ክፍል ፴፩
መስከረም ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.) በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት ለቶማስ ቢ ማርሽ የተሰጠ ራዕይ። ወቅቱም የቤተክርስቲያኗ ጉባዔ እንደተጠናቀቀ ወዲያውኑ ነበር (የክፍል ፴ ርዕስን ተመልከቱ)። ይህ ራዕይ ከመሰጠቱ በፊት በወሩ መጀመሪያ ላይ የተጠመቀው ቶማስ ማርሽ በቤተክርስቲያን ውስጥ በሽማግሌነት ተሹሞ ነበር።
፩–፮፣ ቶማስ ቢ ማርሽ ወንጌልን እንዲሰብክ ተጠራ እናም ስለቤተሰቡ ደህንነት ማረጋገጫ ተሰጠው፤ ፯–፲፫፣ ትዕግስተኛ እንዲሆን፣ ዘወትር እንዲጸልይ እናም አጽናኙን እንዲከተል ተመከረ።
፩ ልጄ ቶማስ፣ በስራዬ ባለህ እምነት የተባረክህ ነህ።
፪ እነሆ፣ በቤተሰብህ የተነሳ ብዙ መከራን አይተሀል፤ ሆኖም፣ ቤተስብህን እና አንተን አዎን፣ ህጻናት ልጆችህን እባርካቸዋለሁ፤ እናም የሚያምኑበት እና እውነትን የሚያውቁበት እንዲሁም ከአንተ ጋር በቤተክርስቲያኔ አንድ የሚሆኑበት ቀን ይመጣል።
፫ ልብህን አንሳ እናም ተደሰት፣ የተልዕኮህ ሰዓት መጥቷልና፤ እናም አንደበትህ ይፈታል፣ እናም የታላቅ ደስታን የምስራችንም ለዚህ ትውልድ ታውጃለህ።
፬ ለአገልጋዬ ለጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ፣ የተገለጡለትን ነገሮች ታውጃለህ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ መስበክ፣ አዎን፣ ለነዶ ሊሆን የቀረበውን ስብል መሰብሰብ ትጀምራለህ።
፭ ስለዚህ፣ በሙሉ ነፍስህ እጨድ፣ እናም ኃጢአትህም ተሰርዮልሀል፣ እናም ብዙ ነዶም በጀርባህ ትሸከማለህ፣ ለሰራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና። ስለዚህ ቤተሰቦችህም በህይወት ይኖራሉ።
፮ እነሆ፣ እውነት እልሀለሁ፣ ከእነርሱ ለጥቂት ጊዜ ብቻ ሂድ፣ እናም ቃሌን አውጅ፣ እናም ለእነርሱም ስፍራን አዘጋጅላቸዋለሁ።
፯ አዎን፣ የስዎቹን ልብ እከፍታለሁ፣ እናም ይቀበሉሀል። እና በእጀህም ቤተክርስቲያንን እመሰርታለሁ፤
፰ እናም ታጠነክራቸዋለህ እናም ለሚሰበሰቡበት ቀንም ታዘጋጃቸዋለህ።
፱ በስቃይ ታጋሽ ሁን፣ ክፉ ለሚናገሩህ ክፉ አትመልስ። ቤትህን በትህትና ግዛ፣ እናም የጸናህ ሁን።
፲ እነሆ፣ ስለማይቀበሉህም ለአለም ሳይሆን ነገር ግን ለቤተክርስቲያኗ ሀኪም ትሆናለህ።
፲፩ እኔ ወደምፈቅደው ስፍራ ሁሉ ሂድ፣ እናም የምትሄድበት እና የምትሰራው በአጽናኙ ይሰጥሀል።
፲፪ ወደፈተና እንዳትገባ እና ደመወዝህን እንዳታጣ ዘወትር ጸልይ።
፲፫ እስከ ፍጻሜው ድረስ ታማኝ ሁን፣ እኔም ከአንተ ጋር ነኝ። እነዚህ ቃላት የሰውም ሆነ የሰዎች አይደሉም፣ ነገር ግን በአብ ፈቃድ የእኔ ያዳኛችሁ የኢየሱስ ክርስቶስ ናቸው። አሜን።