ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻፫


ክፍል ፻፫

በየካቲት ፳፬፣ ፲፰፻፴፬ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ኦሀዮ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ይህ ራዕይ ፓርሊ ፒ ፕራት እና ላይመን ዋይት ስለእርዳታ እና በጃክሰን የግዛት ክፍል ውስጥ ወደሚገኘው መሬታቸው ቅዱሳንን ስለመመለስ ከነቢዩ ጋር ለመመካከር ከሚዙሪ ወደ ከርትላንድ ከደረሱ በኋላ የተቀበሉት ነበር።

፩–፬፣ ለምን ጌታ የጃክሰን የግዛት ክፍል ቅዱሳን እንዲሰደዱ እንደፈቀደ፤ ፭–፲፣ ትእዛዛትን ከጠበቁ ቅዱሳን ያሸንፋሉ፤ ፲፩–፳፣ የፅዮን ቤዛነት በሀይል ይመጣል፣ ጌታም በህዝቦቹ ፊት ይሄዳል፤ ፳፩–፳፰፣ ቅዱሳን በፅዮን ይሰብሰቡ፣ እና ህይወታቸውን የሚያጡትም ደግመው ያገኙታል፤ ፳፱–፵፣ የተለያዩ ወንድሞች የፅዮንን ሰፈር እንዲያደራጁና ወደ ፅዮን እንዲሄዱ ተጠሩ፤ ታማኝ ከሆኑም ውጤታማ እንደሚሆኑ የተስፋ ቃል ተሰጥቷቸዋል።

ባልንጀሮቼ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እነሆ፣ በፅዮን ምድር የተበተኑትን ወንድሞቻችሁን ደህንነት እና ቤዛነት በሚመለከት ያላችሁን ሀላፊነት እንዴት እንድትፈፅሙ ታውቁ ዘንድ ራዕይና ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤

ቁጣዬን በጊዜዬ ያለልክ በማወርድባቸው በጠላቶቼ እጆች እየተሰደዱ እና እየተመቱት ስላሉት።

የጥፋታቸውንም መስፈሪያ ይሞሉ ዘንድ፣ ጽዋቸውም ሙሉ ይሆን ዘንድ፣ እስከአሁን ፈቅጄላቸዋለሁና፤

እና በስሜ ራሳቸውን የሚጠሩትም ለጥቂት ዘመን በከፍተኛ እና አሳዛኝ ተግሳፅ ይገሰጹ ዘንድ፣ ምክንያቱም አብረውም የሰጠኋቸውን አስተሳሰብና ትእዛዛት አላዳመጡምና

ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፣ እኔ ጌታ አምላካቸው የምሰጣቸውን ምክር ከዚህ ሰአት ጀምረው የሚያደምጡ ቢሆን፣ ህዝቤ ሊቀበሉ የሚችሉትን አዋጅ አውጃለሁ።

እነሆ፣ ስላወጅኩት፣ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ጠላቶቼን ማሸነፍ ይጀምራሉ።

እና እኔ ጌታ የምናገራቸውን ቃላት ለመከተል ቢያደምጡ፣ የአለም መንግስታት ከእግሮቼ በታች እስከሚገዙ እና ምድርንም ለዘለአለም የራሳቸው እንዲያደርጓት ለቅዱሳን እስከምትሰጥ ድረስ ማሸነፍን አያቆሙም።

ነገር ግን ትእዛዛቴን እስካላከበሩ እና ቃላቴንም እስካልተከተሉ ድረስ፣ የአለም መንግስታት ያሸንፏቸዋል።

ለአለም ብርሀንና ለሰዎች አዳኝ ይሆኑ ዘንድ ተመርጠው ነበርና፤

እና የሰዎች አዳኞች እስካልሆናችሁ ድረስ፣ ጣዕሙን እንዳጣ ጨው ትሆናላችሁ፣ እና ከዚያን ጊዜ በኋላ ከንቱ ትሆናላችሁ፣ ደግሞም ትጣላላችሁ፣ እናም በሰዎችም እግር ትረገጣላችሁ።

፲፩ ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፣ የተበተኑት ወንድሞቻችሁ ወደ ውርስ መሬታቸው እንዲመለሱ፣ እና የፈረሱትን የፅዮን ስፍራዎችንም እንዲገነቡ አውጃለሁ።

፲፪ ከብዙ ስቃይ በኋላ፣ አስቀድሜ እንዳዘዝኳችሁ፣ በረከት ይመጣል።

፲፫ እነሆ፣ ይህም ከስቃያችሁ እና ከወንድሞቻችሁ ስቃይ በኋላ በተስፋ ቃል የሰጠኋችሁ በረከት ነው—ቤዛነታችሁ፣ እና የወንድሞቻችሁ ቤዛነት፣ እንዲሁም የፅዮን ምድር እንደገና እንዳትሸነፍ እንድትመሰረት ዳግም መመለሷ።

፲፬ ይህም ቢሆን፣ ውርሶቻቸውን ካረከሱ ይሸነፋሉ፤ ውርሶቻቸውን የሚያረክሱ ቢሆን አላድናቸውምና።

፲፭ እነሆ እላችኋለሁ፣ የፅዮን ቤዛነት በሀይል ይመጣ ዘንድ ይገባል፤

፲፮ ስለዚህ፣ ሙሴ የእስራኤልን ልጆች እንደመራው፣ የሚመራቸው ሰው ለህዝቤ አስነሳለሁ።

፲፯ እናንት የእስራኤል ልጆች፣ የአብርሐም ዘር ናችሁና፣ እና በሀይሌና በተዘረጋው ክንዴ ከባርነታችሁ ተመርታችሁ መውጣት ያስፈልጋችኋልና።

፲፰ እና አባቶቻችሁ በመጀመሪያ እንደተመሩት፣ የፅዮን ቤዛነትም እንዲሁ ይሆናል።

፲፱ ስለዚህ፣ ልባችሁ አይታወክ፣ ለአባቶቻችሁ እንዳልኳቸው ለእናንተም እላችኋለሁና፥ በፊታችሁ መልአኬን እልካለሁ፣ ነገር ግን እኔ በመካከላችሁ አልገለጥም።

ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፊታችሁ መላዕክቴን እልካለሁ፣ እና በመካከላችሁም እገኛለሁ፣ እና በጊዜም መልካሙን ምድር የራሳችሁ ታደርጋላችሁ።

፳፩ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በሰጠኋችሁ ምሳሌ ውስጥ የወይን ስፍራው ጌታ የሆነው አገልጋይ የተናገረውን የሚመስለው ሰው አጋልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ ነው።

፳፪ ስለዚህ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ ለቤቴ ጥንካሬ፣ ለወጣቶቼና ለጎልማሳዎቼ እንዲህ ይበል—በፅዮን ምድር፣ ለእኔ በተቀደሰው ገንዘብ በገዛሁት ምድር ላይ በአንድነት ተሰብሰቡ።

፳፫ እና ቤተክርስቲያኖቹ ሁሉ ብልህ ሰዎቻቸውን ከገንዘቦቻቸው ጋር ይላኩ፣ እና እንዳዘዝኩትም መሬቶችን ግዙ

፳፬ እና የፅዮን ምድር እንዲሆን ከቀደስኩት ምድር፣ ከመልካሙ መሬቴ፣ እንዲሁም በእነርሱ ላይ በፊቴ ካመጣችሁት ከእነዚህ ምስክሮች በኋላ ከመሬታችሁ ሊያሰድዳችሁ ጠላቶቼ ከመጡባችሁ፣ እርገሟቸው፤

፳፭ እና ማንኛውም የምትረግሟቸውን፣ እረግማቸዋለሁ፣ እና ጠላቶቼንም ትበቅላላችሁ።

፳፮ እና በጠላቶቼ፣ በሚጠሉኝ ሶስተኛ እና አራተኛ ትውልድ ላይ ስትፈርዱም ከእናንተ ጋር እገኛለሁ።

፳፯ ለእኔ ህይወቱን ለመስጠት ማንም ሰው አይፍራ፤ ማንም ለእኔ ህይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ዳግም ያገኘዋልና።

፳፰ እና ለእኔ ህይወቱን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነውም ደቀመዝሙሬ አይደለም።

፳፱ አገልጋዬ ስድኒ ሪግደን፣ ቤተክርስቲያኖችን ስለፅዮን ዳግም መመለስ እና ቤዛነት የሰጠኋቸውን ትእዛዛት እንዲጠብቁ ለማዘጋጀት፣ ለምስራቅ ሀገሮች ተሰብሳቢዎች ድምጹን ከፍ ማድረጉ ፍቃዴ ነው።

አገልጋዬ ፓርሊ ፒ ፕራትና አገልጋዬ ላይመን ዋይት፣ ወደፅዮን ምድር የሚሄዱ ሰዎችን በአስሮች ወይም በሀያዎች ወይም በሀምሳዎች ወይም በመቶዎች እስኪያደራጁ ድረስ፣ ለቤቴ ጥንካሬ አምስት መቶዎችን እስኪያገኙ ድረስ፣ ወደወንድሞቻቸው መሬት እንዳይመለሱ ፍቃዴ ነው።

፴፩ እነሆ ይህም ፍቃዴ ነው፤ ጠይቁ፣ ይሰጣችኋል፤ ነገር ግን ሰዎች ፈቃዴዬን ሁልጊዜም አያደርጉም

፴፪ ስለዚህ፣ አምስት መቶ የማታገኙ ቢሆን፣ ምናልባት ሶስት መቶ ታገኙ ዘንድ በቅንነት ፈልጉ።

፴፫ እና ሶስት መቶ ለማግኘት ባትችሉም፣ ምናልባት አንድ መቶ ታገኙ ዘንድ በቅንነት ፈልጉ።

፴፬ ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፣ ወደ ፅዮን ምድር አብሮአችሁ እንዲሄዱ ከቤቴ ጥንካሬ መቶ እስክታገኙ ድረስ ወደፅዮን ምድር እንዳትሄዱ ትእዛዝን እሰጣችኋለሁ።

፴፭ ስለዚህ፣ እንዳልኳችሁ ጠይቁ፣ ይሰጣችኋል፤ አገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ ምናልባት ከእናንተ ጋር እንዲሄድ፣ እና በህዝቤ መካከል እንዲመራ፣ እና በተቀደሰው ምድርም መንግስቴን ያደራጅ፣ እና የፅዮን ልጆችን በተሰጡት እና ወደፊት በሚሰጣችሁ ህግጋት እና ትእዛዛት መሰረት ይመሠርት ዘንድ በቅንነት ጸልዩ።

፴፮ ድልና ክብር ሁሉ የሚመጣላችሁ በቅንነታችሁ፣ በታማኝነታችሁ፣ እና በእምነት ጸሎታችሁ ነው።

፴፯ አገልጋዬ ፓርሊ ፒ ፕራት ከአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ ጋር ይጓዝ።

፴፰ አገልጋዬ ላይመን ዋይት ከአገልጋዬ ስድኒ ሪግደን ጋር ይጓዝ።

፴፱ አገልጋዬ ሀይረም ስሚዝ ከአገልጋዬ ፍሬድሪክ ጂ ዊሊያምስ ጋር ይጓዝ።

አገልጋዬ ኦርሰን ሀይድ ከአገልጋዬ ኦርሰን ፕራት ጋር፣ አገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ በሚመክራቸው በማንኛውም፣ የሰጠኋቸውን የእነዚህን ትእዛዛት ፍጻሜ ያገኙ፣ ይጓዙ፣ እና የሚቀረውንም በእጆቼ ይተዉት። እንዲህም ይሁን። አሜን።