ክፍል ፻፭
በሰኔ ፳፪፣ ፲፰፻፴፬ (እ.አ.አ.) በሚዙሪ ፊሺንግ ወንዝ ላይ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። በነቢዩ አመራር ስር፣ ከኦሀዮ እና ሌሎች አካባቢዎች የመጡ ቅዱሳን በኋላ የፅዮን ሰፈር ተብሎ በሚታወቀው ጉዞ ወደ ምዙሪ ተሰልፈው ሄዱ። አላማቸውም ከምዙሪ በግድ የወጡትን ቅዱሳን አጅበው በጃክሰን የግዛት ክፍል ወደነበሩበት መሬታቸው ለመመለስ ነበር። ቅዱሳንን ያሳደዱ የምዙሪ ሰዎች የፅዮን ሰፈር ጸያፍ እርምጃ ይወስዱብናል ብለው ፈርተው ነበር እናም በክሌይ የግዛት ክፍል፣ ምዙሪ ውስጥ የሚኖሩትን ቅዱሳን አስቀድመው አጥቅተው ነበር። የምዙሪ ገዢ ቅዱሳንን ለመርዳት የገባውን ቃል መልሶ ሲወስድ፣ ጆሴፍ ይህን ራዕይ ተቀበለ።
፩–፭፣ ፅዮን የምትገነባው የሰለስቲያል ህግን ጠባቂ በመሆን ነው፤ ፮–፲፫፣ የፅዮን ቤዛነት ለጥቂት ጊዜ ተላልፏል፣ ፲፬–፲፱፣ ጌታ የፅዮንን ጦርነት ይዋጋል፤ ፳–፳፮፣ ቅዱሳን ብልሆች ይሁኑ እና ሲሰበሰቡም በታላቅ ስራዎች ኩራት አይሰማቸው፤ ፳፯–፴፣ በጃክሰን እና በአጠገቡ የግዛት ክፍሎች መሬቶች ይገዙ፤ ፴፩–፴፬፣ ሽማግሌዎች በከርትላንድ ውስጥ በጌታ ቤት ውስጥ መንፈሳዊ ስጦታ ይቀበሉ፤ ፴፭–፴፯፣ የተጠሩት እና የተመረጡት ቅዱሳን ይቀደሳሉ፤ ፴፰–፵፩፣ ቅዱሳን ለአለም የሰላም አርማን ያንሱ።
፩ የተሰቃዩ ህዝቤን ቤዛነት በሚመለከት ፈቃዴን ትማሩ ዘንድ ራሳችሁን ለሰበሰባችሁት እውነት እላለሁ—
፪ እነሆ፣ እላችኋለሁ፣ ስለግለሰብ ሳይሆን ስለቤተክርስቲያኗ ስናገር፣ በህዝቤ መተላለፍ ባይሆን ኖሮ፣ አሁንም ይድኑ ነበር።
፫ ነገር ግን እነሆ፣ በእጆቻቸው ለምጠብቃቸው ነገሮች ታዛዥ ለመሆን አልተማሩም፣ ነገር ግን በክፋት የተሞሉ ናቸው፣ እና እቃዎቻቸውን በቅዱሳን እንደሚገባው ለድሆችና በመካከላቸው ለሚሰቃዩት አያካፈሉም፤
፬ እና በሰለስቲያል መንግስት ህግ መሰረት አስፈላጊ በሆነው ህብረትም አይተባበሩም፤
፭ እና ፅዮን ካለሰለስቲያል መንግስት ህግ መሰረታዊ መርሆች ካልሆነ በስተቀር ልትገነባ አይቻላትም፤ አለበለዚያም ወደ ራሴ ልቀበላት አልችልም።
፮ እና ህዝቤ ታዛዥነት እስኪማሩ ድረስ፣ አስፈላጊም ቢሆን በሚሰቃዩባቸው ነገሮች መገሰፅ ያስፈልጋቸዋል።
፯ የምናገረው ህዝቤን እንዲመሩ ስለተመደቡት የቤተክርስቲያኔ የመጀመሪያ ሽማግሌዎች አይደለም፣ ሁሉም በፍርድ ላይ አይደሉምና፤
፰ ነገር ግን በሌላ ስፍራ ስላሉት ቤተክርስቲያኔ በሚመለከት እናገራለሁ—እንዲህ የሚሉ ብዙ አሉ፥ አምላካቸው የት አለ? እነሆ፣ በችግር ጊዜ ያድናቸዋል፣ አለበለዚያም ወደፅዮን አንሄድም፣ እና ገንዘባችንንም እናስቀራለን።
፱ ስለዚህ፣ በህዝቤ መተላለፍ ምክንያት ሽማግሌዎቼ የፅዮን ቤዛነት ለትንሽ ዘመን ይጠብቁ ዘንድ ፍቃዴ ነው—
፲ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ፣ እና ህዝቤ በፍጹም እንዲማሩ፣ እና አጋጣሚም እንዲያገኙ፣ እና ሀላፊነታቸውንና ከእጆቻቸው የምፈልገውን ነገሮች በሚመለከት በፍጹም ይማሩ ዘንድ ነው።
፲፩ እና ሽማግሌዎቼ ከላይ የኃይል መንፈሳዊ ስጦታ እስኪሰጣቸው ድረስ ይህም ሆኖ አይሆንም።
፲፪ እነሆ፣ ታማኝ ቢሆኑ እና በፊቴም በትህትና እስከቀጠሉ ድረስ፣ ታላቅ መንፈሳዊ ስጦታ እና በረከት በእነርሱ ላይ ለማፍሰስ አዘጋጅቻለሁ።
፲፫ ስለዚህ ለፅዮን ቤዛነት ሽማግሌዎቼ ለጥቂት ዘመን ይጠብቁ ዘንድ ፍቃዴ ነው።
፲፬ እነሆ፣ የፅዮንን ጦርነት እንዲዋጉ በእጆቻቸው አልፈልግባቸውምና፤ ከዚህ በፊት ትእዛዝ እንደሰጠሁት፣ ይህንንም አሟላለሁና—ጦርነታችሁን እዋጋላችኋለሁ።
፲፭ እነሆ፣ አጥፊው ጠላቶቼን እንዲያጠፋ እና እንዲያባክን ልኬዋለሁ፤ እና ከብዙ አመታት በኋላ ውርሴን እንዲበክሉ፣ እና ለቅዱሳኔ መሰብሰብ በቀደስኩባቸው ምድሮች ላይ ስሜን እንዲሰድቡ አይተዉም።
፲፮ እነሆ፣ አገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ ለቤቴ ጥንካሬ፣ እንዲሁም ጀግኖቼን፣ ወጣት ወንዶቼን፣ እና ጎልማሳዎቼን ለህዝቤ ቤዛነት እንዲሰበሰቡ፣ እና የጠላቶቼን ማማዎች እንዲጥሉ፣ እና ጠባቂዎቻቸውንም እንዲበትኑ እንዲነግራቸው አዘዝኩት፤
፲፯ ነገር ግን የቤቴ ጥንካሬ ቃላቴን አላደመጡም።
፲፰ ነገር ግን ቃላቴን ያደመጡ እስካሉ ድረስ፣ በታማኝነት ቢቀጥሉ በረከት እና የመንፈስ ስጦታ አዘጋጅቼላቸዋለሁ።
፲፱ ጸሎታቸውን ሰምቻለሁ፣ እና ስለታቸውን እቀበላለሁ፤ እና እምነታቸውም ተፈትኖ እስከዚህ ድረስ ይመጡም ዘንድ ፍቃዴ ነው።
፳ አሁንም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ትእዛዝንም እሰጣችኋለሁ፣ ወደዚህ እስከመጣችሁ ድረስ በአካባቢው ለመቆየት የሚችሉ ይቆዮ፤
፳፩ መቆየት የማይችሉት፣ በምስራቅ ቤተሰብ ያላቸውም፣ አገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ፣ እስከመደባቸው ድረስ ለትንሽ ዘመን ይቆዩ፤
፳፪ ስለዚህ ጉዳይ እመክረዋለሁ፣ እና ለእነርሱ የሚመደቡላቸው ማናቸውም ነገሮች ሁሉ ይሟላሉ።
፳፫ እና በዚህ አካባቢ የሚኖሩት ህዝቤ ሁሉ ታማኝ እና ጸሎተኛ እና በፊቴ ትሁት ይሁኑ፣ እና የገለጥኩላቸውን ነገሮችንም እንዲገልጹ በእኔ ዘንድ ጥበብ እስኪሆን ድረስ አይግለጿቸው።
፳፬ ስለፍርድም አትናገሩ፣ ስለእምነት ወይም ስለታላቅ ስራም ኩራት አይሰማችሁ፣ ነገር ግን በምትችሉት መጠን በአንድ አካባቢ፣ ለሰዎች ስሜት እያሰባችሁ በጥንቃቄ ተሰብሰቡ።
፳፭ እነሆም፣ በሰላም እና በደህንነት ታርፉ ዘንድ፣ ለህዝቦቹም፥ ፍርድ እና ጽድቅን በህጉ መሰረት ፈፅሙ፣ እና በደላችንን መልሱልን እያላችሁ፣ በአይኖቻቸው ውስጥም ውለታ እና ጸጋ እሰጣችኋለሁ።
፳፮ እነሆ፣ ባልንጀሮቼ አሁን እላችኋለሁ፣ በዚህም መንገድ፣ የእስራኤል ሰራዊት እጅግ ታላቅ እስኪሆን ድረስ፣ በህዝቡ አይኖች ፊት ሞገስን ታገኛላችሁ።
፳፯ እና አገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ እና የመደብኳቸው ሽማግሌዎቼ የቤቴን ብርታት ለመሰብሰብ ጊዜን እስከሚያገኙ ድረስ በፈርኦን ልብ እንዳደረግሁት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ የህዝቡን ልብ አራራለሁ፣
፳፰ እና ብልህ ሰዎችንም፣ በጃክሰን የግዛት ክፍል ውስጥ እና በአካባቢው በሚገኙት የግዛት ክፍሎች ውስጥ ሊገዙ የሚችሉትን መሬቶችን ሁሉ ስለመግዛት የሰጠሁትን ትእዛዝ ይፈጸሙ ዘንድ ነው።
፳፱ እነዚህ መሬቶች እንዲገዙ ፍቃዴ ነው፤ እና ከተገዙም በኋላ ቅዱሳኔ በሰጠኋችሁ የቅድስና ህግጋት መሰረት ይወስዷቸውም ዘንድ ፍቃዴ ነው።
፴ እና እነዚህ መሬቶች ከተገዙ በኋላ፣ የእስራኤል ሰራዊት በገንዘባቸው የገዙትን መሬቶቻቸውን መልሰው በመውሰዳቸው፣ እና በእነዚያም የሚገኙትን የጠላቶቼን ማማዎች በመጣላቸው፣ እና ጠባቂዎቻቸውን በመበተናቸው፣ እና የሚጠሉኝ ጠላቶቼን እስከ ሶስተኛ እና አራተኛ ትውልዶች ስለተበቀሉልኝ ከበደል ነጻ አደርጋቸዋለሁ።
፴፩ ነገር ግን በቅድሚያ ሰራዊቴ ታላቅ ይሁን፣ እና እንደጸሀይም የጠራ፣ እንደ ጨረቃ የተዋበ፣ እና ዓርማዎቿ ለሁሉም ህዝብ የሚያስፈራ ይሆንም ዘንድ በፊቴም ይቀደስ፤
፴፪ የዚህ አለም መንግስትም የፅዮን መንግስት በእርግጥም የአምላካችን እና የእርሱ ክርስቶስ መንግስት እንደሆነም ለማወቅ ይገደዱ ዘንድ፤ ስለዚህ፣ ለህግጋቷ ተገዢ እንሁን።
፴፫ እውነት እላችኋለሁ፣ በከርትላንድ ምድር ውስጥ ለስሜ እንዲገነባ ባዘዝኩት በቤቴ ውስጥ የቤተክርስቲያኔ ሽማግሌዎች የመንፈስ ስጦታቸውን ይቀበሉ ዘንድ ፍቃዴ ነው።
፴፬ እና ከቤዛነቷ በኋላ ስለፅዮን እና ስለህጓ የሰጠሁት ትእዛዛት ይሟሉ እናም ይፈጸሙ።
፴፭ የጥሪ ቀን ነበር፣ ነገር ግን ለመምረጫ ቀን ጊዜው መጥቷል፤ እና ብቁ የሆኑ እነርሱ ይመረጡ።
፴፮ እና የተመረጡትም በመንፈስ ድምፅ ለአገልጋዬ ይገለጣሉ፤ እና እነርሱም ይቀደሳሉ፤
፴፯ እና የተቀበሉትን ምክር እስከተከተሉ ድረስ፣ ከብዙ ቀናት በኋላ ፅዮንን የሚመለከቱ ነገሮችን ሁሉ ያከናውኑ ዘንድ ሀይል ይኖራቸዋል።
፴፰ ደግሞም እላችኋለሁ፣ ለመቷችሁ ሰዎች ብቻ ሳይሁን ለሁሉም ሰዎች፣ የሰላም ሀሳብ አቅርቡ፤
፴፱ እና የሰላም አርማ አንሱ፣ እና ለምድር ዳርቻዎችም ሰላምን አውጁ፤
፵ እና በውስጣችሁ ባለው በመንፈስ ድምፅ መሰረት ለመቷችሁም የሰላም ሀሳብ አቅርቡላቸው፣ እና ሁሉም ነገሮች ለጥቅማችሁ አብረው ይሰራሉ።
፵፩ ስለዚህ፣ ታማኝ ሁኑ፤ እነሆ፣ እናም አስተውሉ፣ እስከመጨረሻውም እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ። እንዲሁም ይሁን። አሜን።