ክፍል ፻፳፩
በመጋቢት ፳፣ ፲፰፻፴፱ (እ.አ.አ.) በልብረቲ ሚዙሪ በእስር ቤት ውስጥ እስረኛ ሆኖ እያለ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ለቤተክርስቲያኗ በተሰጠ ደብዳቤ ውስጥ የተጻፉ ጸሎት እና ትንቢቶች። ነቢዩ እና አያሌ ባልንጀሮቹ በእስር ቤት ውስጥ ብዙ ወራትን አሳልፈው ነበር። ወደ ውሳኔ ሰጪ ዋና ሰዎችና ወደ ፍርድ ቤቶች የላኩት አቤቱታቸው እና ልመናቸው ምንም እርዳታ አላመጡላቸውም።
፩–፮፣ ነቢዩ ስለቅዱሳን ስቃይ ጌታን ለመነ፤ ፯–፲፣ ጌታም ለእርሱም ሰላምን ተናገረ፤ ፲፩–፲፯፣ በጌታ ህዝብ ላይ በሀሰት መተላለፍ ክስን የሚከሷቸው ሁሉ የተረገሙ ናቸው፤ ፲፰–፳፭፣ ለክህነት ስልጣን መብትም አይኖራቸውም እና ይኮነናሉ፤ ፳፮–፴፪፣ በብርታት ለሚጸኑትም የክብር ራዕዮች ቃል ተገብተውላቸዋል፤ ፴፫–፵፣ ለምን ብዙዎችም እንደተጠሩ እና ጥቂቶችም እንደተመረጡ፤ ፵፩–፵፮፣ ክህነትን በፅድቅ ብቻ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ።
፩ እግዚአብሔር ሆይ፣ የት ነህ? እና የተሰወርክበትን ስፍራ የሚሸፍነው ድንኳን የት ነው?
፪ እስከመቼ እጅህ፤ አይንህ አዎን ንጹህ አይኖችህ ከዘለአለማዊው ሰማይ በህዝብህ እና በአገልጋዮችህ ላይ የሚደረጉትን ክፋቶች እያዩ ለቅሶአቸውም ወደ ጆሮህ እያስተጋባ ትታገሳለህ?
፫ አዎን፣ ጌታ ሆይ፣ ልብህ ለእነርሱ ከመለሳለሱ በፊት፣ እና ለእነርሱም አንጀትህ በርህራሄ እስከሚሞላ ድረስ ለስንት ጊዜ እነዚህን ክፋቶችን እና ህጋዊ ያልሆኑትን ጭቆናዎችን ይሰቃዩ።
፬ ሰማይን፣ እና ምድርን፣ እና ባህሮችን፣ እና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮችን ሁሉ ፈጣሪው፣ እና ዲያብሎስን እና ጥቁር እና ያጨለመውን የሲኦል ግዛት የምትቆጣጠር እና በቁጥጥር ስር የምታደርግ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ—እጅህን ዘርጋ፤ አይንህም በትኩረት ይመልከት፤ ድንኳንህም ይነቀል፤ የተሰወርክበትም ስፍራ አይሸፈን፤ ጆሮህም ያዘንብል፤ ልብህም ይለሳለስ፣ እና አንጀትህም በርህራሄ ወደ እኛ ይሞላ።
፭ ቁጣህም በጠላቶቻችን ላይ ይቀጣጠል፤ እና በልብህ ቁጣ፣ በጎራዴህ ክፉት ስለተደረጉብን ተበቀልልን።
፮ አምላካችን ሆይ፣ የሚሰቃዩትን ቅዱሳንህን አስታውስ እና አገልጋዮችህም በስምህ ለዘለአለም ይደሰታሉ።
፯ ልጄ፣ ለነፍስህ ሰላም ይኑርህ፤ ጭንቀትህ እና ስቃይህ ለጥቂት ጊዜ ቢሆን ነው፤
፰ ከዚያም፣ በመልካም ይህን ብትጸና፣ እግዚአብሔርም ወደ ላይ ዘለአለማዊ ክብር ይሰጥሀል፤ ጠላቶችህንም በሙሉ ታሸንፋቸዋለህ።
፱ ባልንጀሮችህ በአጠገብህ ቆመዋል፣ እና በሞቀ ልብ እና በጓደኝነት እጆች እንደገናም ሰላምታ ይሰጡሀል።
፲ እንደ ኢያብም ገና አይደለህም፤ ባልንጀሮችህ በኢያብ እንዳደረጉትም በአንተም ላይ በተቃራኒነት አይጣሉህም፣ ወይም በመተላለፍ አይከሱህም።
፲፩ እና በመተላለፍ የሚከሱህም፣ ተስፋቸው ይከስማል፣ እና በምትወጣው ጸሀይ በሚያነድ ጨረር እንደሚቀልጥ በረዶም፣ ተስፋ ያደረጉበትም ነገር ይጠፋል፤
፲፪ ደግሞም እግዚአብሔር እጁም ተገልጧል እና ድንቅ ስራዎቹ እንዳይገቧቸው ዘንድ ጊዜያትን እና ዘመናትን ለመቀየርና አዕምሮዎቻቸውን ያጨልም ዘንድ፤ ደግሞም እንዲያረጋግጥላቸውም እና በአታላይነታቸው ይይዛቸው ዘንድ አትሟል፤
፲፫ ደግሞም ልቦቻቸው የረከሱ ስለሆኑ፣ እና በሌሎች ላይ ክፉ ነገሮች እንዲወድቅባቸው ፈቃደኛ ስለሆኑ፣ እና ሌሎች እንዲሰቃዩ ለማድረግ ስለሚወዱ፣ ይህም በእነርሱ ላይ በሚበልጥ መጠን ይመጣባቸዋል፤
፲፬ ተስፋ ያጡ ዘንድ፣ እና ተስፋቸውም እንዲቆረጥ፤
፲፭ እና ከዚህ ጊዜ አያሌ አመታት ሳያልፉም፣ እነርሱ እና መጪዎቹ ትውልዶቻቸው ከሰማይ በታች ይጠረጋሉ፣ ይላል እግዚአብሔር፣ ማናቸውም በግድግዳው ቆመው አይቀሩም።
፲፮ በእኔ በተቀቡት ላይ ተረከዛቸውን የሚያነሱት፣ ይላል ጌታ፣ እና ምንም እንኳን በአይኖቼ ብቁ የሆኑትን እና ያዘዝኳቸውን የሚያደርጉትን፣ በፊቴ ኃጢአትን ያልሰሩት ኃጢአት ሰርተዋል በማለት የሚጮሁት ሁሉ የተረገሙ ናቸው፣ ይላል ጌታ።
፲፯ ነገር ግን ስለመተላለፍ የሚጮሁት ይህን የሚያደርጉት የኃጢአት አገልጋዮች እና ራሳቸውም የአመጸኞች ልጆች ስለሆኑ ነው።
፲፰ እና ወደባርነት እና ወደ ሞት ያመጧቸው ዘንድ በአገልጋዮቼ ላይ በሀሰት የሚመሰክሩትም—
፲፱ ወዮላቸው፤ ታናናሾቼን ስለሚያሰናክሉ ከቤቴ ስርዓቶች ይቆረጣሉ።
፳ ቅርጫታቸውም አይሞላም፣ ቤታቸውና ጎተራዎቻቸውም ይጠፋሉ፣ እና እራሳቸውም በሚያባብሏቸው ይጠላሉ።
፳፩ እነርሱ ወይም መጪዎቹ ትውልዶቻቸውም ከትውልድ እስከ ትውልድ፣ ለክህነት ስልጣንም መብት አይኖራቸውም
፳፪ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቶቻቸው ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስመጥ በተሻላቸው ነበር።
፳፫ ህዝቤን እንዳይመቻቸው ለሚያደርጉም፣ እና ለሚያሳድዷቸው፣ እና ለሚገድሏቸው፣ እና በእነርሱም ላይ ለሚመሰክሩባቸው ሁሉ ወዮላቸው ይላል የሰራዊት ጌታ፤ የእፉኝት ልጆች ከገሀነም ፍርድ አያመልጡም።
፳፬ እነሆ፣ አይኖቼ ያያሉ እና ስራቸውን ሁሉ አውቃለሁ፣ እና ለሁሉም በጊዜውም ፈጣን ፍርድም አኑሬላቸዋለሁ፤
፳፭ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ስራው የተመደበለት ጊዜ አለውና።
፳፮ እግዚአብሔር እውቀቱን በቅዱስ መንፈሱ፣ አዎን አለም ከነበረበት እስከ አሁንም ድረስ ባልተገለጠውን፣ ለመናገርም የማይቻለውን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታውን ይሰጣችኋል፤
፳፯ በመጨረሻዎቹ ዘመናት እንዲገለጡ የቀደሙት አባቶቻችን በጉጉት የጠበቋቸውን፣ ለክብራቸው ሙላት በኋላም የተጠበቁትን በመላዕክት ሀሳብ የተመሩበትን እውቀት ይሰጣችኋል፤
፳፰ እነርሱ ስለሚገለጡ፣ አንድ አምላክም ይኑር ብዙ አማልክት፣ ይህም ማንኛውም ነገር የማይሰወርበት ጊዜ ነው።
፳፱ ዙፋናት ቢሆኑ እና ጌትነት እና አለቅነት እና ሥልጣናት ሁሉ ይገለጣሉ እና ለኢየሱስ ክርስቶስም ወንጌል በብርታት ለጸኑት ሁሉ ይሰጧቸዋል።
፴ ደግሞም፣ ለሰማያት ወይም ለባህሮች፣ ወይም ለደረቅ መሬት፣ ወይም ለጸሀይ፣ ጨረቃ፣ ወይም ለከዋክብት ገደብ ቢሆን—
፴፩ የሚዞሩባቸው ጊዜያት ሁሉ፣ በተመደቡላቸው ቀናት፣ ወራት፣ እና አመታት ሁሉ፣ እና በየቀናቶቻቸው ቀናት፣ ወራት፣ እና አመታት ሁሉ፣ እና በክብሮቻቸው፣ በህግጋታቸው፣ እና በተወሰኑት ጊዜያቶቻቸው ሁሉ፣ በዘመን ፍጻሜ ቀናት ሁሉ ይገለጣሉ—
፴፪ ሁሉም ሰው ወደ ዘለአለማዊነቱ እና ወደ ህያው እረፍቱ ሲገቡ፣ እስከመጨረሻው እና ለዚህ መጨረሻም ይጠበቅ ዘንድ፣ ከዚህ አለም በፊት በሌሎች አማልክት ዘለአለማዊ አምላክ ሸንጎ መካከል በተመደበው መሰረት ያም ሊሆን ይገባዋል።
፴፫ እስከመቼ ጊዜ የሚደበላለቀው ውሀ ንጹህ ሆኖ ሊቆይ ይቻለዋል? የትኛውስ ሀይል ሰማያትን ሊያቆም ይችላል? በኋለኛው ቀን ቅዱሳን ራሶች ላይ ሁሉን የሚገዛው ከሰማይ እውቀቶችን ማፍሰሱን ከሚያቆም፣ ሰው ደካማ ክንዶቹን ዘርግቶ የሚዙሪን ወንዝ ከተወሰነለት መንገዱ ያቆም ዘንድ ወይም ተቃራኒው እንዲዞር ለማድረግ ቢሞክር ይቀለዋል።
፴፬ እነሆ፣ ብዙዎች ተጠርተዋል፣ ነገር ግን የተመረጡት ጥቂቶች ናቸው። እና ያልተመረጡትስ ለምንድን ነው?
፴፭ ምክንያቱም ልባቸውን በአለም ነገሮች ላይ ስለሚያደርጉ እና በሰዎች ይሞገሱ ዘንድ ስለሚነሳሱ፣ ይህን አንድ ትምህርት አይማሩም—
፴፮ የክህነት መብቶች እና የሰማይ ሀይላት የማይነጣጠሉ ናቸው፣ እና የሰማይ ሀይላት በፅድቅ መሰረታዊ መርሆች የሚካሄድ ካልሆነ በስተቀር ሊቆጣጠሯቸው እና ሊጠቀሙባቸውም ዘንድ አይቻልም።
፴፯ ለእኛ ሊሰጡን መቻሉ እውነት ነው፤ ነገር ግን ኃጢአታችንን ለመሸፈን፣ ወይም ኩራታችንን እንዲሁም ከንቱ ፍላጎታችንን ለማርካት፣ ወይም በማንኛውም የፅድቅ ባልሆነ መንገድ በሰዎች ልጆች ነፍሳት ላይ ቁጥጥር ወይም የበላይነትን ወይም ግዴታን ለማድረግ ብንሞክር፣ እነሆ፣ ሰማያት ራሳቸውን ያገልላሉ፤ የጌታም መንፈስም ያዝናል፤ እና ይህ ሲወሰድም፣ የሰው ክህነት ወይም ስልጣን ፍጻሜ ይሆናል።
፴፰ እነሆ፣ ይህን ከማወቁም በፊት፣ የመውጊያውን ብረት ይቃወም ዘንድ፣ ቅዱሳንን ያሳድድ፣ እና ከእግዚአብሔርም ጋር ይዋጋ ዘንድ ብቻውን ይተዋል።
፴፱ ወዲያውኑም ትንሽ ስልጣን ያገኙ ሲመስላቸው፣ ፈጥነው ጻድቅ ባልሆነ ሁኔታ በበላይነት ስልጣናቸውን ሲጠቀሙበት፣ ይህም የሰው ሁሉ ተፈጥሮ እና ባህርይ መሆኑንም ከአሳዛኝ አጋጣሚዎች ተምረናል።
፵ ስለዚህ፣ ብዙዎች ተጠርተዋል፣ ግን የተመረጡት ጥቂቶች ናቸው።
፵፩ በማሳመን፣ በትእግስት፣ በደግነት፣ እና በትህትና፣ እና ግብዝነት በሌለው ፍቅር ካልሆነ በስተቀር፣ ምንም ሀይል ወይም ተጽዕኖ በክህነት ስልጣን ዘዴ ሊደገፍ አይቻልም ወይም አይገባውም፤
፵፪ ይህም በርህራሄ፣ እና ያለግብዝነትና ያለተንኮል መንፈስን በታላቅ በሚያሳድግ ንጹህ እውቀት ብቻ ነው ሊደገፍ የሚችለው፤
፵፫ መንፈስ ቅዱስ በሚነሳሳበት በትክክለኛው ጊዜ በሀያልነት በመቆጣት፤ ከዚያም በኋላ እንደጠላት እንዳያይህ፣ ለተቆጣኸውም ተጨማሪ ፍቅር አሳይ፤
፵፬ በእዚህም እምነትህ ከሞት ሀይል በላይ እንደሆነ ይወቅ።
፵፭ አንጀትህም ለሁሉም ሰው እና ለእምነት ቤተ ሰዎች በልግስና ይሞላ፣ እና ምግባረ በጎነትም ሳያቋርጥ አስተሳሰብህን ያሳምር፤ ከዚያም ልበ ሙሉነትህ በእግዚአብሔር ፊት እየጠነከረ ይሄዳል፤ እና የክህነት ትምህርትም በነፍስህ ላይ እንደ ሰማይ ጠል ትንጠባጠብልሀለች።
፵፮ መንፈስ ቅዱስም የዘወትር ባልንጀራህ ይሆናል፣ እና በትርህም የማይቀየር የፅድቅ እና የእውነት በትር ይሆናል፤ እና ስልጣንህም ዘለአለማዊ ስልጣን ይሆናል፣ እና በማያስገድድ ዘዴም ይህም ወደ አንተ ለዘለአለም ይፈሳል።