ክፍል ፻፱
በመጋቢት ፳፯፣ ፲፰፻፴፮ (እ.አ.አ.) በክርትላን ኦሀዮ ቤተመቅደስ ቅደሳ የቀረበ ጸሎት። በነቢዩ ፅሁፍ መሰረት፣ ይህ ጸሎት የተሰጠው በራዕይ ነበር።
፩–፭፣ የከርትላንድ ኦሀዮ ቤተመቅደስ የተገነባው የሰው ልጅ የሚጎበኘው ስፍራ እንዲሆን ነው፤ ፮–፳፩፣ የጸሎት፣ የጾም፣ የእምነት፣ የመማሪያ፣ የክብር፣ እና የስርዓት ቤት፣ እና የእግዚአብሔር ቤት ይሁን፤ ፳፪–፴፫፣ የጌታን ህዝብ የሚቃወሙ ንስሀ ያልገቡት ዝም ይበሉ፤ ፴፬–፵፪፣ ቅዱሳን በሀይል ጻድቃንን ወደ ፅዮን ለመሰብሰብ ይሂዱ፣ ፵፫–፶፫፣ በመጨረሻው ቀን በክፉዎች ላይ ከሚፈሰው መጥፎ ነገሮች ቅዱሳን ይዳኑ፤ ፶፬–፶፰፣ ሀገሮች፣ ህዝብና ቤተክርስቲያናት ለወንጌሉ ይዘጋጁ፤ ፶፱–፷፯፣ አይሁዶች፣ ላማናውያን፣ እና እስራኤል ሁሉ ይዳኑ፤ ፷፰–፹፣ ቅዱሳን በክብር የክብርን አክሊል ይጫኑ እና ዘለአለማዊ ደህንነትንም ያግኙ።
፩ ቃል ኪዳንን የሚጠብቁትንና በልቦቻቸው ሙላት በቅንነት በፊትህ የሚሄዱት አገልጋዮችህን ምህረት የምታሳየው የእስራኤል ጌታ አምላክ ሆይ፣ ለስምህ ምስጋና ይሁን—
፪ በዚህ ስፍራ (ከርትላንድ) ውስጥ በስምህ ቤት እንዲገነቡ አገልጋዮችህን ያዘዝህ ሆይ።
፫ አሁንም ጌታ ሆይ፣ አገልጋዮችህ ባዘዝኸው መሰረትም እንዳደረጉ ትመለከታለህ።
፬ አሁንም ቅዱስ አባት ሆይ፣ በስሙ ብቻ ደህንነት ለሰው ልጆች በሚሰጠው በእቅፍ ባለው ልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንጠይቅሀለን፣ ጌታ ሆይ እንድንገነባው ያዘዝከውን ይህን ቤት፣ የእኛ የአገልጋዮችህ እጆች ስራን ትቀበል ዘንድ እንጠይቅሀለን።
፭ ይህን ስራ በታላቅ ስቃይ ዘመን እንደሰራነው ታውቃለህ፤ እና ለስምህ ቤት ለመስራት፣ የሰው ልጅ ለህዝቦቹ እራሱን የሚያሳይበት ስፍራ ይኖረው ዘንድ፣ ከድህነታችን እቃዎቻችንን ሰጥተናል።
፮ እና ባልንጀሮች ብለህ ጠርተኸን እንዲህ በማለት በሰጠኸን ራዕይ እንዳልከው፣ እንዳዘዝኳችሁ የክብር ስብሰባን ጥሩ፤
፯ እና ሁላችሁም እንደ እምነታችሁ፣ ተግታችሁ ፈልጉ እና እርስ በርስም የጥበብን ቃላት ተማማሩ፤ አዎን፣ ከምርጥ መፅሐፎች ውስጥ የጥበብ ቃላትን ፈልጉ፣ ትምህርትንም ፈልጉ፣ እንዲሁም በጥናትና ደግሞም በእምነት ይሁን፤
፰ ራሳችሁን አደራጁ፤ ለእያንዳንዱ አስፈላጊ ነገሮችም ተዘጋጁ፣ እና ቤት፣ እንዲሁም የጸሎት ቤት፣ የጾም ቤት፣ የእምነት ቤት፣ የመማሪያ ቤት፣ የክብር ቤት፣ የስርዓት ቤት፣ የእግዚአብሔርን ቤት መስርቱ፤
፱ መግባታችሁ በጌታ ስም ይሆን ዘንድ፣ መውጣታችሁም በጌታ ስም ይሆን ዘንድ፣ ወደ ልኡል እጆቻችሁን ከፍ በማድረግ ሰላምታዎቻችሁም በጌታ ስም እንዲሆን—
፲ አሁንም፣ ቅዱስ አባት፣ የክብር ስብሰባችንን ስንጠራ፣ በክብርህ እና በአንተ መለኮታዊ መስማማት ይደረግ ዘንድ፣ እኛን ህዝብህን በጸጋህ እንድትረዳን እንጠይቅሀለን፤
፲፩ እና በዚህም ለእኛ ለህዝብህ በተሰጠን ራእዮች የገባህልን ቃል ኪዳኖች የሚሟሉበትንም ለማግኘት በፊትህ በብቃት እንድንገኝም፤
፲፪ ቅዱስ እንዲሆን እንዲቀደስና ለስዕለትም ይገባ ዘንድ፣ ቅዱስ ፊትህ በዚህ ቤት ውስጥ ሁልጊዜም ይገኝ ዘንድ፣ ክብርህ በህዝብህ ላይ እና ለአንተ በምንቀድሰው በዚህ በቤትህ ላይም ያርፍ ዘንድ፤
፲፫ እና በጌታ ቤት መግቢያ በር ላይ የሚገቡት ህዝብ ሁሉ ሀይልህ እንዲሰማቸው፣ እና እንደቀደስከውም፣ ይህም ቤትህ፣ የቅድስናህ ስፍራ እንደሆነም በማወቅ ይሰማቸው ዘንድ።
፲፬ እና ቅዱስ አባት ሆይ በዚህ ቤት የሚያመልኩት ሁሉ የጥበብን ቃላት ከምርጥ መፅሀፍት ውስጥ ይማሩ ዘንድ፣ እና ትምህርትንም ይሹ ዘንድ፣ እንዲሁም አንተ እንዳልከው በጥናት፣ እና ደግሞም በእምነት፣ ይሆን ዘንድ ፍቀድልን፤
፲፭ እና በአንተም እንዲያድጉ፣ እና የመንፈስ ቅዱስን ሙላት እንዲቀበሉ፣ እና በህግጋትህ መሰረት እንዲመሰረቱ፣ እና አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ ለመቀበል ይዘጋጁም ዘንድ፤
፲፮ እና ይህም ቤት የጸሎት ቤት፣ የጾም ቤት፣ የእምነት ቤት፣ የክብር እና የእግዚአብሔር ቤት፣ እንዲሁም የአንተ ቤት ይሆን ዘንድ፤
፲፯ የህዝብህን ወደዚህ ቤት መግባታቸውም በጌታ ስም ይሆን ዘንድ፤
፲፰ ከዚህ ቤት መውጣቸው በጌታ ስም ይሆን ዘንድ፤
፲፱ እና ሰላምታቸውም ሁሉ፣ ወደ ልዑል ከፍ በተዘረጉ በቅዱስ እጆች በጌታ ስም ይሆን ዘንድ፤
፳ እና ምንም ምንም እርኩስ ነገር ወደቤትህ ውስጥ እንዲገባ ተፈቅዶለት እንዳያቆሽሸው ዘንድ፤
፳፩ እና ማናቸውም ህዝብህ ሲተላለፉም፣ ወዲያው ንስሀ እንዲገቡና ወደ አንተ እንዲመለሱ፣ እና በፊትህም ሞገስን እንዲያገኙ፣ እና በቤትህ ለሚያከብሩህ ሁሉ እንዲፈስ ለመደብካቸው በረከቶች ደግመው እንዲመለሱም ዘንድ እንጠይቅሀለን።
፳፪ እና ቅዱስ አባት ሆይ፣ አገልጋዮችህ ከዚህ ቤት በሀይልህ ይታጠቁ ዘንድ፣ እና ስምህም በእነርሱ ላይ እንዲሆን፣ እና ክብርህም በዙሪያቸው፣ እና መላእክትህም ይጠብቋቸው ዘንድ እንጠይቅሀለን፤
፳፫ እና ከዚህም ስፍራ፣ በእውነት፣ በጣም ታላቅ እና የክብር ዜና ወደ ምድር ዳርቻዎች እንዲወሰድ፣ ይህም ያንተ ስራ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ፣ እና ስለመጨረሻዎቹ ቀናት በነቢያትህ አንደበት የተናገርካቸው እንዲሟሉ እጅህን ትዘረጋም ዘንድ እንጠይቅሀለን።
፳፬ ቅዱስ አባት ሆይ፣ የሚያመልኩህን እና በቤትህ ለሁሉም ትውልዶች እና ለዘለአለም የተከበረ ስም እና ቋሚነት የያዙ ህዝብን እንድትመሰርት እንጠይቅሀለን፤
፳፭ በእነርሱም ላይ የሚሰራ ምንም መሳሪያ እንዳይከናወን፣ ጉድጓድ የሚቆፍረውም በዚያው ውስጥ ይወድቅ ዘንድ፤
፳፮ በዚህ ቤት ውስጥ ስምህን በሰጠሀቸው ህዝብህ ላይ ምንም የክፋት ሴራ እንዳይነሳና እንዳይሰለጥን፤
፳፯ እና በዚህ ህዝብ ላይ ማንም ህዝብ ቢነሳባቸው፣ ቁጣህ በእነርሱ ላይ ይቀጣጠል ዘንድ፤
፳፰ እና ይህን ህዝብ ቢመቱም አንተ እንድትመታቸው፣ ከጠላቶቻቸው እጆች ይድኑም ዘንድ፣ በጦርነት ቀን እንዳደረከው ለህዝብህ እንድትዋጋ እንጠይቅሀለን።
፳፱ ቅዱስ አባት ሆይ፣ በአለም ሁሉ በአገልጋይህ ወይም አገልጋዮችህ ላይ የሀሰት ዘገባ የሚያባዙትን ሁሉ፣ ዘለአለማዊው ወንጌልም በጆሮዎቻቸው ውስጥ ሲታወጅ ንስሀ ባይገቡ፣ ታሳፍራቸው፣ እና ታስደንቃቸው፣ እና ውርደትንና ግራ መጋባትንም ታመጣባቸው ዘንድ እንጠይቅሀለን፤
፴ እና ስራዎቻቸውም ሁሉ ከንቱ ይሆኑ ዘንድ፣ ከቁጣህም የተነሳ በሚመጣባቸው በበረዶና በቁጣህ ፍርድ ይጠረጉ ዘንድ፣ በህዝብህም ላይ የተነሳው ሀሰት እና ስም ማጥፋት ማብቂያ ይኖረው ዘንድም እንጠይቅሀለን።
፴፩ ጌታ ሆይ፣ ለእነዚህ ነገሮች የተሰቃዩት አገልጋዮችህ ስለአንተም ስም በመመስከር በፊትህ ንጹሀን እንደሆኑ ታውቃለህና።
፴፪ ስለዚህ ከዚህ ቀንበር ለሙሉና ፍጹም ደህንነት እንለምንሀለን፤
፴፫ ጌታ ሆይ፣ ስበረው፣ በዚህ ትውልድ መካከል እንድንነሳ እና ስራህንም እንሰራ ዘንድ፣ ከአገልጋዮችህ አንገት በሀይልህ ስበረው።
፴፬ ያህዌህ ሆይ፣ ምህረትህ በህዝብህ ላይ ምህረት ትሁን፣ እና ሁሉም ሰዎች ኃጢአትን ስለሚሰሩም፣ የህዝብህን መተላለፍ ይቅር በል፣ እና ለዘለአለምም ይደምሰስ።
፴፭ የአገልጋዮችህ ቅባትም ከላይ በሆነው ሀይልህም ይታተምባቸው።
፴፮ በበአለ ሀምሳ ቀን በነበሩት ላይ እንደደረሰም፣ በእነርሱም ላይ ይሁን፤ የልሳኖች፣ እንዲሁም በእሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች፣ እነርሱም የመተርጎም ስጦታ በህዝብህ ላይ ይፍሰስ።
፴፯ እና ቤትህም በድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ በክብርህ ይሞላ።
፴፰ ሲወጡና ቃልህን ሲያውጁ ህግን ለማተም እንዲችሉ፣ በቁጣህ በምድር ኗሪዎች ላይ በመተላለፋቸው ምክንያት በምታመጣቸው ፍርዶች ሁሉ የቅዱሳንህን ልብ ያዘጋጁ ዘንድ፣ ህዝብህም በመከራ ቀን እንዳይደክሙ የቃል ኪዳንህ ምስክርነት በአገልጋዮችህ ላይ ይረፍ።
፴፱ እና አገልጋዮችህ በሚገቡበት በማንኛውም ከተማ፣ እና በዚያም ከተማ ምስክርነታቸውን ህዝብ ቢቀበሉት፣ በፅድቅ ከዚያ ከተማ ተሰብስበው ይወጡ ዘንድ፣ ወደ ፅዮንም ወይም አንተ ወደ ወሰንክላቸው ስፍራዎች በዘለአለማዊ ደስታ መዝሙር ወደ ስቴኳ ይመጡ ዘንድ፣ ሰላምና መድሀኒትህ በዚያ ከተማ ላይ ይሁን፤
፵ እና ይህም እስኪከናወን ድረስ፣ በዚያ ከተማ ላይ ፍርድህ አይውደቅበት።
፵፩ አገልጋዮችህ የሚገቡበት በማንኛውም ከተማ፣ እና በዚያም ከተማ የአገልጋዮችህን ምስክርንት ህዝብም ባይቀበሉት፣ ከዚህ ጠማማ ትውልድ ወደፊት ራሳቸውን እንዲያድኑ አገልጋዮችህ ቢያስጠነቀቋቸው፣ በነቢያትህ አንደበት በተናገርከው መሰረት በዚያ ከተማ ላይ ይሁን።
፵፪ ነገር ግን ያህዌህ ሆይ፣ አገልጋዮችህን ከእጆቻቸው ታድናቸውና ከደማቸው ታነጸቸው ዘንድ እንለምንሀለን።
፵፫ ጌታ ሆይ፣ በሰዎች ጥፋት አንደሰትም፤ ነፍሶቻቸውም በፊትህ የከበሩ ናቸው።
፵፬ ነገር ግን ቃልህ መፈጸም አለበት። በጸጋ እየተረዱ አገልጋዮችህ እንዲህ እንዲሉ እርዳቸው፥ ጌታ ሆይ፣ የአንተ ፈቃድ እንጂ የእኛ አይሁን።
፵፭ ቁጣህን ያለልክ እንድታወርድ—በመጨረሻዎቹ ቀናት፣ ስለክፉዎች በሚመለከት በነቢያትህ አንደበት ብዙ አስፈሪ ነገሮች ተናግረሀልና፤
፵፮ ስለዚህ፣ ጌታ ሆይ፣ ህዝብህን ከክፉዎች አሰቃቂ አደጋ አድናቸው፤ በመቃጠል ቀን ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ዘንድ፣ አገልጋዮችህ ህግን እንዲያትሙና ምስክርነትንም እንዲያስሩ አስችላቸው።
፵፯ ቅዱስ አባት፣ በሚዙሪ በጃክሰን የግዛት ክፍል ውስጥ፣ ከውርስ መሬቶቻቸው የተባረሩትን አስታውስ፣ እና ጌታ ሆይ፣ ይህን በእነርሱ ላይ የተደረገውን የስቃይ ቀንበር ስበረው።
፵፰ ጌታ ሆይ፣ በክፉ ሰዎች በጣም ተበድለዋል እናም ተሰቃይተዋል፤ እና እነርሱ በተሸከሙት አስቸጋሪ ሸከም ምክንያት ልባችን በሀዘን ተሞልቷል።
፵፱ ጌታ ሆይ፣ ይህን ስቃይ እንዲሸከሙ፣ እና የየዋሆቻቸውም ለቅሶ ወደ ጆሮዎችህ እንዲመጡ፣ እና ደማቸውም በፊትህ ምስክር በመሆን እንዲመጣ የምትፈቅደው፣ እና ለእነርሱም ምስክርነትህን የማታሳየውስ እስከመቼ ነው?
፶ ጌታ ሆይ፣ ጥፋታቸውን ያቆሙ ዘንድ፣ ንስሀ መግባት የሚቻላቸውም ቢሆን ለኃጢአታቸው ንስሀ ይገቡ ዘንድ፣ ህዝብህን በሚያሳድዱ ክፉ አመጸኛ ቡድኖች ላይ ምህረትህን አኑር፤
፶፩ ነገር ግን ይህን የማያደርጉ ቢሆን፣ ጌታ ሆይ፣ ክንድህን ግለጥ እና ለህዝብህም በፅዮን የመደብከውን አድን።
፶፪ እና ይህም ባይሆን፣ የህዝብህ ተግባራቸው እንዳይወድቅ፣ ከሰማይ በታች ሥርና ቅርንጫፍም ይባክን ዘንድ ንዴትህ ይቀጣጠል፣ እና ቁጣህም ይውረድባቸው፤
፶፫ ነገር ግን ንስሀ እስከገቡ ድረስ ግን፣ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህ፣ እና በአንተ የተቀቡትን ፊታቸውን ስትመለከት ቁጣህን ትመልሳለህ።
፶፬ ጌታ ሆይ፣ ምህረትህ በምድር ህዝብ ሁሉ ላይ ትሁን፤ በምድራችን መሪዎች ላይም ምህረት ትኑር፤ በአባቶቻችን በክብር እና በድንቅ የሚጠበቁት እነዚያ መሰረታዊ መርሆች፣ እንዲሁም የምድራችን ህገ መንግስት ለዘለአለም ይቋቋም።
፶፭ ንጉሶችን፣ ልኡሎችን፣ ባላባቶችን፣ እና የምድርን ታላቆች፣ እና ሁሉንም ህዝብ፣ እና ቤተክርስቲያናትን፣ ድሆችን ሁሉ፣ እርዳታ የሚሹትን፣ እና በምድር የሚሰቃዩትን አስታውስ፤
፶፮ ያህዌህ ሆይ፣ አገልጋዮችህ ስለስምህ ለመመስከር ከቤትህ የሚወጡትን ልባቸው ያሰላስል ዘንድ፣ ጥላቻቸውም በእውነት ፊት ይከሰም ዘንድ፣ እና ህዝብህም በሁሉም አስተያየት ሞገስን ያገኙ ዘንድ፤
፶፯ እኛ አገልጋዮችህ ድምፅህን እንደሰማን እና አንተ እንደላከንም የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያውቁ ዘንድ፤
፶፰ ከእነዚህም መካከል፣ አንተ እንዳዘዝካቸው፣ አገልጋዮችህ የያዕቆብ ልጆች ጻድቃንን በስምህ ቅዱስ ከተማን ለመገንባት ይሰበስቡም ዘንድ አስታውስ።
፶፱ የህዝብህ መሰባሰብ በታላቅ ሀይል ይቀጥል ዘንድ፣ ስራህም በፅድቅ በአጭር ይከናወን ዘንድ፣ አንተ ከመደብከው ከዚህ በላይ ሌላ ካስማ በፅዮን እንድትመሰርት እንጠይቅሀለን።
፷ ጌታ ሆይ፣ እንደ አህዛብ በተለየነው አንተ የሰጠኸንን ራዕዮች እና ትእዛዛት በመመልከት አሁን በፊትህ እነዚህን ቃላት ተናግረናል።
፷፩ ነገር ግን በጨፈገገ እና በጭለማ ቀን በተራራው ላይ ለተበተኑት ለያዕቆብ ልጆች ታላቅ ፍቅር እንዳለህ ታውቃለህ።
፷፪ ስለዚህ፣ ምህረት በያዕቆብ ልጆች ላይ ትሆን ዘንድ፣ ከዚህ ሰአት ጀምሮ ኢየሩሳሌምን ቤዛነት ትጀምር ዘንድ እንጠይቅሀለን፤
፷፫ እና የባርነትም ቀንበር ከዳዊት ቤት መሰበር እንዲጀምር፤
፷፬ እና የይሁዳ ልጆችም ለአባታቸው አብርሐም በሰጠኸው ምድር መመለስ እንዲጀምሩ እንጠይቅሀለን።
፷፭ እና በመተላለፋቸው ተረግመው እና ተመትተው የነበሩት የያዕቆብ ቅሪቶችም ከዱር እና ከአውሬነት ሁኔታቸው ወደ ዘለአለማዊ ወንጌል ሙላት እንዲቀየሩም አድርግ፤
፷፮ የደም ማፍሰስ መሳሪያዎቻቸውንም እንዲያስቀምጡ እና አመጻቸውንም ያቆሙ ዘንድ አድርግ።
፷፯ እና ወደ ምድር ዳርቻም የተበተኑት የእስራኤል ቅሪቶችም ወደ እውነት እውቀት ይምጡ፣ በመሲህም ይመኑ፣ እና ከመበደልም ይዳኑ፣ እና በፊትህም ይደሰቱ።
፷፰ ጌታ ሆይ፣ አገልጋይህን ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊን፣ እና ስቃዮቹን እና በደሎቹን ሁሉ—ከያህዌህ ጋር እንዴት ቃል ኪዳን እንደገባ፣ እና የያዕቆብ አምላክ ሆይ፣ ለአንተ መሀላ እንደገባ—እና የሰጠኸውን ትእዛዛት፣ እና ፈቃድህን ለማከናወን በቅንነት እንደሚጥር አስታውስ።
፷፱ ጌታ ሆይ፣ በባለቤቱ እና በልጆቹ ላይ፣ በፊትህ ዘለአለማዊ ክብር ይኖራቸው ዘንድ እና በሚታደገው እጅህ እንድታድናቸው ዘንድ ምህረትን አድርግ።
፸ ጥላቻቸው ይሰበር እና በጎርፍ ይጠረግ ዘንድ፣ ከእስራኤል ጋር እንዲለወጡና እንዲድኑ፣ እና አንተም አምላክ እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ በዘመዶቻቸው ላይም ምህረት አድርግ።
፸፩ ጌታ ሆይ፣ ፕሬዘደንቶችን፣ እንዲሁም የቤተክርስቲያንን ፕሬዘደንቶች፣ ቀኝ እጅህ ከቤተሰቦቻቸው ሁሉና ከዘመዶቻቸው ጋር ዘለአለማዊ ክብር ትሰጣቸው ዘንድ፣ ስሞቻቸውም ቀጣይ እንዲሆኑና ከትውልድ ወደ ትውልድ ለዘለአለምም ይታወሱ ዘንድ አስታውስ።
፸፪ ጌታ ሆይ፣ ቤተክርስቲያንህን ሁሉ፣ ከየቤተሰባቸው ጋር፣ እና ከዘመዶቻቸው ጋር፣ ከታመሙት እና ከሚሰቃዩት ሁሉ ጋር፣ ከምድር ድሀ እና ትሁታን ጋር አስታውስ፤ በእጆችህ የመሰረትከው መንግስትህ ታላቅ ተራራ እንዲሆንና ምድርንም ሁሉ ይሞላ ዘንድ አስታውስ፤
፸፫ ቤተክርስቲያንህ ከምድረበዳው ጭለማ ወጥታ እንደ ጨረቃ የጠራች እንድትሆን፣ እንደጸሀይም ያማረች እንድትሆን፣ እና ሰንደቅ ዓርማም እንደያዘ ሰራዊት የምታስፈራ ትሆን ዘንድ፤
፸፬ እና ሰማይን በምትገልጥበት፣ እና በፊትህም ተራሮች እንዲመጡ እና ሸለቆዎችም ከፍ እንዲሉ፣ ሸካራውም መንገድ የቀና እንዲሆን በምታደርግበት ቀን እንደ ሙሽራ እንድትለብስ፤ ክብርህም ምድርን ሁሉ ይሞላ ዘንድ፤
፸፭ ለሙታን መለከቱ ሲነፋ፣ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቅ ዘንድ፣ እንዲሁም ሁልጊዜም ከጌታ ጋር እንሆን ዘንድ፤
፸፮ ልብሶቻችን ንጹህ ይሆኑ ዘንድ፣ በእጆቻችንም የዘንባባንም ዝንጣፊዎች ይዘን፣ እና የፅድቅ ልብስ እንድንለብስ፣ እናም በራሳችንም የክብርን አክሊል ተጎናጽፈን፣ እና ለስቃዮቻችንም የዘለአለም ደስታ እናጭድ ዘንድ አስታውሰን።
፸፯ ጌታ ኤልሻዳይ ሆይ፣ በእነዚህ ያቀረብናቸውን ልመናችንን ውስጥ ስማን፣ እና በግርማ፣ በክብር፣ በሀይል፣ በስልጣን፣ በእውነት፣ በመፍትሄ፣ በፍርድ፣ በምህረት፣ እና በዘለአለም ሙላት፣ ከዘለአለም እስከ ዘለአለም በዙፋንህ ላይ ከምትቀመጥበት ከቅዱስ መኖሪያህ ሰማይም መልስ ስጠን።
፸፰ ጌታ ሆይ፣ አቤቱ አድምጠን፣ አቤቱ አድምጠን፣ አቤቱ አድምጠን! እና እነዚህ የምናቀርባቸውን ልመናዎቻችንን መልስ፣ እና በስምህ የገነባነውን፣ የእጆችህ ስራ የሆንነውን፣ የዚህንም ቤት ለአንተ መቀደስ ተቀበል፤
፸፱ ደግሞም ያንተን ስም ለመያዝ፣ ይህችንም ቤተክርስቲያን ተቀበል። እና ከዙፋንህ ዙሪያ ከሚገኙት ከደማቅ፣ አንጸባራቂ ሱራፌሎች ጋር በአድናቆት ምስጋና፣ ለአምላክ እና ለበጉ ሆሳዕና በመዘመር ድምጻችንን እናሰማ ዘንድ በመንፈስህ ሀይልም እርዳን!
፹ እነዚህ የተቀቡትም በደህንነት እንዲለብሱ፣ እና ቅዱሳንህም በደስታ እንዲጮሁ ፍቀድ። አሜን፣ እናም አሜን።