ክፍል ፴፬
ህዳር ፬፣ ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.) በፈያት፣ ኒው ዮርክ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት ለኦርሰን ፕራት የተሰጠ ራዕይ። በዚህ ጊዜ ወንድም ፕራት አስራ ዘጠኝ አመቱ ነበር። ከስድስት ሳምንት ቀደም ብሎ ከታላቅ ወንድሙ፣ ከፓርሊ ፒ ፕራት ዳግም ስለተመለሰው ወንጌል ስብከት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰማ ተለወጠና ተጠመቀ። ይህ ራዕይ የተሰጠው በፒተር ዊትመር ቀዳማዊ ቤት ውስጥ ነበር።
፩–፬፣ በእምነት የተሞሉት በኃጢአት ክፍያው አማካይነት የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ፤ ፭–፱፣ የወንጌል ስብከት የዳግም ምጽአትን መንገድ ያዘጋጃል፤ ፲–፲፪፣ ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ሀይል አማካይነት ይመጣል።
፩ ልጄ ኦርሰን፣ እኔ ጌታ አምላክ፣ እናም እንዲሁም ቤዛህን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአንተ የምንናገረውን ስማ እናም አድምጥ፣ እንዲሁም ተመልከት፤
፪ በጭለማ የሚያበራ እና ጭለማም የማይረዳውን፣ እኔ የአለም ብርሀን እና ሕይወት የሆንኩትን፤
፫ ያመኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ አለምን በመውደድ እርሱ ህይወቱን አሳልፎ የሰጠውን ስማ እናም አድምጥ፣ እንዲሁም ተመልከት። ስለዚህም አንተ ልጄ ነህ፤
፬ እናም በማመንህ ምክንያት የተባረክ ነህ፤
፭ እናም ይበልጡን የተባረክ ነህ ምክንያቱም ወንጌሌን እንድትሰብክ በእኔ ተጠርተሀል—
፮ ለጠማማና ክፉ ትውልዶች፣ ለዳግም ምፅአቱ የጌታን መንገድ በማዘጋጀት ንስሀን ጩህ እናም ረጅም እና ጉልህ እንደሆነው መለከት ድምጽ ድምጽህን ከፍ አድርግ።
፯ እነሆ፣ እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ውስጥ የምመጣበት ጊዜ ተቃርቧልና።
፰ እናም ሁሉም ህዝብ ስለሚንቀጠቀጡ፣ የምጽአቴም ጊዜ ታላቅ ቀን ይሆናል።
፱ ነገር ግን ያ ታላቁ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ጸሀይ ትጨልማለች፣ ጨረቃም ወደ ደምነት ትለወጣለች፤ እናም ከዋክብትም ብርሀናቸውን መስጠት ይከለክላሉ፣ አንዳንዶቹም ይወድቃሉ፣ እና ታላቅ ጥፋትም ኃጢአተኞችን ይጠብቃቸዋል።
፲ ስለዚህም፣ ጌታ እግዚአብሔር ስለተናገረ፣ ድምጽህን ከፍ አድርገህ ከመናገር አትቆጠብ፣ ስለዚህ ትንቢትን ተናገር፣ እና ይህም በመንፈስ ቅዱስ ሀይል አማካይነት ይሰጣል።
፲፩ እናም እምነት ካለህ፣ እነሆ፣ እስከምመጣ ድረስ እኔም ከአንተ ጋር ዘወትር እሆናለሁ—
፲፪ እናም እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ በቶሎም እመጣለሁ። እኔ ጌታህ እና ቤዛህ ነኝ። እንዲህም ይሁን። አሜን።