አጠቃላይ ጉባኤ
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ይመጣል
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


14:49

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ይመጣል

አሁን እኔ እና እናንተ ለጌታችንና ለአዳኛችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት የምንዘጋጅበት ጊዜ ነው።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ጌታ እናንተን ማነጋገር እንድችል ስለባረከኝ አመስጋኝ ነኝ።

በዚህ ጉባኤ፣ ጌታ በአገልጋዮቹ አማካኝነት ተናግሮናል። መልዕክቶቻቸውን እንድታጠኑ በቅንነት አበረታታችኋለሁ። የአንድ ኬሚካል ይዘት አሲድ ይሁን ቤዝ ለመለየት እንደሚውለው የሊትመስ ወረቀት፣ እውነት የሆነውን እና ያልሆነውን ለመለየት ለመጪዎቹ ስድስት ወራት ተጠቀሙባቸው።

በሶልት ሌክ ቤተመቅደስ እና በሌሎች የቤተመቅደስ አደባባይ ባሉ ቦታዎች ላይ የሚደረገው ጥገና እና እድሳት ለአምስት ዓመታት ያህል በመካሄድ ላይ ይገኛል። አሁን ያሉት ትንበያዎች እንደሚያሣዩት ከሆነ፣ ይህ ሥራ በ2026 (እ.አ.አ) መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል። በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ላይ በመሥራት ላይ ስላሉት ሠዎች ሁሉ አመስጋኞች ነን።

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ፣ በስድስት አገሮች ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ ቤተመቅደሦችን አስመርቀናል ወይም በድጋሚ አስመርቀናል። ከአሁን ጀምሮ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ አምስት ተጨማሪ ቤተመቅደሦችን እናስመርቃለን፡፡

ዛሬ፣ እንዲገነቡ ስለታቀዱት 17 ተጨማሪ ቤተመቅደሦች የምናሣውቀው በደስታ ነው። እባካችሁ፣ ቦታዎቹን በምገልጽበት ጊዜ በጥልቅ አክብሮት አዳምጡ።

  • ሁታን ዴ ዜሪጎዛ፣ ሜክሲኮ

  • ሳንታ አና፣ ኤል ሳልቫዶር

  • ሜድሊን፣ ኮሎምቢያ

  • ሳንቲያጎ፣ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ

  • ፖርቶ ሞንት፣ ቺሊ

  • ደብሊን፣ አየርላንድ

  • ሚላን፣ ጣልያን

  • አቡጃ፣ ናይጄሪያ

  • ካምፓላ፣ ኡጋንዳ

  • ማፑቶ፣ ሞዛምቢክ

  • ኮር ደሌን፣ አይደሆ

  • ኩዊን ክሪክ፣ አሪዞና

  • ኤል ፓሶ፣ ቴክሳስ

  • ኸንትስቪል፣ አላባማ

  • ሚልዋኪ፣ ዊስኮንሲን

  • ሰሚት፣ ኒው ጀርዚ

  • ፕራይስ፣ ዩታ

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በዚህ ወቅት በፊታችሁ እየተከናወነ ያለውን ነገር እያያችሁ ናችሁ? የዚህን ወቅት ታላቅነት የምናስተውልበት ዕድል እንዳያመልጠን እጸልያለሁ! በእርግጥ ጌታ ስራውን እያፋጠነ ነው።

ቤተመቅደሦችን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየገነባን ያለነው ለምንድን ነው? ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጌታ እንዲህ እንድናደርግ ስላዘዘን ነው። የቤተመቅደሥ በረከቶች በመጋረጃው በሁለቱም በኩል ያለውን እስራኤል ለመሰብሰብ ይረዳሉ። በተጨማሪም፣ እነዚህ በረከቶች ዓለምን ለጌታ ዳግም ምጽዓት ለማዘጋጀት የሚረዱ ሰዎችን ለማዘጋጀት ይረዳሉ!

የአዳኙ ዳግሞ ምፅዓት

ነቢዩ ኢሣይያስ እንደተነበየው እና መሲሕ በተሠኘው በሃንዴል ሥራ ውስጥ እንደተገለፀው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ፣ “የእግዚአብሔር ክብር ይገለጣል ሥጋ ለባሽም ሁሉ በአንድነት ያየዋል።”

በዚያ ቀን፣ “አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፦ ስሙም ድንቅ መካር፣ ሀያል አምላክ፣ የዘለአለም አባት፣ የሠላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።”

ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥንቷ ኢየሩሳሌም እና “በአሜሪካ አህጉር ከተመሠረተችው” ከአዲሲቷ ኢየሩሳሌም ይገዛል። ከእነዚህ ሁለት ማዕከላት የቤተክርስቲያኑን ጉዳዮች ይመራል።

በዚያ ቀን፣ ጌታ “የነገሥታት ንጉሥ፣ እና የጌቶች ጌታ” በመባል ይታወቃል። ከእርሱ ጋር የሚሆኑት “የተጠሩ፣ የተመረጡ እና የታመኑም” ይሆናሉ።

ወንድሞች እና እህቶች፣ አሁን እኔ እና እናንተ ለጌታችንና ለአዳኛችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት የምንዘጋጅበት ጊዜ ነው። አሁን ለደቀመዝሙርነታችን ከሁሉ የላቀ ቅድሚያ የምንሰጥበት ጊዜ ነው። ትኩረትን በወንጌል ላይ እንዳናደርግ በሚያደርጉ ነገሮች በተሞላ ዓለም ውስጥ፣ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

የሮም ጣልያን ቤተመቅደስ

ዘወትር በቤተመቅደስ የሚደረግ አምልኮ ይረዳናል። በጌታ ቤት ውስጥ ትኩረታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እናደርጋለን። ከእርሱ እንማራለን። እርሱን ለመከተል ቃል ኪዳን እንገባለን። የበለጠ እያወቅነው እንሄዳለን። የጌታን የሚያጠነክር ኃይል ይበልጥ እናገኛለን። በቤተመቅደስ ውስጥ፣ በዓለም ካለው መሠቃየት ጥበቃን እናገኛለን። የኢየሱስ ክርስቶስን እና የሰማይ አባታችንን ንፁህ ፍቅር በተትረፈረፈ መልኩ እናገኛለን። በዓለም ካለው ግጭት ተቃራኒ በሆነ መልኩ፣ ሰላም እና መንፈሳዊ ማረጋገጫ ይሰማናል።

ለእናንተ የምገባው ቃል ይህ ነው፦ ኢየሱስ ክርስቶስን በቅንነት የሚፈልጉ ሁሉ በቤተመቅደስ ያገኙታል። ምሕረቱ ይሰማችኋል። በጣም ለሚያስጨንቁ ጥያቄዎቻችሁ መልስ ታገኛላችሁ። ከወንጌሉ ስለሚገኘው ደሥታ የተሻለ ግንዛቤ ታገኛላችሁ።

እያንዳንዳችን መመለስ ያለብን በጣም ወሳኝ ጥያቄ የሚከተለው መሆኑን ተምሪያለሁ፦ ህይወቴን የምሰጠው ለማን ነው? ወይንም ህይወቴን የምሰጠው ለምን ነገር ነው?

ፕሬዚዳንት ኔልሰን የቀዶ ጥገና ሃኪም እያሉ

ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ያደረኩት ውሳኔ እስካሁን ካደረኳቸው ውሳኔዎች ሁሉ በጣም ቁልፍ የሆነው ነው። በሕክምና ትምህርት ቤት ሣለሁ፣ እግዚአብሔር አብ እና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እንደሆኑ ምስክርነት አግኝቻለሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ አዳኛችን ሕይወቴን የገነባሁበት ዓለት ነበር። ያ ያደረኩት ምርጫ በሌሎች ነገሮች ምርጫ ላይ ተፅዕኖ አሣድሯል! ያ ምርጫ በብዙ ሌሎች ነገሮች ላይ ምርጫዎችን ማድረግን ቀላል አድርጓል። ያ ያደረኩት ምርጫ ዓላማ እና አቅጣጫ ሰጥቶኛል። የሕይወትን ማዕበል እንድቋቋም ረድቶኛል። ሁለት ምሳሌዎችን ላካፍል፦

በመጀመሪያ፣ ባለቤቴ ዳንትዘል በድንገት በሞተችበት ጊዜ አንዳቸውንም ልጆቻችንን ማግኘት አልቻልኩም ነበር። በጣም አዝኜ እና እርዳታ ለማግኘት በመጮህ ብቻዬን ነበርኩኝ። ምስጋና ይግባውና፣ ጌታ፣ የእኔ ውድ ዳንትዘል ለምን እንደሞተች እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተመለሠች በመንፈሱ አማካኝነት አስተማረኝ። ያንን በማወቄ ተጽናናሁ። በጊዜ ሂደት ሀዘኔን በተሻለ ሁኔታ መቋቋም ቻልኩኝ። ከዚያ በኋላም፣ ውዷን ባለቤቴን ዌንዲን አገባሁ። የሁለተኛው ምሳሌዬ ዋና ክፍል እርሷ ናት።

እኔና ዌንዲ የሥራ ምደባ ተሠጥቶን በአንድ ሩቅ አገር በነበርንበት ጊዜ የታጠቁ ዘራፊዎች መሣሪያ ጭንቅላቴ ላይ ደገነው ምላጩን ሣቡት። ነገር ግን መሣሪያው ከሸፈ። በዚያ ክንውን ውስጥ የሁለታችንም ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ይሁን እንጂ እኔና ዌንዲ የማይካድ ሠላም ተሰምቶን ነበር። “አዕምሮንም ሁሉ የሚያልፍ” ሠላም ነበር።

ወንድሞች እና እህቶች፣ ጌታ እናንተንም ያጽናናችኋል! እርሱ ያጠነክራችኋል። በግራ መጋባት ውስጥም እንኳን በሰላም ይባርካችኋል።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ

እባካችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን ይህን ተስፋ ስሙ፦ “በቀ[ኛችሁና] በግራ[ችሁ] እሆናለሁ፥ መንፈሴም በልባችሁ ይሆናል፥ እናንተንም ለመሸከም መላእክቶቼ በዙሪያችሁ ይሆናሉ።”

አዳኙ እናንተን ከመርዳት የሚያግደው የአቅም ውሱንነት የለበትም። ለመገንዘብ የማይቻል ሥቃይ በጌቴሴማኒ ውስጥ እና በጎልጎታ ላይ የደረሰበት የለእናንተ ነው! ወሰን የሌለው የሃጢያት ክፍያ መስዋዕቱ ለእናንተ ነው!

ስለኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ያላችሁን ግንዛቤ ለማሣደግ—በቀሪው ህይወታችሁ ሙሉ—በየሳምንቱ ጊዜ እንድትመድቡ አበረታታችኋለሁ። በሀጢያት ለተተበተቡ እንዲሁም በንሥሃ አማካኝነት እንዴት መንፃት እንደሚችሉ ለማያውቁ ርህራሄ ይሠማኛል። ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንዳደረገላቸው ባለመረዳታቸው በመንፈሳዊ እየታገሉ ላሉት ወይም ከባድ ሸክሞችን ለብቻቸው ለተሸከሙት አነባለሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስ የእናንተን ኃጢያቶች፣ የእናንተን መከራዎች፣ የእናንተን ጭንቀቶች እና የእናንተን ህመሞች በራሱ ላይ ወስዷል። ብቻችሁን ልትሸከሟቸው አይገባም። ንስሀ ስትገቡ ይቅር ይላችኋል። የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች በመሥጠት ይባርካችኋል። የቆሰለውን ነፍሣችሁን ይፈውሳል። ቀንበሩን በራሳችሁ ላይ ስትሸከሙ ሸክሞቻችሁ እንደቀለሉ ይሰማችኋል። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ቃል ኪዳኖችን የምትገቡ​እንዲሁም የምትጠብቋቸው ከሆነ፣ በህይወታችሁ ውስጥ ያሉት የመከራ ወቅቶች ለጊዜው እንደሆኑ ትገነዘባላችሁ። ሥቃያችሁ “በክርስቶስ ፍቅር ይዋጣል።”

ቀናተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ትሆኑ ዘንድ በጣም ገና አይደለም፣ እንዲሁም በጣም አልረፈደም። ከዚያም የኃጢያት ክፍያውን በረከቶች ሙሉ በሙሉ ታገኛላችሁ። እሥራኤልን ለመሰብሰብ በመርዳት ረገድም የበለጠ ውጤታማ ትሆናላችሁ።

የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ወደፊት ኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት መሲሕ ሆኖ ወደ ምድር ይመለሣል። ስለዚህም ዛሬ፣ ሕይወታችሁን እንደገና ለኢየሱስ ክርስቶስ እንድትሠጡ ጥሪ አደርግላችኋለሁ። የተበተኑትን እስራኤልን በመሰብሠብ እና ዓለምን ለጌታ ዳግም ምጽአት በማዘጋጀት እንድትረዱ ጥሪ አደርግላችኋለሁ። ስለክርስቶስ እንድትናገሩ፣ ስለክርስቶስ እንድትመሰክሩ፣ በክርስቶስ እንድታምኑ እንዲሁም በክርስቶስ ደስ እንዲላችሁ ጥሪ አደርግላችኋለሁ!

ወደ እርሱ ኑ፣ እናም “መላ ነፍሳችሁን” ለእርሱ እንደ መስዋዕትነት አቅርቡ። የደሥታ ሕይወት ሚሥጥር ይህ ነው

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ አዳኙ ዳግም የሚመጣ በመሆኑ ከሁሉም የተሻለው ገና ይመጣል! ጌታ ሥራውን እያፋጠነው በመሆኑ ከሁሉም የተሻለው ገና ይመጣል። ልባችንን እና ሕይወታችንን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ስንመልስ ከሁሉም የተሻለው ገና ይመጣል!

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በትህትና እመሰክራለሁ፡፡ እኔ የእርሱ ደቀመዝሙር ነኝ። የእርሡ አገልጋይ በመሆኔ ክብር ይሰማኛል። በዳግም መመለሡ፣ “የእግዚአብሔር ክብር ይገለጣል፣ ሥጋ ለባሽም ሁሉ በአንድነት ያየዋል።” በዚያን ቀን ፃድቃን በደስታ ይሞላሉ!

በያዝኳቸው ቅዱስ የክህነት ቁልፎች ኃይል አማካኝነት ይህንን እውነት ለእናንተ እና ለመላው ዓለም አውጃለሁ! በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።