አጠቃላይ ጉባኤ
ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መጣመር፦ የምድር ጨው መሆን
የጥቅምት 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


10:49

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መጣመር፦ የምድር ጨው መሆን

ከጌታ ጋር እንደተጣመርን ስንቆይ፣ ህይወታችን የእርሱን ብርሃን ያንጸባርቃል፣ እንዲሁም “የምድር ጨው” እንሆናለን።

“ወደ ዘለአለማዊ ወንጌ[ሉ] [ስንጠራ]፣ እና በዘለአለማዊነትም ቃል ኪዳንን [ስንገባ]፣ እንደምድር ጨው እና የሰዎች ጣዕም ሆነ[ን] [እንደምንቆጠር] አዳኙ አስተምሯል። ጨው አንድ ላይ ከተጣመሩ ሁለት ንጥረ ነገሮች የተሰራ ነው። በራሳችን ጨው መሆን አንችልም፤የምድር ጨው ለመሆን ከጌታ ጋር መጣመር አለብን እና እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ካሉ የቤተክርስቲያን አባላት ጋር ስቀላቀል የማየው ያንን ነው—ታማኝ የቤተክርስቲያኗ አባላት ከጌታ ጋር ሲጣመሩ፣ ሌሎችን ለማገልገል በሚያደርጓቸው ጥረቶች ቁርጠኛ ሲሆኑ እና የምድር ጨው ሲሆኑ።

የማይወላውል ቁርጠኝነታችሁ የሚደነቅ ምሣሌ ነው። አገልግሎታችሁ የሚደነቅ እና የተከበረ ነው።

ወጣቶቻችን አስደናቂ ድፍረት እና መሠጠት አሳይተዋል። የቤተሰብ ታሪክ ሥራን በደሥታ ተቀብለዋል። እንዲሁም የጌታን ቤት ደጋግመው መጎብኘታቸው የመሰጠታቸው ምሥክር ነው። በዓለም ዙሪያ በሚስዮን ለማገልገል ጊዜን እና ጉልበትን ለመስጠት ያላቸው ፍላጎት ጥልቅ እና ፅኑ እምነትን ይወክላል። ዝም ብለው እየተሳተፉ ብቻ ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተጣመሩ ደቀመዛሙርት የመሆንን መንገድ እየመሩ ነው። አገልግሎታቸው፣ ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ሕይወቶች ላይ ተፅዕኖ በማሣደር መነሣሣትን እና ተስፋን ይሠጣል። እናንተ የቤተክርስቲያኗ ወጣቶች፣ ለሚያነሣሣ አገልግሎታችሁ ያለንን ልባዊ ምስጋና እናቀርባለን። እናንተ የቤተክርስቲያኗ የወደፊት ተሥፋ ብቻ ሳትሆኑ የዛሬም ተሥፋዋ ናችሁ። በእርግጥ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ!

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እወደዋለሁ እንዲሁምም በጌታ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከእናንተ ጋር ለማገልገል ባገኘሁት ዕድል እንደተባረኩኝ ይሰማኛል። በምንጋራው እምነታችን ላይ የተመሰረተው አንድነታችን እና ጥንካሬያችን በዚህ ጉዞ ላይ በፍፁም ብቻችንን አለመሆናችንን ያረጋግጥልናል። በአገልግሎት፣ በፍቅር እና በማያወላውል የእምነት ጠንካራ መሠረት ላይ በአንድነት የእግዚአብሄርን መንግሥት መገንባታችንን መቀጠል እንችላለን።

ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ባስተማረበት ጊዜ ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማስተላለፍ አድማጮቹ የሚያውቋቸውን ዕለት ተዕለት የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች ይጠቀም ነበር። ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ጨው ነበር። ኢየሱስ፣ “[እናንተ] የምድር ጨው ናችሁ” በማለት ሲናገር ፣ በተለይም የጨውን የተለያየ ዓይነት ዋጋ ለሚገነዘቡ በዘመኑ ለነበሩ ሰዎች ጥልቅ ትርጉም እና ጠቀሜታ ነበረው።

በትውልድ ሀገሬ በፖርቹጋል ደቡባዊ ክልል በአልጋርቭ የሚገኘው የጥንት ጨው የማምረት ሥራ የተጀመረው በሮማ አገዛዝ ዘመን በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ነበር። በሚያስደንቅ ሁኔታ፣ ጨው አምራች ሠራተኞች የሚጠቀሙበት፣ ማርኖቶስ በመባል የሚታወቀው ዘዴ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እምብዛም አልተለወጡም። እነዚህ የተሠጡ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ለክፍለ ዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ቅርስ በመጠበቅ ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ በእጃቸው በማከናወን ባህላዊ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ።

በዚህ የጥንት ዘዴ የሚመረተው ምርት “የጨው አበባ” ተብሎ ይጠራል። የጨው አበባን የማምረት ውስብስብ ሂደት በደንብ ለማድነቅ፣ የሚመረትበትን አካባቢ መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። የአልጋርቭ የባህር ዳርቻ የጨው ረግረጋማ መሬት ጨው ለማምረት አመቺ ሁኔታዎች አሉት። የባህር ውሃ የጨው ማጠራቀሚያ በመባል ወደሚታወቁት ጥልቀት ወደሌላቸው ኩሬዎች እንዲገባ ይደረጋል ከዚያም በኃይለኛው ፀሃይ እንዲተን ይደረጋል። ውሃው በሚተንበት ጊዜ የጨው አበባው በጨው ማጠራቀሚያዎቹ ወለል ላይ ለስላሳ ክሪስታሎችን ይሠራል። እነዚህ ክሪስታሎች ከሚገባው በላይ ንፁህ ናቸው እንዲሁም ልዩ የሆነ ሸካራነት አላቸው። ማርኖቶሶች ልዩ መሣሪያዎችን በመጠቀም በውሃው ወለል ላይ ያሉትን ክሪስታሎች በጥንቃቄ ገፈው ያነሣሉ፤ ይህ ሂደት ከፍተኛ ብቃት እና ትክክለኛ ልኬትን ይጠይቃል። ፖርቹጋል ውስጥ ይህ ከፍተኛ ጥራት ያለው ጨው “የጨው ክሬም” በመባል ይታወቃል፤ ምክንያቱም በወተት አናት ላይ እንደሚንሣፈፍ ክሬም በጥንቃቄ ተገፎ ሊነሣ ስለሚችል ነው። ይህ ለሥላሣ ጨው በጥራቱ እና ልዩ በሆነው ጣዕሙ የተወደደ ነው፤ ይህም በምግብ አሰራር ሙያ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ግብዓት ያደርገዋል።

ማርኖቶዎች ከፍተኛ ጥራት ያለውን ጨው ለማምረት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ሁሉ፣ እኛም ጌታ የቃል ኪዳን ሕዝቦች እንደ መሆናችን ፍቅራችን እና ምሳሌነታችን በተቻለ መጠን የአዳኙ የኢየሱስ ክርስቶስ ንፁህ ነጸብራቅ እንዲሆን ሁል ጊዜ ከሁሉም በላይ የተቻለንን እናደርጋለን።

በጥንቱ ዓለም ጨው ከምግብ ማጣፈጫ ቅመም በላይ ነበር— ምግብ ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያደርግ ወሳኝ የሆነ ነገር እንዲሁም የንጽህና እና የቃል ኪዳን ምልክት ነበር። ሰዎች፣ ጨው ምግብ ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ እና ጣዕሙን ለመጨመር አስፈላጊ እንደሆነ ያውቁ ነበር። በተጨማሪም ጨው በመበከል ወይም በመሟሟት አልጫ ቢሆን ወይም ባይጣፍጥ ለምንም እንደማይጠቅም ተረድተው ነበር።

ጨው አስፈላጊነቱን ሊያጣ እንደሚችል ሁሉ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ዘላቂ ካልሆነ እኛም መንፈሳዊ ጥንካሬያችንን ልናጣ እንችላለን። ላይ ላዩን አንድ ዓይነት የሆንን ልንመስል እንችላለን፣ ነገር ግን ያለ ጠንካራ ውስጣዊ እምነት፣ በዓለም ላይ ለውጥ ለማምጣት እና በዙሪያችን ያሉት ሰዎች ሊሆኑ የሚችሉትን ምርጥ ማንነታቸውን እንዲሆኑ የማበረታታት አቅማችንን እናጣለን።

ታዲያ፣ ሃይላችንን እና ጥረታችንን ለለውጥ የምናውለው እና ዛሬ ዓለም የሚፈልገውን ለውጥ ማምጣት የምንችለው እንዴት ነው? ደቀ መዝሙርነታችንን የምናስጠብቀው እና በጎ ተፅዕኖ በማሳደር መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

የውድ ነቢያችን ቃላት አሁንም በአእምሮዬ ያቃጭላሉ፦ “እግዚአብሔር አብረን እንድንሠራ እና እርስ በርሣችን እንድንረዳዳት ይፈልጋል። በቤተስብ ውስጥ አድርጎ ወደ ምድር የላከን እንዲሁም በአጥቢያዎች እና በካስማዎች ያደራጀን በዚህ ምክንያት ነው። ለዚህም ነው እርስ በርሳችን እንድናገለግል የጠየቀን። ለዚህም ነው በአለም ውስጥ እንድንኖር ነገር ግን ከአለም እንዳንሆን የሚጠይቀን።

ሕይወታችን በዓላማ እና አገልግሎት በመሥጠት ሲሞላ፣ በመንፈሳዊ ግድየለሽ ከመሆን እናርቃለን፤ በሌላ በኩል፣ ሕይወታችን መለኮታዊ ዓላማ፣ ለሌሎች ትርጉም ያለው አገልግሎት ከመሥጠት እንዲሁም ለማሰላሰል እና ለማሠብ የተቀደሡ ዕድሎችን ሲነፈግ፣ ቀስ በቀስ ጣዕማችንን የማጣት አደጋ ውስጥ በመውደቅ በራሣችን ተግባራት እና የግል ጥቅም ሣቢያ በአግባቡ ማደግ ያቅተናል። ለዚህ መፍትሄው አገልግሎት በመስጠት መሣተፋችንን መቀጠል ነው—ይኸውም፣ መልካም ሥራን በጉጉት በማከናወን እና ራሳችንን እና የምንኖርበትን ህብረተሰብ በማሻሻል መሣተፍ ነው።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ዛሬ ሁላችንም የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት በመሆናችን እና በእርሱ ቤተክርስቲያን ውስጥ የማገልገል ዕድል በማግኘታችን ምንኛ ተባርከናል? ያለንባቸው ሁኔታዎች ሊለያዩ ይችላሉ ነገርግን ሁላችንም ለውጥ ለማምጣት እንችላለን።

ጨው አምራች ሠራተኞች የሆኑትን ማርኖቶሶችን፣ አስታውሱ፤ ምርጥ ክሪስታሎችን፣ ምርጥ ጨው ለማምረት ቀላል መሣሪያዎችን ይጠቀማሉ! እኛም ትናንሽ እና ትርጉም የሚሰጡ ተግባራትን ለማከናወን የማያቋርጡ ጥረቶችን በማድረግ ደቀ መዝሙርነታችንን እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ቁርጠኝነት የሚያጠናክሩ ቀላል ነገሮችን ማድረግ እንችላለን። “የምድር ጨው” ለመሆን ጥረት የምናደርግርባቸው አራት ቀላል ኖሆም ታላቅ የሆኑ መንገዶች ቀጥሎ ቀርበዋል፦

  1. የጌታን ቤት የአምልኳችን በጣም አስፈላጊው ክፍል ማድረግ። አሁን ቤተመቅደሶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በቅርበት ይገኛሉ፤ የዘወትር አምልኳችንን በጌታ ቤት ውስጥ ማድረግን ቅድሚያ መስጠት በጣም አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ እንድናተኩር እንዲሁም ሕይወታችንን ክርስቶስን ያማከለ ለማድረግ ይረዳናል። በቤተመቅደስ ውስጥ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የማመንን ዋና ክፍል እና ለእርሱ የመሠጠታችንን እውነተኛ አስፈላጊነት እናገኛለን።

  2. ወንጌልን በጋራ በመኖር ሌሎችን ለማጠናከር የምናደርገውን ጥረት አስበንበት ማድረግ። የወንጌል መርሆችን ወደ ህይወታችን እና ወደ ቤታችን ለማምጣት በሚደረጉ የማያቋርጡ እና የታሰበባቸው ጥረቶች ቤተሰቦቻችንን ማጠናከር እንችላለን።

  3. ጥሪን ለመቀበል እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኛ መሆን። በአካባቢያችን በሚገኙ መሠብሠቢያዎች የምንሠጠው አገልግሎት እርስ በርስ እንድንደጋገፍና አብረን እንድናድግ ያስችለናል። ማገልገል ሁልጊዜ የሚመች ባይሆንም ሁልጊዜ በረከትን ያመጣል።

  4. በመጨረሻም፣ ዲጂታል የመገናኛ መሣሪያዎችን በዓላማ መጠቀም። ዲጂታል የመገናኛ መሳሪያዎች ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መገናኘት እንድንችል አድርገውናል። እንደ አብዛኞቻችሁ ሁሉ እነዚህን መሳሪያዎች በቤተክርስቲያኗ ካሉ ወንድሞች እና እህቶች እንዲሁም ከቤተሰቤ እና ከጓደኞቼ ጋር ለመገናኘት እጠቀማለሁ። ከእነርሱ ጋር ስገናኝ ወደ እነርሱ ይበልጥ እንደቀረብኩ ይሰማኛል፤ እርዳታ በሚያስፈልግበት ጊዜ በአካል መገኘት በማይቻልበት ጊዜ እርስ በርሳችን ማገልገል እንችላለን። እነዚህ መሳሪያዎች ያለ ጥርጥር በረከት ናቸው፣ ነገር ግን እነዚህ ተመሳሳይ መሳሪያዎች ከትርጉም መስተጋብር ጥልቅነት ሊጎትቱን እና በመጨረሻም አላማ በሌላቸው እንቅስቃሴዎች ጊዜያችንን ወደሚያባክኑ ልማዶች እንድንሳብ ያደርጉናል። የምድር ጨው ለመሆን ጥረት ማድረግ በ15 ሣ.ሜ ስክሪን ላይ አጫጫር ቪዲዮዎችን ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው ጊዜያት ወደ ላይ እና ወደታች ከማድረግ የበለጠ ነገርን ይጨምራል።

በህይወታችን ውስጥ የጌታን ቤት ማዕከል ስናደርግ፣ አስበንበት ወንጌልን በመኖር ሌሎችን ስናጠናክር፣ ለማገልገል የሚቀርቡ ጥሪዎችን ስንቀበል እና ዲጂታል መሳሪያዎችን በዓላማ ስንጠቀም፣ መንፈሳዊ ጥንካሬያችንን ጠብቀን እናቆያለን። ንጹህ ጨው የማጣፈጥ እና ሣይበላሽ የማቆየት ኃይል እንዳለው ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነትም በእኛ እንደ ክርስቶስ ዓይነት የሆነ አገልግሎት እና ፍቅር መሠጠት ሲመገብና ሲጠበቅ ይጨምራል።

ከጌታ ጋር እንደተጣመርን ስንቆይ፣ ህይወታችን የእርሱን ብርሃን ያንጸባርቃል፣ እንዲሁም “የምድር ጨው” እንሆናለን። በዚህ ጥረት የራሳችንን ህይወት ማበልጸግ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻችንን እና ማህበረሰባችንን እናጠናክራለን። ይህን ከጌታ ጋር ያለን ግንኙነት ለመጠበቅ እንጣር፣ በምንም አዳኛችንን አንጣ፣ እንዲሁም ጌታ እንድንሆን የሚፈልገን ትንሹ፣ ግልፅ የጨው ክርስታል አንሁን። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።