የክርስቶስ እና የመንፈስ ቅዱስ ቃላት ወደ እውነት ይመሩናል
ይህን አስደናቂ እቅድ ማወቃችን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን እና እንደ እርሱ ለመሆን እንደምንችል እንድናውቅ ይረዳናል።
እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን ነው። እኛ የመንፈስ ልጆቹ ነን፣ የተፈጠርነውም በእርሱ አምሳል ነው። ስለዚህ፣ እያንዳንዳችን፣ እንደ እግዚአብሔር ልጅ፣ እርሱን የመምሰል መለኮታዊ አቅም አለን።
ወደዚህ ምድር ከመምጣታችን በፊት እንደ መንፈስ ከእርሱ ጋር ኖረናል። የሰማይ አባት፣ እንደ መንፈሳችን ወላጅ፣ ይወደናል፣ መልካሙን እንዲሆንልን ይፈልገናል፣ እናም ለእኛ የማይሞት እና የዘለአለም ህይወት የሆኑትን የእርሱን ታላቅ በረከቶች እንድንቀበል እቅድ አዘጋጅቶልናል። በእቅዱ መሰረት፣ እኛ እንደ መንፈስ ልጆች፣ የእርሱን እቅድ እንድንመርጥ ነፃ ምርጫ ይሰጠናል። ወደ ምድር በመምጣት፣ ከእግዚአብሔር ፊት መገኘትን እንተወዋለን፣ የቀድሞ ህይወታችንን እንረሳለን፣ የስጋና የአጥንት አካል እንቀበላለን፣ ለራሳችን ተሞክሮ ማግኘት እንዲሁም እምነት እናዳብራለን። በሥጋ ሰውነታችንና አጥንታችን፣ እንደ ተፈጥሮ ሰዎች በፈተና እንሸነፋለን፣ እንረክሳለን፣ ከእግዚአብሔር እንርቃለን፣ እናም ወደ ቅዱሱ ስፍራ መመለስ አንችልም። የሰማይ አባት ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሳ፣ የበኩር ልጁን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን፣ አዳኛችን እንዲሆን ላከው። በእርሱ መስዋዕትነት፣ የኃጢያት ክፍያ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሀጢያታችን እንድንዋጅ እና ትንሣኤ እና የዘለአለም ህይወት እንድንቀበል አስችሎናል።
የአብን የማዳን እቅድ፣ የምሕረት እቅድ ወይም የደስታ እቅድ ብለን ስለምንጠራቸው፣ ለእነዚህ ክቡር እውነቶች እጅግ በጣም አመስጋኝ ነኝ። እነዚህን አስፈላጊ እውነቶች መማሬ እውነተኛ ማንነቴን እንዳውቅ ረድቶኛል እናም እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀልንን የድህንነትን እና የዘለአለም ህይወትን ታላቅ በረከቶች እንዳውቅ ረድቶኛል። ነቢዩ ኔፊ መንገዱን አስተምሮናል፦ “ስለሆነም፣ የክርስቶስን ቃል ተመገቡ እላችኋለሁ፤ እነሆ የክርስቶስ ቃል ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች በሙሉ ይነግራችኋልና።”። አክሎም፦ “በመንገዱ የምትገቡ፣ እናም መንፈስ ቅዱስን የምትቀበሉ ከሆነ፣ ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች ሁሉ ያሳያችኋል።” ዛሬ፣ የክርስቶስ እና የመንፈስ ቅዱስ ቃላቶች እነዚህን ጠቃሚ እውነቶች በጉርምስና ዘመኔ እንዴት እንዳገኝ እንደረዱኝ ማካፈል እፈልጋለሁ።
የክርስቶስ ቃል ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች በሙሉ ይነግራችኋልና።
ልክ ኔፊ በ1ኛ ኔፊ መጽሐፍ የመክፈቻ ቁጥር ላይ እንደተናገረው፣ እኔም “ከመልካም ወላጆች ተወለድኩ።” ያደግኩት በናጋኖ፣ ጃፓን ውስጥ ሐቀኝነት፣ ትጋት እና ትሕትና በሚበረታቱበት ቤት ውስጥ ሲሆን፣ ከጥንት ልማዶች ጋር መጣጣም በጥብቅ ይከተል ነበር። አባቴ በጣም ሃይማኖተኛ ሰው ነበር። በሺንቶ እና ቡዳ መሰዊያዎ ፊት በየእለቱ ጠዋት እና ምሽት ሲጸልይ አየው ነበር። ለማን እንደሚጸልይ እና ምን እንደሚጸልይ ባላውቅም፣ አንድ ዓይነት የማይታይ ኃይል ወይም አምላክ “ሊያድነን ኃያል ነው” ወይም በቅንነት ከጸለይን ሊረዳን እንደሚችል አምን ነበር።
ልክ እንደሌሎች ታዳጊ ወጣቶች ብዙ ችግሮች አጋጥመውኛል። ህይወት ፍትሃዊ እንዳልሆነ እና ብዙ ውጣ ውረዶች እንዳለው በማሰብ ታገልኩ። በህይወቴ ምንም መመሪያ እንደሌልኝ በመሆን እንደጠፋው ተሰምቶኝ ነበር። ሕይወት በጣም አጭር ይመስላል ምክንያቱም ስሞት ያበቃል። የደህንነት እቅድ እውቀት የሌለበት ህይወት ግራ አጋብቶኝ ነበር።
በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንግሊዘኛ መማር ከጀመርኩ ብዙም ሳይቆይ፣ ሁሉም የትምህርት ቤታችን ተማሪዎች የአዲስ ኪዳን ቅጂ ተቀበሉ። የእንግሊዘኛ ቋንቋን ገና ብንጀምርም መምህራችን እንግሊዘኛን በማንበብ መማር እንዳለብን ነገረን። እኔም ይህን ከፍቼ ይዘቱን ገመገምኩ። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉት ቃላት ለእኔ እጅግ በጣም ከባድ ነበሩ። በጃፓን ያሉት ቃላቶችም አስቸጋሪ ነበሩ። ይሁን እንጂ በዚህ የጌዲዮን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ በፊት ስለ ነፍሳት የሚገልጹ በርካታ መግለጫዎች እና ጥያቄዎች፣ እንዲሁም ብቸኝነት እንደመሰማት፣ ቡታት አለመሰማት፣ ግራ እንደመጋባት፣ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ስለመጋፈጥ እና ሌሎችን ስለሚያካትታቸው የጥያቄዎች ተስቤ ነበር። በዝርዝሩ ላይ ያለው እያንዳንዱ ንጥል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች እና ገፆች ማጣቀሻ ተከትሎ ነበር። በተለይ “ሲደክምህ” የሚለው መግለጫ ስቦኝ ነበር። ማጣቀሻው ማቴዎስ 11፥28–30 እንድከፍት አደረገኝ፣ በዚያም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦
“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ።
“ቀንበሬንም በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።
“ቀንበሬም ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነው።”
ይህ የኢየሱስ ክርስቶስን ቃላትን ያነበብኩበት የመጀመሪያ ጊዜ ነበር። የተናገረውን ሁሉ ባላስተውልም፣ ቃሉ አጸናኝ፣ ነፍሴን አነሳት፣ እናም ተስፋ ሰጠኝ። የሱን ቃላት ባነበብኩ ቁጥር፣ የቃሉን በጎነት መሞከር እንዳለብኝ ተሰማኝ። ያን ቀን እንደተሰማኝ ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር። እንደተወደድኩ ተሰማኝ። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደማውቀው ሰው ተሰማኝ።
ጥናቴን ስቀጥል፣ እሱ እንዲህ ሲል በቀጥታ የሚናገረኝ ያህል ተሰማኝ፦ “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።”
ስሜቴን በወቅቱ መግለጽ ባልችልም ንግግሩ ልቤን ሞላው። ምንም እንኳን ኢየሱስ ክርስቶስ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ለኔ በማላውቀው ምድር ቢኖርም ቃሉን በሙሉ ልቤ አምናለሁ ብዬ አስቤ ነበር። አንድ ቀን ወደፊት፣ ተጨማሪ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደምማር ተስፋ አድርጌ ነበር።
መንፈስ ቅዱስ ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች ሁሉ ያሳያችኋል
ያ አንድ ቀን የመጣው ከጥቂት አመታት በኋላ ነው። በአገልግሎታቸው በጣን የተጉ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ወጣት እና የሙሉ ጊዜ ሚስዮናውያንን አገኘሁ። እናም ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል የሚጥሩ ደግ እና ደስተኛ የኋለኛው ቀን ቅዱሳንን ቡድን አገኘሁ። ሙሉ በሙሉ እነሱን ለማመን ጊዜ ቢወስድብኝም፣ አዲስ ኪዳንን ሳጠና የምፈልገውን ነገር ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል እና ከእነሱ የሚመጣውን ተስፋ እና ሰላም በዳግም በተመለሰው ወንጌል ውስጥ ለማየት ችያለሁ።
በተለይ ቅዱስ ተሞክሮ የነበረው ሚስዮናውያን እንድጸልይ ሲያስተማሩኝ ነበር። እግዚአብሔርን በስም መጥራት እንዳለብኝ ተማርኩ። በምንጸልይበት ጊዜ ከልባችን በመነጨ ስሜት መናገር፣ አመስጋኝነታችንን መግለጽ እንዲሁም ተስፋችንንና ፍላጎታችንን ማካፈል ይገባናል። ማለት የምንፈልገውን ሁሉ ከተናገርን በኋላ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን” በማለት ጸሎታችንን እንጨርሳለን። ይህን የምናደርገው ኢየሱስ በስሙ እንድንጸልይ ስላዘዘን ነው። ወደ የሰማይ አባት መጸለይ ማን እንደሆነ እና ከእሱ ጋር ያለኝን ግንኙነት—የተወደደው የመንፈስ ልጁ እንደሆንኩ እንዳውቅ ረድቶኛል። የሰማይ አባት ስለሚያውቅ እና ስለሚወደኝ፣ በግል፣ በልዩ ሁኔታ እና በመንፈስ ቅዱስ በምረዳበት መንገድ እንደሚናገረኝ ተማርኩ።
በእውነት መንፈስ ቅዱስን በመለየት ለማወቅ የማልችልበት ጊዜ ነበር። ማድረግ ያለብኝ የጸሎት እርምጃዎችን መከተል ብቻ ነው እና አንድ አስደናቂ ነገር ይከሰታል ብዬ በማሰብ ተሳስቼ ነበር፣ ። አንድ ቀን፣ ከሚስዮናውያን ጋር በምማርበት ወቅት፣ እረፍት ለመውሰድ ከትምህርቱ ወጣሁ። የኢየሱስ ክርስቶስ በዳግም የተመለሰው ወንጌል እውነት ከሆነ በሕይወቴ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ተጋባሁ።
ሚስዮናውያን ወደሚጠባበቁበት ክፍል ልመለስ ስል የአንዱን ሚስዮናዊ ድምፅ ሰማሁ። ስሜን ሰማሁ። በሩን ከመክፈት ይልቅ በበሩ ማዶ ያለውን ድምጽ አዳመጥኩት። ተደንቄ ነበር። ወደ የሰማይ አባት ይጸልዩ ነበር። ጸሎቱን የሚናገረውም ጸሎቴን ይሰማልኝ ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር ይማጸን ነበር። ጃፓናዊው አቀላጥፎ ባይናገርም ልባዊ ጸሎቱን መስማቴ ልቤን አለሰለሰው። ለምን በጣም እንደሚያስቡልኝ አሰብኩ። ከዚያም በእኔ ምትክ የሚያቀርቡት ጸሎት የሰማይ አባት እና አዳኝ ለእኔ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ እንደሆነ ተገነዘብኩ። ያ ፍቅር ተስፋ ሰጠኝ እና በኋላ፣ እግዚአብሔርን በእምነት እና በቅን ልቦና ጠየቅሁት። ይህን ባደረግኩ ጊዜ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንኩ እና መለኮታዊ አቅም እና እጣ ፈንታ እንዳለኝ የደስታ እና ሰላማዊ ስሜት ተሰማኝ። የመዳን እቅድ በልቤ ውስጥ ዘልቆ ገባ።
ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳሉት፣ “ስለ ማንነታችሁ የምታስቡበት መንገድ … የምታደርጉትን እያንዳንዱን ውሳኔ ይነካል።” ይህ ለእኔ በጣም እውነት ነው። በመጠመቅ እና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በመቀበል አዳኙን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል የወሰንኩበት ላስበው ከሚያልቅ ያህል ህይወቴን ባርኮ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ጥምቀት ቃል ኪዳን ስንገባ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳችን ላይ ለመውሰድ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመጠበቅ እና ለቀሪው ህይወታችን እሱን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናችንን ቃል እንገባለን። የሰማይ አባታችን፣ በተራው፣ ሁልጊዜ መንፈሱ ከእኛ ጋር እንዲሆን ቃል ገብቶልናል—ቀጣይነት ያለው የመንፈስ ቅዱስ መመሪያ።
ኔፊ ያስተማረንን መልእክት እንድታምኑ እጋብዛችኋለሁ፣ የክርስቶስ ቃል እና መንፈስ ቅዱስ ማድረግ ያለባችሁን “ነገሮች በሙሉ ይነግራችኋልና።” ሁሉም ነገር! ይህ የማይታመን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።
ወንድሞች እና እህቶች፣ ለሰማይ አባታችን የደህንነት እቅድ አመስጋኝ ነኝ። እርሱ ስለወደደን፣ በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እርሱ የምንመለስበትን መንገድ አዘጋጅቷል። ይህን አስደናቂ እቅድ ማወቃችን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን እና እንደ እርሱ ለመሆን እንደምንችል እንድናውቅ ይረዳናል። ለዚህ አስፈላጊ እውነት አመስጋኝ ነኝ። የኢየሱስ ክርስቶስ እና የመንፈስ ቅዱስ ቃላት የዘለአለምን ህይወት እንድንቀበል እንደሚመራን ምስክርነቴን እሰጣችኋለሁ። እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን አውቃለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም፣ አሜን።