“የኢየሱስ መወለድ ምልክቶች፣” የመፅሐፈ ሞርሞን ታሪኮች [2023 (እ.አ.አ)]
የኢየሱስ መወለድ ምልክቶች
በነቢይ ትምህርቶች ላይ እምነት
ነቢዩ ሳሙኤል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ውልደት ምልክቶች ካስተማረ አምስት ዓመት አካባቢ ሆነው። ብዙ ሰዎች አምነው ምልክቱን ይጠብቁ ነበር። ሌሎች ሰዎች ሳሙኤል እንደተሳሳተ እና የምልክቶቹ ጊዜ እንዳለፈ ተናገሩ። ኢየሱስ አይመጣም በማለት በአማኞች ላይ ተሳለቁባቸው።
አማኞች ተጨንቀው የነበረ ቢሆንም እምነት ነበራቸው። ምልክቶቹን መጠባበቃቸውን ቀጥለው ነበር። አንዱ ምልክት የማይጨልምበት አንድ ሌሊት ነበር። ፀሐይ ከጠለቀች በኋላም እንኳን እንደ ቀን ብሩህ ይሆናል። ጨለማ የሌለበት ሌሊት ኢየሱስ በቀጣዩ ቀን በሌላ አገር እንደሚወለድ ምልክት ይሆናል።
ያላመኑ ሰዎች እቅድ አወጡ። አንድ ቀን መረጡ፣ ምልክቱ በዚያ ቀን ካልተከሰተም አማኞች ይገደላሉ አሉ።
በዚህ ጊዜ ኔፊ የሚባል ሰው ነቢይ ነበር። አንዳንድ ሰዎች አማኞችን ለመግደል በመፈለጋቸው በጣም አዘነ።
ኔፊ መሬት ላይ ተደፍቶ በእምነታቸው ምክንያት ሊሞቱ ስለነበሩ አማኞች ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ቀኑን ሙሉ ጸለየ።
ለጸሎቱ መልስ፣ ኔፊ የኢየሱስን ድምጽ ሰማ። ኢየሱስ ምልክቱ በዚያ ሌሊት እንደሚሆን፣ ከዚያም ደግሞ በሚቀጥለው ቀን እንደሚወለድ ተናገረ።
በዚያች ሌሊት ፀሐይ ብትጠልቅም ጨለማ አልነበረም። የሳሙኤልን ቃል ያላመኑት ሰዎች በጣም ከመደነቃቸው የተነሳ በምድር ላይ ወደቁ። ባለማመናቸው ፈሩ። ያመኑት ሰዎች ሳይገደሉ ቀሩ።
በማግስቱ ፀሀይዋ እንደገና ወጣች፣ ሰማዩም ብሩህ ሆኖ ቆየ። ኢየሱስ የሚወለድበት ቀን ይህ እንደሆነ ሰዎቹ ሁሉ አወቁ።
ሰዎቹ ሌላ ምልክት አዩ። አዲስ ኮከብ በሰማይ ታየ። ሳሙኤል የተናገራቸው ምልክቶች በሙሉ ተፈጸሙ። ተጨማሪ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ አምነው ተጠመቁ።