ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፲


ክፍል ፲

ምንም እንኳን ከፊሎቹን በበጋ ፲፰፻፳፰ (እ.አ.አ.) አካባቢ የተቀበላቸው ሳይሆን ባይቀርም፣ በሚያዝያ ፲፰፻፳፰ (እ.አ.አ.) አካባቢ በሀርመኒ፣ ፔንስልቬንያ፣ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ የተሰጠ ራዕይ። በዚህ ጌታ ክፉ ሰዎች ከመፅሐፈ ሞርሞን ትርጉም ፻፲፮ ገጽ የሌሒ መጽሐፍ የእጅ ጽሁፍ ላይ ስላደረጉት ለውጥ ለጆሴፍ ነገረው። እነዚህ የእጅ ጽሁፎች ለጊዜው በአደራ ተሰጥተውት ከነበረው ከማርቲን ሀሪስ እጅ ነበር የጠፉት። (የክፍል ፫ ዐርስትን ተመልከቱ።) የክፋት ዓላማውም በጠፉት ገጾች ላይ ያሉት እስኪተረጎሙ መጠበቅ እና በተለወጠው ነገር የተነሳ ትርጓሜው አመኔታን እንዲያጣ ለማደረግ ነበር። ይህ የክፋት ዓላማ በክፉው ተጠንስሶ ነበር እንዲሁም ሞርሞን የጥንቱ የኔፋውያን ባለ ታረክ ሰሌዳዎቹን አሳጥሮ እየጻፈ ሳለ በጌታ ይታወቅ እንደነበር በመፅሐፈ ሞርሞንም ውስጥ ይታያል (የሞርሞን ቃላት ፩፥ ፫–፯ን ተመልከቱ)።

፩–፳፮፣ የጌታን ስራ እንዲቃወሙ ክፉ ሰዎችን ሰይጣን ያነሳሳል፣ ፳፯–፴፫፣ እርሱም የሰዎችን ነፍስ ለማጥፋት ይሻል፣ ፴፬–፶፪፣ ወንጌል በመፅሐፈ ሞርሞን አማካይነት ለላማናውያን እና ለሁሉም ህዝብ ይዳረሳል፤ ፶፫–፷፫፣ ጌታ ቤተክርስቲያኑን እና ወንጌሉን በሰዎች መካከል ይመሰርታል፤ ፷፬–፸፣ የንስሀ ልብ ያላቸውን ወደ ቤተክርስቲያኑ ይሰበስባል እናም ታዛዦቹን ያድናል።

አሁን፣ እንዲህ፣ እልሀለሁ፣ በኡሪም እና ቱሚም አማካኝነት ለመተርጎም ኃይል የተሰጡህን ጽሁፎች ለክፉ ሰው እጅ አሳልፈህ በመስጠትህ አጥፍተሀቸዋል።

እናም ስጦታህንም አብረህ አጥተሀል፣ እናም አእምሮህ ጨልሟል።

ሆኖም፣ አሁን ዳግመኛ ተመልሶልሀል፤ ስለዚህ ታማኝ መሆንህን ተመልከት እናም እንደጀመርኸው የቀረውን የትርጉም ስራ ለመጨረስ ቀጥል።

ለመተርጎም እንዲያስችልህ ከተዘጋጀልህ ብርታት እና መንስዔ በላይ በፍጥነት አትሂድ ወይም አትስራ፤ ነገር ግን እስከመጨረሻው ትጉህ ሁን።

ድል ታደርግ ዘንድ፤ አዎን፣ ሰይጣንን ድል ታደርግ ዘንድ፣ እናም የእርሱን ስራ ከሚደግፉት የሰይጣን አገልጋዮች እጆች ታመልጥ ዘንድ ዘወትር ጸልይ

እነሆ፣ እነርሱ ሊያጠፉህ ፈልገዋል፤ ያመንከው ሰው እንኳን ሊያጠፋህ ፈልጓል።

እምነት የተጣሉብህን ነገሮች ለመውሰድ ስለፈለገ፤ እናም እንዲሁም ስጦታህን ለማጥፋት ስለፈለገ፣ ክፉ ሰው ነው ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው።

እናም ጽሑፎቹን በእጁ አሳልፈህ በመስጠትህ ምክንያት፣ እነሆ፣ ክፉ ሰዎች ከአንተ ወስደዋቸዋል።

ስለዚህ፣ አዎን፣ የተቀደሱትን፣ ለክፋት አሳልፈህ ሰጥተሀቸዋል።

እናም፣ እነሆ፣ እንዲጻፉ ያደረግሀቸውን ወይም አንተ የተረጎምካቸውን፣ ከእጅህ የወጡትን ጽሁፎች፣ እንዲለወጡ ሰይጣን ክፋትን በልባቸው ውስጥ አስቀምጧል።

፲፩ እናም እነሆ፣ እንዲህ እልሀለሁ፣ ቃላቶቹን በመለወጣቸው ምክንያት፣ ከተረጎምካቸው እና እንዲጻፉ ካደረካቸው ተጻራሪ የሆነን ነገር ያነባሉ፤

፲፪ እናም፣ በዚህ ምክንያት ዲያብሎስ ይህን ስራ ለማጥፋት የብልጠት ዕቅድ ለማሳካት ፈልጓል።

፲፫ ለመተርጎም አስመስለህ በነበሩት ቃላት ውስጥ ያዝንህ ብለው በሀሰት በመናገር፣ ይህንን እንዲያደርጉ በልባቸው ውስጥ አስቀምጧልና።

፲፬ እውነት፣ እልሀለሁ፣ ሰይጣን የክፋት እቅዱን እንዲያከናውን አልፈቅድም።

፲፭ እነሆም፣ ዳግም ለመተርጎም በመጠየቅ ጌታ አምላክህን እንድትፈትን በልባቸው ውስጥ ይህን አስቀምጧል።

፲፮ እናም ከዚያም፣ እነሆ፣ እግዚአብሔር ለመተርጎም ኃይልን እንደሰጠው እናያለን፤ ይህም ከሆነ ዳግም እንዲሁ ኃይልን ይሰጠዋል ይላሉ እናም በልባቸውም ይህንን ያስባሉ፤

፲፯ እናም ዳግም እግዚአብሔር ኃይልን የሚሰጠው ከሆነ፣ ወይም ዳግም የሚተረጉም ከሆነ፣ ወይም በሌላ አባባል፣ ዳግም አንድ አይነት ቃላት የሚያመጣ ከሆነ፣ እነሆ፣ ከእኛም ዘንድ እንዲህ አይነት አለን፣ እናም ለውጠናቸዋል፤

፲፰ ስለዚህም አይስማሙም፣ እናም በእነዚህ ቃላት ዋሽቷል፣ እናም ስጦታም የለውም፣ እናም ኃይልም የለውም እንላለን፤

፲፱ ስለዚህ እርሱንም እናም ደግሞ ስራውን እናጠፋለን፤ እናም ይህን የምናደርገው በመጨረሻ እንዳናፍር፣ እናም የአለምን ክብር እንድናገኝ ነው።

እውነት፣ እልሀለሁ፣ ሰይጣን በልባቸው ውስጥ ታላቅ ስፍራ ይዟል፤ መልካም በሆነው ላይ በክፋት እንዲነሱ ያነሣሳቸዋል

፳፩ እናም ልቦቻቸው ተበላሽተዋል፣ እናም በክፋት እና በርኩሰት ተሞልተዋል፤ እናም ምግባሮቻቸው ርኩሰት በመሆናቸው ምክንያት ከብርሀን ይልቅ ጨለማን ይወዳሉ፤ ስለዚህም እኔን አይጠይቁም።

፳፪ ነፍሳቸውን ወደ ጥፋት እንዲመሩ ሰይጣን ያነሣሳቸዋል።

፳፫ እናም ስለዚህ የእግዚአብሔርን እቅድ ለማጥፋት አጨበርባሪ ዕቅድ አስቀምጧል፤ ነገር ግን ይህንን ከእጃቸው እጠይቃለሁ፣ በፍርድ ቀንም ወደ እፍረታቸው እና ወደ ኩነኔያቸው ይለውጣል።

፳፬ አዎን፣ በዚህ ስራ ላይ ልባቸው በቁጣ እንዲነሳሳ ያደርጋል።

፳፭ አዎን፣ እንዲህም አላቸው፥ ማጥፋት ትችሉ ዘንድ፣ አታልሉ እናም ለመያዝ አድፍጡ፤ እነሆ ይህም ጉዳት አይደለም። እናም እንዲህ በማለት ይሸነግላቸዋል፣ እንዲሁም ውሸታምን ሰው ይዞ ለማጥፋት መዋሸት ኃጢአት አይደለም ይላቸዋል።

፳፮ እናም ስለዚህ ይሸነግላቸዋል፣ እናም ነፍሳቸውን ወደ ገሀነም ጎትቶ እስኪጥል ድረስ ይመራቸዋል፤ እናም እንደዚህ እራሳቸው በራሳቸው ወጥመድ ውስጥ እንዲያጠምዱ ያደርጋል።

፳፯ እናም ሰለዚህ የሰዎችን ነፍስ ለማጥፋት በምድር ላይ ወደላይ እና ወደታች፣ ወዲህ እና ወዲያው ይመላለሳል።

፳፰ እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ ሌላው ለማታለል ይዋሻል ብሎ ለማታለል ለሚዋሽ ወዮለት፣ እንደዚህ እይነቶቹ ከእግዚአብሔር ፍትህ አያመልጡምና።

፳፱ አሁን፣ እነሆ ሰይጣን አታሏችኋል ስላላቸው እነዚህን ቃላት ለውጠዋል—እናም በዚህ የተነሳ አንተ ጌታ አምላክህን እንድትፈታተን፣ ኃጢአት እንዲያደርጉ ይሸነግላቸዋል።

እነሆ፣ እንዲህ እልሀለሁ፣ ከእጅህ የወጡትን ዳግመኛ አትተረጉምም፤

፴፩ ስለሆነም በእነዚህ ቃላት ላይ በመዋሸት የክፋት እቅዳቸውን አያከናውኑም። ስለሆነም ዳግም ተመሣሳይ ቃላት ብታመጣ ዋሽተሀል እናም ለመተርጎም አስመስለሀል ነገር ግን ራስህን ተቃውመሀል ይላሉ።

፴፪ እናም እነሆ፣ ይህንንም ያሰራጫሉ እናም ሰይጣን ሰዎች በአንተ ላይ በቁጣ እንዲነሱ፣ ቃላቴን እንዳያምኑ ልባቸውን ያደነድናል።

፴፫ ስለዚህ ስራው በዚህ ትውልድ መካከል እንዳይመጣ ሰይጣን በዚህ ትውልድ ያለህን ምስክርነት ለማሸነፍ ያስባል።

፴፬ ነገር ግን እነሆ፣ ጥበብ ይኸው ነው፣ እናም ለአንተ ጥበብን ስላሳየሁህ እናም እነዚህን በተመለከተ፣ ምንም ማድረግ እንደሚገባህ፣ ትእዛዛትን ስለሰጠሁህ፣ የትርጉሙን ስራ እስክታጠናቅቅ ድረስ ለአለም እንዳታሳይ።

፴፭ ጥበብ ይኸው ነው፣ ለአለም እንዳታሳየው ስላልኩህ አትደነቅ—ለአለም እንዳታሳየው ያልሁህ ምክንያት አንተን ለማዳን ነው።

፴፮ እነሆ፣ ለጻድቃንን አታሳያቸው አላልኩም፤

፴፯ ነገር ግን ዘወትር ጻድቁን ለመፍረድ ስለማትችል፣ ወይም ክፉን ከጻድቁ ዘወትር ለመለየት ስለማትችል፣ ስለዚህ እንዲህ እልሀለሁ፣ ነገሩን በተመለከተ ለአለም እስካሳውቅ ድረስ ዝም በል።

፴፰ እናም አሁን፣ እውነት እልሀለሁ፣ ከእጅህ የወጡት የጻፍካቸው ነገሮች መዝገብ በኔፊ ሰሌዳዎች ላይ ተቀርጸው ይገኛሉ፤

፴፱ አዎን፣ እናም በእነዚህ ጽሁፎች ውስጥ የበለጠ ዝርዝር በኔፊ ሰሌዳ ላይ ተሰጥቷል መባሉን አስታውስ።

እናም አሁን፣ በኔፊ ሰሌዳ ላይ የተቀረጸው ታሪክ በጥበቤ በዚህ ታሪክ ውስጥ ላሉት ህዝብ ከማመጣው እውቀት አንጻር በቀረበ በመሆኑ ምክንያት—

፵፩ ስለዚህ፣ በኔፊ ሰሌዳዎች ላይ ያሉትን ጽሁፎች እስከ ንጉስ ቢንያም አገዛዝ ድረስ፣ ወይም ተርጉመህ በእጅህ እስከ አስቀረሀቸው ድረስ ትተረጉማለህ፤

፵፪ እናም እነሆ፣ እንደ ኔፊ መዝገብ ታሳትመዋለህ፤ እና እንደዚህም ቃላቴን የለወጡትን አምታታቸዋለሁ።

፵፫ ሥራዬን ያጠፉ ዘንድ አልፈቅድም፤ አዎን፣ ጥበቤ ከአጋንንት ብልጠት የላቀ መሆኑንም አሳያቸዋለሁ።

፵፬ እነሆ፣ አጥሮ የተጻፈውን ወይም አነስተኛውን የኔፊ ታሪክን ብቻ ነው ያገኙት።

፵፭ እነሆ፣ በወንጌሌ ላይ ታላቅ መረዳትን የሚያስገኙ ብዙ ነገሮች በኔፊ ሰሌዳ ላይ ተቀርጸው ይገኛሉ፤ ስለዚህ፣ ይህን የኔፊ ቅርጾች የመጀመሪያ ክፍሎችን መተርጎምህ እናም ይህንም ስራ መላክህ በእኔ ዘንድ ጥበብ ነው።

፵፮ እናም፣ እነሆ፣ የቀሩት እነዚህ ስራዎች የእኔ ቅዱሳን ነቢያቶች፣ አዎን፣ እናም እንዲሁም ደቀመዛሙርቴ በጸሎታቸው ለዚህ ህዝብ እንዲመጣ የፈለጉትን የወንጌሌን ክፍሎች የያዘ ነው።

፵፯ እናም እንዲህ አልኳቸው፣ በጸሎታቸው ባላቸው እምነት መጠን ሊሰጣቸው ይገባል፤

፵፰ አዎን፣ እናም ይህም እምነታቸው ነበር፣ በጊዜያቸው እንዲሰብኩ ለእነርሱ የሰጠኋቸውን ወንጌል ለወንድሞቻቸው ለላማናውያን እናም ደግሞ በመገንጠላቸው ምክንያት ላማናውያን ለሆኑት ሁሉ ይመጣ ዘንድ ነበር።

፵፱ አሁን፣ ይህ ብቻም አይደለም—ሌሎች ህዝብ ይህን ምድር እንዲይዙ የሚቻል ቢሆን፣ ይህ ወንጌል እንዲሁ ይታወቅ ዘንድ የጸሎት እምነታቸው ነበር፤

እናም ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ በዚህ ወንጌል የሚያምን ሁሉ ዘለአለማዊ ህይወት ይኖረው ዘንድ፣ በዚህ ምድር ላይ በጸሎታቸው በረከትን ትተዋል፤

፶፩ አዎን፣ ለማንኛውም ሀገር፣ ነገድ፣ ቋንቋ፣ ወይም ህዝብ ሁሉ ይህ ነጻ ይሆን ዘንድ በጸሎታቸው በረከትን ትተዋል።

፶፪ እና፣ አሁን፣ እነሆ በጸሎታቸው ውስጥ ባለው እምነት የተነሳ የዚህን የወንጌሌን ክፍል ወደ ሀዝቦቼ እውቀት አመጣለሁ። እነሆ፣ የሚመጣው የተቀበሉትን ለመሻር ሳይሆን፣ ነገር ግን ለመገንባት ነው።

፶፫ እናም በዚህ ምክንያት እንዲህ ብያለሁ፥ ይህ ትውልድ ልቡን የማያደነድን ከሆነ፤ ቤተክርስቲያኔን በመካከላቸው እመሰርታለሁ።

፶፬ አሁን ይህንን የምለው ቤተክርስቲያኔን ለማፍረስ አይደለም፣ ነገር ግን ቤተክርስቲያኔን ለመገንባት ነው።

፶፭ ስለዚህ፣ የቤተክርስቲያኔ ሰው የሆነ ሁሉ መፍርሀት የለበትም፣ እንደዚህ አይነቱ መንግሥተ ሰማይን ይወርሳልና

፶፮ ነገር ግን የማይፈሩኝ፣ ትእዛዛቴን የማይጠብቁ ነገር ግን ለራሳቸው ጥቅምን ለማግኘት ቤተክርስቲያንን የሚገነቡ፣ አዎን፣ እርኩሰትን የሚያደርጉ ሁሉ እናም የአጋንንትን መንግስት የሚገነቡ—አዎን፣ እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ አውካቸዋለሁ፣ እና መላ ሰውነታቸው እንዲርበተበት እና እንዲቀጠቀጥ አደርጋለሁ።

፶፯ እነሆ፣ እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ። የእኔው ወደሆኑት መጣሁ፣ የራሴም አልተቀበሉኝም።

፶፰ እኔ በጭለማ የማበራ ብርሀን ነኝ፣ እናም በጨለማም ያሉት አይረዱትም።

፶፱ ለደቀመዛሙርቴ ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ ያልሁት እኔው ነኝ። እናም ያልተረዱኝ ብዙ ነበሩ።

እናም ለዚህ ህዝብ የያዕቆብ ቤት ቅርንጫፍም እንደነበሩ፤ እና ሌሎች በጎች እንዳሉኝ አሳያቸዋለሁ፤

፷፩ እናም በስሜ የሰሩትን ድንቅ ስራዎቻቸውን ወደ ብርሀን አመጣለሁ፤

፷፪ አዎን፣ እናም ለእነርሱ አገልግሎት የዋለውን ወንጌሌን ወደ ብርሀን አመጣዋለሁ፣ እናም እነሆ፣ እናንት የተቀበላችሁትን አይክዱም ነገር ግን ይገነቡታል፣ እናም የትምህርቴን እውነተኛ ነጥቦች፣ አዎን፣ በእኔ ያለውን ብቸኛ ትምህርት ወደ ብርሀን ያመጡታል።

፷፫ እናም ወንጌሌን እመሰረት ዘንድ፣ ብዙ ፀብ እንዳይኖር ዘንድ ይህንን አደርጋለሁ፤ አዎን፣ የትምህርቴ ነጥቦች በተመለከተ ሰይጣን የሰዎችን ልብ ለፀብ ያነሣሳል፤ በዚህም ስህተት ይሰራሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጣምማሉ እናም አይረዷቸውም።

፷፬ ስለዚህ፣ ይህንን ታላቅ ሚስጥር እገልጽላቸዋለሁ፤

፷፭ ስለሆነም፣ ልባቸውን የማያደነድኑ ከሆኑ፣ ዶሮ ጫቹቶቿን በክንፎቿ እንደምትሰበስብ እንዲሁ እኔም እሰበስባቸዋለሁ

፷፮ አዎን፣ ከመጡ ከህይወት ውሀ በነፃ ይጠጣሉ።

፷፯ እነሆ፣ ይህ ትምህርቴ ነው—ንስሀ የሚገባ እና ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ የቤተክርስቲያኔ ሰው ነው።

፷፰ በዚህ ላይ ጨምሮ ወይም ቀንሶ የሚያውጅ ሁሉ ከእኔ አይደለም፣ ነገር ግን ተቃዋሚዬ ነው፤ ስለዚህ ከቤተክርስቲያኔም አይደለም።

፷፱ እናም አሁን፣ እነሆ፣ የቤተክርስቲያኔ የሆነ ሁሉ እናም በቤተክርስቲያኔ እስከመጨረሻው የሚጸና በአለቴ ላይ የምመሰርተው እርሱን ነው እናም የሲዖል ደጆችም አይቋቋሙትም።

የአለም ብርሀን እና ህይወት የሆነውን፣ የአዳኛችሁን፣ የጌታችሁን እና የአምላካችሁን ቃላት አስታውሱ። አሜን።