ቅዱሳት መጻህፍት
ሞሮኒ ፰


ምዕራፍ ፰

ህጻናትን ማጥመቅ የከፋ ርኩሰት ነው—ህፃናት በክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ አማካይነት ህያው ናቸው—እምነት፤ ንሰሃ፤ የዋህነት እናም የልብ ርህራሄ፤ መንፈስ ቅዱስን መቀበል፣ እና እስከ መጨረሻው ፅኑ መሆን ወደ ደህንነት ይመራል። ፬፻፩–፬፻፳፩ ዓ.ም. ገደማ።

አባቴ ሞርሞን ለእኔ ለሞሮኒ የፃፈልኝ ደብዳቤ፤ እናም የተፃፈልኝ ወዲያው ለአገልግሎት ከተጠራሁ በኋላ ነበር። እናም በዚህም ሁኔታ እንዲህ ሲል ነበር የፃፈልኝ፥

የተወደድክ ልጄ ሞሮኒ፣ ጌታህ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለአንተ ስለሚያስብልህ እናም ለአገልግሎት እናም ለቅዱሱ ስራው ስለጠራህ እጅግ ተደስቻለሁ።

እናም በቅዱሱ ልጁ በኢየሱስ ስም ወደ እግዚአብሔር አብ ያለማቋረጥ በመፀለይ፣ እርሱም ወደር በሌለው ቸርነቱ እንዲሁም ፀጋው እስከመጨረሻው በእምነት የፀናህ እንድትሆን ይጠብቅህ ዘንድ፣ ሁል ጊዜ በፀሎቴ ስለአንተ አስባለሁ።

እናም እንግዲህ፣ ልጄ እጅግ ያሳዘነኝን ነገር በተመለከተ እነግርሃለሁ፤ በመካከላችሁ ክርክር በመነሳቱ እኔን አሳዝኖኛል።

እውነቱን እንደተረዳሁት ከሆነ፣ የህጻናትን ጥምቀት በሚመለከት በመካከላችሁ ክርክር ነበር።

እናም እንግዲህ፣ ልጄ ይህ ታላቅ ስህተትም ከመካከላችሁ እንዲወገድ ተግተህ እንድትሰራ እፈልጋለሁ፤ ለዚህ ስልም ይህንን ደብዳቤ ፃፍኩልህ።

ስለእነዚህን ነገሮች ካንተ ካወቅሁኝ በኋላ ሁኔታውን በሚመለከት ጌታን ወዲያው ጠየቅኩኝ። እናም የጌታ ቃልም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲህ ሲል መጣልኝ፥

የአዳኝህን፣ የጌታህን እናም የአምላክህን የክርስቶስን ቃል አድምጥ። እነሆ፣ ወደ ዓለም የመጣሁት ፃድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ንሰሃ እንዲገቡ ልጠራ ነው፤ ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ስለሆነም፣ ህፃናት ፍፁማን ናቸው፤ ኃጢያትንም ለመፈፀም አይችሉምና፤ ስለሆነም፣ የአዳም እርግማን ከእነርሱ በእኔ ተወስዷል፤ በእነርሱ ላይ ምንም ኃይል የለውም፤ የግርዘት ህግም በእኔ ተሽሯል።

እናም በዚህ ሁኔታ ነው መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል የገለጠልኝ፤ ስለሆነም፣ የተወደድክ ልጄ፣ ህፃናትን ማጥመቅህ በእግዚአብሔር ፊት ከባድ ፌዝ መሆኑን አውቃለሁ።

እነሆ ይህንን ነገር እንድታስተምር እልሃለሁ—ንስሀ መግባትን እና ጥምቀትን ተጠያቂ ለሆኑት እና ኃጢያትን ለሚፈጽሙት፤ አዎን፣ ወላጆች ንሰሃ መግባት እናም መጠመቅ እንዳለባቸው፣ እናም እንደ ህፃናቱ ልጆቻቸው እራሳቸውን የዋህ እንዲያደርጉ አስተምራቸው፣ እናም ሁሉም ከህፃናት ከልጆቻቸው ጋር ይድናሉ።

፲፩ እናም ህፃናት ልጆቻቸው ጥምቀትም ሆነ ንሰሃ አያስፈልጋቸውም። እነሆ ለንሰሃ መጠመቅ ትዕዛዙን ለመፈፀም እናም ለኃጢያት ስርየት ነው።

፲፪ ነገር ግን ህፃናት ልጆች በክርስቶስ ከዓለም መፈጠር ጀምሮም ህያው ናቸው፤ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ እግዚአብሔር ፍትህ የሌለው እናም ደግሞ የሚለወጥ አምላክ እናም ለሰዎች የሚያደላ ነው፤ ምን ያህል ህፃናትስ ጥምቀትን ሳያገኙ ሞተዋልና!

፲፫ ስለዚህ፣ ህፃናት ያለጥምቀት መዳን ባይቻላቸው ኖሮ እነዚህም መጨረሻ ወደሌለው ገሃነም ይሄዱ ነበር።

፲፬ እነሆ እንዲህ እልሀለሁ፤ ህፃናት መጠመቅ እንዳለባቸው የሚገምት እርሱ በመራራው መርዝ እናም በክፋት ሰንሰለት ውስጥ ነው፤ ምክንያቱም እርሱ እምነት፣ ተስፋም ሆነ ልግስና የለውምና፣ ስለዚህ፣ ይህንን እያሰበ ከሞተም፣ እርሱ ወደ ሲኦል መውረድ አለበት።

፲፭ እግዚአብሔር በጥምቀት አንድን ልጅ ያድናል፤ እናም ያልተጠመቁት ሌሎቹ ግን ይጠፋሉ ብሎ ማሰብ የከፋ ኃጢያት ነው።

፲፮ በዚህ ሁኔታ የጌታን መንገድ ለሚበክሉት ወዮላቸው፤ ምክንያቱም እነርሱ ንሰሃ ካልገቡ ይጠፋሉና። እነሆ፣ ከእግዚአብሔር ስልጣን ስለተሰጠኝ በድፍረት እናገራለሁ፤ እናም ሰው ለማድረግ የሚችለውን አልፈራም፤ ምክንያቱም ፍፁም የሆነ ፍቅር ፍርሃትን ሁሉ አውጥቶ ይጥላልና።

፲፯ እናም እኔ ዘለዓለማዊ ፍቅር በሆነው ልግስና ተሞልቻለሁ፤ ስለሆነም፣ ህፃናት ሁሉ ለእኔ የሚመሳሰሉ ናቸው፤ ስለሆነም፣ ህፃናትን ፍፁም በሆነ ፍቅር እወዳቸዋለሁ፤ እናም ሁሉም ተመሳሳይ ናቸው እናም ከደህንነቱም ተካፋዮች ናቸው።

፲፰ እግዚአብሔር የማያዳላ እናም የማይለወጥ አምላክ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ነገር ግን እርሱ ከዘለዓለም እስከዘለዓለም በሙሉ አይለወጥም።

፲፱ ህፃናት ንሰሃ ለመግባት አይችሉም፤ ስለሆነም፣ ለእነርሱ ንፁህ የሆነውን የእግዚአብሔርን ምህረት መካድ የከፋ ኃጢያት ነው፤ ምክንያቱም በምህረቱ ሁሉም ህያው ሆነዋልና።

እናም ህፃናት መጠመቅ አለባቸው የሚል የክርስቶስን የኃጢያት ክፍያ የካደ ነው፣ እናም የእርሱን የኃጢያት ክፍያ እናም የቤዛነቱን ኃይል እንደምንም ንቀውታል።

፳፩ እነርሱም በሞት፣ በሲኦል፣ እናም መጨረሻ በሌለው ቅጣት አደጋ ላይ በመሆናቸው ወዮላቸው። በድፍረት እናገራለሁ፤ እግዚአብሔርም አዞኛል። እነርሱን ስሙ እናም አድምጡ፣ አለበለዚያ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት በእናንተ ላይ ለምስክር ይቆማሉና።

፳፪ እነሆ ህፃናት በሙሉ፣ እናም ደግሞ ህጉ የሌላቸው ሁሉ በክርስቶስ ህያው ናቸውና። ምክንያቱም የቤዛነት ኃይል ህጉ ለሌላቸው ሁሉ ይመጣልና፤ ስለሆነም ያልተኮነነ ወይንም ኩነኔ የሌለበት ንሰሃ ለመግባት አይችልም፤ እናም ለእንደዚህ አይነቱ ሰው ጥምቀት ምንም ጥቅም የለውም—

፳፫ ነገር ግን ይህ በእግዚአብሔር ፊት መሳለቅ፣ የክርስቶስን ምህረት እናም የመንፈስ ቅዱሱን ኃይል መካድ፣ እናም በሞተ ስራ ላይ ተስፋ ማድረግ ነው።

፳፬ እነሆ ልጄ ይህ ነገር መሆን የለበትም፤ ምክንያቱም ንሰሃ የሚያስፈልገው በኩነኔ እናም በተጣሰው ህግ እርግማን ሥር ላሉት ነውና።

፳፭ እናም የንሰሃ የመጀመሪያው ፍሬ ጥምቀት ነው፤ እናም ጥምቀት የሚመጣው በእምነት ትዕዛዙን በመፈፀም ነው፤ እናም ትዕዛዙን መፈፀም የኃጢያት ስርየትን ያመጣል፤

፳፮ እናም የኃጢያት ስርየት የዋህነትን፣ እና የልብ ርህራሄን ያመጣል፤ እናም የዋህነት እናም የልብ ርህራሄ በመንፈስ ቅዱስ መጎብኘትን ያመጣል፤ ይህም አፅናኝ በተስፋ እናም በፍፁም ፍቅር ይሞላል፣ ይህም ፍቅር ቅዱሳን በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖሩበት መጨረሻው እስከሚመጣ በትጋት በመፀለይ ይጸናል።

፳፯ እነሆ፣ ልጄ፣ ከላማናውያን ጋር ለመዋጋት ወዲያው ካልሄድኩ በድጋሚ እፅፍልሃለሁ። እነሆ፣ የዚህ ሀገር ወይም የኔፋውያን ኩራት፣ ንሰሃ ካልገቡ በቀር እንደሚጠፉ አረጋግጦአል።

፳፰ ልጄ ንሰሃ ይመጣላቸው ዘንድ ለእነርሱ ፀልይላቸው። ነገር ግን እነሆ፣ መንፈስ ከእነርሱ ጋር መስራቱን እንዳያቆም እፈራለሁ፤ እናም በዚህች ምድርም ደግሞ ሁሉንም ከእግዚአብሔር የመጣውን ኃይልና ስልጣን ለማናናቅ ይፈልጋሉ፤ እናም እነርሱም መንፈስ ቅዱስን ክደዋል

፳፱ እናም ልጄ፣ ታላቁን እውቀት አንቀበልም ካሉ በኋላ፣ እነርሱ በነቢያት የተነገሩትን ትንቢቶች፣ እናም ደግሞ በአዳኛችን በራሱ የተነገሩትን ቃላት ይፈፅሙ ዘንድ በፍጥነት መጥፋት አለባቸው።

ልጄ እስከምፅፍልህ ወይንም በድጋሚ እስከማገኝህ ድረስ ደህና ሁን። አሜን።