ምዕራፍ ፪
ንጉስ ቢንያም ለህዝቡ ንግግር አደረገ—የንግስናውን ፍትሀዊነት፣ ተገቢነት፣ እና መንፈሳዊነት ገለፀ—የሰማዩን ንጉሳቸውን እንዲያገለግሉ መከራቸው—በእግዚአብሔር ላይ የሚያምፁ በማይጠፋው እሳት አይነት ጭንቀት ይሰቃያሉ። ፻፳፬ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ ሞዛያ አባቱ እንዲያደርግ እንዳዘዘው ከፈጸመና፣ በምድሪቱ ሁሉ ላይ አዋጅን ካደረገ በኋላ፣ ንጉስ ቢንያም የሚነግራቸውን ቃላት ለማዳመጥ ወደቤተ መቅደሱ ለመምጣት ህዝቡ በምድሪቱ ሁሉ በአንድ ላይ ተሰበሰቡ።
፪ እናም እጅግ በርካታ እንዲያውም በጣም በዝተው ስለነበረ አልቆጠሯቸውም ነበር፤ ምክንያቱም በምድሪቱ ላይ በእጅግ ተባዝተውና በጣም ታላቅ ሆነው ነበርና።
፫ እናም ደግሞ በሙሴ ህግ መሰረት መስዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፣ እናም መስዋዕቱን ያቃጥሉ ዘንድ ከመንጋዎቻቸው የመጀመሪያውን አመጡ፤
፬ እናም ደግሞ ከኢየሩሳሌም ምድር ላወጣቸውና፣ ከጠላቶቻቸው እጅ ላዳናቸውን፣ እንዲሁም አስተማሪዎቻቸው ይሆኑ ዘንድ ትክክለኛ ሰዎችን ለሾመላቸው፣ እናም ደግሞ በዛራሔምላ ምድር ሰላምን የመሰረተውንና፣ ሰዎች ሁሉ እንዲደሰቱና በእግዚአብሔርና በሁሉም ሰዎች ፍቅር እንዲሞሉ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንዲጠብቁ ያስተማራቸውን ጻድቅ ሰው የእነርሱ ንጉስ እንዲሆን ላደረገው ለጌታ አምላካቸው ደግሞ ምስጋናን ያቀርቡ ዘንድ የሚሰውአቸውን መንጋዎች አመጡ።
፭ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ቤተመቅደሱ በመጡ ጊዜ፣ ማናቸውም በየቤተሰቦቻቸው ሚስቱን፣ ወንድ ልጆቹንና፣ ሴት ልጆቹን እናም ወንድና ሴት ልጆቻቸውን፣ ከታላቁ እስከ ታናሹ፣ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ የሆነ በዙሪያው ተለያይተው ድንኳናቸውን ተከሉ።
፮ እናም ንጉስ ቢንያም ለእነርሱ የሚናገረውን ድንኳኑ ውስጥ ተቀምጠው ያደምጡ ዘንድ፣ እያንዳንዱ ሰው የድንኳኑን መዝጊያ ወደ ቤተ መቅደሱ በማድረግ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተከሉ፤
፯ ህዝቡ በጣም ብዙ ስለነበሩ ንጉስ ቢንያም በመቅደሱ አጥር ዙሪያ ሁሉንም ለማስተማር አልቻለም፤ ስለዚህ ህዝቡ እርሱ የሚናገራቸውን ቃላት ያደምጡ ዘንድ ሰገነት እንዲቆም አደረገ።
፰ እናም እንዲህ ሆነ በሰገነት ላይ ሆኖ ለህዝቡ መናገር ጀመረ፤ እናም ህዝቡ ብዙ በመሆኑ ሁሉም ሊሰሙት አልቻሉም፤ ስለዚህ ድምፁን ባልሰሙት ቃሉንም ደግሞ ይቀበሉት ዘንድ፣ የተናገራቸው ቃላት እንዲፃፉና በመካከላቸው እንዲላክ አደረገ።
፱ እናም እርሱ የተናገራቸው እናም እንዲፃፉ ያደረጋቸው ቃላት እነዚህ ናቸው፥ በዚህ ቀን ለእናንተ ስናገር ቃሌን ማዳመጥ የቻላችሁ እናንተ በአንድነት የተሰበሰባችሁ ወንድሞቼ፤ የምናገራቸውን ቃላት በከንቱ እንድትመለከቷቸው ዘንድ ወደእዚህ እንድትመጡ አላዘዝኳችሁም፣ ነገር ግን እኔን አዳምጡ፣ እናም ትሰሙኝ ዘንድ ጆሮአችሁን፣ ትረዱኝ ዘንድም ልባችሁን፣ የእግዚአብሔርም ሚስጥር ዓላማው ይገለጥላችሁ ዘንድም አዕምሮአችሁን ክፈቱ።
፲ እኔን እንድትፈሩኝ ወይም እኔንም ከሟች ሰው የበለጠ አድርጋችሁ እንድታስቡኝ ዘንድ ወደዚህ እንድትመጡ አላዘዝኳችሁም።
፲፩ ነገር ግን እኔ እንደ እናንተው ነኝ፣ በሁሉም አይነት የሰውነትና የአዕምሮ ጉስቁልና ስር የሆንኩ፤ ይሁን እንጂ በዚህ ህዝብ ተመርጫለሁ፣ በአባቴም ተቀብቻለሁ፣ በዚህ ህዝብ ላይ ገዢና ንጉስ እንድሆንም በጌታ እጅ ተፈቅዶልኛል፣ እናም ጌታ በሰጠኝ በሙሉ ኃይል፣ አዕምሮና፣ ብርታት እናንተን እንዳገለግል ወደር በሌለው ኃይሉ ተቀምጫለሁ፣ እንዲሁም ተጠብቄአለሁ።
፲፪ እንዲህ እላችኋለሁ እስካሁን ድረስ እንኳን ጊዜዬን እናንተን በማገልገል እንዳጠፋ ተፈቅዶልኛል፣ እናም ወርቅም ሆነ፣ ብር ባለፀጋ የሚያደርግ ማንኛውንም አይነት ነገር ከእናንተ አልፈለግሁም፤
፲፫ እናንተ በግዞት እንድትቀመጡ፣ ወይም አንዳችሁ ለአንዳችሁ ባርያ እንድትሆኑ፣ ወይም እንድትገድሉ፣ ወይም እንድትዘርፉ፣ ወይም እንድትሰርቁም፣ ሆነ ዝሙትን እንድትፈፅሙ አልፈቀድኩም፤ ወይም ምንም ዓይነት ኃጢያት እንድትፈፅሙ አልፈቅድኩም፣ እናም በሁሉም ነገር እንዳዘዛችሁ የጌታን ትዕዛዛት እንድትጠብቁ አስተምሬአችኋለሁ—
፲፬ እናም እኔ ራሴ፣ እናንተን አገለግል ዘንድና፣ ቀረጥ እንዳይከብድባችሁ፣ እናም ልትቋቋሙት የማይቻል ፅኑ የሆነ ምንም ነገር በእናንተ ላይ አንዳይመጣባችሁ ዘንድ በእጄ ሰርቻለሁ—እናም እኔ ለተናገርኳችሁ ለእነዚህ ነገሮች ሁሉ በዚህ ቀን እናንተ ራሳችሁ ምስክር ናችሁ።
፲፭ ሆኖም ወንድሞቼ፣ እነዚህን ነገሮች ለጉራ አይደለም ያደረግኋቸው፣ ወይም እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ እናንተን ለመውቀስ አይደለም፤ ነገር ግን በዚህ ቀን በእግዚአብሔር ፊት በንጹህ ህሊና መመለስ መቻሌን ታውቁ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እነግራችኋለሁ።
፲፮ እነሆ፣ እላችኋለሁ ዘመኔን እናንተን በማገልገል አሳልፌአለሁ ስላልኳችሁ መኩራት አልፈልግም፣ በእውነት በእግዚአብሔርም አገልግሎት ላይ ነበርኩና።
፲፯ እናም እነሆ፣ እናንተ ጥበብን ትማሩ ዘንድ፤ እናንተ ሰዎችን በምታገለግሉበት ጊዜ እግዚአብሔርን ብቻ እያገለገላችሁ እንደሆነ እንድትማሩ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እናገራችኋለሁ።
፲፰ እነሆ፣ የእናንተ ንጉስ ብላችሁ ጠርታችሁኛል፣ እናንተ ንጉስ ብላችሁ የምትጠሩኝ እኔ እናንተን ለማገልገል ከሰራሁ፣ እናንተስ እርስ በራሳችሁን ለማገልገል መስራት አይገባችሁምን?
፲፱ እናም እነሆ ደግሞ፣ ዘመኑን እናንተን በማገልገል የሚያሳልፈው፣ የእናንተ ንጉስ ብላችሁ የምትጠሩኝ፣ እናም አሁንም አምላክን የማገለግለው፣ ከእናንተ ምስጋና የሚገባኝ ከሆንኩኝ፣ አቤቱ ምን ያህል የሰማይን ንጉሳችሁን ማመስገን ይገባችኋል!
፳ ወንድሞቼ እላችኋለሁ፣ እናንተን ለፈጠረውም፣ ለጠበቀውና ላዳነውም፣ እንድትደሰቱ ላደረገውም፣ እንዲሁም እርስ በእርሳችሁ በሰላም እንድትኖሩ ለረዳችሁ እግዚአብሔር ነፍሳችሁ ያለውን ሁሉንም ምስጋና እና ውዳሴ ብትሰጡ—
፳፩ እንዲህ እላችኋለሁ ከመጀመሪያ ጀምሮ የፈጠራችሁና፣ እንደፈቃዳችሁ ትኖሩና ትንቀሳቀሱ፣ እናም ትሰሩ ዘንድ እስትንፋሱን በመስጠት ከቀን ቀን የጠበቃችሁን፣ እናም ከአንዱ ወቅት ወደ ሌለኛው እንኳን የደገፋችሁን የምታገለግሉ ከሆነ፣ እላችኋለሁ፣ በሙሉ ነፍሳችሁ እርሱን የምታገለግሉ ብትሆኑም የማትጠቅሙ ባሪያዎች ትሆናላችሁ።
፳፪ እናም እነሆ፣ እርሱ ከእናንተ የሚፈልገው ሁሉ ትዕዛዛቱን እንድትጠብቁ ነው፤ እናም እናንተ ትዕዛዛቱን የምትጠብቁ ከሆነ በምድሪቱ እንደምትበለፅጉ ቃል ገብቷል፤ እናም ከተናገረው የተለየ ነገር አያደርግም፤ ስለዚህ፣ ትዕዛዛቱን የምትጠብቁ ከሆነ እርሱ ይባርካችኋልም ያበለፅጋችኋልም።
፳፫ እናም አሁን፣ በመጀመሪያ ፈጥሯችኋል፣ ህይወታችሁንም ሰጥቷችኋል፣ ለእዚህም እናንተም ለእርሱ እዳ አለባችሁ።
፳፬ እናም ሁለተኛ፣ እርሱ እንዳዘዛችሁ እንድታደርጉ ይፈልጋል፤ እናንተም የምታደርጉት ከሆነ ወዲያው ይባርካችኋል፤ ስለዚህም ከፍሎአችኋል። እና አሁንም እናንተ በእርሱ እዳ አላችሁ፤ እናም ከዘለዓለም እስከዘለዓለም አላችሁም፣ ይኖራችኋልም፤ ስለሆነም፣ በምን ትኮራላችሁ?
፳፭ እናም አሁን ስለራሳችሁ መናገር የምትችሉት አለን? ብዬ እጠይቃለሁ፣ እኔ የለም ብዬ እመልስላችኋለሁ። እናም እናንተ ከምድር ትቢያ እኩል ነን ለማለት አትችሉም፤ ይሁን እንጂ እናንተ ከምድር ትቢያ ነው የተፈጠራችሁት፤ እነሆ ያም የእርሱ፣ እናንተን የፈጠረው ነው።
፳፮ እናም በተለይ፣ እናንተ ንጉስ ብላችሁ የምትጠሩኝ እኔ ከእናንተ የተሻልኩ አይደለሁም፤ እኔም ደግሞ ከአፈር የተፈጠርኩ ነኝና። እናም እንደምታዩኝ አርጅቻለሁም ወደመጣሁበት እናት ምድር ልመለስም ተቃርቤአለሁ።
፳፯ ስለዚህ፣ እንዳልኳችሁ በእግዚአብሔር ፊት በንጹህ ህሊና በመራመድ እናንተን አገልግያለሁ፤ ቢሆንም እኔ በዚህ ጊዜ እናንተን በተመለከተ እግዚአብሔር ባዘዘኝ ነገሮች እንዲፈረድብኝ በምቆምበት ጊዜ እንከን የለሽ ሆኜ እንድገኝ፣ እናም ደማችሁ በእኔ ላይ እንዳይመጣ፣ እናንተን በአንድ ላይ እንድትሰበሰቡ አድርጌአለሁ።
፳፰ እላችኋለሁ ወደመቃብሬ ልወርድ ባልኩበት በዚህ ጊዜ በሰላም እወርድ ዘንድ፣ የማይሞተው መንፈሴ ትክክለኛውን አምላክ ለማመስገን ከመዘምራን ጋር ይገኝ ዘንድ፣ ደችሁን ከልብሴ ላይ አፀዳው ዘንድ፣ ራሳችሁን በአንድ ላይ እንድትሰበስቡ አደረግሁ።
፳፱ እናም በተጨማሪ፣ ከእንግዲህ የእናንተ አስተማሪም ሆነ ንጉስ መሆን አለመቻሌን እነግራችሁ ዘንድ በአንድ ላይ እንድትሰባሰቡ አድርጌአለሁ።
፴ በዚህ ጊዜ እንኳን፣ ለእናንተ ለመናገር በምሞክርበት ጊዜ ሰውነቴ በሙሉ እጅግ ይንቀጠቀጣል፣ ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛል፤ እናም ለእናንተ እንድናገር ፈቅዶልኛል፣ ልጄ ሞዛያ በእናንተ ላይ ንጉስና ገዢ መሆኑን በዚህ ቀን ለእናንተ እንዳውጅም አዝዞኛል።
፴፩ እናም አሁን፣ ወንድሞቼ፣ እስካሁን እንዳደረጋችሁት ሁሉ እንድታደርጉ እፈልጋለሁ። ትዕዛዛቴንና፣ ደግሞ የአባቴን ትዕዛዛት እንደጠበቃችሁና፣ እንደበለፀጋችሁ፣ እንዲሁም በጠላቶቻችሁ እጅ ከመውደቅ እንደተጠበቃችሁ፣ በተመሳሳዩም የልጄን ትዕዛዛት ወይም እርሱ ለእናንተ የሚሰጣችሁን የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ከጠበቃችሁ፣ በምድሪቱ ላይ ትበለፅጋላችሁ፣ እናም ጠላቶቻችሁ በእናንተ ላይ ኃይል አይኖራቸውም።
፴፪ ነገር ግን ህዝቤ ሆይ በመካከላችሁ ፀብ እንዳይነሳ፣ እና በአባቴ በሞዛያ የተነገሩትን እርኩስ መንፈስ ለመታዘዝ ከመምረጥ ተጠንቀቁ።
፴፫ እነሆም፣ ያንን መንፈስ ሰምቶ ለመቀበል ለመረጠው ወዮለት፣ እርሱን ለመስማት ከመረጠ፣ እናም በኃጢአቱ ከቀረ፣ እናም ከሞተ፣ እርሱም ለነፍሱ ኩነኔን ይጠጣል፤ ከራሱ እውቀት ጋርም ተፃራሪ በመሆን የእግዚአብሔርን ህግ በመተላለፉ ለስራው ዘለዓለማዊ ቅጣትን እንደ ደሞዙ ይቀበላልና።
፴፬ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ስለእነዚህ ነገሮች ከትናንሽ ልጆቻችሁ በስተቀር ከእናንተ መካከል ማንም ያልተማረ፣ ነገር ግን እናንተ ለሰማዩ አባታችሁ ያላችሁን ሁሉና ራሳችሁንም ለእርሱ ለመስጠት ለዘለዓለም እዳ እንዳላችሁ የማያውቅ፣ እናም ደግሞ በቅዱሳን ነቢያት አባታችን ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ እስከወጣ ድረስ የተነገሩትን ትንቢቶችን የያዙትን መዛግብት በተመለከተ ያልተማረ ማንም የለም፤
፴፭ ደግሞም፣ እስከ አሁን ድረስ በአባቶቻችን የተነገሩት ሁሉ ያልተማረ ማንም የለም። እናም እነሆ፣ ደግሞ ነቢያቱ የተናገሩት በጌታ የታዘዙትን ነበር፤ ስለዚህ ትክክል እና እውነተኛ ናቸው።
፴፮ እናም አሁን፣ ወንድሞቼ እላችኋለሁ፣ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ካወቃችሁና ከተማራችሁ በኋላ እናንተ የምትተላለፉና ከተነገረው በተቃራኒ የምትሄዱ ከሆነ፣ ከጌታ መንፈስ ራሳችሁን አርቃችሁ፣ ትባረኩበት፣ ትበለፅጉበት፣ እናም ትጠበቁበት ዘንድ በጥበብ ጎዳና እናንተን እንዲመራ ቦታ አይኖረውም—
፴፯ እላችኋለሁ፣ ይህንን የሚያደርገው ሰው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ተቃራኒ በመሆን በአመፃ ይመጣል፤ ስለዚህ እርኩስ መንፈስን ለመስማት ይመርጣል፣ እናም ለፅድቅ ሁሉ ጠላት ይሆናል፤ ስለዚህ ጌታ በእርሱ ውስጥ ሥፍራ አይኖረውም፣ ምክንያቱም እርሱ ቅዱስ ባልሆኑ ቤተመቅደሶች ውስጥ አይኖርምና።
፴፰ ስለዚህ ያ ሰው ንስሀ ካልገባ፣ እናም ለእግዚአብሔር ጠላት እንደሆነ ቀርቶ ቢሞት፣ መለኮታዊ የሆነው ትክክለኛው ፍትህ ዘለዓለማዊ የሆነውን ነፍሱን ሀይለኛ የሆነ የጥፋተኛነት ስሜት ይቀሰቅሰዋል፤ እርሱንም በጌታ ፊት ያሸማቅቀዋል፣ እናም ደረቱን ነበልባሉ ከዘለዓለም እስከዘለዓለም ከፍ እንደሚል ልክ እንደማይጠፋው እሳት በጥፋተኝነትና፣ በህመም፣ እንዲሁም በጭንቀት ይሞላዋል።
፴፱ እናም አሁን እላችኋለሁ፣ ምህረት ለዚያ ሰው ምንም ሥፍራ አይኖራትም፤ ስለዚህ የመጨረሻ ዕጣው ማለቂያ የሌለውን ቅጣት መጋፈጥ ነው።
፵ ቃሌን የምትረዱ እናንተ ሽማግሌዎችና፣ ደግሞ እናንተ ወጣቶች፣ ደግሞም እናንተ ትናንሽ ልጆች፣ እናንተ ትረዱት ዘንድ በግልፅ ተናግሬአለሁና፣ ወደ መተላለፍ የወደቁትን አሰቃቂ ሁኔታ ነቅታችሁ እንድታስታውሱ እፀልያለሁ።
፵፩ እናም በተጨማሪ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን የተባረከና አስደሳቹን ሁኔታ እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ። እነሆም እነርሱ በሁሉም ነገሮች፣ ለጊዜያዊም ሆነ ለመንፈሳዊ፣ የተባረኩ ናቸውና፤ እናም እስከ መጨረሻው በታማኝነት ከዘለቁ፣ ለዘለአለም በማያልቀው ደስታ ከእግዚአብሔር ጋር ይኖሩ ዘንድ፣ መንግስተ ሰማይ ትቀበላቸዋለች። አቤቱ አስታውሱ፤ እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን አስታውሱ፣ ምክንያቱም ጌታ እግዚአብሔር ተናግሮታልና።