ቅዱሳት መጻህፍት
ሙሴ ፭


ምዕራፍ ፭

[ሰኔ–ጥቅምት ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.)]

አዳምና ሔዋን ልጆችን ወለዱ—አዳም መሥዋዕት አቀረበ፣ እግዚአብሔርንም አገለገለ—ቃየንና አቤል ተወለዱ—ቃየን አመጸ፣ ሰይጣንንም ከእግዚአብሔር በላይ ወደደ፣ እናም የጥፋት ልጅ ሆነ—ገዳይነትና ክፉነት ተስፋፋ—ወንጌሉም ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ የተሰበከ ነው።

እንዲህም ሆነ እኔ እግዚአብሔር አምላክ እነርሱን ካስወጣኋቸው በኋላ አዳም መሬቱን ማረስ ጀመረ፣ እና በዱር እንስሣቱም ላይ ስልጣን ነበረው፣ እናም እኔ ጌታ እንዳዘዝኩት እንጀራውን በፊቱ ወዝ በላ። እናም ሚስቱ ሔዋንም ከእርሱ ጋር አብራው ሰራች።

አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፣ እርሷም ወንድና ሴት ልጆችን ወለደች፣ እና እነርሱም በምድር ላይ በዙም ተባዙም።

እናም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአዳም ወንድና ሴት ልጆች ሁለት በሁለት በምድር ላይ ተከፋፈሉ፣ እናም መሬቱን ማረስ፣ መንጋዎችን መጠበቅ፣ እናም ወንድና ሴት ልጆችን መውለድ ጀመሩ።

አዳምና ሚስቱ ሔዋን የጌታን ስም ጠሩ፣ እናም ከዔድን ገነት አካባቢም የጌታን ድምጽ እያናገራቸው ሰሙ፣ እና አላዩትም ነበር፤ ከእርሱ ፊት ተዘግተው ነበርና።

እግዚአብሔር አምላካቸውን እንዲያመልኩ፣ እናም ከመንጋዎቻቸው መካከል በመጀመሪያ የተወለደውን ለጌታ መሥዋዕት እንዲያቀርቡም ትእዛዛትን ሰጣቸው። እና አዳምም ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ታዛዥ ነበር።

ከብዙ ቀናት በኋለ የአምላክ መልአክ ወደ አዳም መጥቶ እንዲህ አለው፥ ለጌታ መሥዋዕት ለምን ታቀርባለህ? አዳምም እንዲህ አለው፥ እግዚአብሔር ስላዘዘኝ እንጂ፣ ለምን እንደሆነ አላውቅም።

ከዚያም መልአኩ እንዲህ ብሎ ተናገረ፣ ይህ ነገር በጸጋና በእውነት የተሞላው የአብ አንድያ ልጅ መስዋዕት አምሳል ነው።

ስለዚህ፣ የምታደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ በወልድ ስም አድርግ፣ እና ንስሀ ግባ እና በወልድም ስም እግዚአብሔርን ለዘለአለም ጥራ

እናም በእዚያ ቀን ስለአብና ወልድ የሚመሰክረው መንፈስ ቅዱስ አዳም ላይ በማረፍ እንዲህ አለ፥ እኔ ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ እናም እስከዘለአለም ድረስ የአብ አንድያ ልጅ ነኝ፣ እንደ ወደቅህም አንተና ፍላጎት ያላቸው የሰው ዘሮች ሁሉ ለመዳን ይችላሉ።

በዚያም ቀን አዳም እግዚአብሔርን ባረከ እናም ተሞላ፣ እና በምድር ላይ ስላሉት ቤተሰቦች ሁሉ እንዲህ ብሎ መተንበይ ጀመረ፥ የእግዚአብሔር ስም ይባረክ፣ በጥፋቴ ምክንያት አይኖቼ ተከፈተዋልና፣ እና በዚህ ህይወትም ደስታ ይኖረኛል፣ እንደገና በስጋዬም እግዚአብሔርን አያለሁ።

፲፩ እና ሚስቱ ሔዋንም እነዚህን ነገሮች በሙሉ ሰማች እና በደስታ እንዲህ አለች፥ ባናጠፋ ኖሮ ዘርም አይኖረንም ነበር፣ እና መልካምና ክፉን፣ እናም የመዳንን ደስታ፣ እናም ለታዛዡ ሁሉ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ዘለአለማዊ ህይወትን አናውቅም ነበር።

፲፪ እና አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ስም ባረኩ፣ እና ሁሉንም ነገሮች ለሴቶችና ለወንዶች ልጆቻቸው አሳወቁ

፲፫ እናም ሰይጣን ከመካከላቸው መጥቶ እንዲህ አለ፣ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ፣ እናም እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፥ ይህን አትመኑ፤ እና ይህንንም አላመኑም፣ እና ሰይጣንን ከእግዚአብሔር በላይ ወደዱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰዎችም ስጋዊ፣ ስሜትዊና ዲያብሎሳዊ መሆን ጀመሩ።

፲፬ እና እግዚአብሔር አምላክም በሁሉም ስፍራ ሰዎችን በመንፈስ ቅዱስ ጠራቸውና ንስሀ እንዲገቡም አዘዛቸው።

፲፭ በወልድ ያመኑትና ለኃጢአታቸው ንስሀ የገቡት ሁሉ ይድናሉ፤ እናም የማያምኑትና ንስሀ የማይገቡት ሁሉ ይፈረድባቸዋል፤ እና በፅኑ ትእዛዝም ቃላት ከእግዚአብሔር አንደበት ሄዱ፤ ስለዚህ መሟላት አለባቸው።

፲፮ እና አዳምና ሚስቱ ሔዋን የእግዚአብሔርን ስም መጥራት አላቆሙም። አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፣ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም ወንድን ከእግዚአብሔር አገኘሁ፤ ስለዚህ እርሱም ቃላቶቹን የማይቃወም ይሆናል አለች። ነገር ግን እነሆ፣ ቃየን እንዲህም በማለት አላደመጠም፥ ጌታ ማን ነው ማወቅ የሚያስፈልገኝ?

፲፯ ደግማም ፀንሳ ወንድሙን አቤልን ወለደች። እና አቤልም የእግዚአብሔርን ድምፅ አደመጠ። አቤልም በግ ጠባቂ ነበር፣ ነገር ግን ቃየን ምድርን የሚያርስ ነበረ።

፲፰ እና ቃየን ሰይጣንን ከእግዚአብሔር በላይ ወደደ። እና ሰይጣን እንዲህ በማለት አዘዘው፥ ለጌታ መስዋዕት አቅርብ

፲፱ እናም ከጊዜም በኋላ እንዲህ ሆነ ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ።

እና አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እና እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መስዋዕቱ ተመለከተ፤

፳፩ ነገር ግን ወደቃየንና ወደ መሥዋዕቱ አልተመለከተም። አሁን ሰይጣን ይህን አወቀ፣ እና ይህም አስደስተው። እና ቃየን እጅግ ተናደደ፣ ፊቱም ጠቆረ።

፳፪ እናም እግዚአብሔር ለቃየን እንዲህ አለው፥ ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ?

፳፫ መልካም ብታደርግ፣ ተቀባይ ትሆናለህ። እና መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፣ እና ሰይጣንም ይፈልግሀል፤ እና ትእዛዛቴን ካላደመጥህ በስተቀር፣ አሳልፌ እሰጥሀለሁ፣ እና በአንተም ላይ እንደ ፈቃዱ ይሆንብሀል። አንተም ገዢው ትሆናለህ።

፳፬ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሀሰት አባት ትሆናለህ፤ ጥፋት ተብለህም ትጠራለህ፤ ከአለም በፊት ነበርክና።

፳፭ ወደፊት በሚመጣውም ጊዜ እንዲህ ይባላል—እነዚህ ጸያፎች ከቃየን የመጡ ናቸው፤ ከእግዚአብሔር የመጣውን ታላቅ ምክር አስወግዷልና፤ እና ንስሀ ካልገባህ በስተቀር፣ ይህ በአንተ ላይ የማደርግብህ እርግማን ነው።

፳፮ እናም ቃየንም በጣም ተናደደ፣ እና የአምላክንና በጌታ ፊት በቅድስና የሚሄደው ወንድሙ የአቤልን ድምጽም ከዚህ በኋላ አላደመጠም።

፳፯ እናም አዳምና ሚስቱ በቃየንና በወንድሞቹ ምክንያት በጌታ ፊት አለቀሱ።

፳፰ እና እንዲህ ሆነ ቃየንም ከወንድሞቹ ሴት ልጆች አንዷን አገባ፣ እና ሰይጣንን ከእግዚአብሔር በላይ ወደዱ

፳፱ እና ሰይጣን ለቃየን እንዲህ አለው፥ በጉሮሮህ ማልልኝ፣ እናም ይህን ከነገርህ በእርግጥ ትሞታለህ፤ እና ወንድሞችህ እንዳይናገሩት በጭንቅላታቸውና በህያው እግዚአብሔር እንዲምሉ አድረግ፤ ይህን ከነገሩም በእርግጥ ይሞታሉና፤ እናም ይህም አባትህ እንዳያውቀው ነው፤ እናም በዚህ ቀን አቤል ወንድምህን በእጅህ ላይ እሰጥሀለሁ።

እና ሰይጣንም እንደ ትእዛዙ እንደሚያደርግም ለቃየን ማለለት። እና እነዚህ ነገሮች ሁሉ የተደረጉት በሚስጥር ነበር።

፴፩ እናም ቃየን አለ፥ በእውነት እኔ በመግደል ትርፍ አገኝ ዘንድ፣ በእርግጥም የዚህ ታላቅ ሚስጥር ጌታ ማኸን ነኝ። ስለዚህ ቃየንም ጌታ ማኸን ተብሎ ተጠራ፣ እናም በጥፋቱም ከበረ።

፴፪ እናም ቃየን ወደ ሜዳ ወጣ፣ እናም ቃየን ከወንድሙ አቤል ጋር ተነጋገረ። እናም እንዲህ ሆነ በሜዳው ላይ እያሉ፣ በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፣ ገደለውም።

፴፫ እና ባደረገውም ክብር ተሰምቶት እንዲህ አለ፥ ነጻ ነኝ፣ በእርገጥም የወንድሜ መንጋዎች በእጆቼ ወደቁ።

፴፬ እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፥ ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? እርሱም አለ፥ አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?

፴፭ ጌታም እንዲህ አለ፤ ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃል።

፴፮ አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች ምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።

፴፯ ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።

፴፰ ቃየንም እግዚአብሔርን አለው፥ ሰይጣን በወንድሜ መንጋዎች ምክንያት ፈተነኝ። ደግሞም ተናድጄ ነበር፤ አንተም የእኔን ሳይሆን የእርሱን መስዋዕት ተቀብለህ ነበርና፤ ቅጣቴም ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት።

፴፱ እነሆ ዛሬ ከጌታ ፊት አሳደድኸኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ እንዲህ ይሆናል የሚያገኘኝም ሁሉ በጥፋቴ ምክንያት ይገድለኛል፣ እነዚህ ነገሮች ከአምላክ ሊሸሸጉ አይችሉምና።

እኔ ጌታም እንዲህ አልኩት፥ የገደለህ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል። እና እኔ ጌታም ያገኙት ሁሉ እንዳይገድሉት፣ በቃየን ላይ ምልክት አደረግሁለት።

፵፩ እናም ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ፣ እናም ከሚስቱና ከብዙ ወንድሞቹ ጋር ከዔደን በስተምስራቅ በምትገኘው በኖድ ምድር ተቀመጠ።

፵፪ ቃየንም ሚስቱን አወቀ፤ ፀነሰችም፣ ሔኖህንም ወለደች፣ እናም እርሱም ብዙ ወንድና ሴት ልጆችን ወለደ። ከተማም ሠራ፣ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም ሔኖህ አላት።

፵፫ ሄኖሕም ጋይዳድን ወለደ፤ እናም ሌሎች ወንድና ሴት ልጆች ወለደ። ጋይዳድም ሜኤልን ወለደ፣ እና ሌሎች ወንድና ሴት ልጆችን ወለደ። እናም ሜኤልም ማቱሳላን ወለደ፣ እናም ሌሎች ወንድና ሴት ልጆች ወልደ። እናም ማቱሳላም ላሜህን ወለደ።

፵፬ ላሜሕም ለራሱ ሁለት ሚስቶችን አገባ፤ የአንዲቱ ስም ዓዳ፣ የሁለተኛይቱ ስም ሴላ ነበረ።

፵፭ ዓዳም ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ፤ የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፤ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ።

፵፮ ሴላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባል ቃየንን ወለደች። የቱባልቃይንም እኅት ናዕማ ነበረች።

፵፯ ላሜሕም ለሚስቶቹ ለዓዳና ለሴላ አላቸው፥ እናንት የላሜሕ ሚስቶች ቃሌን ስሙ፣ ነገሬንም አድምጡ፤ እኔ ጕልማሳውን ለቍስሌ፣ ብላቴናውንም ለመወጋቴ ገድዬዋለሁና።

፵፰ ቃየንን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፣ በእውነትም ላሜሕን ግን ሰባ ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤

፵፱ ላሜህ እንደ ቃየን ከሰይጣን ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ሰይጣን ለቃየን ለሰጠው ታላቅ ሚስጥር ጌታ በመሆን ጌታ ማኸን ሆኖአልና፤ እናም የሔኖክ ልጅ ጋይዳድም የእነርሱን ሚስጥር በማወቁ፣ ለአዳም ልጆች ይህን መግለፅ ጀመረ፤

ስለዚህ ቃየን ወንድሙን አቤልን ሃብት ለማግኘት እንዳደረገው ሳይሆን፣ ላሜሕ በቃለ መሀላው ምክንያት ተናዶ ነበር የገደለው።

፶፩ ከቃየን ቀናት ጀምሮ፣ የሚስጥር ሴራ ነበር፣ ስራቸውም በጭለማ ውስጥ ነበር፣ እና እያንዳንዱም ወንድሙን ያውቅ ነበር።

፶፪ ስለዚህ እግዚአብሔርም ላሜሕን፣ ቤቱን፣ እናም ከሰይጣን ጋር ቃል የገቡትን ሁሉ ረገማቸው፤ ትእዛዛትን አላከበሩምና፣ ይህም እግዚአብሔርን አላስደሰተውም፣ እነርሱንም አላገለገላቸውም፣ እና ስራቸውም ጸያፎች ነበሩ፣ እና በሰዎች ወንድ ልጆች ሁሉ መካከልም መሰራጨት ጀመረ። እና ይህም በሰዎች ልጆች መካከል ነበር።

፶፫ እናም ላሜህ ለሚስቶቹ ሚስጥሩን ስለነገራቸው፣ እና ስለአመጹበትና ለሌሎችም ስለነገሩበት፣ እና ርህራሄ ስላልነበራቸው፣ ከሰዎች ሴት ልጆች መካከል እነዚህን ነገሮች አይነጋገሩባቸውም።

፶፬ ስለዚህ ላሜህ ተጠልቶ ነበር፣ እና አስወጡትም፣ እና እንዳይሞትም፣ ከሰዎች ልጆች መካከል አይመጣም ነበር።

፶፭ እንደዚህም የጭለማ ስራዎች በሰው ልጆች ሁሉ መካከል መሳካት ጀመሩ።

፶፮ እግዚአብሔርም ምድርን በከባድ እርግማን ረገማት፣ እና በመጥፎዎችም፣ በፈጠራቸው የሰዎች ልጆች ሁሉ ተናድዶ ነበር፤

፶፯ እነርሱም ድምጹን አያደምጡም፣ ወይም አለም ከመፈጠሯ በፊት ተዘጋጅቶ የነበረው፣ በመካከለኛው ዘመን ይመጣል ብሎ በተገለጠላቸው በአንድያ ልጅ አያምኑም ነበርና።

፶፰ እንደዚህም ወንጌሉ ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር ፊት በተላኩት በቅዱስ መላእክት፣ እና በድምጹ፣ እና በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በመገለፅ ይሰበክ ጀመር።

፶፱ እንደዚህም ሁሉም ነገሮች በቅዱስ ስርአቶች ለአዳም ተረጋግጠውለታል፣ እና ወንጌልም ተሰብኳል፣ እናም በአለም ውስጥ ይሆን ዘንድ ታውጇል፤ እናም እንደዚህም ነበር። አሜን።