ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፷፬


ክፍል ፷፬

መስከረም ፲፩፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.)፣ በከርትላንድ ኦሀዮ ውስጥ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል ለቤተክርስቲያኗ ሽማግሌዎች የተሰጠ ራዕይ። በሚዙሪ ውስጥ እያለ ለሌላ ጊዜ ያስተላለፈውን የመፅሐፍ ቅዱስን ትርጉም ስራ ደግሞ ለመጀመር፣ ነቢዩ ወደ ሀይረም ኦሀዮ ለመሄድ እየተዘጋጀ ነበር። ወደ ፅዮን (ሚዙሪ) እንዲጓዙ የታዘዙት ወንድሞችም በጥቅምት ለመሄድ በቅንነት እየተዘጋጁ ነበር። በዚህ ስራ በበዛበት ጊዜ፣ ይህን ራዕይ ተቀብሎ ነበር።

፩–፲፩፣ በራሳቸው ታላቅ ኃጢአት እንዳይቀር፣ ቅዱሳን እርስ በራሳቸውም ይቅር እንዲባባሉ ታዘዋል፤ ፲፪–፳፪፣ ንስሀ የማይገቡት በቤተክርስቲያኗ ለፍርድ ይቅረቡ፤ ፳፫–፳፭፣ አስራትን የሚከፍል በጌታ መምጫ ጊዜ አይቃጠልም፤ ፳፮–፴፪፣ ቅዱሳን እዳን እንዲያስወግዱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፤ ፴፫–፴፮፣ አመጸኞች ከፅዮን ውስጥ ይቆረጣሉ፤ ፴፯–፵፣ ቤተክርስቲያኗ አገሮችን ትፈርዳለች፤ ፵፩–፵፫፣ ፅዮን ታብባለች።

እነሆ፣ ጌታ አምላካችሁ እንዲህ ይላችኋል፣ አቤቱ እናንት የቤተክርስቲያኔ ሽማግሌዎች ሆይ፣ አድምጡ እናም ስሙ፣ እናም እኔ እናንተን በተመለከተ ያለኝን ፈቃድ ተቀበሉ።

እውነት እላችኋለሁ፣ አለምን እንድታሸንፉ እፈልጋለሁ፤ ስለዚህ፣ በእናንተ ላይ ርህራሄ ይኖረኛል።

በመካከላችሁ ኃጢአት የሰሩ አሉ፤ ነገር ግን በእውነት እላለሁ፣ አንድ ጊዜ፣ ለክብሬ ስል፣ እናም ለነፍሳት ደህንነት ስል፣ ለኃጢአታችሁ ይቅርታን አድርጌአለሁ።

ለእናንተም መሀሪ እሆናለሁ፣ መንግስትንም ሰጥቻችኋለሁና።

ስርዓቶቼን እስካከበረ ድረስ፣ በህይወት እያለ፣ የመንግስቱ የሚስጥራት ቁልፎችም ከአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ፣ በመሰረትኩበት መንገድ፣ አይወሰድበትም።

በከንቱ በእርሱ ላይ ምክንያት የሚፈልጉበት አሉ፤

ይሁን እንጂ፣ እርሱም ኃጢአትን ሰርቷል፤ ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአታቸውን በፊቴ የሚናዘዙ፣ እና ይቅርታን የሚጠይቁ፣ ለሞት ኃጢአትን ላልሰሩት፣ እኔ ጌታ ይቅርታ አደርግላቸዋለሁ።

ደቀ መዛሙርቶቼ፣ በቀደሙት ቀናት፣ እርስ በርሳቸው ምክንያት ይፈልጉ ነበር እና በልቦቻቸውም ይቅርታን አያደርጉም ነበር፤ እናም በዚህ ክፉ ነገርም ተሰቃይተው እናም በምሬት ተቀጥተው ነበር።

ስለዚህ፣ እርስ በርሳችሁ ይቅርታን መስጠት አለባችሁ እላችኋለሁ፤ ወንድሙ ለተላለፈው ይቅርታን የማይሰጠው በጌታ ፊት ይኮነናል፤ ምክንያቱም በእርሱ ታላቁ ኃጢአት ይኖራልና።

እኔ ጌታ ይቅር የምለውን ይቅር እላለሁ፣ ነገር ግን እናንተ ለሁሉም ሰዎች ይቅርታን ታደርጉ ዘንድ ይጠበቅባችኋል።

፲፩ እና በልባችሁም እንዲህ ማለት ይገባችኋል—በእኔ እና በአንተ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ፣ እናም እንደስራህም ይከፍልሀልና።

፲፪ እናም ለኃጢአቶቹ ንስሀ ያልገባውም፣ እና ያልተናዘዘውንም፣ በቤተክርስቲያኗ ፊት አምጡት፣ እናም በቅዱሳን መጻህፍት ውስጥ በትእዛዝም ሆነ በራዕይ እንደሚላችሁም እንዲሁ አድርጉበት።

፲፫ እናም ይህንንም የምታደርጉት ለእግዚአብሔር ክብር ነው፣ ይቅርታ ስላላደረጋችሁ፣ ወይም ርህራሄ ስለሌላችሁ ሳይሆን፣ ነገር ግን በህግ ፊት ይህንኑ ለማረጋገጥ፣ ህግን የሰጣችሁን እንዳታስቀይሙ ነው—

፲፬ እውነት እላለሁ፣ በእነዚህ ምክንያቶች እነዚህን ነገሮች አድርጉ።

፲፭ እነሆ፣ እኔ ጌታ አገልጋዬ በነበረው ኤዝራ ቡዝ፣ እና ደግሞም በአገልጋዬ አይዛክ ሞርሊ ተቆጥቻለሁ፣ ምክንያቱም ህግንም ይሁን ትእዛዝን አላከበሩምና።

፲፮ በልቦቻቸው ክፋትን ፈልገዋል፣ እናም እኔ ጌታ መንፈሴን ከእነርሱ አርቄአለሁ። ክፉት የሌለባቸውን ነገሮች እንደክፉ ኮንነዋልና፤ ይሁን እንጂ፣ አገልጋዬን አይዛክ ሞርሊን ይቅር ብዬዋለሁ።

፲፯ እና ደግሞም አገልጋዬ ኤድዋርድ ፓርትሪጅ፣ እነሆ፣ ኃጢአትን ሰርቷል፣ እናም ሰይጣንም ነፍሱን ሊያጠፋ ይሻል ነገር ግን፣ እነዚህን ነገሮች ሲያውቋቸው፣ እናም ለክፋታቸው ንስሀ ሲገቡ፣ ይቅርም ይሰጣቸዋል።

፲፰ እናም አሁን፣ እውነትም እላለሁ፣ አገልጋዬ ስድኒ ጊልበርት፣ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ሀላፊነቱ፣ እና በፅዮን ምድር ወዳለው ወኪሉ፣ ይመለስ ዘንድ ፍቃዴ ነው፤

፲፱ እናም፣ እንዳይጠፉም፣ ያያቸውን እና የሰማቸውን ነገሮች ደቀ መዛሙርቴ እንዲያውቋቸው ያደርጋል። እናም በእዚህም ምክንያት እነዚህን ነገሮች ተናግሬአለሁና።

እና እንዲህም እላችኋለሁ፣ አገልጋዬ አይዛክ ሞርሊ ለመሸከም ከሚችለው በላይ እንዳይፈተን፣ እናም ሊጎዳችሁም የስህተት ምክር እንዳይሰጥም፣ የእርሻ ቦታው ይሸጥ ዘንድ አዘዝኩኝ።

፳፩ አገልጋዬ ፍሬድሪክ ጂ ዊልያምስ የእርሻ ቦታውን መሸጡ የእኔ ፈቃድ አይደለም፣ እኔ ጌታ፣ ኃጢአተኞችን በማልጥልበት አምስት አመት ጊዜያት፣ በዚህም የተወሰኑትን አድን ዘንድ፣ በከርትላንድ ምድር የምሽግ ስፍራን ለመጠበቅ እፈልጋለሁና።

፳፪ እናም ከዚያ ቀን በኋላ፣ እኔ ጌታ ወደ ፅዮን ምድር በተከፈተ ልብ የሚሄደውን ማንንም እንደ ጥፋተኛ አልቆጥርም፤ እኔ ጌታ የሰው ልጆችን ልብ እሻለሁና።

፳፫ እነሆ፣ አሁን እስከ ሰው ልጅ ምፅዓት ድረስ ቀኑም ዛሬ ተብሎ ይጠራል፣ እናም እውነትም የመስዋዕት ቀን ነው፣ እናም ህዝቤ አስራትን የሚከፍሉበትም ቀን ነው፤ አስራትን የሚከፍልም በእርሱ ምፅዓት ጊዜ አይቃጠልም

፳፬ ከዛሬ በኋላ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣልና—ይህም እንደ ጌታ አባባል ነው—እውነትም እላለሁ፣ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ እናም አቃጥላቸዋለሁ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነኝና፤ እናም በባቢሎን ውስጥ የሚቀሩትንም አላድንም።

፳፭ ስለዚህ፣ ካመናችሁኝ፣ ዛሬ ተብሎ በሚጠራው ቀን ትሰራላችሁ።

፳፮ እናም አገልጋዬ ኒወል ኬ ውትኒ እና ስድኒ ጊልበርት በዚህ ያላቸውን ንብረት እና ግምጃዎቻቸውን መሸጣቸው አስፈላጊ አይደለም፤ በዚህ ስፍራ ቤተክርስቲያን የሚቀሩት ወደ ፅዮን ምድር ከመሄዳቸው በፊት ይህም ጥበብ አይደለምና።

፳፯ እነሆ፣ በህግጋቴ ውስጥ በጠላታችሁ ዘንድ እዳ አትግቡ ይላል፣ ወይም የተከለከለ ነው፤

፳፰ ነገር ግን እነሆ፣ በሚያስደስተው ጊዜ ጌታ አይወስድም፣ እናም መልካም በመሰለውም ይከፍላል አልተባለም።

፳፱ ስለዚህ፣ እናንት ወኪል ስለሆናችሁ፣ በጌታ መልእክት ትጓዛላችሁ፤ እናም እንደ ጌታ ፈቃድ በኩል የምታደርጉት ነገር ሁሉ የጌታ ስራ ነውና።

እናም በእነዚህም የመጨረሻ ቀናት ለቅዱሳኑ፣ በፅዮን ምድር ውርስን እንዲያገኙ ታደርጉ ዘንድ ተሹማችኋል።

፴፩ እናም እነሆ፣ ቃላቴ እርግጥ በመሆናቸውና ስለማይወድቁ፣ እነርሱም እንደሚያገኟቸው እኔ ጌታ እገልፅላችኋለሁ።

፴፪ ነገር ግን ሁሉም ነገሮች በጊዜአቸው ይከናወኑ ዘንድ ግድ ነው።

፴፫ ስለዚህ፣ መልካም ሥራን ትሰሩ ዘንድ አትታክቱ፣ የታላቅ ስራን መሰረት እየገነባችሁ ነውና። እናም ከትትንሽ ነገሮች ታላቅ ነገሮች ይወጣሉና።

፴፬ እነሆ፣ ጌታ ልብን እና መልካም ፈቃድ ያለውን አዕምሮ ይሻል፤ እናም ፈቃድ ያለው እና ታዛዡ የሆነው እርሱ በእነዚህ በመጨረሻዎቹ ቀናት የፅዮንን ምድርን በረከት ይበላሉ።

፴፭ እናም አመጸኞችም ከፅዮን ምድር ይቆረጣሉ፣ እናም ተለይተው ይሄዳሉ፣ እናም ምድሩንም አይወርሱም።

፴፮ በእውነት እላለሁ፣ አመጸኞቹ ከኤፍሬም ወገን አይደሉም፣ ስለዚህም ይነቀላሉ።

፴፯ እነሆ፣ እኔ ጌታ በእነዚህ በመጨረሻዎቹ ቀናት ቤተክርስቲያኔን በኮረብታ ላይ እንደተቀመጠ ዳኛ በአህዛብ ትፈርድ ዘንድ እንድትቀመጥ ሰርቻታለሁ።

፴፰ እንዲህም ይሆናል የፅዮን ኗሪዎች ፅዮንን በሚመለከቱ ነገሮችን ላይ በፍርድ ይቀመጣሉ።

፴፱ እናም ሐሰተኞች እና ግብዞች በእነርሱ ይፈተናሉ፣ እናም ሐዋርያት እና ነቢያት ያልሆኑትም ይታወቃሉ።

እናም ዳኛ የሆነው ኤጲስ ቆጶስ እና አማካሪዎቹም፣ በሀላፊነታቸው ታማኝ ካልሆኑ፣ ይኮነናሉ፣ እናም ሌሎችም በእነርሱ ስፍራ ይተከላሉ።

፵፩ እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ ፅዮን ታብባለች፣ እናም የጌታም ክብር በእርሷ ላይ ያርፋል፤

፵፪ እናም እርሷም ለህዝብ ምልክት ሆና ትቆማለች፣ እናም ከሰማይ በታች ካሉት ሀገሮች ውስጥም ወደ እርሷ ይመጣሉ።

፵፫ እናም በእርሷ ምክንያት የአለም ሀገሮች ሁሉ የሚንቀጠቀጡበት፣ እናም በአስፈሪዎቿም ምክንያት የሚደነግጡበት ቀን ይመጣል። ጌታም ይህን ተናግሯል። አሜን።