አጠቃላይ ጉባኤ
“ጓደኛዎቼም ናቸሁ”
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:49

“ጓደኛዎቼም ናቸሁ”

“ጓደኞዎቼም ናችሁ” የሚለውን የአዳኙን ንግግር በሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች መካከል ክቡር እና ቅዱስ የሆነ ግንኙነቶችን እንድንገነባ የቀረበ በጣም ግልፅ ጥሪ ነው።

ህዝባዊ ውይይት በፍርድና በንቀት በተቀየረበት፣ ጓደኝነት በልዩ ልምምዶች በሚገለጽበት ክርክርና ክፍፍል በተሞላበት ዓለም ውስጥ፣ አንድነትን፣ ፍቅርን እና አባልነትን ለመፈለግ የሚያስችለን ግልጽ፣ ቀላል እና መለኮታዊ የሆነ ምሳሌ እንዳለ አውቄያለሁ። ይህ ምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ ታላቅ አስተባባሪ እንደሆነ እመሰክራለሁ።

እኛ ጓደኞቹ ነን

ቤተክርስቲያኗ ከተቋቋመበችበት ጊዜ ጀምሮ ከነበረው ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ፣ “በሀገሮች መካከል የሚታዩ ችግሮች” “ይበልጥ እየታዩ” በነበረበት በታኅሣሥ 1832 (እ.አ.አ) ወቅት፣ በከርትላንድ ኦሀዮ የሚገኙት የኋለኛው ቀን ቅዱሳን መሪዎች ለጉባኤ ተሰበሰቡ። “ጌታ ለእነርሱ ያለውን ፈቃድ እንዲገልጥላቸው በተናጠል እና ድምፃቸውን አውጥተው” ጸለዩ። ከባድ ችግር ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ላቀረቡት ለእነዚህ ታማኝ አባላት ጸሎት እውቅና በመስጠት፣ ጌታ ቅዱሳንን ሦስት ጊዜ በሁለት ኃይለኛ ቃላት —“የእኔ ጓደኞች” እያለ በመጥራት አጽናናቸው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለረጅም ጊዜ ታማኝ ተከታዮቹን ጓደኞቼ ብሎ ጠርቷል። በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ውስጥ አዳኙ የተቀደሰ እና የተወደደ ግንኙነትን ለመግለጽ አስራ አራት ጊዜ ጓደኛ የሚለውን ቃል ተጠቀሟል። በዓለም ትርጓሜ መሠረት በማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ስለሆኑት ወይም “ላይክ” ስለሚያደርጉ ዓይነት ጓደኛ እየተናገርኩ አይደለም። በሃሽታግ ወይም በኢንስታግራም ወይም ኤክስ ላይ በሚገኝ የተከታዮች ቁጥር ሊወከል አይችልም።

እውነት ነው፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለሁ፣ “ሄይ፣ ጓደኛሞች ብቻ መሆን እንችላለን?” ወይም “በጓደኛ ዞን ውስጥ መቆየት እንችላለን” የሚሉትን አሳማሚ ቃላት የሰማሁባቸውን የሚያስደነግጡ ንግግሮች አስታውሳለሁ። በቅዱስ ቃሉ በየትኛውም ቦታ “እናንተ ጓደኞቼ ብቻ ናችሁ” ሲል አንሰማም። ይልቁንም እንዲህ አስተምሯል፣ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” እንዲሁም “እናንተም አብ የሰጠኝ ናችሁ፣ ጓደኛዎቼም ናችሁ።”

ስሜቱ ግልጽ ነው፦ አዳኙ እያንዳንዳችንን በግለሠብ ደረጃ ያውቀናል እንዲሁም ይጠብቀናል። ይህ ጥበቃ ተራ የሆነ ወይም አነስተኛ አይደለም። ይልቁንም ከፍ ከፍ የሚያደርግ፣ ይበልጥ ጠቃሚ ወደሆነ ደረጃ የሚያሳድግ እና ዘላለማዊ ነው። “ጓደኞዎቼም ናችሁ” የሚለውን የአዳኙን ንግግር “እኛም አንድ እንሆን ዘንድ” በሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች መካከል ክቡር እና ቅዱስ የሆኑ ግንኙነቶችን ለመገንባት የቀረበ በጣም ግልፅ ጥሪ አድርጌ አየዋለሁ። ይህንን የምናደርገው የመተባበር ዕድሎችን እና ሁሉም የአባልነት ሥሜትን እንዲሠማው በመሻት አንድ ላይ ስንሰባሰብ ነው።

በእርሱ አንድ ነን

አዳኝ “ኑ፣ ተከተሉኝ” በሚለው ጥሪው ይህንን በሚያምር ሁኔታ አሳይቷል። ሐዋሪያቱን ለመጥራት የተለያዩ የተከታዮች ቡድን ያላቸውን ስጦታዎች እና ግለሰባዊ ባህሪያት ተጠቅሟል። ዓሣ አጥማጆችን፣ ቀናተኞችን፣ በነጎድጓድ ማንነታቸው የሚታወቁ ወንድማማቾችን፣ እና ቀራጭን ሣይቀር ጠርቷል። በአዳኙ ላይ ያላቸው እምነት እና ወደ እርሱ ለመቅረብ ያላቸው ፍላጎት አንድ አድርጓቸዋል። ወደ እርሱ ተመለከቱ፣ እግዚአብሔርን በእርሱ አዩት እንዲሁም “ወዲያው መረባቸውን ትተው ተከተሉት።”

እኔም ከፍ ያሉ እና የተቀደሱ ግንኙነቶችን መገንባት እንዴት አንድ እንደሚያደርገን አይቻለሁ። እኔና ባለቤቴ ጄኒፈር አምስት ልጆቻችንን በኒው ዮርክ ሲቲ በማሳደግ ተባርከናል። በዚያ በተጨናነቀ ከተማ ውስጥ ከጎረቤቶቻችን፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞች፣ ከቢዝነስ አጋሮች፣ ከእምነት መሪዎች እና ከቅዱሳን ጋር ውድ እና የተቀደሰ ግንኙነት ፈጥረናል።

በግንቦት 2020 (እ.አ.አ) ልክ ዓለም ከዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ስርጭት ጋር ስትታገል፣ የኒው ዮርክ ከተማ የሃይማኖት መሪዎች ኮሚሽን አባላት በድንገት በተጠራ በኮምፒተር የታገዘ የገፅ ለገፅ ስብሰባ ላይ ተገናኙ። አጀንዳ አልነበረም። ምንም የተለዩ ተጋባዝ እንግዶች አልነበሩም። እንደ እምነት መሪዎች ሁላችንም ተሰባስበን ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች ለመወያየት ብቻ የቀረበ ጥያቄ ነበር። የበሽታ መቆጣጠሪያ ማእከል ከተማችን በዩናይትድ ስቴትስ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዋና ማዕከል እንደነበረች ሪፖርት አድርጓል። ይህ ማለት ከእንግዲህ በአካል መሰብሰብ የለም ማለት ነው። ከእንግዲህ አንድ ላይ መሰብሰብ የለም ማለት ነው።

ለእነዚህ የሃይማኖት መሪዎች የግል አገልግሎትን፣ የጉባኤ ስብሰባን እና ሳምንታዊ አምልኮን ማቆም ከባድ ጉዳት ነበር። ካርዲናልን፣ ቄስን፣ ረቢን፣ ኢማምን፣ ፓስተርን፣ ካህንን እና አንድ ሽማግሌን የሚያካትተው የእኛ ትንሽ ቡድን አባላት እርስ በርሳቸው ተደማመጡ፣ አንዳቸው ሌላውን አፅናኑ እንዲሁም ተደጋገፉ። በልዩነታችን ላይ ከማተኮር ይልቅ በጋራ የነበሩንን ተገነዘብን። ስለ እድሎች እና ከዚያም ሊሆኑ ስለሚችሉት ነገሮች ተነጋገርን። ተሰብስበን ስለእምነት እና ስለወደፊቱ አስመልክቶ ለተነሡ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጠን። ከዚያም ጸለይን። አቤት! እንዴት እንደጸለይን።

ውስብስብ እና እርስ በርስ በሚጋጩ ባህሎች በተሞላች የበለጸገች ከተማ፣ በአንድ ድምፅ፣ በአንድ ዓላማ እና በአንድ ጸሎት ወዳጆች ሆነን አብረን ስንሰራ ልዩነታችን ተንኖ ሲጠፋ አየን።

በግል ልዩነቶቻችን ላይ ከማተኮር ይልቅ ከፈጣሪ እርዳታን ለመጠየቅ ተባበርን። ከእያንዳንዱ ቀጣይ ስብሰባ ስንወጣ የበለጠ አንድ ሆነን እንዲሁም “አካፋችንን” ለማንሳት እና ወደ ሥራ ለመግባት ተዘጋጀን። ያስገኘው ትብብር እና በሺዎች ለሚቆጠሩ የኒውዮርክ ነዋሪዎች የተሠጠው አገልግሎት፣ ለመከፋፈል፣ ለመራራቅ እና ለመለያየት በሚያነሣሣ ዓለም ውስጥ ከመከፋፈል ይልቅ እንድንቀራረብ የሚያደርገን ብዙ ነገር እንዳለ አስተምሮኛል። አዳኙ፣ “አንድ ሁኑ፤ እናም አንድ ካልሆናችሁ የእኔ አይደላችሁም” ሲል ተማፅኗል።

ወንድሞች እና እህቶች፣ ለመከፋፈል ምክንያቶች መፈለግን ትተን በምትኩ “አንድ ለመሆን” እድሎችን መፈለግ አለብን። አንዳችን ከሌላችን እንድንማር እና የግል እድገትን እንድናሣይ በሚጋብዙ ልዩ ስጦታዎች እና ባህሪያት ባርኮናል። ብዙ ጊዜ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎቼ፣ እናንተ የምታደርጉትን እኔም የማደርገው ከሆነ እና እኔ የማደርገውን እናንተም የምታደርጉት ከሆነ አንፈላለግም እላቸው ነበር። ነገር ግን፣ እኔ የማደርገውን እናንተ ስለማታደርጉት እና እናንተ የምታደርጉትን እኔ ስለማላደርገው እርስ በርሳችን እንፈላለጋለን። እና ይህ ፍላጎት አንድ ያደርገናል። መከፋፈል እና ማሸነፍ ጓደኝነትን፣ ቤተሰብን እና እምነትን ለማጥፋት የሚጠቀምበት የጠላት እቅድ ነው። አንድ የሚያደርገው አዳኙ ነው።

እኛ የእርሱ ነን

“አንድ መሆን” እንደሚያመጣቸው ቃል ከተገቡ በረከቶች አንዱ ጠንካራ የአባልነት ስሜት ነው። ሽማግሌ ክዊንተን ኤል. ኩክ እንዳስተማሩት “በእውነት አባል የመሆን ዋናው መሰረት በክርስቶስ አንድ መሆን ነው።”

በቅርቡ ከቤተሰቤ ጋር ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና በሄድንበት ወቅት ያየሁትን አንድ የአካባቢውን ባሕል በጣም ወድጄው ነበር። ቤተ ክርስቲያን ወይም ቤት እንደደረስን፣ “እንኳን ደህና መጣችሁ” በሚሉት ቃላት ተቀበሉን። ምግብ ሲቀርብ አስተናጋጃችን “ተጋብዛችኋል” በማለት ያሣውቃል። እነዚህ ቀላል ሰላምታዎች የተላለፉት በዓላማ እና ሆን ተብለው ነው። እንኳን ደህና መጣችሁ። ተጋብዛችኋል።

ተመሳሳይ ቅዱስ ቃላትን በመሠብሠቢያ አዳራሾቻችን በሮች ላይ እናደርጋለን። ነገር ግን ጎብኚዎች እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚለው ምልክት በቂ አይደለም። በበሮቹ የሚገቡትን ሁሉ ሞቅ ያለ አቀባበል እናደርጋለን? ወንድሞች እና እህቶች፣ በአግዳሚው ላይመቀመጥ ብቻ በቂ አይደለም። ከሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች ጋር ከፍ ያለ እና የተቀደሰ ግንኙነት እንድንገነባ የቀረበልንን የአዳኙን ጥሪ ልንሰማ ይገባል። እምነታችንን መኖር አለብን! አባቴ ብዙ ጊዜ፣ በጋራጅ ውስጥ መተኛት መኪና እንደማያደርግ ሁሉ፣ በሰንበት ቀን ዝም ብሎ በአግዳሚ ላይ መቀመጥም ጥሩ ክርስቲያን እንደማያደርግ ያስታውስኝ ነበር።

ህይወታችንን መኖር ያለብን ዓለም እኛን እንዲያየን ሳይሆን በእኛ ውስጥ እርሱን እንዲያይ ነው። ይህ የሚከናወነው እሁድ እሁድ ብቻ አይደለም። ይህ የሚከናወነው በግሮሰሪ፣ በነዳጅ ማደያ፣ በትምህርት ቤት ስብሰባ፣ በሰፈር መሰባሰብ፣ የተጠመቁ እና ያልተጠመቁ የቤተሰባችን አባላት በሚሰሩበት እና በሚኖሩባቸው ቦታዎች ሁሉ ነው።

እሁድ የማመልከው እርስ በርሳችን እንደምንፈላለግ እና አብረን እርሱን እንደምንፈልግ ለማስታወስ ነው። በዓለማዊው ዓለም ውስጥ የሚለዩን የእኛ ልዩ ስጦታዎች እና ተሰጥኦዎች በተቀደሰ ቦታ ውስጥ አንድ ያደርገናል። አዳኙ እርስ በርሳችን እንድንረዳዳ፣ እርስ በርስ እንድንበረታታ እና አንዳችን ሌላችንን እንድናንፅ ጥሪ አድርጎልናል። ደም ይፈሳት የነበረችውን ሴት በፈወሰ ጊዜ፣ እንዲምረው የተማጸነውን ለምጻም ባነፃው ጊዜ፤ ከዚህ በላይ ምን ማድረግ እንደሚችል ለጠየቀው ለወጣቱ ልዑል ምክር በሠጠው ጊዜ፤ እምነት እንዳለው የሚያውቀውንና በእምነቱ የደከመውን ኒቆዲሞስን በወደደው ጊዜ፤ እንዲሁም ከዘመኑ ሥርዓት ጋር ያልተመሣሰለችውን ሆኖም መሲሃዊ ተልእኮውን ከገለጸላት ሴት ጋር በውኃ ጉድጓድ አጠገብ በተቀመጠ ጊዜ ያደረገው ይህንኑ ነበር። የመሰብሰቢያ እና የማገገሚያ፣ የመጠገኛ እና የትኩረት ቦታ—ይህ ነው ለእኔ ቤተክርስቲያን። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳስተማሩት፣ “የወንጌል የመረጃ መረብ በዓለም ላይ ትልቁ የመረጃ መረብ ነው። እግዚአብሔር፣ ሁላችንም ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይጋብዘናል።… ለሁሉም ሰው የሚሆን ቦታ አለ።”

አንዳንዶቻችሁ አባል እንዳልሆናችሁ እንዲሰማችሁ የሚያደርጉ ልምዶች አጋጥሟችሁ ይሆናል። አዳኙ ለእናንተ እና ለእኔ የሰጠው መልእክት አንድ አይነት ነው፦ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ለእኛ ፍጹም ቦታ ነው። ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት የተሻሉ ቀናት እንደሚመጡ፣ ብቻችሁን እንዳልሆናችሁ ቃል ኪዳን እና እኛ የምንፈልገውን ያህል የሚፈልገን ቤተሰብ እንዳለ ተስፋ ይሰጣል። ሽማግሌ ዲ. ቶድ ክሪስቶፈርሰን “ከአብ፣ ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ መሆን ያለ ጥርጥር አባል የመሆን የመጨረሻው ነገር እንደሆነ” አረጋግጠዋል። ለኮበለሉት እና ለመመለስ እድል ለሚፈልጉ፣ ዘለዓለማዊ እውነትን እና ግብዣን አቀርባለሁ፦ አባል ናችሁ። ተመለሱ። ጊዜው ነው።

ክርክር በሞላበት እና በተከፋፈለ አለም፣ አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ አሰባሳቢ መሆኑን እመሰክራለሁ። እያንዳንዳችንን “አንድ ሁኑ” ለሚለው የአዳኙ ግብዣ እና እርሱ እንዳደረገው በድፍረት “እናንተ ጓደኞቼ ናችሁ” ለማለት ብቁ እንድንሆን እጋብዛለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም፣ አሜን።