31. ኤፌሶን
ሐዋሪያው ጳውሎስ የሰበከበት በኤፌሶን የሚገኝ የግሪክ ቤተ ተውኔት ፍራሽ። በአዲስ ኪዳን ዘመናት፣ ኤፌሶን ለሮሜ ሴት ጣዖት አርጤምስ ክብር በተገነባው አስደናቂ መቅደስ ምክንያት በጣም ታዋቂ ነበረች። አሁን የፈረሰች ብትሆንም፣ ኤፌሶን በእስያ ውስጥ ያለው የሮሜ ክፍለ-ሀገር ዋና ከተማ እና የንግድ ቦታ ነበረች። የከተማው የብር አንጣሪዎች የአርጤምስ ምስልን በመሸጥ ጥሩ ንግድን መስርተው ነበር።
ታላቅ ድርጊቶች፥ ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛው የሚስዮን ጉዞው መጨረሻ ላይ ኤፌሶንን ጎበኘ (የሐዋ. ፲፰፥፲፰–፲፱)። በሶስተኛው ጉዞው በከተማዋ ለሶስት አመት ቆየ። ከከተማዋ በግድ እንዲወጣ የተደረገው ጳውሎስ የሀሰት ጣዖት የሆነችውን አርጤምስ ማምለክን በመቃወም በመስበኩ ምክንያት የብር አንጣሪዎች ንግድ እያጡ ስለነበር ነው (የሐዋ. ፲፱፥፩፣ ፲፣ ፳፫–፵፩፤ ፳፥፩)። የኤፌሶን ቤተ ተወኔት በግሪኮች ከተሰሩት ሁሉ በላይ ትልቅ እናም የጳውሎስ ጓደኞች በአመጽ የተነሱትን የተቋቋመበት ቦታ ነበር (የሐዋ. ፲፱፥፳፱–፴፩)። ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩት የቤተክርስቲያኗ አባላት በሮሜ እስር ቤት ውስጥ እያለ መልእክት ጻፈላቸው። በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ የተጠቀሰው በእስያ ካሉት የቤተክርስቲያኗ ቅርንጫፎች አንዱ የሚገኘው በኤፌሶን ውስጥ ነው (ራዕ. ፩፥፲–፲፩፤ ፪፥፩)።