ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፴፰


ክፍል ፴፰

ጥር ፪፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.) በፈየት፣ ኒው ዮርክ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት የተሰጠ ራዕይ። ወቅቱ የቤተክርስቲያን ጉባዔ የሚካሄድበት ነበር።

፩–፮፣ ክርስቶስ ሁሉን ነገሮች ፈጠረ፤ ፯–፰፣ እርሱም በቅርብ በሚያዩት በቅዱሳኑ መካከል ነው፤ ፱–፲፪፣ ሁሉም ስጋ በእርሱ ፊት በስባሽ ነው፤ ፲፫–፳፪፣ ለጊዜአዊ እና ለዘለአለም የሚሆን የቃል ኪዳን ምድርን ለጻድቃኖቹ አስቀምጧል፤ ፳፫–፳፯፣ ቅዱሳን አንድ እንዲሆኑ እና እርስ በራሳቸው እንደ ወንድም እንዲተያዩ ታዘዋል፤ ፳፰–፳፱፣ የጦርነቶች ትንቢቶች ተነግረዋል፤ ፴–፴፫፣ ቅዱሳን ከላይ ስልጣን ይሰጣቸዋል እናም በሁሉም ህዞቦች መካከልም ይሄዳሉ፤ ፴፬–፵፪፣ ቤተክርስቲያኗ ድሆችን እና የተቸገሩን እንድትንከባከብ እና ዘለአለማዊ ሀብትን እንድሻ ታዛለች።

ጌታ አምላካቹ፣ እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ታላቁ እኔ ነኝ፣ አልፋ እና ኦሜጋ፣ የመጀመሪያው እና የመጨረሻው፣ አለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ ዘለአለማዊነትን እና ሁሉን የሰማይ ሱራፌላዊ ሰራዊትን የተመለከተው እንዲህ ይላል፤

ሁሉንም ነገሮች የሚያውቀው እንዲህ ይላል፣ ምክንያቱም ሁሉም ነገሮች በአይኖቼ ፊት ናቸውና፤

የተናገርኩትም እኔ ነኝ፣ እናም አለም በእኔ ሆነ፣ እናም ሁሉም ነገሮች በእኔ መጡ።

የሔኖክን ፅዮን ወደ እቅፌ የወሰድኩ እኔው ነኝ፤ እናም እውነት፣ እላለሁ፣ በስሜ የሚያምኑ ሁሉ፣ እኔ ክርስቶስ በመሆኔ፣ በስሜ፣ ባፈሰስኩት ደም ምክንያት በአብ ፊት አማልጃቸዋለሁ።

ነገር ግን እነሆ፣ በምድር ዳርቻ በሚመጣው እስከ ታላቁ ፍርድ ቀን ድረስ የቀሩትን ኃጢአተኞች በጨለማ ሰንሰለት ውስጥ አስቀምጫቸዋለሁ።

እናም ድምጼን የማይሰማው እና ግን ልባቸውን የሚያደነድኑት ጥፋተኞች እንዲሁ እንዲቀመጡ አደርጋለሁ፣ እናም ወዮላቸው ጥፋታቸው ይሆናል።

ነገር ግን እነሆ፣ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ አይኖቼም በእናንተ ላይ ናቸው። እኔም በመካከላችሁ ነኝ እናም እናንተም አታዩኝም፤

ነገር ግን የምታዩኝም ቀን በቶሎ ይመጣል፣ እናም እኔም እንደሆንኩ ታውቃላችሁ፤ የጨለማም መጋረጃም ይገፈፋል፣ እናም ያልነጻ እርሱ ቀኑን አይቋቋምም

ስለዚህ፣ ወገባችሁን ታጠቁ እናም ተዘጋጁ። እነሆ፣ መንግስትም የእናንተ ናት፣ እናም ጠላትም አይቋቋማችሁም።

እውነት እላችኋለሁ፣ ንጹሐን ናችሁ፣ ነገር ግን ሁላችሁም አይደላችሁም፤ እናም ከእናንተ ሌላ የተደሰትኩበት ማንም የለም፤

፲፩ በፊቴ ሁሉም ስጋ በስባሽ ነው፤ እናም በምድር ላይ፣ በሰው ልጆች መካከል፣ እና በሁሉም የሰማይ ሰራዊት ፊት የጭለማው ሀይል እያሸነፈ ነው—

፲፪ ይህም ዝምታ እንዲነግስ አደረገ፣ እናም ዘለአለማዊውም ሁሉ ተጎድቷል፣ እናም መላእክትም ገለባውን ሰብስበው እንዲያቃጠሉ ምድርን የሚሰበስቡበትን ታላቁን ትእዛዝ እየጠበቁ ናቸው፤ እናም፣ እነሆ ጠላትም ተባብሯል።

፲፫ እናም አሁን በጊዜ ሂደትም ጥፋታችሁ እንዲፈጸም፣ እልፍኝ ውስጥ ተቀምጦ የነበረውን አንድ ሚስጥርም አሳያችኋለሁ፣ እናም እናንተም አላወቃችሁትም፤

፲፬ ነገር ግን ይህን ለእናንተ እናገረዋለሁ፣ እና እናንተም የተባረካችሁት በኃጢአታችሁ ወይም በልባችሁ አለማመን ምክንያት አይደለም፤ አንዳንዶቻችሁ በፊቴ ጥፋተኞች ብትሆኑም፣ ነገር ግን ለድክመታችሁ ምህረትን አደርጋለሁ።

፲፭ ስለዚህ፣ ከአሁን ጊዜ ጀምሮ ብርቱዎች ሁኑ፤ አትፍሩ፣ መንግስተ ሰማይ የእናንተ ናትና።

፲፮ እናም ለደህንነታችሁ ትእዛዝን እሰጣችኋለሁ፣ ጸሎታችሁንም ሰምቻለሁና፣ እናም ድሆችም በፊቴ አጉረምርመዋል፣ እናም ባለጠጎችንም የሰራኋቸው እኔው ነኝ፣ ስጋ ለባሽ ሁሉ የእኔ ነው፣ እኔም ለማንም አላደላም

፲፯ እናም ምድርን ባለጸጋ እንድትሆን አድርጌአለሁ፣ እናም እነሆ የእግሬ መረገጫ ናት፣ ስለዚህም ዳግምም እቆምባታለሁ።

፲፰ እናም ጌታ በሚመጣበት ጊዜ እርግማን የሌለበትን ማር እና ወተት የሚፈስበትን እንዲሁም የቃል ኪዳንን ምድር፣ ከሁሉም በላይ ታላቅ የሆኑትን ሀብቶች፣ እሰጣችሁ ዘንድ እጄን እዘረጋለሁ እናም ይህም ይሆን ዘንድ ፍቃዴ ነው።

፲፱ እናም በሙሉ ልባችሁ የምትሹ ቢሆን የምትወርሱት ምድር እንዲሆን እስጣችኋለሁ።

እናም ይህም ከእናንተ ጋር ቃልኪዳኔ ይሆናል፣ ለዘለአለም፣ ምድርም እስከቆመች ድረስ፣ ይህ ለእናንተ ውርስ ምድር እናም ለልጆቻችሁም የውርስ ይሆንላችኋል፣ እናም ደግሞም ለዘለአለም ዳግም ላያልፍ የእናንተ ይሆናል።

፳፩ ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ በዚያን ጊዜ ንጉስም ሆነ ገዢ አይኖራችሁም፣ እኔ ንጉሳችሁ እሆናለሁ እናም እጠብቃችኋለሁና።

፳፪ ስለዚህ፣ ድምጼን ስሙና ተከተሉኝ፣ እናም ነፃ ህዝብም ትሆናላችሁ፣ እናም እኔ በምመጣበት ጊዜ ከእኔ ህግ በስተቀር ሌሎች ሕጎች አይኖሯችሁም፣ ህግን የምሰጣችሁ እኔ ነኝና፣ እናም እጄንስ ምን ያግደዋል?

፳፫ ነገር ግን፣ እላችኋለሁ፣ በሾምኳችሁ ስልጣን መሰረት እርስ በርስ ተማማሩ

፳፬ እናም እያንዳንዱ ሰው ወንድሙን እንደራሱ ይመልከት፣ እናም በፊቴ መልካምነትን አና ቅድስናን ተለማመዱ።

፳፭ እናም ዳግም እላችኋለሁ፣ ሁሉም ሰው ወንድሙን እንደራሱ ይመልከት።

፳፮ ከእናንተ መካከል አስራ ሁለት ልጆች ኖሮት፣ እነርሱም በታዛዥነት እያገለገሉት፣ እናም ለአንዱ፥ ያማረ ልብሰ ለብሰህ እዚህም ተቀመጥ፤ ለሌላኛውም፥ ብጣሽ ልብስ ለብሰህ እዚህ ተቀመጥ በማለት በእነርሱ ላይ አድሎን የሚያደርግ ማን ሰው በመካከላችሁ አለ—እናም ልጆቹን ተመልክቶ እኔ ፍትሀዊ ነኝ የሚል ማን ነው?

፳፯ እነሆ፣ ይህን ለእናንተ እንደምሳሌ ሰጠኋችሁ፣ እናም እኔም እንዲሁ ነኝና። እንዲህ እላችኋለሁ፣ አንድ ሁኑ፤ እናም አንድ ካልሆናችሁ የእኔ አይደላችሁም።

፳፰ እናም ዳግም፣ ጠላትም በተሰውረ ስፍራ ሆኖ ሕይወታችሁን ይፈልጋል እላችኋለሁ።

፳፱ ሩቅም ከሆኑ ሀገሮች ጦርነትን ትሰማላችሁ፣ እናም ሩቅ ባሉ ሀገራትም ታላቅ ጦርነት በቅርቡም ይሆናል ትላላችሁ፣ ነገር ግን በምድራችሁ የሚገኙትን ህዝብ ልብ አታውቁም።

በጸሎቶቻችሁ ምክንያት እነዚህ ነገሮችን እነግራችኋለሁ፤ ስለዚህ በልባችሁ ጥበብን አከማቹ፣ አለበለዚያ የሰዎች ኃጢአት መሬትን በሚነቀንቅ እና ከፍ ባለ ድምጽ በጆሮቻችሁ በመናገር፣ በኃጢአታቸው እነዚህ ነገሮች እንዲገለጡ ያደርጉላችኋል፤ ነገር ግን ከተዘጋጃችሁ ፍርሀት አይኖራችሁም።

፴፩ እናም የጠላትን ኃይል ታመልጡ ዘንድ፣ እናም እንከን የሌላችሁ እና ያልነቀፉ ጻድቅ ህዝብ በመሆን ትሰበሰቡ ዘንድ—

፴፪ ሰለዚህ፣ በዚህም ምክንያት ወደ ኦሀዮ እንድትሄዱ ትእዛዛትን ሰጠኋችሁ፤ በዚያም ህጌን እሰጣችኋለሁ፤ እና በዚያም ከላይ የሚመጣ ኃይል ትቀበላላችሁ

፴፫ እናም ከዚያም ስፍራ፣ ፍቃዴ የሆነላቸው በሁሉም ህዝብ መካከል ይሄዳሉ፣ እና ምን እንደሚያደርጉም ይነገራቸዋል፤ ያስቀመጥቁት ታላቅም ስራ አለኝና፣ እስራኤልም ትድናለችና፣ እና ወደምፈልግበትም ስፍራ እመራቸዋለሁ፣ እናም እጄን ምንም ኃይል አያግደውም

፴፬ እናም አሁን፣ በዚህ ስፍራ ለምትገኘው ቤተክርስቲያን የተወሰኑ ሰዎች በመካከላቸው እንዲሾሙ ትእዛዝን እሰጣለሁ፣ በቤተክርስቲያኗም ድምጽ ይሾማሉ፤

፴፭ ድሆችን እና ችግረኞችን ይንከባከባሉ፣ እንዳይሰቃዩም በሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ያገልግሏቸዋል፤ ወደ አዘዝኳቸውም ስፍራ እልካቸዋለሁ፤

፴፮ እናም የዚህች ቤተክርስቲያን ንብረት ጉዳይ ማስተዳደርም የእነርሱ ስራ ይሆናል።

፴፯ እናም ሊሸጥ የማይቻል የእርሻ ስፍራዎች ያሏቸው፣ መልካም እንደመሰላቸው ያከራዩት ወይም እንዲተዉ ያድርጉ።

፴፰ ሁሉም ነገሮች ተጠብቀው ያሉ መሆናቸውን አረጋግጡ፤ እናም ሰዎች ከላይ መንፈሳዊ ስጦታ ሲሰጣቸውና ወደፊትም ሲላኩ፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በቤተክርስቲያኗ እቅፍ ውስጥ ይሰበሰባሉ።

፴፱ እናም አብ ሊሰጣችሁ የፈቀደውን ሀብት ከፈለጋችሁ፣ ከሁሉም ሰዎች በላይ ባለጠጋም ትሆናላችሁ፣ የዘለአለም ሀብትም ይኖራችኋልና፤ እናም እሰጣቸው ዘንድ የምድር ሀብት ሁሉ የእኔ ነው፤ ነገር ግን ከኩራት ተጠበቁ፣ አለበለዚያም እንደ ጥንቶቹ ኔፋውያን ትሆናላችሁ።

እናም ደግሞም፣ እላችኋለሁ፣ እያንዳንዱ ሰው፣ ሽማግሌው፣ ካህኑ፣ መምህሩ፣ እንዲሁም አባል ያዘዝኩትን፣ ባለው ሀይል ሁሉ እየተጓዘ በእጆቹ ስራዎች፣ እንዲዘጋጅ እና እንዲያከናውን ትእዛዛትን እሰጣችኋለሁ።

፵፩ እናም እያንዳንዱ ሰው ለባልጀራው በደግነት እና በትህትና ሆኖ፣ ስብከታችሁም የማስጠንቀቂያ ድምጽ ይሁን።

፵፪ እናም ከኃጢአተኞችም መካከል ውጡ። ራሳችሁን አድኑ። የጌታን ዕቃ የምትሸከሙ ንፁሀን ሁኑ። እንዲህም ይሁን። አሜን።