የጌታን የንስሀ ስጦታ መቀበል
ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ከመመለሣችን በፊት ነገሮች እስኪከብዱ ድረስ አንጠብቅ። በእውነት ንስሐ ለመግባት እስከ ምድራዊ ህይወታችን ፍጻሜ ድረስ አንጠብቅ።
ደግ እና አፍቃሪ ስለሆነው የሰማይ አባት እመሰክራለሁ። በሚያዝያ 2019 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ፣ እንደ ሰባዎቹ አጠቃላይ አመራር አዲስ ሀላፊነቴ ድጋፍ ከተሰጠኝ በኋላ፣ መዘምራን ልቤን እና ነፍሴን የነካውን “ተገርሜ ቆማለሁ” የሚለውን መዝሙር ዘምረው ነበር።
እነዚህን ቃላት ሠማ፣ ተደንቄ ነበር። የብቃት ማነስ እንዲሁም ጉድለቶች ቢኖሩብኝም፣ ጌታ “[በኃይሉ] ሁሉንም ነገር ማድረግ [እንደምችል]” እንዳውቅ እንደባረከኝ ሆኖ ተሰማኝ።
የብቃት ማነስ፣ ድክመት ወይም ብቁ አለመሆን ብዙዎቻችን አንዳንድ ጊዜ የምንቸገርበት የተለመደ ስሜት ነው። አሁንም ይህን ችግር ለማሸነፍ እታገላለሁ፤ በተጠራሁበትም ቀን ይህም ይሰማኝ ነበር። ይህም ብዙ ጊዜ ተሰምቶኛል እንዲሁም አሁን እናንተን በማነጋግርበት ጊዜም ይሰማኛል። ይህም ቢሆን፣ በእነዚህ ስሜቶች ብቸኛ እንዳልሆንኩኝ ተምሬአለሁ። እንዲያውም በቅዱሳት መፃሕፍት ውስጥ ተመሳሳይ ስሜት የተሰማቸው የሚመስሉ ስለነበሩ ሰዎች ብዙ ዘገባዎች ይገኛሉ። ለምሳሌ፣ ኔፊን እንደ ታማኝ እና ጀግና የጌታ አገልጋይ እናስታውሰዋለን። አንዳንድ ጊዜ፣ እርሱም እንኳን ብቁ ካለመሆን ፣ ከደካማነት፣ እና ከብቃት ማነስ ስሜት ጋር ይታገል ነበር።
እንዲህ ብሏል፣ “ጌታ ታላቅና ድንቅ ስራውን ለእኔ ለማሳየት ምንም እንኳን ቸርነቱ ታላቅ ቢሆንም ልቤ ይጮሀል—አቤቱ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! አዎን፣ ልቤ በስጋዬም የተነሳ ያዝናል፤ ነፍሴም በክፋቴ የተነሳ ታዝናለች።”
ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ብዙም ጊዜ “በድክመ[ቶቹ] እና ፍፁም ስላልሆ[ነ]”፣ በወጣትነቱ “እንደተኮነነ” ይናገር ነበር። ነገር ግን የጆሴፍ ብቁ ያለመሆን እና የጭንቀት ስሜት እንዲያሰላስል፣ እንዲያጠና፣ እንዲማር እና እንዲጸልይ ካደረጉት ነገሮች መካከል ነበሩ። እንደምታስታውሱት እውነትን፣ ሰላምን እና ይቅርታን ለማግኘት በቤቱ አቅራቢያ በሚገኘው ቁጥቋጦ ውስጥ ለመጸለይ ሄዶ ነበር። ጌታም እንዲህ ሲለው ሰማ፦ “ጆሴፍ፣ ልጄ፣ ኃጢአትህ ተሰርየውልሃል። ሂድ፣ በህጌ ተመላለስ፣ ትእዛዜንም ጠብቅ። እነሆ እኔ የክብር ጌታ ነኝ ፡፡ በስሜ የሚያምኑ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖራቸው ለዓለም ተሰቅዬአለሁ፡፡”
ጆሴፍ ከልቡ ንስሃ ለመግባት እና ነፍሱን ለማዳን መሻቱ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመጣ እና የኃጢአቱን ስርየት እንዲያገኝ ረድቶታል። የቀጠለው ጥረት ውጤት የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በዳግም መመለስን ለመቀጠል በርን ከፈተ።
ይህ አስደናቂ የነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ተሞክሮ፣ የድክመት እና የብቃት ማነስ ስሜት እንዴት የወደቀውን ተፈጥሮአችንን እንድንገነዘብ እንደሚያግዘን ያሳያል። ትሁት ከሆንን፣ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን ጥገኝነት እንድናውቅ ሊረዳን፣ እንዲሁም በልባችን ውስጥ በሙሉ አላማ ወደ አዳኙ የመመለስ እና ለኃጢአታችን ንስሃ የመግባትን ከልብ የመነጨ ፍላጎት ሊያነቃቃ ይችላል።
ጓደኞቼ፣ ንስሀ መግባት ደስታ ነው! ጣፋጭ ንስሐ ጌታ በአስተምሮው ላይ ያተኮረ ህይወት እንድንኖር “ትእዛዝ በትእዛዝ፥ በሥርዓት ላይ ሥርዓት” የሚያስተምረን የዕለት ተዕለት ሂደት አካል ነው። እንደ ጆሴፍ እና ኔፊ፣ “ለምህረት ወደ [እግዚአብሔር መጮህ እንችላለን]፤ ምክንያቱም እርሱ ለማዳን ኃያል ነውና።” እርሱ ማንኛውንም የጽድቅ ፍላጎት ወይም ጉጉት ሊያሟላ እና በህይወታችን ውስጥ ያለን ማንኛውንም ቁስል ሊፈውስ ይችላል።
መፅሐፈ ሞርሞን፦ ሌላኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ውስጥ እኔ እና እናንተ በቅን ንስሀ በመግባት ወደ ክርስቶስ እንደኢት ለመምጣት እንደሚችሉ የተማሩ ብዚ ሰዎች ለማግኘት እንችላለን።
በምወዳት የትውልድ ሀገሬ በፖርቶ ሪኮ በተፈጠረው ልምድ የጌታን ርህራሄ ምሳሌ ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ።
በትውልድ ከተማዬ ፖንሴ፣ ምሳሌ የሆነች የቤተክርስቲያኗ እህት ሴሊያ ክሩዝ አያላ፣ መጽሃፈ ሞርሞንን ለጓደኛዋ ለመስጠት ትወስናለች። ጠቀለለችውና ለእሷ ከአልማዝ ወይም ከእንቁ የበለጠ ውድ ያለችውን ይህን ስጦታ ለመስጠት ሄደች። በመንገድ ላይ እያለች አንድ ሌባ ወደ እርስዋ ቀረበና ቦርሳዋን ውስጡ ካለው ልዩ ስጦታ ጋር ይዞ ሮጠ።
ይህንን ታሪክ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስትናገር ጓደኛዋ፣ “ማን ያውቃል? ምናልባት ወንጌሉን እንድታካፍዪ ይህ አጋጣሚሽ ሆኖ ሊሆን ይችላል!”
ታዲያ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ምን እንደተከሠተ ታውቃላችሁ? ሴሊያ ደብዳቤ ደረሳት። ሴሊያ ያጋራችውን ያንን ደብዳቤ ዛሬ በእጄ ይዤዋለሁ። እንዲህም ይላል፦
ወይዘሮ ክሩዝ፡
ይቅር በይኝ፣ ይቅር በይኝ። አንቺን በማጥቃቴ ምን ያህል እንዳዘንኩ ልታውቂ አትችይም። በዚህ ምክንያት ግን ህይወቴ ተለውጧል እንዲሁም መለወጡን ይቀጥላል።
“ያ መጽሐፍ [መጽሐፈ ሞርሞን] በሕይወቴ ረድቶኛል። የዚያ የእግዚአብሔር ሰው ሕልም ውስጤን ነክቶታል። አምስት ዶላርሽን ልጠቀመው ስለማልችል እመልስልሻለሁ። ብሩህ የሆነ ገጽታ እንዳለሽ እንድታውቂ እፈልጋለሁ። ያ ብርሃን [እንዳልጎዳሽ] የከለከለኝ ይመስለኛል ለዚያም ነው በምትኩ ሮጬ የሄድኩት።
“ዳግመኛ እንደምታይኝ እንድታውቂ እፈልጋለሁ፣ በምታዪኝ ጊዜ ግን ወንድምሽ ስለምሆን አታውቂኝም። … እዚህ በምኖርበት ጌታን ማግኘት እና አንቺ ወደምትሄጂበት ቤተ ክርስቲያን መሄድ አለብኝ።
በዚያ መጽሐፍ ላይ የጻፍሽው መልእክት እንዳነባ አድርጎኛል። ከረቡዕ ምሽት ጀምሮ ማንበቡን ማቆም አልቻልኩም። እግዚአብሔር ይቅር እንዲለኝ እጸልያለሁ፣ አንቺ[ም] ይቅር እንድትይኝ እጠይቅሻለሁ። … የታሸገው ስጦታሽ መሸጥ የምችለው ነገር መስሎኝ ነበር። [ከዚያ ይልቅ] ሕይወቴን መቀየር እንድፈልግ አድርጎኛል። ይቅር በይኝ፣ ይቅር እንድትይኝ፣ እለምንሻለሁ።
ወንድሞች እና እህቶች፣ ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን የአዳኙ ብርሃን ወደ ሁላችንም ሊደርስ ይችላል። ፕሬዚዳንት ሆላንድ “ወሰን ከሌለው የክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ብርሃን ዝቅ ብላችሁ መስመጥ አትችሉም” በማለት ተናግረዋል።
ያልታሰበውን የሴሊያን ስጦታ፣ መፅሐፈ ሞርሞንን በተመለከተ፣ ይህ ወንድም የጌታን ምህረት ለመመስከር ችሏል። ምንም እንኳን ይህ ወንድም ራሱን ይቅር ለማለት ጊዜ ቢወስድበትም በንስሐ ደስታን ማግኘት ችሏል። እንዴት ያለ ተአምር ነው! አንዲት ታማኝ እህት፣ አንድ መጽሐፈ ሞርሞን፣ ልባዊ ንስሐ፣ እና የአዳኝ ኃይል በጌታ ቤት ውስጥ የወንጌልን እና የቅዱሳት ቃል ኪዳኖችን ሙላት ወደመደሰት አመሩ። ሌሎች የቤተሰብ አባላት በሙሉ ጊዜ የሚስዮናዊነት አገልግሎትን ጨምሮ በጌታ የወይን ቦታ ውስጥ የተሰጡትን ቅዱስ ኃላፊነቶች ተከትለው ተቀበሉ።
ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ስንመጣ፣ ከልብ የሆነው የንስሐ መንገዳችን በስተመጨረሻ ወደ አዳኙ ቅዱስ ቤተመቅደስ ይመራናል።
ንጹህ ለመሆን መጣር፣ በሰማይ አባታችን እና በልጁ፣ በተቀደሱ የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች በኩል ለተቻሉ የበረከቶች ሙላት ብቁ ለመሆን፣ እንዴት ያለ የፅድቅ ማነሳሻ ነው! በጌታ ቤት ውስጥ ዘወትር ማገልገል እና እዚያ የምንገባቸውን ቅዱስ ቃል ኪዳኖች ለመጠበቅ መጣር ፍላጎታችንን እንዲሁም አዳኛችንን እንድንመስል የሚያስፈልጉትን የልብ፣ የሃይል፣ የአዕምሮ እና የነፍስ ለውጥ የመለማመድ ችሎታችንን ይጨምራል። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን “በቤተ መቅደስ ውስጥ ከማምለክ የበለጠ ሰማያትን የሚከፍት ነገር የለም። ምንም የለም!” በማለት መስክረዋል።
ውድ ጓደኞቼ፣ በቂ እንዳልሆናችሁ ይሰማችኋል? ብቁ እንዳልሆናችሁስ ይሰማችኋል? እራሳችሁን እየተጠራጠራችሁ ነው? ምናልባት እንዲህ እያላችሁ ልትጨነቁ እና ልትጠይቁ ትችላላችሁ፦ እመጥናለሁ? በጣም ዘግይቶብኛል? ፍጹም የተሻልኩ ለመሆን የቻልኩትን ሁሉ እያደረኩ በተደጋጋሚ ለምን እወድቃለሁ?
ወንድሞች እና እህቶች፣ በሕይወታችን ጉዞ ላይ በእርግጥ ስህተት እንሠራለን። ነገር ግን እባካችሁ ሽማግሌ ጌረት ደብሊው. ጎንግ ያስተማሩትን አስታውሱ፣ “የአዳኛችን የኃጢያት ክፍያ ወሰን የሌለው እና ዘላለማዊ ነው። እያንዳንዳችን እንስታለን እንዲሁም ጉድለት ይኖረናል። ለጊዜው ከመንገዳችን ልንወጣ እንችላለን። የትም ብንሆን ወይም ያደረግነው ነገር ምንም ቢሆን አለመመለስ ጥቅም እንደሌለው እግዚአብሔር በፍቅር አረጋግጦልናል። እኛን ለማቀፍ ተዘጋጅቶ ይጠብቀናል።”
ውዷ ባለቤቴ ካሪ ሉም ደግሞ እንዳስተማረችኝ፣ ሁላችንም ንስሀ መግባት፣ ማዞር፣ እና ወደ “ዜሮ ሰአት” በየዕለቱ መመለስ እንዳለብን ስተምራኛለች።
የምንሰናቀልበት ይመጣል። ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ከመመለሣችን በፊት ነገሮች እስኪከብዱ ድረስ አንጠብቅ። በእውነት ንስሐ ለመግባት እስከ ምድራዊ ህይወታችን ፍጻሜ ድረስ አንጠብቅ። ይልቁንስ፣ በየትኛውም የቃል ኪዳን ጎዳና ክፍል ላይ ብንሆን፣ አሁን በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ኃይል እና የሰማይ አባት ወደ እርሱ እንድንመለስ ባለው ፍላጎት ላይ እናተኩር።
የጌታ ቤት፣ ቅዱሳን ቅዱሳት መጻህፍት፣ ቅዱሳን ነቢያት እና ሐዋርያት በክርስቶስ ትምህርት ወደ ግል ቅድስና እንድንተጋ ያነሳሱናል።
ኔፊ እንዲህ ብሏል፣ “እናም አሁን፣ እነሆ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ መንገዱ ይህ ነው፤ [ወንድ] ሰው [እና ሴት] በእግዚአብሔር መንግስት መዳን የሚችልበት ከሰማይ በታች የተሰጠ ሌላ ምንም መንገድም ሆነ ስም የለምና። እናም አሁን፣ እነሆ፣ ይህ የክርስቶስ ትምህርትና፣ መጨረሻ የሌለው አንድ አምላክ፣ የአብ፣ የወልድና፣ የመንፈስ ቅዱስ ብቸኛውና እውነተኛው ትምህርት ነው።”
ከእግዚአብሔር ጋር “አንድ የመሆን” ሂደት አስቸጋሪ እንደሆነ ሊሰማ ይችላል። ነገር ግን እኔ እና አንተ ቆም ብለን ቆም ማለት፣ አዳኝን መመልከት፣ እና እንድንለውጥ የሚፈልገውን ለማግኘት መፈለግ እና እርምጃ መውሰድ እንችላለን። ይህንንም በሙሉ ልብ ካደረግን የእርሱን ፈውስ እንመሰክራለን። እናም የጌታን የንስሃ ስጦታ ስንቀበል የእኛ ዘሮች እንዴት እንደሚባረኩ አስቡ!
አባቴ፣ ጠቢቡ ሸክላ ሠሪ እንደሚቀርፀን እና እንደሚያጠራን ይህም ከባድ ሊሆን እንደሚችል አስተምሯል። ይሁን እንጂ፣ ጠቢቡ ፈዋሽ ንፁህ ያደርገናል። ይህንን የፈውስ ኃይል ቀምሻለሁ፣ ማጣጣሜንም ቀጥያለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እና በየእለቱ ንስሃ በመግባት እንደሚመጣ እመሰክራለሁ።
ስለእግዚአብሔር ፍቅር እና ወሰን ስለሌለው ስለ ልጁ የኃጢያት ክፍያ ሃይል እመሰክራለሁ። በቅንነት እና በሙሉ ልብ ንስሀ ስንገባ ይህ በጥልቅ ሊሰማን ይችላል።
ጓደኞቼ፣ እኔ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካኝነት ዳግም ስለተመለሰው ታላቅ ወንጌል እና በነቢዩ በፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን በኩል ስለአዳኙ መለኮታዊ ምሪት ምስክር ነኝ። ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው እንደሆነ እና የነፍሳችን ፈዋሽ እንደሆነ አውቃለሁ። ስለዚህ የማውቀው እና የምመሰክረው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደሰ፣ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።