ክፍል ፴፭
በታህሳስ ፯፣ ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.) በፈየት፣ ኒው ዮርክ፣ ወይም በአቅራቢያው፣ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እና ለሲድኒ ሪግደን የተሰጠ ራዕይ። በዚህን ጊዜ ነቢዩ ከሞላ ጎደል በየቀኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተጠምዶ ነበር። ትርጉሙ የተጀመረው በሰኔ ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.) መባቻ ላይ ነበር፣ እናም ኦሊቨር ካውድሪ እና ጆን ዊትመር እንደ ጸሀፊ በመሆን አገልግለው ነበር። ለሌላም ስራ ስለተጠሩ፣ ስድኒ ሪግደን በመለኮታዊ ምርጫ ለነቢዩ እንደ ጸሀፊ በመሆን እንዲያገለግል ተጠርቶ ነበር (አንቀጽ ፳ን ተመልከቱ)። ከዚህ ራዕይ አስቀድሞ እንደተጻፈው፣ የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ እንዳሚገልጸው፣ “ በታህሳሥ ሲድኒ ሪግደን ከኦሀዮ ጌታን ለመጠየቅ መጣ፣ እናም ከእርሱ ጋርም ኤድዋርድ አብሮት መጥቶ ነበር።… ከእነዚህ ወንድሞች መድረስ ጥቂት ጊዜ በኋላ ጌታ ይህን ተናገረ።”
፩–፪፣ እንዴት ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች መሆን እንደሚችሉ፤ ፫–፯፣ ሲድኒ ሪግደን እንዲጠምቅ እና መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጥ ተጠርቷል፤ ፰–፲፪፣ ምልክቶች እና ታእምራት የሚሰሩት በእምነት ነው፤ ፲፫–፲፮፣ የጌታ አገልጋዮች በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ህዝብን ያሄዷቸዋል፤ ፲፯–፲፱፣ ጆሴፍ ስሚዝ የሚስጥራቱን ቁልፎች ይዟል፤ ፳–፳፩፣ የተመረጡት ዳግም ምጽአትን ይታገሳሉ፤ ፳፪–፳፯፣ እስራኤል ትድናለች።
፩ አልፋና ኦሜጋ፣ የመጀመሪያና የመጨረሻ፣ መንገዱም አንድ ዘለአለማዊ ዙሪያ የሆነው፣ ዛሬም፣ ትላንት እንዲሁም ለዘለአለም አንድ አይነት የሆነውን የጌታ አምላካችሁን ድምጽ አድምጡ።
፪ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ፣ እንዲሁም እኔ በአብ እንዳለሁ እርሱም በእኔ እንዳለ፣ እነርሱም በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ ለአለም ኃጢአቶች፣ እንዲሁም በእኔ ስም ለሚያምኑ ሁሉ የተሰቀልኩት የእግዚአብሔር ልጅ የሆንኩት እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ።
፫ እነሆ፣ እውነት፣ እውነት፣ ለአገልጋዬ ለስዲኒ እናገራለሁ፣ ስራዎችህን እና አንተን ተመልክቻለሁ። ጸሎቶችህን ሰምቻለሁ፣ እናም ለታላቅ ስራም አዘጋጅቼሀለሁ።
፬ ታላላቅ ነገሮችን ስለምታደረግ የተባረክ ነህ። እነሆ እንደ ዮሐንስ፣ በእኔ እና ከሚመጣው ኤልያስ በፊትም መንገድን እንድታዘጋጅ ተልከሀል፣ እና መላክህንም አላወክም።
፭ ለንሰሀ በውሀ ጠምቀሀል፣ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን አልተቀበሉም፤
፮ ነገር ግን አሁን በውሀ እንድታጠመቅ ትእዛዛትን እሰጥሀለሁ፣ እናም ልክ እንደ ጥንቶቹ ኃዋሪያት እጆችን በመጫን መንፈስ ቅዱስን ይቀበላሉ።
፯ እናም እንዲህም ይሆናል ሞኝነታቸውና አጸያፊ ስራቸው ለሁሉም ሰዎች አይን ግልጽ ስለሚሆን፣ በምድሩ ላይ፣ እንዲሁም በአህዛቦችም መካከል ታላቅ ስራ ይሆናል።
፰ እኔ እግዚአብሔር ነኝና፣ እናም ክንዴም አጭር አይደለም፤ እናም ተአምራትን፣ ምልክቶችን፣ እንዲሁም ድንቅ ስራዎችን በስሜ ለሚያምኑት ሁሉ አሳያለሁ።
፱ እና በእምነት በስሜ የሚጠይቁትም፣ ዲያብሎስን ያስወጣሉ፣ የታመሙትንም ይፈውሳሉ፤ እውሮች ብርሀናቸውን እንዲያገኙ፣ ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፣ እናም ዱዳዎች እንዲናገሩ፣ እናም ሽባዎች እንዲራመዱ ያደርጋሉ።
፲ እናም የሰዎች ልጆች ታላላቅ ነገሮችን እንዲያዩ የሚደረጉበት ጊዜ በቶሎ ይመጣል፤
፲፩ ነገር ግን የዝሙቷን ቁጣ ወይን ጠጅ ህዝብ እንዲጠጡ ካደረገችው ባቢሎን ጥፋት በስተቀር፣ ያለእምነት ምንም ነገር እንዲታይ አይደረግም።
፲፪ እናም ለዚህ ትውልድ የላኩትን የወንጌሌን ሙላት ለመቀብል ከተዘጋጁት በስተቀር፣ መልካምን የሚያድርጉ የሉም።
፲፫ ስለዚህ፣ በመንፈሴ ኃይል ህዝብን እንዳውቃቸው ያልተማሩትን እና የተናቁትን፣ የአለም ደካማ ነገሮችን እጠራለሁ።
፲፬ እናም ክንዳቸው የእኔ ክንድ ይሆናል፣ እናም ጋሻና መከታ እሆናቸዋለሁ፤ እናም ወገባቸውን አስርላቸዋለሁ፣ እናም ለእኔ በወንድነትም ይዋጋሉ፤ ጠላቶቻቸው ከእግሮቻቸው ስር ይሆናሉ፤ ሰይፉንም ስለእነርሱ እሰነዝራለሁ፣ እናም በንዴቴም እሳት እጠብቃቸዋለሁ።
፲፭ እናም ለድሆች እና ትሁቶች ወንጌል ይሰበክላቸዋል፣ እናም የምጽአቴንም ጊዜ ይጠባበቃሉ፣ ይህም ተቃርቧልና—
፲፮ እናም አሁን የበጋም ወቅት ስለተቃረበ፣ የበለሱን ዛፍ ምሳሌ ትምህርት ይማራሉ።
፲፯ እናም የወንጌሌን ሙላት በአገልጋዬ በጆሴፍ እጅ ልኬአለሁ፤ እናም በድክመቱም ባርኬዋለሁ፤
፲፰ እናም የታተሙትን የሚስጥራቱን ቁልፎች፣ እንዲሁም አለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ያሉትን ነገሮች፣ እናም በእኔ የሚያምን ከሆነ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከእኔ ምጽአት ድረስ የሚመጡትን ነገሮች ሰጥቼዋለሁ፣ የማያምን ከሆነ በእርሱ ምትክ ሌላ ሰው አደርጋለሁ።
፲፱ ስለዚህ፣ ከእምነቱ እንዳይሰናከል ጠብቀው፣ እናም ሁሉንም ነገሮች በሚያውቀው በአጽናኙ በመንፈስ ቅዱስ ይህም ይሰጣል።
፳ እናም ለእርሱም እንድትጽፍ ትእዛዝን እሰጥሀለሁ፤ እናም በልቤ ውስጥ ያሉትን ቅዱሳን መጻህፍት እንኳን በእኔ ለተመረጡት መዳን ይሆን ዘንድ ይሰጣል።
፳፩ ድምጼንም ይሰማሉ፣ እኔንም ያያሉ፣ እናም እንቅልፍም አይተኙም፣ እናም የምጽአቴንም ቀን ይጠባበቃሉ፤ እኔም ንጽሁ እንደሆንኩት ሁሉ እነርሱም ንጹኃን ይሆናሉና።
፳፪ እናም አሁን ለአንተ እንዲህ እልሀለሁ፣ ከእርሱ ጋር ቆይ፣ እናም ከአንተ ጋርም ይጓዛል፤ አትተወው፣ እናም በእርግጥም እነዚህ ነገሮች ይፈጸማሉ።
፳፫ እስካልጻፋችሁ ድረስ፣ እነሆ፣ ለእርሱ እንዲተነብይ ይሰጠዋል፤ እና አንተም ወንጌሌን ትሰብካለህ እናም ለእርሱ በተሰጡ መጠን ቃላቶቹን ያረጋግጡ ዘንድ ቅዱሳን ነቢያትን ትጠቅሳለህ።
፳፬ የታሰራችሁበትን ትእዛዛት እና ቃልኪዳኖች ጠብቁ፤ እናም መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ሰማያትን አናውጣለሁ፣ እና ሰይጣንም ይንቀጠቀጣል እናም ፅዮንም በከፍታዎች ላይ ሀሴትን ታደርጋለች እናም ታብባለች፤
፳፭ እና እስራኤልም በእኔ ጊዜ ትድናለች፤ እናም በሰጠሁት ቁልፎችም ይመራሉ፤ እናም ከአሁን በኋላ በፍጹምም አያፍሩም።
፳፮ ልባችሁን አቅኑ ሀሴትንም አድርጉ፣ መዳናችሁ ቀርቧልና።
፳፯ እናንት ትንንሽ መንጎች፣ አትፍሩ፣ እስከምመጣ ድረስ መንግስቱ የእናንተ ነው። እነሆ፣ በቶሎም እመጣለሁ። እንዲህም ይሁን። አሜን።