“አሞን፣” የመፅሐፈ ሞርሞን ታሪኮች [2023 (እ.አ.አ)]
አሞን
ትሁት አገልጋይ
አሞን እና ወንድሞቹ ላማናውያንን ስለ ጌታ ሊያስተምሯቸው ፈለጉ። ላማናውያን ይኖሩበት ወደነበረ ምድር ሄዱ። በመንገዳቸውም ጌታ እንዲረዳቸው ጾሙ እንዲሁም ጸለዩ። ጌታም አፅናናቸው። ታጋሽ እና ጥሩ ምሳሌ እንዲሆኑ ነገራቸው። እያንዳንዳቸውም ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመሄድ ማስተማር ጀመሩ።
አሞን እስማኤል ወደሚባል ቦታ ሄደ። በዚያ ያሉት ሰዎች አስረውት ወደ ንጉሥ ላሞኒ ወሰዱት። አሞን ከላማናውያን ጋር መኖር እንደሚፈልግ ለላሞኒ ነገረው። ላሞኒ አሞንን ስለወደደው ነጻ አወጣው። አሞን ከሴት ልጆቹ መካከል አንዷን እንዲያገባ ፈለገ፣ ነገር ግን አሞን የላሞኒ አገልጋይ መሆንን መረጠ።
ላሞኒ፣ አሞን እንስሳቱን እንዲንከባከብ ነገረው። አንድ ቀን፣ አሞን እና አንዳንድ አገልጋዮች ውሃ ለመቅዳት እንስሳቱን ይዘው ሄዱ። እንስሳቱ እየጠጡ ሳለ ዘራፊዎች መጥተው አባረሯቸው። ሌሎቹ አገልጋዮች የላሞኒ እንስሳት በመጥፋታቸው እንዳይቀጡ ፈሩ።
አሞን ይህ የጌታን ኃይል ለማሳየት አጋጣሚ እንደሆነ አወቀ። ሌሎቹ አገልጋዮች እንዳይጨነቁ ነገራቸው እንዲሁም የጠፉትን እንስሳት እንዲያገኙ ረዳቸው።
ዘራፊዎቹ እንደገና እንስሳቱን ለመበታተን ተመለሱ። ነገር ግን በዚህ ጊዜ፣ አሞን ሌሎች አገልጋዮች እንዲቆዩ እና እንስሳቱ እንዳይጠፉ እንዲጠብቁ ነገራቸው።
አሞን ዘራፊዎቹ በጎቹን እንዳይበትኑ ለማስቆም ሄደ። ዘራፊዎቹ አሞንን አልፈሩትም። ከእርሱ በላይ ጠንካሮች የሆኑ መስሏቸው ነበር። ነገር ግን ጌታ አሞንን እየረዳ እንደነበረ አላወቁም።
አሞን በዘራፊዎቹ ላይ በወንጭፉ ድንጋይ ወረወረ። አንዳንዶቹ ሞቱ። ይህ ሌሎቹን ዘራፊዎች አስቆጣ፣ ስለሆነም አሞንን ሊገድሉት ፈለጉ። አሞንን በድንጋያቸው መምታት ባለመቻላቸው ተደነቁ። ይህን ያህል ኃያል ይሆናል ብለው አልጠበቁም ነበር።
ዘራፊዎቹ አሞንን በዱላቸው ሊመቱት ሞከሩ። ነገር ግን በሞከሩ ቁጥር አሞን እንዳይዋጉ እጆቻቸውን በሰይፍ ይቆርጥ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ውጊያውን ለመቀጠል በጣም ፈሩና ሮጠው ሸሹ።
አገልጋዮቹ አሞን እንስሳትን እንዴት እንዳዳናቸው ለላሞኒ ነገሩት። ላሞኒ ተገረመ። አሞን ታላቅ ኃይል ያለው እና ሁሉንም ነገር የሚያውቀውን ታላቁ መንፈስ እንደሆነ አሰበ።
ላሞኒ ከአሞን ጋር መነጋገር ፈልጎ ነበር፣ ነገር ግን ተጨንቆም ነበር።
አሞን ላሞኒን ለማየት ሄደ፣ ነገር ግን ላሞኒ ምን ማለት እንዳለበት አላወቀም ነበር። ጌታ፣ አሞን የላሞኒን ሃሳብ እንዲያውቅ ረዳው። አሞን ታላቁ መንፈስ እሱ እንዳልሆነ ተናገረ። ታላቁ መንፈስ እግዚአብሔር እንደሆነ ለላሞኒ ነገረው። ላሞኒ ስለ እግዚአብሔር የበለጠ ለማወቅ ፈለገ።
አሞን እግዚአብሔር አለምን እና በውስጡ ያሉትን ሁሉ እንደፈጠረ ተናገረ። ከዚያም አሞን እግዚአብሔር የማዳን እቅድ እንዳለው ለላሞኒ ነገረው። እንደዚያ እቅድ አካል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል። ላሞኒም አሞን ያለውን አመነ። ላሞኒ እግዚአብሔር ለእሱ እና ለህዝቡ ምህረት እንዲያደርግ በጸሎት ጠየቀ።