ኤልያስ
በኋለኛው ቀናት የመተሳሰርን ሀይል ቁልፍ ለጆሴፍ ስሚዝና ለኦሊቨር ካውደሪ ለመስጠት የተመለሰው የብሉይ ኪዳን ነቢይ። በኖረበት ቀን፣ ኤልያስ በእስራኤል ሰሜን መንግስት ውስጥ አገለገለ (፩ ነገሥ. ፲፯–፳፪፤ ፪ ነገሥ. ፩–፪)። በጌታ ታላቅ እምነት ነበረው እናም በብዙ ታአምራት የታወቀ ነበር። እርሱ ስለጠየቀውም፣ ዝናብን ለ፫ አመት ተኩል ከመዝነብ አገደው። ልጅን ከሞት አስነሳው እናም እሳትን ከሰማይ አወረደ (፩ ነገሥ. ፲፯–፲፰)። የአይሁድ ህዝቦች ሚልክያስ እንደሚመለሰ እንደተነበየው፣ የኤልያስ መመለስን እየጠበቁ ናቸው (ሚል. ፬፥፭)። በአይሁድ ፋሲካ አሁንም የተከፈተ በርና ማንም የማይቀመጥበት ወንበር የሚጠብቀው የተጋበዘ እንግዳ ነው።
ነቢዩ ጆዜፍ ስሚዝ ኤልያስ የመልከ ጼዴቅ ክህነትን የመተሳሰር ሀይልን ይዟል እናም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜ በፊት ይዞት የነበረው የመጨረሻው ነቢይ ነው ብሏል። በመለወጫ ተራራ ላይ ከሙሴ ጋር በመታየት የክህነት ቁልፎችን ለጴጥሮስ፣ ለያዕቆብ፣ እና ለዮሐንስ ሰጠ (ማቴ. ፲፯፥፫)። በሚያዝያ ፫፣ ፲፰፻፴፮ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ኦሀዮ ቤተመቅደስ ውስጥ ከሙሴ እና ከሌሎች ጋር እንደገናም ታየ እናም እንደዚህ አይነት ቁልፎችን ለጆሴፍ ስሚዝና ለኦልቨር ካውደሪ ሰጠ (ት. እና ቃ. ፻፲፥፲፫–፲፮)። ይህም ሁሉ በሚልክያስ ፬፥፭–፮ ውስጥ እንደተናገረው፣ ለጌታ ዳግም ምፅዓት ለመዘጋጀት ነበር።
የኤልያስ ሀይል በምድር ላይ የታሰሩ ወይም የተፈቱ ነገሮች በሰማይ ውስጥ እንዲታሰሩ ወይም እንዲፈቱ የሚያደርግ የክህነት የመተሳሰር ሀይል ነው (ት. እና ቃ. ፻፳፰፥፰–፲፰)። ዛሬ በጌታ የተመረጡ አገልጋዮች ይህ የመተሳሰር (የማተም) ሀይል አላቸው እናም እነዚህን የወንጌል ስነስርዓቶች ለህያውንና ለሙታኖች ያከናውናሉ (ት. እና ቃ. ፻፳፰፥፰)።