ክፍል ፻፲፱
በሐምሌ ፰፣ ፲፰፻፴፰ (እ.አ.አ.) በፋር ዌስት ሚዙሪ፣ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ “ጌታ ሆይ፣ የህዝብህን ንብረቶች ለአስራት እንዴት እንዲሆን እንደምትሻ ለአገልጋዮችህ አሳይ” በማለት ለለመነው መልስ የተሰጠ ራዕይ። የአስራት ህግ፣ በዚህ ጊዜ እንደተረዳነው፣ ከዚህ ራዕይ በፊት ለቤተክርስቲያኗ አልተሰጣትም ነበር። በተጠቀሰው ጸሎት እና ከዚህ በፊት በነበሩት ራዕዮች (፷፬፥፳፫፤ ፹፭፥፫፤ ፺፯፥፲፩) ውስጥ አስራት አንድ አስረኛ ማለት ብቻ አልነበረም፣ ነገር ግን ለቤተክርስቲያኗ ገንዘብ በፈቃድ የሚሰጥበትን ወይም የሚያዋጡት ሁሉ ማለት ነበር። ከዚህ በፊት ጌታ ለቤተክርስቲያኗ አባላት (ዋና መሪ ሽማግሌዎች) ለዘለአለም የሚሆነውን ቃል ኪዳን የገቡበት የቅድስና እና የንብረት መጋቢነት ህግጋትን ሰጥቷቸው ነበር። ብዙዎች በዚህ ቃል ኪዳን መሰረት ለመኖር ስለአዳገታቸው፣ ጌታ ይህን ለጊዜው ወሰደው እና በዚህ ምትክ ለቤተክርስቲያኗ ሁሉ የአስራት ህግን ሰጠ። ነቢዩ ጌታን ከንብረታቸው ምን ያኽሉን ለዚህ ቅዱስ አላማ እንደሚፈልግባቸው ጠየቀ። መልሱም ይህ ራዕይ ነበር።
፩–፭፣ ቅዱሳን ትርፍ ንብረቶቻቸውን ያበርክቱ እና ከዚያም እንደ አስራት በየአመቱ የወለዳቸውን አንድ አስረኛውን ይስጡ፤ ፮–፯፣ እንደዚህ አይነት ድርጊት የፅዮንን ምድር ይቀድሳል።
፩ በእውነት ጌታ እንዲህ ይላል፣ በፅዮን ውስጥ ባለው በቤተክርስቲያኔ ኤጲስ ቆጶስ እጆች ውስጥ የሚገኙትን የትርፍ ንብረቶቻቸውን ሁሉ እንዲሰጡ እጠይቃቸዋለሁ፣
፪ ቤቴን ለመገንባት፣ እና የፅዮንን መሰረት ለማዘጋጀት እና ለክህነት ስልጣን፣ እና ለቤተክርስቲያኔ አመራር እዳዎችም እንዲሰጡ እጠይቃቸዋለሁ።
፫ እና ይህም የህዝቤ አስራት መጀመሪያ ይሆናል።
፬ እና ከዚህ በኋላ፣ እንደዚህ አስራት የከፈሉት በየአመቱ የገቢያቸውን ሁሉ አንድ አስረኛውን ይስጡ፤ እና ይህም ለዘለአለም ለእነርሱ፣ ለቅዱስ ክህነቴ ቋሚ ህግ ይሆንላቸዋል፣ ይላል ጌታ።
፭ እውነት እላችኋለሁ፣ እንዲህም ይሆናል፣ በፅዮን ምድር ውስጥ የተሰበሰቡት ሁሉ በትርፍ ንብረቶቻቸው ላይ አስራት ይከፍላሉ፣ እና ይህን ህግም ይከተላሉ፣ አለበለዚያ በመሀከላችሁ ለመኖር ብቁ አይሆኑም።
፮ እና እላችኋለሁ፣ ህዝቤ ይህን ህግ በቅድስና በመጠበቅ የማይከተሉ ቢሆን፣ እና ህጌን እና ውሳኔዬን በእንዲህም ይጠበቁ ዘንድ፣ ከሁሉም በላይ ቅዱስም ይሆን ዘንድ በዚህ ህግ የፅዮንን ምድርን የሚቀድሱልኝ ባይሆን፣ እነሆ እውነት እላችኋለሁ፣ ለእናንተ የፅዮን ምድር አይሆንላችሁም።
፯ እና ይህም ለሁሉም የፅዮን ካስማዎች ምሳሌ ይሁን። እንዲህም ይሁን። አሜን።