ክፍል ፻፩
በታህሳስ ፲፮ እና ፲፯፣ ፲፰፻፴፫ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ኦሀዮ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። በዚህ ጊዜ በሚዙሪ የተሰበሰቡት ቅዱሳን በታላቅ ስደት ላይ ነበሩ። ለአመፅ የተነሱ ህዝብ እነርሱን በጃክሰን የግዛት ክፍል ውስጥ ካሉት ቤቶቻቸው አሣደዋቸዋል እና አንዳንድ ቅዱሳን ራሳቸውን በቫን ቢዩረን፣ ላፈየት፣ እና ሬይ የግዛት ክፍሎች ውስጥ ለማሰባሰብ ሞከሩ፣ ነገር ግን ስደቱ ተከተላቸው። በዚያ ጊዜ የቅዱሳኑ ዋና ክፍል በክሌይ የግዛት ክፍል ሚዙሪ ውስጥ ነበር። በቤተክርስቲያኗ ግለሰቦች ላይም ብዙ የሞት ማስፈራሪያዎች ነበሩ። የጃክሰን የግዛት ክፍል ቅዱሳን የቤት እቃዎቻቸውን፣ ልብሶቻቸውን፣ ከብቶቻቸውን፣ እና ሌሎች የግል ንብረቶቻቸውን አጥተው ነበር፤ እና ብዙዎቹም እህሎቻቸውም ተደምስሠውባችው ነበር።
፩–፰፣ ቅዱሳን የተገሰጹት እና የተሰቃዩት በመተላለፋቸው ምክንያት ነው፤ ፱–፲፭፣ የጌታ ቁጣ በህዝብ ላይ ያርፋል፣ ነገር ግን ህዝቦቹ ይሰበሰባሉ እና ይፅናናሉ፤ ፲፮–፳፩፣ ፅዮን እና ስቴኳ ይመሰረታሉ፤ ፳፪–፴፩፣ በአንድ ሺህ አመት ጊዜ ህይወት ምን እንደሚመስል ተገልጿል፤ ፴፪–፵፪፣ በዚያም ጊዜ ቅዱሳን ይባረካሉ እናም ዋጋን ይቀበላሉ፤ ፵፫–፷፪፣ የልኡል ሰው እና የወይራ ዛፍ ምሳሌ የፅዮንን ችግር እና የመጨረሻም ደህንነትን ያመለክታል፤ ፷፫–፸፭፣ ቅዱሳኑ አብረው መሰብሰባቸውን ይቀጥሉ፤ ፸፮–፹፣ ጌታ የዩናትድ ስቴትን ህገ መንግስት መስርቷል፤ ፹፩–፻፩፣ ቅዱሳንን፣ እንደ ሴቷ እና እንዳልጸደቀው ዳኛ ምሳሌ መሰረት፣ ቅዱሳንን ለስቃያቸው ክፍያ በቅንነት ይጠይቁ።
፩ ስለተቸገሩት፣ ስለተሰደዱ፣ እና ከውርስ መሬታቸው ተወርውረው ስለወጡት ወንድሞቻችሁ እውነት እላችኋለሁ—
፪ እኔ ጌታ የተሰቃዩበት ስቃይ በመተላለፋቸው ምክንያት እንዲመጣባቸው ፈቅጃለሁ፤
፫ ግን የእኔ አደርጋቸዋለሁ፣ እና መጥቼ ጌጤን በምሰራበት በዚያን ቀን የእኔ ይሆናሉ።
፬ ስለዚህ አንድያ ልጁን ለመስዋት እንዲያቀርብ እንደታዘዘው አብርሐም መገሰፅና መፈተን አለባቸው።
፭ በግሰጻው የማይጸኑት፣ ግን የሚከዱኝ፣ ሁሉ ሊቀደሱ አይችሉም።
፮ እነሆ፣ እላችኋለሁ፣ ክርክር፣ እና ጸብ፣ እና ቅናት፣ እና ጠብ፣ እና የመቋመጥ እና የመመኘት ፈቃድ በመካከላቸው ነበር፤ ስለዚህ በእነዚህ ነገሮች ውርሶቻቸውን በክለዋል።
፯ የጌታ አምላካቸውን ድምፅ ለማድመጥ ይዘገዩ ነበር፤ ስለዚህ፣ ጌታ አምላካቸው ጸሎታቸውን ያደምጥ ዘንድ፣ በችግር ቀናቸውም ይልስላቸው ዘንድ ዘግይቷል።
፰ በሰላም ቀናቸው ምክሬን ትንሽ ዋጋ እንዳለው ተመለከቱት፤ ነገር ግን፣ በችግራቸው ቀን፣ ሲያስፈልጋቸው ይፈልጉኛል።
፱ እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአቶቻቸው ቢያስቆጡም፣ ለእነርሱ አንጀቴ በርህራሄ ተሞልቷል። ሙሉ ሁሉ አላስወግዳቸውም፤ እና በቁጣም ቀን በምህረት አስታውሳቸዋለሁ።
፲ መሀላ ገብቻለሁ፣ እና የቁጣዬ ጎራዴ ለህዝቤ እንደሚወድቅ ከዚህ በፊት በሰጠኋችሁ ትእዛዝም መሰረት አዋጁ ወጥቷል፣ እና እንዳልኩትም፣ ይሆናል።
፲፩ ቁጣዬ በሁሉም ህዝብ ላይ ያለሚዛን በቅርብም ይፈሳል፤ እና ይህን የማደርገውም የጥፋታቸው ጽዋ ሲሞላ ነው።
፲፪ እና በዚያ ቀን በመመልከቻ ማማ ላይ የሚገኙት ሁሉ፣ ወይም በሌላ ቃላት፣ የእኔ የሆኑት እስራኤል ሁሉ ይድናሉ።
፲፫ እና የተበተኑት ሁሉ ይሰበሰባሉ።
፲፬ እና የሚያዝኑትም ሁሉ መፅናናትን ያገኛሉ።
፲፭ እና ለስሜ ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡም ሁሉ አክሊል ይጫንላቸዋል።
፲፮ ስለዚህ፣ ፅዮንን በሚመለከት ልባችሁ ይፅናኑ፤ ሁሉም ስጋዎች በእጆቼ ውስጥ ናቸውና፤ ዕረፉ እና እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤
፲፯ ልጆቿ ቢበተኑም፣ ፅዮን ከስፍራዋ አትወጣም።
፲፰ የሚቀሩት እና ንጹህ ልብ ያላቸው፣ ይመለሳሉ እና እነርሱና ልጆቻቸው በዘለአለማዊ ደስታ መዝሙሮች፣ በፅዮን የፈረሱትን ለመገንባት ወደውርሳቸው ይመጣሉ—
፲፱ እና እነዚህ ነገሮች ሁሉ ነቢያት ይፈጽሙ ዘንድ ነው።
፳ እነሆም፣ ከመደብኩት ስፍራ በስተቀር የተመደበ ምንም ሌላ ስፍራ የለም፤ ወይም፣ ለቅዱሳን መሰብሰቢያ ስራ፣ ከመደብኩት ስፍራ ሌላ የሚመደብ ምንም ስፍራ የለም—
፳፩ ለእነርሱ በቂ ክፍል የማይገኝበት ቀን እስኪመጣም ድረስ፤ ከዚያም እኔ የምመድብላቸው ሌሎች ስፍራዎች አሉኝ፣ እና ለፅዮን ይጋርዱ እና ብርታቷም ይሆኑ ዘንድ፣ እነዚህም ካስማ ተብለው ይጠራሉ።
፳፪ እነሆ፣ ስሜን የሚጠሩ፣ እና በዘለአለማዊ ወንጌሌ መሰረት የሚያመልኩኝ ሁሉ እንዲሰበሰቡና በተቀደሱ ስፍራዎች እንዲቆሙ ፍቃዴ ነው፤
፳፫ እና ለሚመጣው ራዕይም ተዘጋጁ፣ በድንኳኔ ውስጥ፣ ምድርን የሚደብቀው፣ ቤተመቅደሴን የሚሸፍነው መጋረጃ ይወልቃል፣ እና ስጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ያዩኛል።
፳፬ እና የሚበሰብሱ እያንዳንዱ ነገሮች፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች፣ ወይም የሜዳ እንስሳት፣ ወይም የሰማይ አዕዋፋት፣ ወይም የባሕር ዓሦች ሁሉ ይነድዳሉ፤
፳፭ ደግሞም አለቶችም በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣሉ፤ እና እውቀቴና ክብሬ በምድር ሁሉ እንዲኖሩ፣ ሁሉም ነገሮች አዲስ ይሆናሉ።
፳፮ እና በዚያም ቀን የሰዎች ጥላቻ፣ የእንስሳትም ጥላቻ፣ አዎን፣ የሁሉም ስጋ ለባስ ጥላቻ ከፊቴ ይቋረጣል።
፳፯ እና በዚያም ቀን ማንም ሰው ያሻውን ቢጠይቅ፣ ይሰጠዋል።
፳፰ እና በዚያም ቀን ሰይጣንም ሰውን ለመፈተን ሀይል አይኖረውም።
፳፱ እና ሀዘንም አይኖርም ምክንያቱም ሞት የለምና።
፴ በዚያም ቀን ህጻን አርጅቶ ካልሆነ በቀር አይሞትም፤ እና ህይወቱም እንደ ዛፍ ህይወት ይሆናል፤
፴፩ እና ሲሞትም አያንቀላፋም፣ ያም በምድር ውስጥ አይቆይም፣ ነገር ግን በቅጽበት ዓይን ይለወጣል፣ እና ይነጠቃል፣ እና ማረፊያውም የከበረ ይሆናል።
፴፪ አዎን፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታ በሚመጣበት በዚያ ቀን፣ ሁሉንም ነገሮች ይገልጣል—
፴፫ ያለፉትን ነገሮች፣ እና ማንም ሰው የማያውቃቸውን የተደበቁ ነገሮችን፣ የምድር ነገሮችን፣ የተሰራበትን፣ እና አላማቸውን እና እቅዳቸውንም ይገልጣል—
፴፬ በጣም ውድ ስለሆኑ ነገሮች፣ ከበላይ ስላሉ ነገሮች፣ እና ከበታች ስላሉ ነገሮች፣ በምድር ውስጥ፣ እና በምድር ላይ፣ እና በሰማይ ውስጥ ስላሉ ነገሮችም ይገልጣል።
፴፭ እና ስለስሜ በመሰደድ የተሰቃዩት ሁሉ፣ እና በእምነት የሚፅናኑት፣ ምንም እንኳን ህይወታቸውን ስለእኔ እንዲሰጡ ቢጠሩም በዚህ ክብር ሁሉ ተካፋዮች ይሆናሉ።
፴፮ ስለዚህ፣ እስከሞትም አትፍሩ፤ በዚህ አለም ደስታችሁ ሙሉ አይደለምና፣ ነገር ግን በእኔ ደስታችሁ ሙላት አለው።
፴፯ ስለዚህ፣ ስለሰውነት አታስቡ፣ ወይም ስለሰውነት ህይወት፤ ነገር ግን ለነፍስ፣ እና ስለ ነፍስ ህይወትም አስቡ።
፴፰ እና በትዕግስት ነፍሶቻችሁን ታገኙ ዘንድ፣ የጌታን ፊት ዘወትር እሹ፣ እና ዘለአለማዊ ህይወትም ይኖራችኋል።
፴፱ ሰዎች ወደ ዘለአለማዊ ወንጌሌ ሲጠሩ፣ እና በዘለአለማዊነትም ቃል ኪዳንን ሲገቡ፣ እንደምድር ጨው እና የሰዎች ጣዕም ሆነው ይቆጠራሉ።
፵ የሰዎች ጣዕም እንዲሆኑም ይጠራሉ፤ ስለዚህ፣ ያ የምድር ጨው ጣዕሙን ካጣ፣ እነሆ፣ ጨውም ከዚያን ጊዜ በኋላ ከንቱ ይሆናል፣ ነገር ግን ይጣላል፣ እናም በሰዎች እግርም ይረገጣል።
፵፩ እነሆ፣ ስለፅዮን ልጆች፣ እንዲሁም ሁሉም ሳይሆን ብዙዎቹን፣ የሚመለከት ጥበብ ይህም ነው፤ ተላላፊዎች ሆነው ተገኝተዋል፣ ስለዚህ መገሰፅም ያስፈልጋቸዋል—
፵፪ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።
፵፫ አሁንም፣ ስለፅዮን ቤዛነት በሚመለከት ፈቃዴን ታውቁ ዘንድ፣ ምሳሌ አሳያችኋለሁ።
፵፬ አንድ መኮንን በጣም ምርጥ የሆነ ምድር ነበረው፤ እና ለአገልጋዮቹም እንዲህ ይላል፥ ወደ ወይን ስፍራዬ፣ እንዲሁም ወደዚህ በጣም ወደ ተመረጠ ምድር ሂዱ፣ እና አስራ ሁለት የወይራ ዛፎችንም ትከሉ፤
፵፭ እና ጠላት ለማጥፋትና የወይን ስፍራዬን ፍሬ ለራሳቸው ለመውሰድ ሲመጡ፣ የወይራ ዛፎቼን እንዳይሰበሩ ዘንድ፣ በማማው ላይ ጠባቂዎች ይሆኑላችሁ ዘንድ፣ በአካባቢያቸውም ጠባቂዎችን አኑሩ፣ እና በዙሪያውም የሚገኘውን ምድር በሚመለከት ማማን ስሩ።
፵፮ አሁን፣ የመኮንኑ አገልጋዮች ጌታቸው እንዳዘዛቸው ሄደው አደረጉ፣ እና የወይራ ዛፎችን ተከሉ፣ እና በዙሪያም ቅጥርን ሰሩ፣ እና ጠባቂም አስቀመጡ፣ እና ማማ መስራትም ጀመሩ።
፵፯ እና የዚህን መሰረት እየገነቡ እያሉ፣ እርስ በራሳቸው እንዲህ መባባል ጀመሩ፥ ለጌታዬ ይህ ማማ ምን ይሰራለታል አለው?
፵፰ እና ለብዙም ጊዜ እርስ በራሳቸው እንዲህ በመባባል ተማከሩ፥ የሰላም ጊዜ እንደሆነ እያየ፣ ጌታዬ ከዚህ ማማ ምን ጉዳይ አለው?
፵፱ ገንዘቡ ለለዋጮች አደራ ቢሰጥ አይሻልምን? ለእነዚህ ነገሮች ምንም የሚያስፈልጉ አይደሉምና።
፶ እና እርስ በራሳቸው ባለመስማማት እያሉ በጣም ሀኬተኛ ሆኑ፣ እና የጌታቸውንም ትእዛዝ አላደመጡምና።
፶፩ እና ጠላትም በምሽት መጣ፣ እና ቅጥሩንም ሰበረ፤ እና የመኮንኑ አገልጋዮችም ተነሱ እና ፈሩ፣ እና ሸሹ፤ እና ጠላትም ስራቸውን አፈረሰው፣ እና የወይራ ዛፎችንም ሰበረ።
፶፪ አሁን፣ እነሆ፣ መኮንኑ፣ የወይኑ ስፍራ ጌታ፣ አገልጋዮቹን ጠራ፣ እናም አላቸው፣ ለምን! የዚህ ታላቅ ጥፋት ምክንያት ምንድን ነው?
፶፫ እና የወይን ስፍራውን ከተከላችሁ፣ እና አጥርንም በዙሪያው ካጠራችሁ፣ እና በግምቡ ላይ ጠባቂን ካስቀመጣችሁ በኋላ ማማን ስሩ፣ እና በማማውም ጠባቂን አስቀምጡ፣ እና የወይን ስፍራዬንም ጠብቁ፣ እና ጠላትም እንዳይመጣባችሁ አታንቀላፉ ብዬ እንዳዘዝኳችሁ አታደርጉም ነበርን?
፶፬ እነሆም፣ በማማው ላይ የነበረው ጠባቂ በሩቅ እያለ ጠላትን ገና በሩቅ ሳለ ያየው ነበር፤ ከዚያም ትዘጋጁ እና ጠላትንም አጥሩን ከመስበር ልታቆሙት፣ እና ከደምሳሹ እጆችም የወይን ስፍራዬን ልታድኑ በቻላችሁ ነበር።
፶፭ እና የወይን ስፍራው ጌታ ከአገልጋዮቹ ለአንዱ አለ፥ ሂድ እና የሚቀሩትን አገልጋዮቼን ሰብስብ፣ እና የቤቴ ብርታት የሆኑትን ጀግኖቼን፣ ወጣት ወንዶቼን፣ እና ከአገልጋዮቼ መካከልም ጎልማሳዎች የሆኑትን የቤቴን ብርቱዎች ሁሉ ውሰድ፣ እንዲቀሩ የመደብኳቸውን ብቻ አስቀር፤
፶፮ እና በቀጥታም ወደወይን ስፍራ መሬቴም ሂድ፣ እና የወይን ስፍራዬን አድን፤ የእኔ ነውና፤ በገንዘብም ገዝቼዋለሁና።
፶፯ ስለዚህ፣ ወደ መሬቴ በቀጥታ ሂድ፣ የጠላቶቼን ግንብ ስበር፤ ማማቸውንም ጣል፣ እና ጠባቂያቸውንም በትን።
፶፰ እና አንተን ለመቃወም እስከተሰበሰቡ ድረስ፣ በአጭር ጊዜ ከሚቀረው ቤቴ ጋር መጥቼና መሬቴን እንድወስደው ዘንድ፣ በጠላቶቼ ላይ ፍረድልኝ።
፶፱ እና አገልጋዩም ለጌታው አለ፥ እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ?
፷ እና ለአገልጋዩም አለ፥ በቀጥታ ሂድ፣ እና እንደፈቀድኩትም ያዘዝኩህን ማንኛቸውን ነገሮች ሁሉ አድርግ፤
፷፩ እና ይህም—በቤቴ መካከል ታማኝና ብልህ መጋቢ፣ በመንግስቴም ውስጥ ገዢ በሆንከው በአንተ ላይ ማህተሜ እና በረከቴ ይሆናል።
፷፪ እና አገልጋዩም በቀጥታ ሄደ፣ እና ጌታው ያዘዘውን ማንኛቸውን ነገሮች ሁሉ አደረገ፤ እና ከብዙ ቀናትም በኋላ ሁሉም ነገሮች ተፈጸሙ።
፷፫ ዳግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በትክክል እና በተገቢ መንገድ ወደ ደህንነታቸው ለመመራት ፈቃደኛ እስከሆኑ ድረስ፣ ስለቤተክርስቲያናት ሁሉ የሚመለከት ጥበቤን አሳያችኋለሁ—
፷፬ የቅዱሳኖቼ መሰብሰቢያ ስራ ይቀጥል ዘንድ፣ በስሜም በቅዱስ ቦታዎች እገነባቸው ዘንድ፤ የመከር ጊዜ መጥቷል፣ እና ቃሌም መፈጸም አለበት።
፷፭ ስለዚህ፣ ወደአባቴ መንግስት እንደ ስራው ደመወዝን ልሰጠው ስመጣ፣ በስንዴዎች እና እንክርዳዶች ምሳሌ መሰረት፣ ስንዴዎች በጎተራው እንዲሰበሰቡ እና የዘለአለም ህይወት ያገኙ ዘንድ፣ እና በሰለስቲያል ክብር አክሊል እንዲሰጣቸው፣ ህዝቤን መሰብሰብ አለብኝ፤
፷፮ በማይጠፋ እሳት ይቃጠሉ ዘንድ፣ እንክርዳዶችም አንድ ላይ ይታሰራሉ፣ እና ማሰሪአቸውም ጠንካራ ይሆናል።
፷፯ ስለዚህ፣ በመደብኩት ስፍራ አብረው ለመሰብሰብ ይቀጥሉ ዘንድ፣ ለሁሉም ቤተክርስቲያኖች ትእዛዝን እሰጣለሁ።
፷፰ ይህም ቢሆን፣ በፊቱ ትእዛዝ እንዳልኳችሁ፣ መሰብሰቢያችሁ በችኮላ ወይም በሽሽት አይሁን፤ ነገር ግን በፊታችሁ ሁሉም ነገሮች ይዘጋጁ።
፷፱ እና ሁሉም ነገሮች በፊታችሁ ይዘጋጁ ዘንድ፣ ስለእነዚህ ነገሮች የሰጠኋችሁን ትእዛዝ አክብሩ—
፸ እንዲህ ያለውን ወይም የሚያስተምረውን፣ ለቅዱሳኔ መሰብሰብ መጀመሪያ እንዲሆን፣ የፅዮን ምድር እንዲሆን በመደብኩት ምድር አካባቢ በገንዘብ ለመገዛት የሚቻለውን መሬቶችን ሁሉ በገንዘብ ለመግዛት ያለውን ወይም የሚያስተምረውን፤
፸፩ በጃክሰን የግዛት ክፍል፣ እና በዙሪያው በሚገኙት የግዛት ክፍሎች፣ ሊገዛ የሚቻለውን መሬት ሁሉ፣ እና የሚቀረውን በእጄ ተዉት።
፸፪ አሁን እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሉም ቤተክርስቲያናት ገንዘባቸውን ሁሉ አብረው ይሰብስቡ፤ በችኮላ ሳይሆን፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በጊዜአቸው ይደረጉ፤ እና በፊታቸሁ ሁሉንም ነገሮች እንዲዘጋጁ አድርጉ።
፸፫ እና የተከበሩ ሰዎች፣ እንዲሁም ብልህ ሰዎች፣ ይመደቡ፣ እና እነዚህን መሬቶች እንዲገዙ ላኳቸው።
፸፬ እና በምስራቅ አገሮች ያሉ ቤተክርስቲያናትም፣ ከተመሰረቱ በኋላ፣ ይህን ምክር ካደመጡ መሬቶችን መግዛትና መሰብሰብ ይችላሉ፤ እና በዚህም መንገድ ፅዮንን ይመስርቱ።
፸፭ አሁንም፣ በስሜ የሚጠሩት ቤተክርስቲያናት ድምጼን ለማድመጥ ፈቃደኞች ቢሆኑ፣ ፅዮንን ለማዳን እና፣ ደግሞም እንዳይጣሉ የፈረሱትን ስፍራዎቿን ለመመስረት በብቁ፣ እንዲሁም በሚትረፈረፍ፣ ተከማችቷል።
፸፮ ደግሞም እላችኋለሁ፣ በጠላቶቻቸው የተበተኑትም እንደገዢ በተመደቡት እጆች እና በእናንተ ላይ ስልጣን ባላቸው ሰዎች በኩል ለስቃያቸው ክፍያ፣ እና ለቤዛነት በቅንነት እንዲጠይቁ ፍቃዴ ነው—
፸፯ የፅድቅ እና ቅዱስ በሆኑ መሰረታዊ መርሆች፣ እንዲመሰረት እና ለሁሉም ስጋ ለባሽ መብት እና ጥበቃ እንዲደገፍ በፈቀድኩት በህዝብ ህግጋት እና ህገ መንግስት መሰረት፤
፸፰ ሁሉም ሰው ስለወደፊቱ፣ በሰጠሁት ስነምግባር ምርጫ መሰረት፣ በትምህርትና በመሰረታዊ መርሆችም ይሰራ ዘንድ፣ እያንዳንዱም ሰው ለራሱ ኃጢአቶች በፍርድ ቀን ይጠየቅበት ዘንድ ለቤዛነት በቅንነት እንዲጠይቁ ፍቃዴ ነው።
፸፱ ስለዚህ፣ ማንም ሰው ለሌላ በባሪያነት መተሳሰሩ ትክክል አይደለም።
፹ እና ለዚህ አላማ የዚህን ህገ መንግስት፣ ለዚህ አላማ ባነሳኋቸው የጥበብ ሰዎች እጅ አማካይነት፣ መስርቼአልሁ እና ምድሩንም ደም በማፍሰስ አድኜዋለሁ።
፹፩ አሁን፣ የፅዮን ልጆችን ከምን ጋር አመሳስላቸዋለሁ? ሰዎች ሳይታክቱ ዘወትር መጸለይ አለባቸውና፣ እንዲህ ከሚለው የሴቷ እና ፍትሀዊ ያልሆነ ዳኛ ምሳሌ ጋር አመሳስላቸዋለሁ—
፹፪ በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበር።
፹፫ በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፣ ወደ እርሱም እየመጣች ከጠላቴ ፍረድልኝ ትለው ነበር።
፹፬ ለአያሌ ቀንም ይህን ያደርግ ዘንድ አልወደደም፣ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ፥ ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፣ ይህች መበለት ስለምታደክመኝ ዘወትር እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ አለ።
፹፭ የፅዮንንም ልጆች በዚህም እመስላቸዋለሁ።
፹፮ በዳኛው እግር ላይም በቅንነት ይማጸኑ፤
፹፯ እና ካልሰማቸውም፣ በአስተዳዳሪው እግር ላይም በቅንነት ይማጸኑ፤
፹፰ አስተዳዳሪውም የማያደምጣቸው ከሆነ፣ በፕሬዘደንት እግር ላይም በቅንነት ይማጸኑ፤
፹፱ ፕሬዘደንቱም የማያደምጣቸው ከሆነ፣ ከዚያም ጌታ ይነሳል እና ከተሰወረበትም ስፍራ ይመጣል፣ እና በንዴቱም ህዝብን ያስጨንቃቸዋል፤
፺ በመዓቱም፣ እና በሀይለኛ ቁጣው፣ በጊዜው ክፉዎችን፣ ታማኝ ያልሆኑትን፣ እና ጻድቅ ያልሆኑትን መጋቢዎች ያገልላል፣ እና እድላቸውንም ከግብዞችና ከማያምኑት ጋር ያደርግባቸዋል፤
፺፩ እንዲሁም በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት በሆነበት፣ ወደ ድቅድቅ ጨለማ።
፺፪ ስለዚህ ጆሮዎቻቸው ለልቅሶዎቻችሁ ይከፈቱ ዘንድ፣ እኔ ለእነርሱ መሀሪ እሆን ዘንድ፣ እነዚህም ነገሮች እንዳይመጣባቸው ጸልዩ።
፺፫ ሁሉም ሰዎች ያለምክንያት ይቀሩ ዘንድ፣ ያልኳችሁ ሁሉ መፈጸም አለባቸው፤
፺፬ ብልህ ሰዎች እና መሪዎች ያላሰቧቸውን ነገሮች ይሰሙ እና ያውቁ ዘንድ መሆን አለባቸው፤
፺፭ ስራዬን ለማምጣት፣ እና ስራዬን፣ ማለት እንግዳ ስራዬን፣ እቀጥል ዘንድ፣ ሰዎችም በጽድቅ እና ኃጢአት መካከል ለመለየት ይችሉ ዘንድ ነው፣ ይላል ጌታ።
፺፮ ደግሞም፣ እላችኋለሁ፣ አገልጋዬ ስድኒ ጊልበርት ለህዝቤ የመደብኩትን የጎተራ ስፍራዬን ወደ ጠላቶቼ እጆች ውስጥ መሸጡ ትእዛዜን እና ፈቃዴን የሚቃረን ነው።
፺፯ በጠላቶቼ፣ ራሳቸውንም በስሜ በሚጠሩት ፈቃድ፣ እኔ የመደብኩት ይራከስ ዘንድ አትፍቀዱ።
፺፰ ይህም በእኔና በህዝቤ ላይ የተደረገው ከፍተኛ እና አሳዛኝ ኃጢአት ነውና፣ በዚህም ምክንያት በአህዛብ ላይ በቅርብ የሚወድቁትን እነዚያን ነገሮች አውጃለሁ።
፺፱ ስለዚህ፣ ምንም እንኳን እንዲኖሩባቸው ባይፈቀድላቸውም፣ ህዝቤ ለእነርሱ የመደብኩላቸውን እንደገና እንዲይዙ፣ እና በመብትም እንዲይዙ ፍቃዴ ነው።
፻ ይህም ቢሆን፣ በዚያ አይኖሩም አላልኩም፤ ለመንግስቴ ብቁ የሆኑ ፍሬዎችና ስራዎች እስካመጡ ድረስ በእነዚያም ላይ ይኖራሉ።
፻፩ ይገነባሉ፣ እና ሌላም አይወርሰውም፤ የወይን ስፍራንም ይተክላሉ፣ እና የእነዚህን ፍሬዎቻቸውንም ይበላሉ። እንዲህም ይሁን። አሜን።