ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፹፩


ክፍል ፹፩

በመጋቢት ፲፭፣ ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.) በሀይረም ኦሀዮ ውስጥ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ፍሬድሪክ ጂ ዊልያምስ ሊቀ ካህን እና ለታላቅ ክህነት አመራር አማካሪ እንዲሆን ተጠርቷል። ይህ ራዕይ በመጋቢት ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.) ሲመጣ፣ ጄሲ ጋውዝ በአመራሩ ውስጥ ለጆሴፍ ስሚዝ አማካሪነት እንደተጠራ የታሪክ መዝገቡ ያሳይ ነበር። ነገር ግን፣ በተመደበበት በትክክል ስላልሰራ፣ ጥሪው ከዚያም ወደ ፍሬድሪክ ጂ ዊልያምስ ተለውጦ ነበር። ይህ ራዕይ [በመጋቢት ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.) የተጻፈው] ቀዳሚ አመራርን በስርዓት የማደራጀት፣ በዚህም ሀላፊነት የአማካሪ ሹመቶችን የመጥራት፣ እና የሹመቱም ክብር የሚገለጥበት የመጀመሪያው እርምጃ እንደነበር ሊታሰብበት ይገባል። ወንድም ጋውዝ ለጊዜያዊነት አገለገለ ነገር ግን በታህሳስ ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.) ከቤተክርስቲያኗ ተወገዘ። ወንድም ዊልያምስ በዚህ ሹመት በመጋቢት ፲፰፣ ፲፰፻፴፫ (እ.አ.አ.) ተሹሞ ነበር።

፩–፪፣ የመንግስት ቁልፎች በቀዳሚ አመራር ዘወትር ይያዛሉ፤ ፫–፯፣ ፍሬድሪክ ጂ ዊልያምስ በአገልግሎቱ ታማኝ ነው፣ ዘለአለማዊ ህይወትም ይኖረዋል።

እውነት፣ እውነት እልሀለሁ ለአገልጋዬ ፍሬድሪክ ጂ ዊልያምስ፥ የሚናገረው ድምፅ፣ የጌታ አምላክህን ቃል ስማ፣ እናም የተጠራህበትን፣ እንዲሁም የቤተክርስቲያኔ ሊቀ ካህን እናም ለአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ አማካሪነት ጥሪን አድምጥ፤

ለእርሱም፣ ዘወትር ለታላቅ ክህነት አመራር የሚሆነውን፣ የመንግስቱን ቁልፎች ሰጥቻለሁ፥

ስለዚህ፣ በእውነት እቀበለዋለሁ እናም እባርከዋለሁ፣ እናም በምክር፣ በሰጠሁህ ሀላፊነት፣ ሁልጊዜ ድምፅህን አውጥተህ እናም በልብህ፣ በአለም ፊት እና በስውር በመጸለይ፣ ደግሞም ወንጌልን በምድር ኗሪዎች ምድር፣ እናም በወንድሞችህ መካከል በማወጅ ለማገልገል ታማኝ እስከሆንክ ድረስ፣ አንተም ትባረካለህ።

እነዚህን ነገሮች በማድረግ ከሁሉም በላይ የሆነ መልካም ነገሮችን ለሰዎች ታደርጋለህ፣ እናም ጌታህ የሆነውን የእርሱን ክብር ከፍ ታደርጋለህ።

ስለዚህ፣ የታመንህ ሁን፤ በመደብኩህ ሀላፊነት ቁም፤ ደካማውን ደግፍ፣ የዛሉትን እጆች አቅና፣ እናም የሰለሉትን ጉልበቶች አጠንክር

እናም እስከመጨረሻው ታማኝ ብትሆን የህያውነት አክሊልን፣ እና በአባቴ ዘንድ ቤት ባዘጋጀሁት ቤት ውስጥ ዘለአለማዊ ህይወት ይኖርሀል።

እነሆ፣ እናም እነዚህ የአልፋ እና ኦሜጋ፣ እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቃላት ናቸው። አሜን።