“ወጣት ሠራዊት፣” የመፅሐፈ ሞርሞን ታሪኮች [2023 (እ.አ.አ)]
ወጣት ሠራዊት
በእግዚአብሔር የታመኑ ወንድ ልጆች
ኔፋውያን ከላማናውያን ጋር ጦርነት ገጥመው ስለነበር እርዳታ አስፈለጋቸው። አንቲ-ኔፊ-ሌሂዎች መርዳት ፈለጉ። ነገር ግን ላለመዋጋት ለጌታ ቃል ገብተው ነበር። ሁለት ሺህ ወጣት ወንድ ልጆቻቸው ግን ይህን ቃል አልገቡም። ይልቁንም ወንዶች ልጆቹ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠበቅ ለመዋጋት ቃል ገቡ። እነዚህ ልጆች ብላቴና ሠራዊት ይባላሉ።
የብላቴኖቹ ሠራዊት፣ ነቢዩ ሔለማን ይመራቸው ዘንድ መረጡት። ከትልቁ የላማናውያን ሠራዊት ጋር ሲነጻጸሩ ትንሽ ቡድን ነበሩ። ነገር ግን ሔለማን ብላቴና ሠራዊቶቹ እውነተኛ፣ ደፋር እና ታማኝ መሆናቸውን ያውቅ ነበር። ሔለማን እየመራቸው፣ ኔፋውያንን ለመርዳት ሄዱ።
የኔፋውያን ወታደሮች ደክመው ነበር። ነገር ግን የብላቴኖቹ ሠራዊት በመጡ ጊዜ ኔፋውያን ደስ አላቸው። ወጣት ሠራዊቱ ተስፋና ብርታት ሰጣቸው። በአንድነት ላማናውያንን ለመዋጋት ተዘጋጁ። እንዲሁም የብላቴኖቹ ሠራዊት ወላጆች ምግብና ቁሳቁስ በማምጣት ረዱ።
ላማናውያን ብዙ ከተሞችን በምርኮ ያዙ እንዲሁም ሠራዊቶቻቸውን በውስጣቸው አስቀመጡ። የኔፋውያን መሪዎች ላማናውያንን ከአንዷ ከተማ ለማስወጣት ፈለጉ። እቅድ አወጡ እንዲሁም የብላቴኖቹን ሠራዊት እርዳታ ጠየቁ።
የብላቴኖቹ ሠራዊት በአቅራቢያው በምትገኝ ከተማ ውስጥ ለሚኖሩ ኔፋውያን ምግብ የሚያደርሱ አስመሰሉ። ላማናውያን ትንሹን ቡድን ባዩ ጊዜ ከተማቸውን ለቀው የብላቴኖቹን ሠራዊት አሳደዱ። ላማናውያን እነሱን መያዝ ቀላል እንደሆነ አስበው ነበር።
ብላቴኖቹ ሠራዊት ከላማናውያን ሸሹ። ከዚያም የኔፋውያን ሠራዊት ላማናውያንን ማሳደድ ጀመረ። ኔፋውያን እነርሱ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ላማናውያን የብላቴኖቹን ሠራዊት ለመያዝ ፈለጉ። ኔፋውያን የብላቴኖቹ ሠራዊት ችግር ውስጥ እንደሆኑ አይተው እነርሱን ለመርዳት በፍጥነት ዘመቱ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ የብላቴኖቹ ሠራዊት ላማናውያንን ማየት አልቻሉም። ኔፋውያን ላማናውያን ላይ ደርሰው እየተዋጉ ይሆን ሲሉ ማሰብ ጀመሩ።
ሔለማን ተጨነቀ። ላማናውያን እነሱን ለማጥመድ እየሞከሩ ሊሆን ይችላል በማለት አሰበ። ከላማናውያን ጋር ለመዋጋት ለመሄድ ፈቃደኛ እንደሆኑወጣት ወታደሮቹን ጠየቃቸው።
የብላቴኖቹ ሠራዊት እናቶቻቸው ያስተማሯቸውን አስታወሱ። እናቶቻቸው፣ እግዚአብሔር ደህንነታቸውን ስለሚጠብቅ እንዲታመኑበት እና እንዳይጠራጠ አስተምረዋቸው ነበር። እነዚህ ወንዶች ልጆች በእግዚአብሔር ታመኑ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ለመጠበቅ የገቡትን ቃል ለመፈጸም ፈለጉ።። ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን ለሔለማን ነገሩት።
ሔለማን በድፍረታቸው ተገረመ። ላማናውያንን ይዋጉ ዘንድ እየመራ መለሳቸው።
የብላቴኖቹ ሠራዊት ላማናውያን እና ኔፋውያን ሲዋጉ ተመለከቱ። ኔፋውያን ደክመው ነበር። ወጣቶቹ ወታደሮች በደረሱበት ጊዜም ሊሸነፉ ተቃርበው ነበር።.
የብላቴኖቹ ሠራዊት በእግዚአብሔር ጥንካሬ ተዋጉ። ላማናውያን ፈርተዋቸው መዋጋት አቆሙ። የብላቴኖቹ ሠራዊት ጦርነቱን ለማሸነፍ ረዱ!
ብዙ ኔፋውያን እና ላማናውያን በጦርነቱ ሞቱ። ሔለማን አንዳንድ ወጣት ወታደሮቹም ሞተው ሊሆን ይችላል ብሎ ተጨንቆ ነበር። ነገር ግን ከጦርነቱ በኋላ ሔለማን ሁሉንም ቆጠረ። ከብላቴኖቹ ሠራዊት መካከል አንዳቸውም እንዳልተገደሉ ሲመለከት በጣም ተደሰተ። እግዚአብሔር ጠበቃቸው።
ተጨማሪ ወንዶች ልጆች ከብላቴኖቹ ሠራዊት ጋር ተቀላቀሉ። ኔፋውያንን በውጊያ መርዳታችውን ቀጠሉ። በእነዚህ ሌሎች ጦርነቶች፣ የብላቴኖቹ ሠራዊት በሙሉ ቆሰሉ፣ ነገር ግን አንዳቸውም አልሞቱም። እናቶቻቸው ያስተማሯቸውን አስታወሱ። በእግዚአብሔር ታመኑ፣ እርሱም ጠበቃቸው።