ክፍል ፲፰
ሰኔ ፲፰፻፳፱ (እ.አ.አ.) በፈየት፣ ኒው ዮርክ፣ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ፣ ኦሊቨር ካውድሪ፣ እና ዴቪድ ዊትመር የተሰጠ ራዕይ። ነቢዩ እንዳለው፣ ይህ ራዕይ እንዲታወቅ የተደረገው “ስለአስራ ሁለት ሐዋሪያት በእነዚህ በኋለኛው ቀናት መጠራት ነበር፣ እና ደግሞም ቤተክርስቲያኗን ለመገንባት መመሪያዎችን ስለመስጠት ነበር።”
፩–፭፣ ቅዱሳን መጻህፍት ቤተክርስቲያን እንዴት እንደሚገነባ ያሳያሉ፤ ፮–፰፣ አለም በኃጢአት እየበሰለ ነው፤ ፱–፲፮፣ የነፍሳት ዋጋ ታላቅ ነው፤ ፲፯–፳፭፣ ደህንነትን ለማግኘት ሰዎች የክርስቶስን ስም በላያቸው ላይ መውሰድ አለባቸው፤ ፳፮–፴፮፣ የአስራ ሁለቱ ጥሪ እና ተልዕኮ ተገልጧል፤ ፴፯–፴፱፣ ኦሊቨር ካውድሪ እና ዴቪድ ዊትመር አስራ ሁለቱን መፈለግ ይገባቸዋል፤ ፵–፵፯፣ ደህንነትን ለማግኘት ሰዎች ንሰሀ መግባት፣ መጠመቅ፣ እና ትእዛዛቶቹን መጠበቅ አለባቸው።
፩ አሁን፣ እነሆ፣ አንተ አገልጋዬ፣ ኦሊቨር ካውድሪ ከእኔ ለማወቅ በምትሻው ነገር ምክንያት፣ እነዚህን ቃላት ለአንተ እሰጥሀለሁ፥
፪ እነሆ፣ አንተ የጻፍካቸው ነገሮች እውነት እንደሆኑ፣ በብዙ አጋጣሚ በመንፈሴ ገልጬልሀለሁ፤ ስለዚህም እውነት እንደሆኑ ታውቃለህ።
፫ እናም እውነት እንደሆኑ ካወቅህ፣ እነሆ፣ በተጻፉት ላይ እንድትደገፍ፣ ትእዛዛትን ለአንተ እሰጥሀለሁ፤
፬ ስለሆነ በውስጣቸው የቤተክርስቲያኔን፣ የወንጌሌን፣ እና የአለቴን መሰረት በተመለከተ ሁሉም ነገሮች ተጽፈዋል።
፭ ስለዚህ፣ በወንጌሌ እና በአለቴ መሰረት ላይ ቤተክርስቲያኔን ከገንባህ የሲዖል ደጆችም አይቋቋሙህም።
፮ እነሆ፣ አለም በኃጢአት እየበሰለ ነው፣ እናም የሰው ልጆች፣ አሕዛብ እና ደግሞም የእስራኤል ቤት፣ ለንስሀ መነሳሳት አለባቸው።
፯ ስለዚህ፣ እኔ ባዘዝኩት መሰረት በአገልጋዬ በጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ፣ እጅ እንደተጠመቅህ ሁሉ፣ ያዘዝኩትን ነገር ፈጽሟል።
፰ በእኔ ለሚታወቀው አላማ፣ ለአላማዬ ስለጠራሁት አትደነቅ፤ ስለዚህ፣ ትእዛዛቴን በመጠበቅ ትጉህ ከሆነ፣ በዘለአለም ህይወት ይባረካል፤ ስሙም ጆሴፍ ነው።
፱ እናም አሁን፣ በትእዛዝ መልክ ለአንተ ለኦሊቨር ካውድሪ እናም እንዲሁም ለዴቭድ ዊትመር እናገራለሁ፤ ስለሆነም፣ እነሆ፣ በሁሉም ስፍራ ሁሉም ሰዎች ንስሀ እንዲገቡ አዝዛለሁና፣ እናም እርሱ በተጠራበት ጥሪ ስለተጠራችሁ እንደ ኃዋሪያዬ ጳውሎስ እናገራችኋለሁ።
፲ የነፍስ ዋጋ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ እንደሆነ አስታውሱ፤
፲፩ ስለሆነም፣ እነሆ ጌታ አዳኛችሁ የስጋ ሞትን ሞተ፤ ስለዚህ ሰዎች ንስሀ ገብተው ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ የሰዎችን ሁሉ ህመም ተሰቃየ።
፲፪ እናም በንስሀ ብቻ ሰዎችን ሁሉ ወደእርሱ ያመጣ ዘንድ፣ ከሞት ዳግም ተነሳ።
፲፫ እናም ንስሀ በሚገባ ነፍስ ደስታው እንዴት ታላቅ ነው!
፲፬ ሰለዚህ፣ ለዚህ ህዝብ ንስሀን እንድትጮሁ ተጠርታችኋል።
፲፭ እናም በቀኖቻችሁ ሁሉ ንስሀን ወደ እነዚህ ህዝብ በመጮህ ብታገለግሉ፣ እናም አንድም ነፍስ ቢሆን እንኳን ወደ እኔ ዘንድ ብታመጡ፣ በአባቴ መንግስት ከእርሱ ጋር ደስታችሁ እንዴት ታላቅ ይሆናል!
፲፮ እናም አሁን፣ ወደ አባቴ መንግስት ባመጣችሁት አንድ ነፍስ ደስታችሁ ታላቅ ከሆነ፣ ወደ እኔ ብዙ ነፍሳትን ብታመጡ ደስታችሁ ምን ያህል ታላቅ ይሆናል!
፲፯ እነሆ፣ ወንጌሌ፣ እና አለቴ፣ እናም ማዳኔም በፊታችሁ ነው።
፲፰ እንደምትቀበሉ በማመን በእምነት አባቴን በስሜ ጠይቁ፣ እናም ለሰው ልጆች አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ የሚገልጠው መንፈስ ቅዱስ ይኖራችኋል።
፲፱ እናም እምነት፣ ተስፋ፣ እናም ለጋስነት ከሌላችሁ፣ ምንም ነገር ማድረግ አትችሉም።
፳ የዲያብሎስ ቤተክርስቲያን ካልሆነ በስተቀር ከማንም ቤተክርስቲያን ጋር አትከራከሩ።
፳፩ የክርስቶስ ስም በላያችሁ ላይ ውሰዱ እናም እውነትን በቅንነት ተናገሩ።
፳፪ እናም ስሜ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ ንስሀ የሚገቡና የሚጠመቁ እናም እስከመጨረሻው ድረስ የሚጸኑ፣ እንዲሁ ይድናሉ።
፳፫ እነሆ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ዘንድ የተሰጠ ስም ነው፣ እናም ሰው ሊድንበት የሚችል የተሰጠ ሌላ ስም የለምና፤
፳፬ ስለዚህ ይህን፣ ከአብ የተሰጠውን ስም ሁሉም ሰዎች በራሳቸው ላይ ሊወስዱ ይገባል፣ በመጨረሻውም ቀን በዚያ ስም ይጠራሉና፤
፳፭ ስለዚህ፣ የሚጠሩበትን ስም የማያውቁ ከሆነ፣ በአባቴ መንግስት ስፍራ ሊኖራቸው አይችልም።
፳፮ እናም አሁን፣ እነሆ፣ ለአይሁድ እና ለአህዛብ ወንጌሌን እንዲያውጁ የተጠሩ ሌሎች አሉ።
፳፯ አዎን፣ እንዲሁም አስራ ሁለቱ፤ እናም አስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቴ ይሆናሉ፣ እናም በላያቸው ላይ ስሜን ይወስዳሉ፤ እናም አስራ ሁለቱም ዓላማ በተሞላ ልብ ስሜን በላያቸው ለመውሰድ ፈቃድ ያላቸው ናቸው።
፳፰ እናም አላማ በተሞላ ልብ ስሜን በላያቸው ላይ ሊወስዱ ፈቃድ ካላቸው፣ ወደ አለም ሁሉ በመሄድ ወንጌሌን ለፍጥረታት ሁሉ ለማወጅ ተጠርተዋል።
፳፱ እናም በተጻፈው መሰረት በስሜ ለማጥመቅ የተሾሙት እነርሱ ናቸው፤
፴ እናም የተጻፈው በፊታችሁ አለላችሁ፤ ስለዚህ፣ በተጻፉት ቃላት መሰረት ልታከናውኑት ይገባል።
፴፩ እናም ለእናንተ ለአስራ ሁለቱ እናገራለሁ—እነሆ፣ ጸጋዬ ለእናንተ በቂ ነው፤ በፊቴ በቅንነት ተራመዱ እናም ኃጢአትንም አታድርጉ።
፴፪ እናም፣ እነሆ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ እናም እግዚአብሔር ለሰዎች በሰጠው ጥሪ እና ስጦታ መሰረት ካህናትን እና መምህራንን እንድትሾሙ፣ እና ወንጌሌንም እንድታውጁ ዘንድ፣ በእኔ የተሾማችሁት እናንት ናችሁ፤
፴፫ እናም እኔ፣ ጌታችሁ እና አምላካችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ተናግሬዋለሁ።
፴፬ እነዚህ ቃላት የእኔ እንጂ የሰው ወይም የሰዎች አይደሉም፤ ስለዚህ፣ የሰው እንዳልሆኑ እናም የእኔ እንደሆኑ ትመሰክራላችሁ፤
፴፭ ለእናንተ እነዚህን የሚናገራችሁ ድምፄ ነው፤ ለእናንተም የተሰጧችሁ በመንፈሴ ነው፣ እናም በኃይሌም አንዳችሁ ለሌላኛችሁ ልታነቧቸው ትችላላችሁ፤ እናም በሀይሌ ካልሆነ በስተቀር እነርሱ ሊኖሯችሁ ባትችሉም ነበር፤
፴፮ ስለዚህ፣ ድምፄን እንደሰማችሁ እና ቃላቴን እንደምታውቁ መመስከር ትችላላችሁ።
፴፯ እናም አሁን፣ እነሆ፣ ለአንተ ለኦሊቨር ካውድሪ እና እንዲሁም ለዴቪድ ዊትመር የተናገርኩት ነገር ፈቃድ ያላቸውን አስራ ሁለቱን ኃዋሪያት እንድትፈልጉ ኃላፊነትን ሰጥቻችኋለሁ፤
፴፰ እናም በፍላጎታቸው እና በስራቸው ታውቋቸዋላችሁ።
፴፱ እናም ባገኛችኋቸው ጊዜ እነዚህ ነገሮች ታሳይዋቸዋላችሁ።
፵ እናም ትሰግዳላችሁ እናም አባቴን በስሜ ታመልካላችሁ።
፵፩ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ንስሀ ሊገቡ እንደሚገባ እና መጠመቅም እንዳለባቸው በማለት ለአለም መስበክ ይኖርባችኋል፤
፵፪ ሁሉም ወንዶች ንሰሀ መገባት እና መጠመቅ አለባቸው እናም ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ነገር ግን ሴቶች፣ እናም ለተጠያቂነት እድሜ የደረሱ ልጆች ሁሉ ንሰሀ መግባት እና መጠመቅ አለባቸው።
፵፫ እናም፣ አሁን፣ ይህንን ከተቀበላችሁ በኋላ፣ በሁሉም ነገሮች ትእዛዛቴን መጠበቅ አለባችሁ።
፵፬ እናም፣ ወደ ንስሀ እንዲመጡ ብዙ ኃጢዓቶቻቸውንም በማሳመን፣ ወደ አባቴ መንግስት ይመጡ ዘንድ፣ በእጃችሁ ድንቅ ስራን በሰዎች ልጆች መካከል እሰራለሁ።
፵፭ ስለዚህ፣ የምሰጣችሁ በረከቶች ከሁሉም ነገሮች በላይ ናቸው።
፵፮ እናም ይህን ነገር ከተቀበላችሁ በኋላ፣ ትእዛዛቴን የማትጠብቁ ከሆነ በአባቴ መንግስት አትድኑም።
፵፯ እነሆ፣ እኔ፣ ጌታችሁ እና አምላካችሁ እና አዳኛችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሴ ሀይል ይህን ተናግሬዋለሁ። አሜን።