ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፺፬


ክፍል ፺፬

በነሀሴ ፪፣ ፲፰፻፴፫ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ኦሀዮ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ሀይረም ስሚዝ፣ ሬኖልድስ ከሁን፣ እና ጄርድ ካርተር ለቤተክርስቲያን መገንባት በኮሚቴነት ተመድበዋል።

፩–፱፣ ጌታ ለቀዳሚ አመራር ስራ ስለሚገነባው ቤት የሚመለከት ትእዛዝ ሰጠ፤ ፲–፲፪፣ የማተሚያ ቤት ይገንባ፤ ፲፫–፲፯፣ ልዩ ውርሶች ተመድበዋል።

ደግሞም፣ ባልንጀሮቼ እውነት እላችኋለሁ፣ በዚህ በከርትላንድ ምድር ውስጥ፣ በቤቴ በመጀመር፣ የፅዮን ካስማ ከተማን ጅማሬ መሰረት ለመጣል እና ለማዘጋጀት ትእዛዝን እሰጣችኋለሁ።

እነሆም፣ በሰጠኋችሁ ምሳሌ መሰረት መደረግ አለበት።

እና በደቡብ ያለው የመጀመሪያው ከፊል መሬት ለእኔ፣ ራዕዮችን ለሚቀበሉበት ለአመራር ስራ፣ ለአመራር ቤት መሰሪያ ይቀደስ፤ እናም ይህም ቤተክርስቲያኗን እና መንግስቱን በሚመለከቱ ሁሉም ነገሮች ለአመራር አገልግሎት ስራ ነው።

እውነት እላችኋለሁ፣ ይህም፣ በውስጠኛው አደባባይ፣ አስራ ሰባት ሜትር በሀያ ሜትር ስፋት እና ርዝመቱ ይሁን።

እና፣ ከዚህ በኋላ በሚሰጣችሁ ንድፍ መሰረት፣ የታች አደባባይና የላይ አደባባይ ይኑረው።

እና፣ በክህነት ስልጣን ስርዓት መሰረት፣ ከዚህ በኋላ በሚሰጣችሁ ንድፍ መሰረት፣ ይህ ከመሰረቱ ጀምሮ ለጌታ ይቀደስ።

እና ይህም ለአመራር ስራ ለጌታ ሁሉ ይቀደስ።

እና ማንኛውም እርኩስ ነገር ወደውስጥ እንዲገባ አትፍቀዱ፤ እና ክብሬም በዚያ ይሆናል፣ እና በዚያም እገኛለሁ።

ማንኛውም እርኩስ ነገር ቢገባበት ግን፣ ክብሬ በዚያ አይሆንም፤ እና ወደዚህም አልገባም።

ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ሁለተኛው ከፊሉ መሬት ለእኔ ቤት መሰሪያ፣ ለቅዱስ መጻሕፍቴ መታተምና መተርጎም ስራ፣ እና ለማዛችሁ ማንኛቸውም ነገሮች ሁሉ፣ ለእኔ ይቀደስ።

፲፩ እና ይህም፣ በውስጥ አደባባዩ፣ አስራ ሰባት ሜትር በሀያ ሜትር ስፋት እና ርዝመት ይሁን፤ እና የበታች እና የላይ አደባባይ ይኑረው።

፲፪ እና ይህም ቤት ከመሰረቱ ጀምሮ፣ ለህትመት ስራ፣ በሚሰጣችሁ ንድፍ መሰረት በሁሉም ነገሮች ቅዱስ እና ያልረከሰ እንዲሆን ማንኛቸውም በማዛችሁ ሁሉም ነገሮች ሁሉ ለጌታ ይቀደስ።

፲፫ እና በሶስተኛው ከፊል መሬት ላይ አገልጋዬ ሀይረም ስሚዝ ውርሱን ይቀበል።

፲፬ እና በሰሜን ላይ ባለው በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ከፊል ስፍራ ላይ አገልጋዬ ሬኖልድስ ከሁን እና ጀርድ ካርተር ውርሶቻቸውን ይቀበሉ—

፲፭ የመደብኩላቸውን ስራ ያከናውኑ ዘንድ፣ እኔ ጌታ በሰጠኋችሁ ትእዛዝ መሰረት የቤቶቼ የግንባታ ኮሚቴ ይሁኑ።

፲፮ እነዚህ ሁለት ቤቶች እነርሱን በሚመለከት ትእዛዝ እስክሰጣችሁ ድረስ እንዳይገነቡ።

፲፯ አሁንም በዚህ ጊዜ ምንም ተጨማሪ ነገርን አልሰጣችሁም። አሜን።