አጠቃላይ ጉባኤ
“እርሱ ነኝ”
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


15:23

“እርሱ ነኝ”

ለመለኮታዊ ፈቃድ ባለው ፍጹም ታማኝነት የሚታየው የክርስቶስ ልግስና ይጸናል እናም ይቀጥላል።

ቀኑ ሰንበት ነው፣ ስለዚም ስለክርስቶስ እና ስለሥቅለቱ ለመነጋገር ተሰብስበናል። አዳኜ ህያው እንደሆነ አውቃለሁ።

በኢየሱስ ምድራዊ ህይወት የመጨረሻ ሳምንት ላይ የተከናወነውን ይህን ድርጊት አስቡ። ሠይፍና በትር የታጠቁ የሮማውያን ወታደሮችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ነበር። በእጃቸው ችቦ በያዙ የካህናት አለቆች ሎሌዎች የተመራው ይህ በቅንዓት የተነሣሣ ቡድን የሄደው ከተማን ለመቆጣጠር አልነበረም በዚህ ምሽት በመላ ህይወቱ በየትኛውም ጊዜ መሣሪያ በመታጠቅ፣ ወታደራዊ ስልጠና በመውሠድ ወይም አካላዊ ውጊያ በማድረግ የማይታወቅን አንድ ሰው ብቻ እየፈለጉ ነበር።

ወታደሮቹ በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ለመከላከል ሲል ወደፊት ወጣና፣ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። “የናዝሬቱ ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “እኔ ነኝ። … እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ።”

ለእኔ፣ በቅዱሣት መጻሕፍት ውስጥ ካሉት በጣም ቀስቃሽ ቃላት አንደኛው ይህ ነው። ሌሎች ነገሮችን ጨምሮ፣ ምንም መሳሪያ ያልያዘ፣ የብሉይ ኪዳኑ ታላቅ ያህዌ እና የአዲስ ኪዳን መልካም እረኛ በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ ፊት መሆን ብቻ፣ —የዚህ ከማዕበል መሸሸጊያ፣ የሰላም አለቃ የሆነውን ድምፅ መስማት ተቃዋሚዎችን እንዲያፈግፍጉና አንዳቸው በሌላው ላይ ተደራርበው እንዲወድቁ እንዲሁም መላው ቡድን በዚያ ምሽት የማዕድ ቤት ሥራ ለመሥራት ተመድበው በነበረ እንዲመኙ ለማድረግ በቂ እንደሆነ በቀጥታ ይነግረኛል።

ከጥቂት ቀናት በፊት፣ በድል አድራጊነት ወደ ከተማዋ በገባ ጊዜ፣ “ይህ ማን ነው?” ብለው በመጠየቅ “መላው ከተማ ተናወጠ” በማለት ቅዱሳት መጻህፍት ይናገራሉ። ያ “ይህ ማነው?” ተብሎ የተጠየቀው ጥያቄ እነዚያ ሠልፋቸው ያልተስተካከለ ወታደሮች የጠየቁት ጥያቄ እንደሆነ አሁን መገመት እችላለሁ!

የዚያ ጥያቄ መልሥ በፊቱ ገፅታ ላይ ሊነበብ አይችልም ነበር፣ ምክንያቱም ኢሣይያስ ከሠባት መቶ ዘመናት በፊት “መልክና ውበት የለውም፣ ባየነውም ጊዜ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም” በማለት አስቀድሞ ተንብዮ ነበር። እርሱ ምንም ስለሌለው በሚያብረቀርቅ ልብሱ ወይም በታላቅ የግል ሀብቱም እንደማይታይ የተረጋገጠ ነበር። በአካባቢው ካሉ ምኩራቦች በየትኛውም ሙያዊ ስልጠና የወሰደ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም በአንዱም ውስጥ እንደተማረ የሚናገር ምንም ማስረጃ የለም፤ ምንም እንኳን በልጅነቱ እጅግ በጣም የተዘጋጁ ጸሀፊዎችን እና ሕግ አዋቂዎችን “እንደባለሥልጣን [በማስተማር]” በትምህርቱ ያስደንቃቸው ነበር።

በቤተመቅደሱ ውስጥ ካስተማረበት ጀምሮ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም እስከገባበት ጊዜ ድረስ እና በመጨረሻም ፍትሃዊ ባልሆነ ምክንያት እስከታሰረበት ድረስ፣ ኢየሱስ ሁልጊዜ ድል አድርጓቸው በነበሩ አስቸጋሪና ብዙውን ጊዜ ተንኮለኛ ሁኔታዎች ውስጥ ተከቶ ነበር። እነዚህ ድሎች በመለኮታዊ ዘረ መል ምክንያት የመጡ ናቸው ከማለት በስተቀር ምንም ማብራሪያ የላቸውም ነበር።

ሆኖም በታሪክ ውስጥ ብዙዎች ስለ እርሱ ያለንን ምስል እና ማን እንደነበር የሠጠውን ምስክርነት አቅልለዋል፤ አልፎ ተርፎም እዚህ ግባ የማይባል እንዲሆን አድርገዋል። አንዳንድ ሰዎች ጽድቁን ነገሮችን በጣም ፀያፍ እንደሚያደርግ፣ ፍርዱን ወደ ተራ ቁጣ፣ ምህረቱን ችሎ እንደማለፍ ዝቅ አድርገው ተመልክተውታል። የማይመቹ ሆነው የምናገኛቸውን ትምህርቶቹን በሚመች መልኩ ችላ በሚሉ እንደዚህ ባሉ ተቃለው በሚቀርቡ የእርሱ መልኮች ጥፋተኛ አንሁን። ይህ “ሆነ ብሎ ከልክ በላይ ማቃለል” ታላቅ በጎነቱን ይኸውም ፍቅሩን በተመለከተም እንኳን እውነት ነው።

ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ጊዜ፣ ሁለት ታላቅ ትእዛዛት እንዳሉ አስተምሯል። እነዚህ ትምህርቶች በዚህ ጉባኤ ላይ ተሠጥተዋል እንዲሁም ለዘለዓለምም መሠጠታቸውን ይቀጥላሉ፦“ጌታ አምላክህን ውደድ [እና] ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ።” እነዚህን ሁለት ወሳኝ እና የማይነጣጠሉ ተያያዥ ህጎች በመጠበቅ አዳኙን በታማኝነት የምንከተል ከሆነ፣ በትክክል እርሱ ያለውን አጥብቀን መያዝ አለብን። በእርግጥ እርሱ ያለውም፣ “ከወደዳችሁኝ ትዕዛዛቴን ጠብቁ” ነበር፡፡ በዚያው ምሽት፣ “እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ [መዋደድ]” አለባችሁ ሲል ተናግሯል።

በእነዚያ ጥቅሶች ውስጥ እውነተኛ የክርስቶስን የመሰለ ፍቅርን የሚገልጹት ብቃት ያላቸው ሐረጎች ያለጥርጥር አስፈላጊ ናቸው።

እነዚህ ምን ትርጉም ይሰጣሉ? ኢየሱስ የወደደው እንዴት ነበር?

በመጀመሪያ፣ ጥልቅ የሆነውን ህመም የመፈወስ እና ጠንካራ እውነቶችን የማወጅ ችሎታ በሠጠው “በሙሉ [ልቡ]፣ ኃይ[ሉ]፣ አዕምሮው እና ጉልበቱ” ወዷል። ሲጠቃለል፣ እርሱ ጸጋን መስጠት እና በዚያውም እውነትን ማፅናት የሚችል ነው። ሌሂ ለልጁ ለያዕቆብ በሠጠው በረከት ላይ እንዳለው፣ “ቤዛነት በቅዱሱ መሲህ እና በእርሱ አማካይነት ይመጣል፤ ምክንያቱም እርሱ በፀጋ እና በእውነት የተሞላ ነው።” በሚያስፈልግ ጊዜ ፍቅሩ የሚያበረታታ እቅፍን እንዲሁም አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ መራራ ጽዋ እንዲጠጣ ያስችላል። እርሱ የሚወደን በዚያ መንገድ ስለሆነ—በሙሉ ልባችን፣ ኃይላችን፣ አዕምሯችን እና ጉልበታችን ለመውደድ እንሞክር።

ሁለተኛው የኢየሱስ መለኮታዊ ልግስና ባህሪ፣ ሁል ጊዜ ፈቃዱን እና ባህሪውን ከሠማይ አባቱ ጋር በማስማማት ከእግዚአብሔር አፍ ለሚወጣው ቃል ሁሉ መታዘዝ ነበር።

ከትንሳኤው በኋላ ወደ ምዕራቡ የዓለም ክፍል በመጣ ጊዜ፣ ክርስቶስ ለኔፋውያን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፣ እኔ … ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ። እናም አብ ከሰጠኝ መራራ ፅዋም ጠጥቻለሁ፣… በዚህም ከመጀመሪያ ጀምሮ … የአብን ፈቃድ ፈፅሜአለሁ።”

ኢየሱስ ራሱን ሊያስተዋውቅ ይችል በነበረባቸውን ሥፍር ቁጥር በሌላቸው መንገዶች፣ ይህ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እርሡን እጅግ በጣም ከፈለገው ጊዜ ብዙም ሣይርቅ በአባቱ ሙሉ በሙሉ እንደተተወ ተሰምቶት የነበረ ቢሆንም፣ ኢየሱስ ይህን ያደረገው፣ ለአብ ፈቃድ ታዛዥነቱን በማወጅ ነበር። ለመለኮታዊ ፈቃድ ባለው ፍጹም ታዛዥነት የሚታወቀው— የክርስቶስ ፍቅር ቀላል እና ምቹ በሆኑት ጊዜያት ብቻ ሳይሆን በልዩም በሚያስጨንቁ እና አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት ውስጥም ጸንቷል እንዲሁም በመፅናቱ ይቀጥላል።

ኢየሱስ “[የ]ሕማም … ሠው፣” እንደነበረ ቅዱሣት መፃሕፍት ይናገራሉ። ሃዘን፣ ድካም፣ ብስጭት እና የሚያሰቃይ ብቸኝነት ተሠምቶታል። በእነዚህ እና በሁሉም ጊዜያት፣ የኢየሱስ ፍቅር አይወድቅም፣ የአባቱም እንዲሁ። በምሳሌ በሚያሳየው፣ ሀይል በሚሰጠው፣ እና በሚያካፍለው፣ በእንደዚህ አይነት የበሰለ፣ እውነተኛ ፍቅር፣ የእኛም አይወድቅም።

ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ በጣም በጣራችሁ መጠን፣ ለማግኘት ይበልጥ አስቸጋሪ ከመሠላችሁ፤ ባሉባችሁ ድክመቶች እና አለፍፅምናችሁ ላይ ለመሥራት ስትሞክሩ፣ እምነታችሁን የሚፈትን ሰው ወይም የሆነ ነገር ከገጠማችሁ፤ በትጋት ስትሠሩ፣ አሁንም የፍርሀት ጊዜያት በጥልቀት ከተሰሟችሁ፣ በእያንዳንዱ ዘመን በነበሩ በድንቅ ሁኔታ ታማኝ በሆኑ አንዳንድ ሰዎች ላይም እንዲሁ እንደነበረ አስታውሱ። በተጨማሪም የምትሞክሩትን እያንዳንዱን መልካም ነገር ለመቃወም የወሰነ ኃይል በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ እንዳለ አስታውስ።

ስለዚህ፣ በመትረፍረፍም ሆነ በድህነት ወቅት፣ በግል መሞገሥም ሆነ በአደባባይ ትችት፣ በዳግም መመለሥ መለኮታዊ ነገሮችም ሆነ የእሱ አካል መሆናቸው ከማይቀረው የሰው ልጅ ድክመቶች ቢኖሩም፣ ከክርስቶስ እውነተኛ ቤተክርስቲያን ጋር በመቀጠል እንሂድ። ለምን? ምክንያቱም እንደ አዳኛችን፣ ለመጀመሪያው አጭር ጥያቄ ሳይሆን ለመጨረሻው ፈተና፣ እንዲሁም ለሙሉ የትምህርት ክፍሉ ተመዝግበናል። በዚህ ውስጥ ያለው አስደሣች ነገር፣ ዋና አስተማሪው ገና ከጅምሩ፣ ለሚኖሩት ጥያቄዎች ለሁላችንም መልሶችን የምናገኝበት መፅሐፍ መስጠቱ ነው። በተጨማሪም፣ በመንገዱ ላይ ባሉት መደበኛ መቆሚያዎች እነዚያን መልሶች የሚያስታውሱን ብዙ አስጠኚዎች አሉን። ሆኖም፣ እርግጥ ነው፣ ከት/ ቤት በመቅረት ከቀጠልን አንዳቸውም በደንቡ አሠሩም።

“ማንን ትፈልጋላችሁ?” በሙሉ ልባችን “የናዝሬቱ ኢየሱስን” ብለን እንመልሳለን። “እኔ እርሱ ነኝ፣” ሲል፣ እርሱ ሕያው ክርስቶስ መሆኑን፣ እርሱ ብቻ የኃጢአት ክፍያውን እንደከፈለልን፣ የተወን በመስለን ጊዜ እንኳን እንደተሸከመን፣ በጉልበታችን ተንበርክከን በአንደበታችን እንመሰክራለን። በፊቱ ቆመን በእጆቹ እና በእግሮቹ ላይ ያሉትን ጠባሳዎች ስንመለከት፣ ለእርሱ ኃጢአታችንን መሸከም እና ኃዘንን የሚያውቅ፣ ሙሉ በሙሉ ለአብ መታዘዝ ምን ትርጉም እንዳለው መገንዘብ እንጀምራለን። እነዚህ ሁሉ የሆኑትም ለእኛ ባለው ንጹህ ፍቅር.የተነሳ ነው። ሌሎችን ከእምነት፣ ንስሐ ከመግባት፣ ከማጥመቅ፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ከመቀበል እና በጌታ ቤት ውስጥ ቅዱስ በረከቶቻችንን ከመቀበል ጋር ለማስተዋወቅ—እነዚህ እውነተኛውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የሚለዩ ለእግዚአብሔር፣ ለባልንጀራችን እና ለቤተክርስቲያኗ ያለንን ታላቅ ፍቅር የሚያሳዩ “መርሆች እና ሥርዓቶች” ናቸው።

ወንድሞች እና እህቶች፣ በምድር ያለችው የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር በዘለዓለማዊ ሕይወት ከፍ ከፍ እንድንል ያዘጋጀልን መንገድ እንደሆነ እመሰክራለሁ። ወንጌል ይህ እውነት እንደሆነ፣ እናም እውነተኛ የሚያደርገው ክህነት ምንጭም የታወቀ ነው። ራስል ኤም. ኔልሰን ከእርሣቸው የቀደሙት እንደነበሩት እና ከእርሣቸው በኋላ የሚመጡት እንደሚሆኑት፣ የአምላካችን ነቢይ እንደሆኑ እመሰክራለሁ። እንዲሁም ያ ነቢያዊ መመሪያ አንድ ቀን የደኅንነት መልእክተኛችን “መብረቅ … ከምሥራቅ” ሲወጣ ወደ ማየት ትውልድን ይመራል፣ እኛም “የናዝሬቱ ኢየሱስ” እንላለን። ለዘለዓለም በተዘረጉ እጆቹ እና ግብዝነት በሌለበት ፍቅር፣ “እኔ ነኝ” በማለት ይመልሳል። ስለዚህ ቃል የምገባው በሐዋርያዊ ሃይል እና በቅዱስ ሥሙ ሥልጣን፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም ነው፣ አሜን።