“ኤልያስ እና የበኣል ነቢያት፣” የብሉይ ኪዳን ታሪኮች [2022 (እ.አ.አ)]
“ኤልያስ እና የበኣል ነቢያት፣” የብሉይ ኪዳን ታሪኮች
1 ነገሥት 18
ኤልያስ እና የበኣል ነቢያት
የጌታ ነቢይ ከሀሰተኛ ካህናት ጋር ሲወዳደር
የእስራኤል መንግሥት በውሃ እጦት መቸገሩን ቀጠለ። ንጉስ አክዓብ ህዝቡ በኣል የሚባለውን የሀሰት አምላክ እንዲከተሉ ነገራቸው።
ጌታ ነቢዩ ኤልያስ ከአክዓብ ጋር እንዲገናኝ ላከው። ኤልያስ ህዝቡን በሙሉ ወደ ተራራው ጫፍ እንዲመጡ ጋበዛቸው። እርሱም ከጌታ እና ከበአል የትኛው እውነተኛ አምላክ እንደሆነ እንዲያዩ ንጉሱን እና ካህናቱን ወደ ፉክክሩ ጋበዛቸው።
ኤልያስ ፉክክሩን ገለጸ። እርሱ እና ካህናት ወይፈን በመሰዊያ ላይ ይሰዋሉ፣ ነገር ግን ራሳቸው እሳትን አያነዱም። ይልቁንም ካህናቱ እሳት ይለኩስ ዘንድ ወደ በኣል ይጸልያሉ። ከዚያም ኤልያስ እሳት ይለኩስ ዘንድ ወደ ጌታ ይጸልያል። ኤልያስ እውነተኛ አምላክ ብቻ እሳቱን እንደሚለኩስ ያውቅ ነበር።
የበኣል ካህናት ወደ አምላካቸው ከጠዋት እስከ ከሰዓት በኋላ ጸለዩ፣ ነገር ግን ምንም አልደረሰም። ኤልያስ ቀለደባቸው እናም አምላካቸው በኣል ተኝቶ ይሆናል አለ።
ካህናቱ ተናደዱ፣ በመሰዊያውም ላይ ዘለሉ፣ እናም እስከምሽቱ ጮሁ። አምላካቸው መልስ ይሰጣል ብለው ተስፋ ነበራቸው፣ ነገር ግን ምንም እሳት አልነበረም።
ከዚያም የኤልያስ ተራ ነበር። የጌታን መሰዊያ አበጀ፣ በመሰዊያውም ዙሪያ ጉድጓድ ቆፈረ፣ እንዲሁም መስዋዕቱን አዘጋጀ።
ኤልያስ ሕዝቡ አራት በርሜል ውሃ እንዲሞሉ እና በመሠዊያው እንጨት ላይ ለሦስት ጊዜ እንዲያፈስሱ ጠየቃቸው። ውሀው እንጨቱን እና መሰዊያውን አረጠበ። ጉድጓዱንም ሁሉ ሞላ።
ኤልያስ እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ሀይል እንዲያሳይ ወደ ጌታ ጸለየ። የጌታ እሳት ወረደች እናም መስዋዕቱን፣ እንጨቱን፣ ድንጋዮቹን፣ እና ውሀውን በላች። ህዝቡም የኤልያስ አምላክ እውነተኛ እግዚአብሔር እንደሆነ አወቁ። ኤልያስ ድርቁ እንዲያበቃ ጸለየ፣ እናም ጌታ ዝናብን ላከ።