አጠቃላይ ጉባኤ
ለመንፈሳዊ ጥያቄዎች መልስ መፈለግ
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


12:27

ለመንፈሳዊ ጥያቄዎች መልስ መፈለግ

ቅን የወንጌል ጥያቄዎቻችን ለሰማይ አባት እና ለኢየሱስ ክርስቶስ እንድናድግ የሚረዱንን እድሎች ይሰጡናል።

ይህ ያልተጠበቀ ሊሆን እንደሚችል አውቃለሁ፣ ነገር ግን በትምህርት ቤት ስንማር በሥርዓተ ፀሐይ መዘውር ውስጥ ዘጠኝ ፕላኔቶች እንደነበሩ ለማስታወስ የሚያስችል ዕድሜ አለኝ። ከእነዚህ ፕላኔቶች አንዱ የሆነው ፕሉቶ፣ በ1930 (እ.አ.አ) ከተገኘ በኋላ በኦክስፎርድ፣ እንግሊዝ የ11 ዓመቷ ቬኔቲያ ባርኒ ስም ተሰጥቶት ነበር። እስከ 1992 (እ.አ.አ) ድረስ በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ በጣም ሩቅ የሆነ ነገር እንደሆነ ይታመን ነበር። በዚህ ወቅት፣ የልጅነት የፕላኔቶችን ሞዴል ወረቀት በክፍል ውስጥ እና በሳይንስ ትርዒቶች ውስጥ ማግኘት የተለመደ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው ፕሉቶ በሚታወቀው ድንበር ላይ ያለውን ቦታ የሚያሳዩ ነበሩ። ብዙ ሳይንቲስቶች ከውጨኛው ጠርዝ ባሻገር ሥርዓተ ፀሐይ ባዶ ቦታ እንዳለው ያምኑ ነበር።

ይሁን እንጂ የክዋክብት ተመራማሪዎች አዘውትረው ስለሚከታተሉት የጅራታም ኮከብ አመጣጥ በተመለከተ በሳይንሱ ማኅበረሰብ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየ ጥያቄ ነበር። ከእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ርቆ የሚገኝ ሌላ አካባቢ እስከሚገኝ ድረስ ይህ ጥያቄም ለአሥርት ዓመታት ቀጠለ። በነበራቸው ውስን ዕውቀት፣ ሳይንቲስቶች በእነዚህ አሥርተ ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ ጥናትና ምርምር ለማድረግ የሚያስችል ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እድገት ለማግኘት በእነዚህ ዓመታት ተጠቅመዋል። ከጊዜ በኋላ የተገኘው ግኝት የፕላኔቷን ቀጠና እንደገና ያስተካከለ ከመሆኑም በላይ፣ ፕሉቶ በዚህ አዲስ የጠፈር ክልል ውስጥ እንድትመደብ እና የእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ባለስምንት ፕላኔት እንዲሆን አስችሏል።

ፕሉቶን በቅርብ የመቃኘት ኃላፊነት የተሰጠው አንድ ታዋቂ የፕላኔቶች ሳይንቲስትና የጠፈር ተልዕኮ ዋና መርማሪ ይህን ተሞክሮ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦“የሥርዓተ ፀሐይን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ተረድተናል ብለን አስበን ነበር። አልተረዳነውም። በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያሉትን ፕላኔቶች ብዛት ተረድተናል ብለን አስበን ነበር። ተሳስተን ነበር።”

በዚህ የህዋ ምርምር ታሪክ ዘመን ላይ የሚገርመኝ ነገር ሳይንሳዊ አድማስ ለማስፋት በምናደርገው ተምሳሌታዊ ጥረት እና እኛ የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን መጠን ለመንፈሳዊ ጥያቄዎቻችን መልስ ለመሻት በምናደርገው ጉዞ መካከል አንዳንድ ተመሳሳይነት እና ቁልፍ ልዩነቶች ናቸው። በተለይ፣ ለመንፈሳዊ መረዳታችን ገደብ እንዴት ምላሽ መስጠት እንችላለን እና ለቀጣዩ የግል እድገት ደረጃ እራሳችንን እንዴት ለማዘጋጀት እንደምንችል እንዲሁም እርዳታ ለማግኘት ወዴት መሄድ እንችላለን።

በስርዓት ላይ ስርዓት

ጥያቄዎችን መጠየቅ እና ትርጉም መፈለግ ተፈጥሯዊ እና የተለመደ የምድራዊ ልምዳችን ክፍል ነው። አንዳንድ ጊዜ፣ የተሟላ መልስ አለማግኘታችን ወደ መረዳታችን ጫፍ ሊያመጣን ይችላል፣ እነዚህ ገደቦች ደግሞ ተስፋ ሊያስቆርጡን ወይም ከአቅማችን በላይ እንደሆኑ ሊሰማን ይችላል ። በአስደናቂ ሁኔታ፣ የሰማይ አባት ለሁላችንም ያለው የደስታ እቅድ፣ የአቅም ውስንነት ቢኖርብንም እንድናድግ እንዲሁም ምንም እንኳን ሁሉንም ነገሮች ሙሉ በሙሉ ባናውቅም በራሳችን ልናከናውን የማንችለውን እንድናከናውን ለመርዳት ያዘጋጀው ነው።። የእግዚአብሔር እቅድ ከሰው ልጆች አቅም ገደብ በላይ መሃሪ የሆነ ነው፣ አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለእኛ መልካም እረኛ አድርጎ አዘጋጀልን፣ እንዲሁም ነጻ ምርጫችንን ተጠቅመን እንድንመርጠውም አነሳሳን።

ሽማግሌ ዲይተር ኤፍ ኡክትዶርፍ “ጥያቄ መጠየቅ የድክመት ምልክት አይደለም” ይልቁንም “የእድገት መነሻ ነው” በማለት አስተምረዋል። እንደ እውነት ፈላጊዎች የግል ጥረታችንን በቀጥታ ሲናገሩ፣ ነብያችን፣ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን ፣“ጥልቅ ምኞት” ሊኖረን እንደሚገባ እና “በቅን ልብ [እና] እውነተኛ ፍላጎት፣ በ[ኢየሱስ] ክርስቶስ ላይ እምነት እንዲኖረን” መጠየቅ እንዳለብን አስተምረዋል። በተጨማሪም “እውነተኛ ፍላጎት” ማለት አንድ ሰው የተሰጠውን መለኮታዊ መመሪያ ለመከተል በእውነት ፍላጎት ይፈልጋል ማለት እንደሆነ አስተምረዋል።

በጥበብ ለማደግ የምናደርገው የግል ጥረት፣ ውስብስብም ሆነ ሌላ ዓይነት ፣ በመንስኤ እና ውጤት ሌንስ በኩል፣ ንድፎችን መፈለግ እና ማወቅ፣ ከዚያም ለግንዛቤያችን ቅርጽ ለመስጠት እና በእውቀት ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ታሪኮችን መፍጠር ጥያቄዎቻችንን እንድንመረምር ሊመራን ይችላል። መንፈሳዊ እውቀትን መከታተልን ስናስብ፣፣ እነዚህ ሂደቶች አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን ከሰማይ አባት እና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከወንጌላቸው፣ ከቤተክርስቲያናቸው፣ እና ለሁላችንም እቅዳቸውን ለመለየት ስንጠባበቅ በራሳቸው ያልተሟሉ ሊሆኑ ይችላሉ።

እግዚአብሔር አብ እና ልጁ ጥበባቸውን ለእኛ የሚያካፍሉበት መንገድ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በህይወታችን ዋና አድርገን፣ የመንፈስ ቅዱስን ሀይል የግል መምህራችን እንዲሆን በመጋበዝ የእነርሱን መልስ እና ትርጉማቸውን በታማኚነት ስንሻው ነው። ቅዱሳት መጻህፍትን በማጥናት እና በኋለኛው ቀን ለዘመናችን የተገለጠውን እውነት ለመፈለግ፣ በዘመናችን ካሉ ነቢያት እና ሀዋርያት በመካፈል እውነትን እንድናገኝ ይጋብዙናል። በጌታ ቤት ቋሚ፣ የአምልኮ ጊዜ እንድናሳልፍ እና “ከሰማይ መረጃ ለማግኘት” በፀሎት እንድንንበረከክ ይለምኑናል። ኢየሱስ የተራራውን ስብከት ለመስማት ለተገኙት የሰጠው ቃል በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት እንደነበረው ሁሉ በእኛም ዘመን ይህም ለእኛ እውን ነው፦ “ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ይከፈትላችኋል።” አዳኛችን “በሰማይ ያለው አባታችሁ የሚለምኑትን መልካም ነገር ይሰጣቸዋል” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቷል።

የጌታ የማስተማር ዘዴ “በትዕዛዝ ላይ ትዕዛዝ፣ በሥርዓት ላይ በሥርዓት” ነው። አሁን ባለን የመረዳት መስመር የሚቀጥለው እስኪመጣ ድረስ“ ጌታን እንድንጠብቅ” ይጠበቅብን ይሆናል። ይህ ቅዱስ ጊዜ ታላቅ መንፈሳዊ ልምድ የሚከናወንበት፣ የኛ ልባዊ ፍላጎት እና ለእግዚአብሄር በቃል ኪዳን የገባነውን ቅዱስ ቃል ለመጠበቅ ጥንካሬያችንን የምንጠብቅበትና የምናድስበት “ትዕግሥተኛ መሆን የምንችልበት” ቦታ ሊሆን ይችላል።

ከሰማይ አባት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለን የቃል ኪዳን ግንኙነት በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ያለንን ዜግነት ያመለክታል። በዚህ ቦታ መኖር ደግሞ ሕይወታችንን ከመለኮታዊ እና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ማስማማትና መንፈሳዊነት ለማደግ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል።

ታዛዥነት

መፅሐፈ ሞርሞን ከሚያስተምረው ቁልፍ መርህ ውስጥ አንዱ የእግዚአብሔር ልጆች ታዛዥነትን ለማሳየት እና ቃል ኪዳናቸውን ለመጠበቅ ሲመርጡ፣ ቀጣይነት ይለው መንፈሳዊ መመሪያ እና አቅጣጫን እንደሚቀበሉ ነው። በመታዘዛችን እና በትጋታችን፣ እውቀትን እና የመረዳት ችሎታን እንደምናገኝ ጌታ ነግሮናል። የእግዚአብሄር ህጎች እና ትእዛዛት በህይወታችን እንቅፋት እንዲሆኑ ሳይሆን ለግል መገለጥ እና ለመንፈሳዊ ትምህርት ሃይል በር እንዲሆኑ ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። ፕሬዚዳንት ኔልሰን “ከእግዚአብሄር የሆነ መገለጥ ሁሌም ከዘለአለማዊ ህጉ ጋር የሚጣጣም ነው፣” እንዲሁም “ከትምህርቱ ጋር በፍፁም አይጋጭም” በማለት ወሳኝ እውነት አስተምረዋል። የእግዚአብሄርን ትእዛዛት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ባታውቁም፣ በፈቃደኝነት መታዘዛችሁ፣ ከነቢያቱ ጋር አንድ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል። ሙሴ 5 በአዳም እና በጌታ መልአክ መካከል ስላለው ልዩ ግንኙነት ያስተምረናል።

እግዚአብሔር አዳም እና ሔዋን “አምላካቸውን እንዲያመልኩ፣ እናም ከመንጋዎቻቸው መካከል በመጀመሪያ የተወለደውን ለጌታ መሥዋዕት እንዲያቀርቡም ትእዛዛትን” ሰጣቸው፣ እናም “አዳምም ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ታዛዥ” እንደነበር ቅዱሳት መጻህፍት ይጠቁማሉ። በመቀጠልም እንዲህ እናነባለን “ከብዙ ቀናት በኋላ የአምላክ መልአክ ወደ አዳም መጥቶ እንዲህ አለው፦ ለጌታ መሥዋዕት ለምን ታቀርባለህ? አዳምም እንዲህ አለው፦ እግዚአብሔር ስላዘዘኝ እንጂ፣ ለምን እንደሆነ አላውቅም።

የአዳም ታዛዥነት መረዳቱንቀድሟል እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ የሀጢያት ክፍያ ቅዱስ ምልክት ውስጥ እየተሳተፈ እንደሆነ ቅዱስ እውቀት እንዲቀበል አዘጋጅቶታል። ልክ እንደዚህ፣ የእኛ በትህትና መታዘዝ የእግዚአብሔርን መንገዶች እና ለእያንዳንዳችን ያለውን መለኮታዊ ዓላማ በመንፈስ እንድናውቅ መንገዱን ይጠርጋል። ታዛዥነታችንን ከፍ ማድረግ ወደ አዳኛችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀርበናል፣ ምክንያቱም ህጎቹን እና ትእዛዛቱን መጠበቅ ከእርሱ ጋር እንደመገናኘት ስለሆነ ነው።

በተጨማሪም፣ የወንጌል መርሆችን እና ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን በታማኝነት በመከተላችን አስቀድመን ላወረስነው ዕውቀትና ጥበብ ታማኝ መሆናችን ከመንፈስ ቅዱስ ግንኝነቶችን ለመቀበል እና መጋቢ ለመሆን ዝግጁ ለመሆናችን ወሳኝ ዝግጅት ነው።

የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ የእውነት ሁሉ ምንጭ ናቸው እንዲሁም ጥበባቸውን በልግስና ያካፍላሉ። በተጨማሪም ከእግዚአብሔር ተለይተን የግል እውቀት እንደሌለን መገንዘባችን ወደ ማን ዞር ማለት እንዳለብንና ዋነኛ እምነታችንን የት መጣል እንዳለብን እንድናውቅ ይረዳናል።

ጽኑ እምነት

በነቢዩ ኤልሳዕ አማካኝነት ከለምጽ የተፈወሰው የጦር መሪ የነበረው የንዕማን የብሉይ ኪዳን ታሪክ በተለየ ሁኔታ የምወደው ነው። ታሪኩ የአንዲት “ታናሽ ብላቴና ሴት” ጽኑ እምነት የአንድን ሰው ህይወት መንገድ እንዴት እንደለወጠ እንዲሁም ለሁሉም አማኞች፣ በእርሱ እና በነቢዩ ለሚታመኑት የእግዚአብሔር ምህረት እንዴት እንደሚገለጥ ያሳያል። ይህች ወጣት ምንም እንኳን ስሟ ባይጠቀስም መረዳታችን እንዲሰፋ አስተዋጽኦ አድርጋለች። ንዕማንም ምስክርነቷን ማመኑ እግዚአብሄር ወደመረጠው አገልጋይ እንዲፈውሰው ልመናውን እንዲያቀርብ አነሳስቶታል።

ንዕማን ነቢዩ ኤልሳዕ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እንዲታጠብ ለሰጠለት መመሪያ የሰጠው ምላሽ መጀመሪያ ላይ ጥርጣሬና ቁጣ ነበር። ሆኖም ነቢዩ ለሰጠው ምክር ታዛዥ እንዲሆን የቀረበለት ግብዣ ለመፈወስና እግዚአብሄር እውን መሆኑን እንዲረዳ መንገድ ከፍቶለታል።

አንዳንድ መንፈሳዊ ልመናዎቻችን ምክንያታዊ መልስ ያላቸውና፤ ከባድ ችግር ላይፈጥሩ ይችላሉ። ወይም ደግሞ እንደ ንዕማን ሌሎች ፍላጎቶች ይበልጥ የሚፈትኑና በውስጣችን አስቸጋሪና ውስብስብ የሆኑ ስሜቶችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ወይም፣ የከዋክብት ተመራማሪዎች ስለ ሥርዓተ ፀሐይ ቀደም ሲል መደምደሚያ ላይ ስለመድረሳቸው በተመሳሳይ ከተገለጸው ጋር መንፈሳዊ እውነትን፣ ለማግኘት በምናደርገው ፍለጋ፣ በራሳችን ውስን ግንዛቤ ላይ ብቻ የምንመካ ከሆነ፣ ከቃል ኪዳን መንገድ ሊያርቀን የሚችል አሳዛኝ እና ያልታሰበ ውጤት ከሆነ እምብዛም ትክክለኛ ያልሆኑ ትርጉሞች ላይ መድረስ እንችላለን። በተጨማሪም በምህረቱ “ሁሉንም ነገር የሚረዳ” እና “ሁሉንም ነገር የሚያገናዝበው” እግዚአብሔር በስሙ ላይ ባለን እምነት የእውቀት ብርሃን እስኪሰጠን ድረስ አንዳንድ ጥያቄዎች ሊቀጥሉ ይችላሉ።

ከንዕማን ዘገባ አንደኛው ጉልህ ጥንቃቄ የእግዚአብሄርን ሕጎችና ትእዛዛት መታዘዝ እድገታችንን ሊያራዝም ወይም ሊያዘገይብን እንደሚችል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታችን ፈዋሽ በመሆኑ ተባርከናል። ለእግዚአብሔር ህግጋት እና ትእዛዛት መታዘዛችን አዳኛችን ለእኛ በታዘዘልን የፈውስ እቅድ መሰረት የሚያስፈልገንን መረዳት እና ፈውስ ለመስጠት መንገድ ይከፍታል።

ሽማግሌ ሪቻርድ ጂ. ስኮት እንዳስተማሩት፣ “ይህ ህይወት በጥልቅ የመተማመን ተሞክሮ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ መታመን፣ በትምህርቶቹ መታመን፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለአሁኑ ለደስታ እነዚያን ትምህርቶች ለመታዘዝ እና በአላማ፣ እጅግ ደስተኛ ለሆነ የዘለአለም ህልውና ለመታዘዝ ባለን ችሎታ ላይ መተማመን። መታመን ማለት መጨረሻውን ከመጀመሪያው ሳናውቅ በፈቃደኝነት መታዘዝ ማለት ነው (ምሳሌ 3፥5–7 ተመልከቱ)። ፍሬ ለማፍራት፣ በጌታ ላይ ያላችሁ እምነት በእራሳችሁ የግል ስሜቶች እና ተሞክሮዎች ላይ ከመተማመን የበለጠ ሀይለኛ እና ፅኑ መሆን አለበት።

“እምነትን በተግባር ማሳየት ጌታ ከእናንተ ጋር የሚያደርገውን እንደሚያውቅ እና እንዴት ማድረግ እንደሚችል መረዳት ባትችሉም ለዘለአለማዊ ጥቅማችሁ ሊፈጽመው እንደሚችል ማመን ነው”በማለት ሽማግሌ ስኮት ይቀጥላሉ።

የመዝጊያ ምስክርነት

ውድ ወዳጆቻችን፣ ቅን የወንጌል ጥያቄዎቻችን ለሰማይ አባት እና ለኢየሱስ ክርስቶስ እንድናድግ የሚረዱንን እድሎች እንደሚሰጡ እመሰክራለሁ። ለራሴ መንፈሳዊ ጥያቄዎችን ከጌታ መልስ ለመፈለግ፣ የግል ጥረቴን በመረዳት መስመሮች እና በእግዚአብሄር መካከል ያለውን ክፍተት እርሱን ለመታዘዝ እና አሁን ያለኝን መንፈሳዊ እውቀት በታማኝነት ለመለማመድ እንድጠቀም አስችሎኛል።

በሰማይ አባት እና እርሱ በላካቸው ነቢያት ላይ መተማመናችሁ በመንፈሳዊነት ከፍ እንድትሉ እና ወደፊት ወደ እግዚአብሔር አድማስ እንድትገፉ እንደሚረዳችሁ እመሰክራለሁ። እናንተ ስለምትቀየሩ እይታችሁም ይቀየራል። እግዚአብሄር ከፍ ባላችሁ መጠን፣ አርቃችሁ ማየት እንደምትችሉ ያውቃል። አዳኛችን ወደዚያ ከፍ እንድትሉ ይጋብዛችኋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።