ክፍል ፹፱
በየካቲት ፳፯፣ ፲፰፻፴፫ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ኦሀዮ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። በስብሰባዎቻቸው ጊዜ የቀድሞዎቹ ቅዱሳን ትምባሆ በመጠቀማቸው ምክንያት፣ ነቢዩ ስለጉዳዩ ያሰላስል ዘንድ ተመርቶ ነበር፤ በዚህም ምክንያት፣ ስለጉዳዩ ጌታን ጠየቀ። የጥበብ ቃል ተብሎ የሚታወቀው ይህም ራዕይ የዚህ ውጤት ነበር።
፩–፱፣ የወይን ጠጅ፣ የሚያሰክሩ መጠጦች፣ ትምባሆ፣ እና ትኩስ መጠጦችን መጠቀም ተከልክለዋል፤ ፲–፲፯፣ የመድሀኒት ቅጠላቅጠል፣ ፍራፍሬዎች፣ ስጋ፣ እና እህል ለሰዎች እና ለእንስሳት ጥቅም የተመደቡ ናቸው፤ ፲፰–፳፩፣ ለወንጌሉ ህግ፣ የጥበብ ቃልን በተጨማሪ፣ ታዛዥ መሆን ስጋዊ እና መንፈሳዊ በረከቶችን ያመጣል።
፩ የጥበብ ቃል፣ በከርትላንድ ውስጥ ለተሰበሰቡት ለሊቀ ካህናት ቡድን፣ እና ለቤተክርስቲያኗ፣ እና ደግሞም ለፅዮን ቅዱሳን ጥቅም—
፪ በትእዛዝ ወይም በማስገደድ ሳይሆን፣ ነገር ግን በራዕይ እና በጥበብ ቃል፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት ለቅዱሳን ሁሉ በጊዜያዊ ደህንነት ውስጥ የእግዚአብሔርን ስርዓት እና ፈቃድ በማሳየት እንደ ሰላምታ የሚላክ፤
፫ ከተስፋ ጋር የሆነ መሰረታዊ መርህ፣ ለደካማው እና ቅዱሳን ለሆኑት ወይም ቅዱሳን ተብለው ለተጠሩት ደካማ ቅዱሳን ሁሉ ችሎታ ይሆን ዘንድ የተሰጠ የጥበብ ቃል ነው።
፬ እነሆ፣ ጌታ ለእናንተ እንዲህ ይላችኋል፥ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ በሚያድሙ ሰዎች ልብ ውስጥ ባሉት እና በሚኖሩት ተንኮል እና አላማዎች ምክንያት፣ በራዕይ ይህን የጥበብ ቃል ለእናንተ በመስጠት አስጠንቅቄአችኋለሁ፣ እናም ጥንቱንም አስቀድሜ አስጠንነቅቄአችኋለሁ
፭ በመካከላችሁ ማንም ሰው ወይን ወይም የሚያሰክር መጠጥ የሚጠጣ ቢሆን፣ በፊቱ ቅዱስ ቁርባናችሁን ታቀርቡ ዘንድ በተሰባሰባችሁበት ጊዜ ብቻ ካልሆነ በስተቀር፣ እነሆ ይህ መልካም አይደለም፣ በአባታችሁም ፊት ተቀባይነት አይኖረውም።
፮ እናም፣ እነሆ፣ ይህም የወይን ጠጅ፣ አዎን፣ ከወይን ፍሬ በራሳችሁ የተሰራ ንጹህ ወይን ይሁን።
፯ ደግሞም፣ የሚያሰክር መጠጥ፣ ሰውነትን ለማጠብ እንጂ፣ ለሆድ አይደለም።
፰ እና ዳግም፣ ትምባሆ ለሰውነት፣ ወይም ለሆድ አይደለም፣ እና ለሰውም መልካም አይደለም፣ ነገር ግን በማመዛዘን እና በጥበብ ቢጠቀሟቸው፣ ለብልዝነት እና ለታመሙ ከብቶች የመድሀኒት ቅጠላት ናቸው።
፱ ደግሞም፣ ትኩስ መጠጦችም ለሰውነት እና ለሆድ አይደሉም።
፲ እናም ደግሞ እውነት እላችኋለሁ፤ ሁሉንም መልካም የሆኑትን ቅጠላ ቅጠል እግዚአብሔር ለሰውነት፤ ለፍጥረት እና ለሰው ጥቅም ይሆኑ ዘንድ መድቧቸዋልና—
፲፩ እያንዳንዶቹን ቅጠላ ቅጠል ሁሉ በወቅታቸው፤ ፍራፍሬዎችም ሁሉ በወቅታቸው መድቧቸዋል፤ እነዚህን ሁሉ በብልሃት እና በምስጋና ይጠቀሟቸው ዘንድ ነው።
፲፪ አዎን፣ የእንስሳትና የሰማይ አዕዋፋትንም ስጋ፣ እኔ ጌታ ለሰው በምስጋና ጥቅም መድቤአቸዋለሁ፤ ነገር ግን እነዚህን እያሰለሱ ይጠቀሟቸው፤
፲፫ እና በክረምት ወይም በብርድ ወይም በረሀብ ጊዜያት ብቻ እንጂ፣ ይህን የማይጠቀሙበት ቢሆን የሚያስደስተኝ ነው።
፲፬ እና እህልም ለሰው እና ለእንስሳት ጥቅም፣ ለህይወት ሀይል፣ የተመደበ ነው፣ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለምድር አራዊትና ለሰማይ አዕዋፋት፣ እና በምድር ላይ የሚሮጡት እና ለሚርመሰመሱት ለዱር እንስሳት ነው፤
፲፭ እና እነዚህንም በድርቅ እና በከፍተኛ የረሀብ ጊዜያት ይሆኑ ዘንድ ብቻ ለሰው ጥቅም እግዚአብሔር እነዚህንም ሰራ።
፲፮ የወይን ፍሬም፤ በምድር ውስጥ ወይም ከምድር በላይ ፍሬ የሚያመጣውም እንደሆነው፣ ሁሉም እህል ለሰው ምግብ ጥሩ ነው—
፲፯ ይህም ቢሆን፣ ስንዴ ለሰው፣ በቆሎ ለበሬ፣ እና አጃ ለፈረስ፣ እና አጃ ለአዕዋፋት እና ለአሳማ፣ እና ለምድር አራዊት ሁሉ፣ እና ገብስ፣ እንደ ሌላ እህልም፣ ለጠቃሚ እንስሳቶች ሁሉ፣ እና ለለስላሳ መጠጥ።
፲፰ እና ትእዛዛትን በማክበር፣ እነዚህን ነገሮች የሚጠብቁ እና ለማድረግ የሚያስታውሱ ቅዱሳን ሁሉ፣ ለስጋቸው ፈውስ እና ለአጥንታቸው መጠገን ይቀበላሉ፤
፲፱ እናም ጥበብ እና ታላቅ የእውቀት ሀብቶች፣ እንዲሁም የተሰወሩ ሀብቶችንም ያገኛሉ፤
፳ እናም ይሮጣሉ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ አይደክሙም።
፳፩ እና እኔ ጌታ፣ አጥፊው መልአክ የእስራኤል ልጆችን እንዳለፋቸው፣ እነርሱን ያልፋቸው ዘንድ እና እንዳይገድላቸውም ዘንድ፣ የተስፋ ቃል እሰጣቸዋለሁ። አሜን።