ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻፲


ክፍል ፻፲

በሚያዝያ ፫፣ ፲፰፻፴፮ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ቤተመቅደስ ውስጥ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝና ለኦሊቨር ካውድሪ የተገለጡ ራዕዮች። ጊዜውም በሰንበት የስብሰባ ቀን ነበር። የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ እንደሚገልጸው፥ “በዚህ ቀን እና ረፋድ፣ የጌታን እራት በቅዱስ ጠረጴዛው ላይ ለማስተዳደር ልዩ መብት ከነበራቸው ከአስራ ሁለቱ በመቀበል ለቤተክርስቲያን ለማደል ሌሎቹን ፕሬዘደንቶች ረዳሁ። ይህን አገልግሎት ለወንድሞቼ ካከናወንኩ በኋላ፣ ወደ መስበኪያው ተመለስኩኝ፣ መጋረጃውን በመዝጋት እና ከኦሊቨር ካውድሪ ጋር በአክብሮት እና ጸጥተኛ ጸሎት አጎነበስኩኝ። ከጸሎት ከተነሳሁም በኋላ፣ የሚቀጥለው ራዕይ ለሁለታችን ተከፈተልን”።

፩–፲፣ ጌታ ያህዌህ በክብር መጣ እና የከርትላንድ ቤተመቅደስን እንደ ቤቱ ተቀበለ፤ ፲፩–፲፪፣ ሙሴ እና ኤልያስ እያንዳንዳቸው ተገለጡ እና ቁልፎቻቸውን እና የዘመን ፍጻሜዎቻቸውንም ሰጡ፤ ፲፫–፲፮፣ በሚልክያስ ቃል እንደተገባውም ኤልያስ ተመለሰ እና የዘመን ፍጻሜውን ቁልፎች ሰጠ።

መጋረጃው ከአዕምሮዎቻችን ተወገደ፣ እና የመረጃ አይኖቻችንም ተከፈቱ።

ጌታን በመስበኪያው መደገፊያ ላይም በፊት ለፊታችን አየነው፤ እና ከእግሮቹም በታች የቡናማ ቢጫ ቀለም አይነት የነበረ ንጹህ ወርቅ የተነጠፈበት የሚመስል ስራ ነበር።

ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ የራሱ ጠጕርም እንደ ንጹህ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ፊቱም ከብርቱ የጸሀይ ብርሀን በላይ የሚያበራ ነበር፤ ድምፁም እንዲህ የሚል እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ፣ እንዲሁም የያህዌህ ድምፅ ነበር፥

እኔ ፊተኛውና ኋለኛው ነኝ፤ እኔ ህያውም ነኝ፣ የተገደልኩትም እኔ ነኝ፤ እኔም በአብ ዘንድ አማላጃችሁ ነኝ።

እነሆ፣ ኃጢአታችሁ ተሰርየዋል፤ በፊቴም ንጹህ ናችሁ፤ ስለዚህም፣ ራሳችሁን አቅኑ እናም ተደሰቱ።

የወንድሞቻችሁ ልብም ይደሰት፣ እና በሀይላቸው ይህን ቤት በስሜ የሰሩት የህዝቤም ልብ ሁሉ ይደሰት።

እነሆ፣ ይህን ቤት ተቀብዬዋለሁ፣ እና ስሜም በዚህ ይሆናል፤ እና በምህረትም ራሴን ለህዝቤ አሳያለሁና።

አዎን፣ ህዝቤ ትእዛዛቴን ቢጠብቁ፣ እና ይህን ቅዱስ ቤት ባያጎድፍ፣ ለአገልጋዮቼ እገልጣለሁ፣ እና በራሴም ድምፅ አናገራቸዋለሁ።

አዎን፣ በሚፈሱት በረከቶች እና አገልጋዮቼ በዚህ ቤት ውስጥ በተቀበሉት መንፈሳዊ ስጦታዎች ምክንያት የሺዎች እና የአስር ሺዎች ልብ በእጅጉ ይደሰታሉ።

እና የዚህ ቤት ዝናም በውጪ አገሮች ይስፋፋል፤ እና ይህም በህዝቤ ራሶች ላይ የሚፈሰው የበረከት መጀመሪያም ነው። እንዲህም ይሁን። አሜን።

፲፩ ይህ ራዕይ ከተፈጸመ በኋላ፣ ሰማያት ዳግም ተከፈቱልን፤ እና ሙሴ በፊታችን መጣ፣ እና ከምድር አራት ማዕዘናትን የእስራኤልን መሰብሰቢያ እና ከሰሜን ምድር የአስሩን ነገዶች መምሪያ ቁልፎችን ሰጠን።

፲፪ ከዚህ በኋላ፣ ኤልያ መጣ፣ እና በእኛና በዘራችን ከእኛም በኋላ የሚመጡ ትውልዶች ሁሉ ይባረካሉ በማለት የአብርሐም ወንጌል የዘመን ፍጻሜን ሰጠን።

፲፫ ይህ ራዕይ ከተፈጸመ በኋላ፣ ሌላ ታላቅ እና የክብር ራዕይ ተከፈተልን፤ ሞትን ሳይቀምስ ወደሰማይ የተወሰደው ነቢዩ ኤልያስ በፊት ለፊታችን ቆመ፣ እናም አለ፥

፲፬ እነሆ፣ በሚልክያስ አንደበት በመመስከር ተነግሮ የነበረው ጊዜ በሙላት መጥቷል—ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ እርሱ [ኤልያስ] እንደሚላክ—

፲፭ ይህም፣ ምድር በእርግማን እንዳትመታ፣ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ለመመለስ እንዳለበት ተነግሮ የነበረው ጊዜ በሙላት መጥቷል።

፲፮ ስለዚህ፣ የዚህ የዘመን ፍጻሜ ቁልፎች በእጆቻችሁ ተሰጥተዋል፤ እና ይህም ታላቁና የሚያስፈራው የጌታ ቀን ቅርብ እንደሆነ፣ እንዲሁም በበር ላይ እንዳለም፣ ታውቃላችሁ።