላጊ እና አስደናቂ የሆነ ነገር ነው” (“The Aaronic Priesthood—a Gift from God [የአሮናዊ ክህነት ስልጣን—የእግዚአብሔር ስጦታ]፣” Ensign፣ ግንብት 1988 (እ.አ.አ) 46)።

    ቅዱስ ቁርባንን የሚያዘጋጁ፣ የሚባርኩ ወይም የሚያልፉ ሠዎች ይህን ሥርዓት ጌታን በመወከል ለሌሎች እየሠጡ ነው። የክህነት ሥልጣንን የያዘ እያንዳንዱ ሰው ይህንን ምደባ በጥሞና፣ በጥልቅ አክብሮት መንፈስ መያዝ አለበት። በደንብ የተዘጋጀ፣ ንፁህ የሆነ ልብስ የለበሰ እንዲሁም አለባበሱ ልከኛ መሆን አለበት። የግል መልክ የስርዓቱን ቅድስና የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት” (“የክህነት ሥርዓቶች እና በረከቶች፣” የቤተሰብ መመሪያ መፅሐፍ [2006 (እ.አ.አ)]፣ 22)።

  11. አልማ 36፥21

  12. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “የመንፈሳዊ ፍጥነት ሃይል፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2022 (እ.አ.አ) 98።

  13. ሞዛያ 24፥13–15 ይመልከቱ።

  14. ዮሐንስ 3፥16–17 ይመልከቱ።

  15. አልማ 26፥35–37