ከያህዌ ጋር የተነጋገረው ሰው
ጆሴፍ ስሚዝ “የመጨረሻውን ዘመን በመክፈት ተባርኮ” ነበር፣ እርሱ ይህን በማድረጉም ተባርከናል።
የዛሬ እንዲሁም የሁል ጊዜም አላማዬ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የአለም ፈጣሪ እና አዳኝ፣ የእኛ ነጻ አውጪ እና ቤዛ እንደሆነ መመስከር ነው። “የሐይማኖታችን መሰረታዊ መርሆዎች ሐዋርያቶች እና ነብያቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸው ምስክርነት [ስለሆነ]፣” ዛሬ፣ በአንድ ቁልፍ ሐዋርያ እና ነቢይ ህይወት እና ትምህርቶች አማካኝነት የጠነከረውን እና ጥልቀት ያገኘውን ስለ አዳኙ ያለኝን እውቀት እና ምስክርነት ለእናንተ አካፍላለሁ።
የጥበብ መጀመሪያ
በአንድ በሚያስደስት ብሩህ በሆነ የ1820 (እ.አ.አ) የጸደይ መጀመሪያ ላይ፣ የ14 ዓመቱ ጆሴፍ ስሚዝ ስለ ሃጢያቶቹ ለመጸለይ እና የትኛውን ቤተክርስቲያን መቀላቀል እንዳለበት ለመጠየቅ ከቤተሰቦቹ ቤት አጠገብ ወደሚገኘው የዛፎች ቁጥቋጦ ውስጥ ገባ። በማይነቃነቅ እምነት ያቀረበው፣ ከልብ የሆነው ጸሎቱ አብን እና ወልድን ጨምሮ በአለም ውስጥ በጣም ከፍተኛ የሆነ ሃይልን ትኩረት አገኘ። እንዲሁም የሰይጣንን። እያንዳንዳቸው በዚያ ጸሎት እና በልጁ ላይ ከፍተኛ ፍላጎትን አደረባቸው።
አሁን የመጀመሪያው ራዕይ ብለን የምንጠራው በዚህ በመጨራሻው ዘመን የሁሉም ነገሮች ዳግም መመለስን ጅማሮ አበሰረ። ነገር ግን ለጆሴፍ ልምዱ ግላዊ እና የሚያዘጋጅም ነበር። እሱ የፈለገው ይቅርታን እና ምሪትን ነበር። ጌታ ሁሉቱንም ሰጠው። “[የማንኛውም] [ቤተክርስቲያን] አባል እንዳ[ት]ሆን” የሚለው መመሪያ ጠቋሚ ነበር። “ኃጢአቶችህ ሁሉ ተሰርየዋል” የሚሉት ቃላት የሚያድን ነበሩ።
ከዚያ የመጀመሪያ ራዕይ ልንማር ከምንችለው ድንቅ እውነታዎች፣ ምናልባት የጆሴፍ ዋናው ግንዛቤ ይህ ነው፣ “የያዕቆብ ምስክርነት እውነት እንደሆነም አወቅሁኝ—ጥበብ የሌለው ሰው እግዚአብሔርን መጠየቅ ይችላል፣ እና አይነቀፍም።”
አንድ ምሁር እንደገለጸው፣ “የመጆመሪያው ራዕይ የዛሬው እውነተኛ ትርጉም፣ ጥበብ ለጎደላቸው ሰዎች መስጠት የእግዚአብሔር ተፈጥሮ መሆኑን ማወቅ ነው። … ለጆሴፍ ስሚዝ እራሱን በተቀደሰው ቁጥቋጦ ውስጥ የገለጸው አምላክ ለታዳጊዎች በችግራቸው ወቅት ምላሽን የሚሰጣቸው አምላክ ነው።”
የጆሴፍ የቁጥቋጦ ውስጥ ልምድ ለቀሪ ህይወቱ ይቅርታን እና ምሪትን እንዲጠይቅ ድፍረትን ሰጥቶታል። የእሱ ልምድ ለእኔ እራሱ ይቅርታን ለማግኘት እና ለቀሪው ህይወቴ ምሪትን ለማግኘት እንድጠይቅ ድፍረትን ሰጥቶኛል።
ተደጋጋሚ ንስሀ
መስከረም 21፣ 1823 (እ.አ.አ)፣ ከሶስት ዓመት በፊት በቁጥቋጦ ውስጥ በነበረው ልምድ ምክንያት ሰማይ በድጋሚ መልስ እንደሚሰጥ በመተማመን ጆሴፍ ይቅርታን ለማግኘት በቅንነት ጸለየ። ይቅርታንም አገኘ። ጌታ መልአኩን፣ ሞሮኒን፣ ላከ እና በእግዚአብሔር ስጦታ እና ሃይል በኋላ ስለሚተረጉመው የጥንት መዝገብ—መጽሐፈ ሞርሞን ነገረው።
በግምት ከ13 ዓመታት በኋላ፣ ጆሴፍ እና ኦሊቨር ካውድሪ በአዲሱ በተባረከው የከርትላንድ ቤተመቅደስ ውስጥ በጸሎት ተንበረከኩ። ስለምን እንደጸለዪ አናውቅም፣ ነገር ግን ጸሎታቸው ለሃጥያት ስርየት ልመናን ያካተተ ይሆናል ምክንያቱም አዳኙ በመገለጽ እንዲህ አለ፣ “እነሆ፣ ኃጢአታችሁ ተሰርየዋል፤ በፊቴም ንጹህ ናችሁ።”
ከዚህ ልምድ ወራቶች እና አመታት በኋላ ጆሴፍ እና ኦሊቨር ሃጥያት እንደገና ይሰሩ ነበር። እናም እንደገና። ነገር ግን በዚያ ወቅት፣ ለዚያ ወቅት፣ ለልመናቸው እና ለታላቁ የክህነት ቁልፎች መመለስ ዝግጅታቸው ምላሽ ኢየሱስ ከሃጥያት ነጻ አደረጋቸው።
የጆሴፍ ተደጋጋሚ የንስሃ ህይወት “[እኔ] ምሕረትን እንድቀበል ወደ ጸጋ ዙፋን በድፍረት እንድቀርብ” ብርታት ይሰጠኛል። ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት “ይቅር ባይ” እንደሆነ ተምሬአለሁ። መፍረድ የእርሱ ተልዕኮ ወይም ተፈጥሮ አይደለም። እርሱ የመጣው ለማዳን ነው።
ጌታን መጠየቅ
ቃል ለተገባው “የሁሉን ነገሮች መመለስ” አካል ጌታ በጆሴፍ ስሚዝ አማካኝነት የወንጌልን ሙላት የያዙትን መጽሐፈ ሞርሞንን እና ሌሎች ራዕዮችን አመጣ። ጆሴፍ በተደጋጋሚ ጌታን ሲጠይቅ ጠቃሚ እውነታዎችን በግልጽ እና በሙሉነት ተሰጠው። የሚከተሉትን አስቡባቸው፦
-
ወደ ክርስቶስ ስንመጣ እርሱ ሃጥያታችንን ይቅር ማለት ብቻ ሳይሆን “ኃጢያትን ለመፈፀም ምንም ፍላጎት እስከማይኖረን” ድረስ ተፈጥሮአችንን ይቀይራል።
-
ክርስቶስ ህዝቦቹ ቤተመቅደስን እንዲገነቡ ሁሌም ያዛቸዋል፣ እራሱን ለእነሱ የሚገልጽበት እና ሃይልን ከላይ የሚሰጥበት [ቦታ ነው]።
እነዚህ ሁሉም ነገሮች እውነት እና አስፈላጊ እንደሆኑ እመሰክራለው። ለጆሴፍ ቀጣይነት ላለው የምሪት ጥያቄዎች ምላሽ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ለጆሴፍ ስሚዝ የተመለሰውን ሙሉነት ጥቂት ክፍል ይወክላሉ።
ይህን መንግስት በቶሎ ማምጣት
በ1842 (እ.አ.አ) በመጨረሻው ዘመን ስለሚከሰቱ አስደናቂ ነገሮች ጆሴፍ ጽፎ ነበር። በዘመናችን፣ “ሰማያዊው ክህነት እነዚያን ታላላቅ ዓላማዎች ለማሳካት ከምድራዊው ጋር ይጣመራል። የእግዚአብሔርንም መንግሥት ለማምጣት በጋራ ጉዳይ አንድ ስንሆን፣ ሰማያዊው ክህነት ግድ የለሽ ተመልካች አይሆንም” በማለት ተናግሯል።
ለጓደኛው ቤንጃሚን ጆንሰን ጆሴፍ እንዲህ አለ፣ “ቢንያም [እኔ ከሞትኩ] ከአንተ አልርቅም፥ በመጋረጃውም በስተጀርባ ብሆንም ይህን መንግስት ለማምጣት ከፍ ባለ ሃይል ከአንተ ጋር እሠራለሁ።”
ሰኔ 27፣ 1844 (እ.አ.አ)፣ ጆሴፍ ስሚዝ እና ወንድሙ ሃይረም ተገደሉ። የጆሴፍ እሬሳ ተቀበረ ነገር ግን ምስክርነቱ በአለም ዙሪያ እና በነፍሴ ውስጥ ማስተጋባቱን ይቀጥላል።
“ራዕይ አይቻለሁ፣ እኔ አውቄዋለሁ፣ እናም እግዚአብሔር እንዳወቀው አውቄዋለሁ፣ እናም ልክደው አልቻልኩም።”
“ፍፁም ነኝ ብዬ መቼም አልነገርኳችሁም፤ ነገር ግን ባስተማርኩት መገለጥ ውስጥ ምንም ስህተት የለም።”
“የሐይማኖታችን መሰረታዊ መርሆዎች ሐዋርያትና ነብያት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሞተ፣ እንደተቀበረ፣ እና በሶስተኛውም ቀን እንደተነሳ፣ እንዲሁም ወደ ሰማይ እንዳረገ የሠጡት ምስክርነት ነው፤ እናም ሁሉም የእኛን ሐይማኖት የሚመለከቱ ሌሎች ነገሮች በሙሉ የዚያ ቅጥያዎች ብቻ ናቸው።”
ስለ መጥምቁ ዮሐንስ የተባለው ነገር ለጆሴፍ ስሚዝም መባል ይችላል፦ “ከእግዚአብሄር የተላከ ስሙ [ጆሴፍ]. የሚባል አንድ ሰው ነበረ። … “ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ … ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፣ እርሱ ያ ብርሃን አልነበረም።”
አምናለሁ። ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን እና የህያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምናለሁ። ህያው እግዚአብሔር አፍቃሪው አባታችን እንደሆነ እመሰክራለሁ። ይህንን የማውቀው የጌታ ድምጽ እንዲሁም ከጆሴፍ ስሚዝ ጀምሮ የነበሩ የጌታ አገልጋዮች፣ ሐዋርያዎች እና ነቢያቶች ድምጽ ለእኔ ስለተናገረኝ ነው።
ጆሴፍ ስሚዝ የእግዚአብሔር ነቢይ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር እና አገልጋይ እንደነበር እና እንደሆነ እመሰክራለሁ፡፡ እሱ “የመጨረሻውን ዘመን ለመክፈት ተባርኮ” ነበር፣ በመክፈቱም እኛ ተባርከናል።
ጌታ ኦሊቨርን እና እኛን ሁላችንን “በታማኝነት ከአገልጋዬ ከጆሴፍ ጎን ቁሙ” ሲል አዞናል። ጌታ ከአገልጋዩ ከጆሴፍ ጎን እንደቆመ እና ዳግም መመለሡም በእርሱ በኩል እንደተከናወነ እመሰክራለሁ።
አሁን ጆሴፍ ስሚዝ የተናገረለት የዚያ የሰማይ ክህነት አካል ነው። እሱ ለጓደኛው ቃል እንደገባለት ከእኛ ብዙም እሩቅ አይደለም ከመጋረጃውም ባሻገር ይህን መንግስት ለማምጣት ከፍ ባለ ሃይል አሁንም ከእኛ ጋር እየሰራ ነው። “ከያህዌ ጋር ስለተነጋገረው ሰው” በደስታ እና በምስጋና ድምጼን አሰማለሁ። ከሁሉም በላይ፣ ከዚያ ሰው ጋር ለተነጋገረው ያህዌ ምስጋና ይሁን! በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።