አጠቃላይ ጉባኤ
ንጹህ ሁኑ
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


9:43

ንጹህ ሁኑ

በየዕለቱ ንስሐ መግባት የጌታን መመሪያ በመንፈስ ቅዱስ እንድንለይ ያስችለናል።

አምስት አመቴ ገደማ ላይ፣ በትንሿ የኮትዲቮር መንደሬ ውስጥ በምትገኘው ቤተክርስቲያን ጀርባ ከጓደኞቼ ጋር እግር ኳስ እጫወት ነበር። ሰባኪው ለአዳኙ ዳግም መመለስ ለመዘጋጀት መዕመናኑ ልብሳቸውን እንዲያጸዱ ጥሪ እንዳቀረበላቸው በግልፅ አስታውሳለው። ትንሽ በመሆኔ፣ ይህንን አባባል የወሰድኩት ቃል በቃል ነበር። ትንሹ እግሬ ሊያስሮጠኝ በሚችለው ፍጥነት በመሮጥ ወደ ቤት ሄድኩኝ እና አዳኙ በሚቀጥለው ቀን በሚመጣበት ጊዜ ልብሶቼ እንከን የለሽ እና ዝግጁ ዘንድ ያሉኝን የተወሰኑ ልብሶች እናቴ እንድታጥብልኝ ለመንኳት። እናቴ ስለአዳኙ የመምጣት እርግጠኛነት የተጠራጠረች ብትሆንም፣ ምርጡን ልብሴን አጠበችው።

በሚቀጥለው ጠዋት፣ ትንሽ እርጥብ የሆነውን ልብሴን ለበስኩኝና የአዳኙን መምጣት ማሥታወቂያ በጉጉት ጠበኩኝ። ቀኑ ሲያልፍ እና ምንም ሳይከሰት ሲቀር፣ ወደ መሰብሰቢያ አዳራሹ ለመሄድ ወሰንኩኝ። ቤተክርስቲያኗ ባዶ ሆና በማግኘቴ እና አዳኙም ባለመምጣቱ በጣም አዝኜ ነበር። እያዘገምኩኝ ወደ ቤት እየሄድኩኝ በነበረበት ጊዜ ምን ዓይነት ሥሜት ውስጥ እንደነበርኩኝ ልታስቡ ትችላላችሁ።

ከአመታት በኋላ፣ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ቤተክርስቲያን አባል ለመሆን ለመዘጋጀት በነበረኝ የሚስዮን ትምህርት ላይ፣ የሚከተለውን አነበብኩኝ፦ “እናም በመንግስተ ሰማይ የረከሰ ነገር ሊገባ አይቻለውም፤ ስለዚህ በእምነታቸው እናም ለኃጠአታቸው ሁሉ ንስሃ በመግባታቸው እናም እስከመጨረሻው ባላቸው ታማኝነት በደሜ ልብሳቸውን ካፀዱት በስተቀር በእረፍቱ የሚገባ ማንም የለም።”

በዚያ ጊዜ የተቀበልኩት ማብራሪያ ከብዙ አመታት በፊት ያልበሰለ አዕምሮዬን ያመለጠውን የእውነትን አስፈላጊነት እንድገነዘብ ረዳኝ። የሰባኪው መልእክት በመንፈሳዊ ንጹህ መሆን ላይ ያተኮረ ነበር። መዕመናኑ ንስሀን እንዲሹ፣ በህይወታቸው ለውጥ እንዲያደርጉ፣ እና ደሕንነትን ለማግኘት ወደ አዳኙእንዲቀርቡ አበረታትቶ ነበር።

የሰማይ አባታችን ስጋዊ ጉዞአችንን እንዲሁም በህይወታችን ውስጥ ከኃጢአት ማምለጥ እንደማንችል ይገነዘባል። ስለመተላለፋችን የሃጢያት ክፍያ እንዲከፍልልን አዳኝ ስለላከልን ጥልቅ ምስጋና አለኝ። በአዳኙ የሚያድን የኃጢአት ክፍያ በኩል፣ እያንዳንዳችን ንስሀ ለመግባት እና ምህረትን ለመፈለግ እናም ንጹህ ለመሆን እንችላለን። በህይወት ችግሮች ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ የወንጌል መሰረታዊ መርህ የሆነው ንስሀ ለመንፈሳዊ እድገታችን እና ተቋቁመን ለመቀጠል አስፈላጊ ነው።

በሚያዝያ 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ፣ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን የቤተክርስቲያኗን አባላት በየዕለቱ ንስሀ በመግባት የሚገኘውን ደስታ እንዲያገኙ ጋብዘዋል። እንዲህም አሉ፦

እባካችሁን ንስሃ መግባት አትፍሩ ወይም ንስሃችሁን አታዘግዩት። ሰይጣን በሃዘናችሁ ይደሰታል። አጭር አድርጉት። ተጽዕኖውን ከህይወታችሁ ውስጥ አስወጡ! ተፈጥሯዊውን ሰው በማውለቅ የሚገኘውን ደስታ ዛሬውኑ ጀምሩ። አዳኙ ሁል ጊዜ ይወደናል በተለይ ንስሃ ስንገባ።

ከቃል ኪዳኑ መንገድ በጣም እንደራቃችሁ ወይም የመመለሻ መንገድ እንደሌላችሁ ከተሰማችሁ በቀላሉ ያ እውነት አይደለም።

ሙሉ ለሙሉ ንስሀ ያልገባችሁበት አንድ ነገር ካለ፣ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ንስሃችሁን እንዳታዘገዩ ያቀረቡትን ጥሪ እንድትሠሙ አበረታታችኋለሁ። በዚህ ጉዳይ ለመስራት ብርቱነት ያስፈል ይሆናል፤ ሆኖም፣ እውነተኛ ከሆነ ንስሀ የሚመጣው ደስታ ከግንዛቤ በላይ ነው። ንስሀ በመግባት፣ የጥፋተኝነት ሸክሞቻችን ይወገዳሉ እንዲሁም ወደ ሰላም እና መረጋጋት ስሜት ይለወጣሉ። በቅንነት ንስሀ ስንገባ፣ ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጣው ማነሳሻ እና ተፅዕኖ ስሜት በደንብ የሚሰማን ሆነን፣ በአዳኙ ደም እንቀደሳለን።

የዘለአለም ጓደኛዬ[ባለቤቴ] የመስማት ችግር ያለባት ሆና ነበር የተወለደችው፣ እናም በዚህ ምክንያት እንድትሰማ የሚረዳትን መሳሪያን ትጠቀም ነበር። አቧራ እና ላብ የእነዚህን መሳሪያዎች ውጤታማነት ይቀንሳሉ፣ እናም በየጠዋቱ በትጋት የመስሚያ መሳሪያዋን እንያንዳንድ ቱቦዎች እና ክፍሎች ስታጸዳ አያት ነበር። ይህ ቀላል እና ተደጋጋሚ ድርጊት ቆሻሻን፣ እርጥበትን፣ ወይም ላቦቱን ያጠፋል፣ በዚህም ለመስማት እና ግንኙነት ለማድረግ ያላትን ችሎታ ታሻሽላለች። ይህን በየቀኑ የምታደርገውን ስራ ስትረሳ፣ ቀኑን በሙሉ ለመስማት ያላትን ችሎታ ይጎዳል፤ የንግግር ቃላት ቀስ በቀስ እየጠፉ ይሄዳሉ እናም የማይሰሙ ይሆናሉ። የማዳመጫ መሳሪያዋን በየቀኑ ማፅዳት በግልፅ እንድትሰማ እንደሚያደርጋት፣ በየቀኑ ንስሀ መግባት ጌታ በመንፈስ ቅዱስ በኩል የሚሰጠንን መመሪያ እንድንረዳ ያስችለናል።

ጌታ የምድራዊ አገልግሎቱ መገባደጃ በቀረበ ጊዜ እና ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ከመሄዱ በፊት፣ ደቀመዛሙርቱን ወደፊት ለሚመጡት ፈተናዎች አዘጋጃቸው። እንዲህ በማለት አረጋገጠላቸው፦ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አፅናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።”

የመንፈስ ቅዱስ አስፈላጊ ከሆኑት ሀላፊነቶች አንዱ፣ ጸጥተኛውን ውስጣዊ ድምፅ የሚሰሙትን እያንዳንዱን ግለሰቦች ማስጠንቀቅ፣ መምራት፣ እና መመሪያ መስጠት ነው። የመስሚያው መሳሪያ የመገናኛ ቱቦ ሲዘጋ በትክክል መስራትን እንደሚከለክለው፣ ከሰማይ አባት ጋር ያለን መንፈሳዊ ግንኙነት ሊታገድ ይችላል፣ ይህም ወደ አደገኛ የተሳሳቱ አመለካከቶች እና ምክሩን ወደ አለመከተል ይመራል። የኢንተርኔት መምጣት መረጃዎች ከዚህ በፊት ከነበረው ይበልጥ እንዲገኙ አድርጓል። ይህም መመሪያ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን ወደ አለም እንድንሄድ ያደርገናል። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ “ወደፊት በሚመጡት ቀናት፣ ያለ መንፈስ ቅዱስ መመሪያ፣ ምሪት፣ መጽናኛ እና ቋሚ የሆነ ተጽዕኖ በመንፈሳዊነት ተቋቁመን ለመቀጠል አይቻልም” ብለዋል፡፡

እያንዳንዳችን የአባልነት ማረጋገጫን በምንቀበልበት ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታን ለመቀበል በመቻላችን አመስጋኝ ነኝ። ይሁን እንጂ ፕሬዘደንት ዳሊን ኤች ኦክስ “በመንፈስ ቅዱስ በኩል የሚገኙት በረከቶች በብቁነት ላይ የሚመኩ ናቸው [እና] ‘የጌታ መንፈስ ቅዱስ ባልሆነ ቤተ መቅደስ ውስጥ አይኖርም’ በማለት አስጠንቅቀዋል [ሄለማን 4፥24]።”

የነቢያትን እና የሐዋሪያትን መመሪያዎች ሆን ብለን ለመከተል ስንመርጥ፣ መንፈስ ቅዱሥን ቋሚ ጓደኛችን የማድረግ ችሎታችን ያድጋል። መንፈስ ቅዱስ፣ ከሰማይ አባት ፍላጎት ጋር አብረው የሚሄዱ ሀሳቦችን እና ግንዛቤዎችን በማነሣሣት፣ ውሳኔ በሚደረግበት ጊዜ ግልጽነትን ይሰጣል። መንፈስ ቅዱስን ቋሚ ጓደኛ ማድረግ ለመንፈሳዊ እድገታችን በጣም አስፈላጊ ነው።

በሶልት ሌክ፣ ዩታ ግሪንጀር ምዕራብ ካስማ ውስጥ የሚካሄደውን የካስማ ጉባኤ እንድመራ ጥሪ ተሰጥቶኝ ነበር። በዚህ ጊዜ፣ በጻድቅ በመኖር እና በየቀኑ ንስሀ በመግባት የመንፈስ ቅዱስን የማነሳሻ ስሜት የመለየት ችሎታ ካሣደገ የካስማ ፕሬዘዳንት ጋር ተገናኘሁ። የአገልግሎታችን ጥረትአካል በማድረግ፣ ሶስት ቤተሰቦችን ለመጎብኘት አቀናጀን። የመጨረሻውን ጉብኝት ካደረግን በኋላ፣ ወደሚቀጥለው ቀጠሮ ለመሄድ 30 ደቂቃ እንደሚቀረን ተረዳን። ወደ ካስማ ማዕከል ለመሄድ ስንጓዥ፣ ፕሬዚዳንት ቸስነት አንድ ተጨማሪ ቤተሰብን እንዲጎበኙ የመነሳሻ ስሜት ተሰማቸው። ሁለታችንም መነሳሻ ስሜቱን ለመከተል ተስማማን።

የጆንስ ቤተሰብን ለመጎብኘት ሄድን፣ በዚህም እህት ጆንስ በበሽታ ምክንያት ተኝታ እንደነበረ አወቅን። የክህነት በረከት እንደሚያስፈልጋት ግልፅ ነበር። በፍቃዷ፣ ይህን አደረገን። ለመሄድ ስንዘጋጅም፣ እህት ጆንስ፣ በረከት በአስቸኳይ ያስፈልጋት እንደነበረ እንዴት እንዳወቅን ጠየቀችን። እውነቱም፣ እኛ አላወቅንም ነበር። ነገር ግን፣ የሚያስፈልጓትን ነገሮች ያውቅ የነበረው የሰማይ አባታችን አውቆት ነበር፤ ስለሆነም ፕሬዚዳንት ቸስነትን የእርሷን ቤት እንዲጎበኝ አነሳሳው። ከተረጋጋው፣ ትንሽ ድምፅ የሚመጣውን መመሪያ የምንቀበል ስንሆን፣ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ውጤታማ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት በተሻለ የተዘጋጀን እንሆናለን።

ደግ እና አፍቃሪ ስለሆነው የሰማይ አባት እመሰክራለሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ዘር አዳኝ እና ቤዛ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአት ክፍያ እውነት እንደሆነ እናም የመንፈስ ቅዱስን መመሪያ መከተልን ስንማር፣ ንስሀ ወደመግባት እና የአዳኙን የኃጢአት ክፍያ ሀይል በህይወታችን ወደመጠበቅ ይመራናል። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን ዛሬ በምድር ላይ ሁሉም የክህነት ቁልፍ ያላቸው የጌታ እውነተኛ በህይወት ያሉ ነቢይ ናቸው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. 3 ኔፊ 27፥19

  2. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “የመንፈሳዊ ፍጥነት ሃይል፣” ሊያሆና፣፣ ግንቦት 2022 (እ.አ.አ) 98–99።

  3. ዮሀንስ 14፥26

  4. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “Revelation for the Church, Revelation for Our Lives፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2018 (እ.አ.አ)፣ 96።

  5. ዳለን ኤች. ኦክስ፣ “Always Have His Spirit [ሁልጊዜ መንፈሱ ይኑራችሁ]፣” Ensign፣ ህዳር 1996 (እ.አ.አ)።

  6. ጆንስ የጎበኘናቸው ቤተሰቦች ስም አይደለም። የግል መረጃን ላለመግለጽ ሲባል የዘፈቀደ ስሞችን ተጠቅሚአለሁ። ከፕሬዘደንት ቸስነትም ስማቸውን እና የካስማቸውን ስም ለመቀበል የተጻፈ ፈቃድ ተቀብያለሁ።