ክፍል ፻፯
በሚያዝያ ፲፰፻፴፭ (እ.አ.አ.) አካባቢ፣ በከርትላንድ ኦሀዮ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል ስለክህነት የተሰጠ ራዕይ። ይህ ራዕይ የተመዘገበው በ፲፰፻፴፭ (እ.አ.አ.) ቢሆንም፣ ከቁጥር ፷ እስከ ፻ አብዛኛዎች በህዳር ፲፩፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.) በጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጡ ራዕዮችን የሚያጠቃልሉ ነበሩ። ይህ ክፍል የአስራ ሁለት ቡድንን በየካቲት እና በመጋቢት ፲፰፻፴፭ (እ.አ.አ.) ከተደራጀበት ጋር የተገናኘ ነው። ነቢዩ ምናልባት በቡድናቸው የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን በግንቦት ፫፣ ፲፰፻፴፭ (እ.አ.አ.) ለመሄድ በሚዘጋጁበት ጊዜ በነበሩት ፊት ይህን ሳያቀርበው አልቀረም።
፩–፮፣ ሁለት ክህነቶች አሉ፥ መልከ ጼዴቅ እና አሮናዊ፤ ፯–፲፪፣ የመልከ ጼዴቅ ክህነትን የያዙት በቤተክርስቲያኗ የሀላፊነት ስፍራዎች ሁሉ ለማስተዳደር ሀይል ይኖራቸዋል፤ ፲፫–፲፯፣ ኤጲስ ቆጶስ ውጪውን ሥርዓት የሚያስተዳድረውን አሮናዊ ክህነትን ያስተዳድራል፤ ፲፰–፳፣ የመልከ ጼዴቅ ክህነት የመንፈሳዊ በረከቶችን ሁሉ ቁልፎች ይዟል፤ የአሮናዊ ክህነት የመላዕክትን አገልግሎት ቁልፎችን ይዟል፤ ፳፩–፴፰፣ በአንድነት እና በፅድቅ ውሳኔዎቻቸው የሚደረጉባቸው ቀዳሚ አመራር፣ አስራ ሁለቱ፣ እና ሰባዎች የአመራር ቡድኖችን ይመሰርታሉ፤ ፴፱–፶፪፣ የአባቶች አለቃ ስርዓትም ከአዳም እስከ ኖህ ጀምሮ ተመስርቷል፤ ፶፫–፶፯፣ የጥንት ቅዱሳን በአዳም-ኦንዳይ-አማን ተሰበሰቡ፣ እና ጌታ በእነርሱም ታየ፤ ፶፰–፷፯፣ አስራ ሁለቱ የቤተክርስቲያኗ ሀላፊዎች በስርዓት ያቀናጁ፤ ፷፰–፸፮፣ ኤጲስ ቆጶሳት እንደ እስራኤል ቋሚ ዳኛ ያገለግላሉ፤ ፸፯–፹፬፣ ቀዳሚ አመራርና አስራ ሁለቱ እንደ ቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ ዳኝነት ስርዓቱን ይመሰርታሉ፤ ፹፭–፻፣ የክህነት ፕሬዘደንቶች የየሀላፊነት ቡድኖቻቸውን ያስተዳድራሉ።
፩ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ፣ የሌዊ ክህነትን ጨምሮ፣ በስም መልከ ጼዴቅና፣ አሮናዊ የሚባሉ ሁለት ክህነቶች አሉ።
፪ የመጀመሪያው የመልከ ጼዴቅ ክህነት ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት መልከ ጼዴቅ ታላቅ ሊቀ ካህን ስለነበር ነው።
፫ ከእርሱ ቀን በፊት እንደ እግዚአብሔር ልጅ ስርዓት ቅዱስ ክህነት ተብሎ የሚጠራ ነበር።
፬ ነገር ግን ለኃያል ጌታ ስም ክብር ወይም አምልኮ፣ ስሙን እጅግ በጣም በመደጋገም መጠቀምን ለማስወገድ፣ የጥንት ጊዜ ቤተክርስቲያኗ የነበሩት እነርሱ፣ ያን ክህነት የመልከ ጼዴቅ ክህነት በማለት ወይም በመልከ ጼዴቅ ስም ጠሩት።
፭ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ያሉ ሌሎቹ ስልጣናት ወይም ሀላፊነቶች ሁሉ ከዚህ ክህነት ጋር የተያያዙ ናቸው።
፮ ነገር ግን ሁለት ክፍሎች ወይም ዋና ክፍሎች አሉ—አንዱ የመልከ ጼዴቅ ክህነት ስልጣን፣ እና ሌላው አሮናዊ ወይም ሌዊ ክህነት ነው።
፯ የሽማግሌ ሀላፊነት ከመልከ ጼዴቅ ክህነት በታች የሚሆን ነው።
፰ የመልከ ጼዴቅ ክህነት የፕሬዘደንትነት አመራርን ይይዛል፣ እና በመንፈሳዊ ነገሮች ለማስተዳደር፣ በአለም ዘመኖች ሁሉ በቤተክርስቲያኗ ሀላፊነቶች ላይ ሁሉ ሀይል እና ስልጣን አለው።
፱ እንደ መልከ ጼዴቅ ስርዓት ሁሉ፣ የታላቅ ክህነት አመራር በቤተክርስቲያኗ ውስጥ በሚገኙት ሀላፊነቶች ሁሉ የማስተዳደር መብት አለው።
፲ ሊቀ ካህናት እንደ መልከ ጼዴቅ ስርዓት፣ በቀዳሚ አመራር መመሪያ በመንፈሳዊ ነገሮች በማስተዳደር ሀላፊነታቸው፣ እና ደግሞም በሽማግሌ አመራር፣ በካህን አመራር (የሌዊው ስርዓት)፣ በመምህርነት፣ በዲያቆንነት፣ እና በአባል ሀላፊነቶች ለማስተዳደር መብት አላቸው።
፲፩ ሊቀ ካህን በማይኖርበት ጊዜ ሽማግሌ በእርሱ ምትክ ማስተዳደር ይችላል።
፲፪ ሊቀ ካህን እና ሽማግሌ፣ ከቤተክርስቲያኗ ቃል ኪዳናት እና ትእዛዛት በመስማማት፣ በመንፈሳዊ ነገሮች ያስተዳድሩ፤ እና ከፍተኛ ባለስልጣናት በማይኖሩበት ጊዜ፣ በእነዚህ የቤተክርስቲያኗ ሀላፊነቶች ሁሉ የማስተዳደር ሀላፊነት አላቸው።
፲፫ ሁለተኛው ክህነት አሮናዊ ክህነት ተብሎ ይጠራል፣ ምክንያቱም በአሮን እና በዘሩ፣ በትውልዶቻቸው ሁሉ፣ የተሰጣቸው ነበርና።
፲፬ አነስተኛው ክህነት ተብሎ የሚጠራበት ምክንያትም ከታላቁ፣ ወይም ከመልከ ጼዴቅ ክህነት፣ ጋር የተያያዘ ስለሆነ እና ለውጪአዊ ስርዓቶችን ለማስተዳደር ሀይል ስላለው ነው።
፲፭ የኤጲስ ቆጶስ አመራርም የዚህ ክህነት ስልጣን አመራር ነው፣ እና የዚህንም ቁልፎች ወይም ስልጣን ይዟል።
፲፮ የአሮን እውነተኛ ተወላጅ ካልሆነ በስተቀር፣ ማንም ሰው ለዚህ ሀላፊነት፣ ወይም የዚህን ክህነት ቁልፎች ለመያዝ፣ ህጋዊ መብት የለውም
፲፯ ነገር ግን እንደ የመልከ ጼዴቅ ክህነት ሊቀ ካህን በአነስተኛ ሀላፊነቶች ሁሉ ለማስተዳደር ስልጣን ስላለው፣ የአሮን እውነተኛ ተወላጅ በማይገኝበት ጊዜ፣ በመልከ ጼዴቅ ክህነት አመራር በኩል ለዚህ ሀይል ከተጠራና ከተለየ እና ከተሾመ በኋላ በኤጲስ ቆጶስ ሀለፊነት ለማስተዳደር ይችላል።
፲፰ የከፍተኛው፣ ወይም የመልከ ጼዴቅ ክህነት፣ ሀይል እና ስልጣን በቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ በረከቶች ላይ ሁሉ ቁልፎችን መያዝ ነው።
፲፱ በተጨማሪም፣ የመንግስተ ሰማያትን ሚስጥራት ለመቀበል ልዩ መብት እንዲኖረው፣ ሰማያት ለእነርሱ እንዲከፈቱላቸው፣ ከበኩሩ ቤተክርስቲያንና ከአጠቃላይ ተሰብሳቢዎች ጋር እንዲገናኝ፣ እና ከእግዚአብሔር አብ እና ከአዲስ ኪዳን አማላጅ ከሆነው ከኢየሱስ ጋር መገናኘትን እና በእነርሱም መገኘት ለመደሰት ነው።
፳ የአነስተኛው ክህነት፣ ወይም የአሮናዊ ክህነት፣ ሀይል እና ስልጣን፣ ከቃል ኪዳናት እና ትእዛዛት ጋር በመስማማት፣ የመላእክትን አገልግሎት ቁልፎች ለመያዝ እና የውጪአዊ ስርዓቶች የሆኑትን የወንጌሉን ፊደል እና ለኃጢአት ስርየት የንስሐ ጥምቀትን ለማስተዳደር ነው።
፳፩ ስለአስፈላጊነታቸውም ፕሬዘደንቶች፣ ወይም ከተለያዩ ከእነዚህ ሁለት ክህነቶች ውስጥ በተላያዩ ሀላፊነቶች ከተሾሙት መካከል የሚመጡ ወይም የሚሾሙ መሪዎች አሉ።
፳፪ ከመልከ ጼዴቅ ክህነትም፣ ሶስቱ ሊቀ ካህን መሪዎች በቡድኑ ተመርጠው፣ ለሀለፊነቱ ተመድበውና ተሹመው፣ እና በቤተክርስቲያኗ እምነት፣ ታማኝነት፣ እና ጸሎት ተደግፈው የቤተክርስቲያኗን አመራር ቡድን ይመሰርታሉ።
፳፫ ተጓዥ አስራ ሁለቱ አማካሪዎች አስራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ወይም ለአለም ሁሉ የክርስቶስ ስም ልዩ ምስክሮች፣ ተብለው ተጠርተዋል—በዚህም በጥሪአቸው ሀላፊነታቸው ከቤተክርስቲያኗ ሌሎች ሀላፊዎች ጋር ይለያያሉ።
፳፬ እና ከዚህ በፊት ከተጠቀሱት ሶስት ፕሬዘደንቶች ጋረ እኩል ስልጣን እና ሀይል ያለው ቡድንም ይሰራሉ።
፳፭ ሰባዎቹ ወንጌልን እንዲሰብኩ፣ እና ለአህዛብና በአለም ሁሉ ልዩ ምስክሮች እንዲሆኑ ተጠርተዋል—በዚህም በጥሪአቸው ሀላፊነታቸው ከቤተክርስቲያኗ ሌሎች ሀላፊዎች ጋር ይለያያሉ።
፳፮ እና ከተጠቀሱት አስራ ሁለቱ ልዩ ምስክሮች ወይም ሐዋርያት ጋር እኩል ስልጣን እና ሀይል ያለው ቡድንም ይሰራሉ።
፳፯ በማንኛቸውም በእነዚህ ቡድኖች የሚያደርጉ እያንዳንዱ ውሳኔዎች በአንድ ድምፅ መሆን አለባቸው፤ ይህም ማለት፣ እርስ በራስ ውሳኔዎቻቸው አንድ ሀይል ወይም ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ የእያንዳንዱ ቡድን እያንዳንዱ አባል በውሳኔው መስማማት አለባቸው—
፳፰ ሁኔታዎች በተቃራኒ እንዲሆን በማያስችሉበት ጊዜም አብላጫዎቹ ቡድንን መስራት ይችላሉ—
፳፱ ጉዳዩ ይህ ካልሆነ በስተቀር፣ ውሳኔዎቻቸው በመልከ ጼዴቅ ስርዓት ተሹመው የነበር እና ጻድቅና ቅዱስ ሰዎች እንደነበሩት የጥንት ሶስት ፕሬዘደንቶች ውሳኔዎች እንደነበራቸው አንድ አይነት በረከቶች መብት አይኖራቸውም።
፴ የእነዚህ ቡድኖች፣ ወይም የማንኛቸውም፣ ውሳኔዎችም ሁሉ ፅድቅ፣ በቅድስና፣ እና ልብን በማዋረድ፣ በየዋህነትና በትዕግስት፣ እና በእምነት፣ እና በበጎነት፣ እና በእውቀት፣ ራስን በመግዛት፣ በመፅናት፣ እግዚአብሔርን በመምሰል፣ በወንድማማች መዋደድ እና በፍቅር ይድረሱ፤
፴፩ ምክንያቱም የተስፋ ቃሉ እነዚህ ነገሮች በእነርሱ አብዝተው የሚገኙ ቢሆን በጌታ እውቀት ፍሬ የሌላቸው አይሆኑም የሚል ነውና።
፴፪ እና እነዚህ ቡድኖች ማንኛውንም ውሳኔ ያለፅድቅ ባለመሆን የሰሩበት ጉዳይ ካለ፣ ይህም የቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ ባለስልጣናት በሆኑት በተለያዩ ቡድኖች አጠቃላይ ተሰብሳቢዎች ፊት ይቅረብ፤ አለበለዚያ ለውሳኔአቸው ምንም ይግባኝ አይኖርም።
፴፫ አስራ ሁለቱ፣ በሰማይ ከተመሰረተው ጋር በመስማማት፣ መጀመሪያ ወደ አህዛብ እና ሁለተኛም የአይሁዶች ቤተክርስቲያኗን ለመገንባት እና የእርሷን ጉዳዮች በሀገሮች ውስጥ ሁሉ ለመቆጣጠር፣ በቤተክርስቲያኗ አመራር መሪነት በጌታ ስም በማስተዳደር የሚጓዙ ከፍተኛ ሸንጎዎች ናቸው።
፴፬ ሰባዎች፣ በአስራ ሁለቱ ወይም በሚጓዙት ከፍተኛ ሸንጎ አመራር በኩል፣ መጀመሪያ ወደ አህዛብ እና ሁለተኛም ወደ አይሁዶች፣ ቤተክርስቲያኗን በመገንባት እና የእርሷን ጉዳዮች በሀገሮች ውስጥ ሁሉ በመቆጣጠር በጌታ ስም ይስሩ—
፴፭ አስራ ሁለቱ፣ መጀመሪያ ወደ አህዛብ እና ሁለተኛም ወደ አይሁዶች፣ በመላክ፣ ቁልፎችን በመያዝ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በማወጅ በሮችን ለመክፈት ተልከዋል።
፴፮ በፅዮን ካስማዎች የአካባቢው ከፍተኛ ሸንጎዎች በቤተክርስቲያኗ ጉዳይ ላይ፣ በውሳኔዎቻቸው ሁሉ ከአመራር ቡድን ወይም ከተጓዥ ከፍተኛ ሸንጎ ጋር እኩል ስልጣን ያላቸው ቡድኖች ያቋቁሙ።
፴፯ በፅዮን ውስጥ ያሉት ከፍተኛ ሸንጎ በፅዮን ካስማ ውስጥ ካሉት የአስራ ሁለቱ ቡድኖች ጋር በውሳኔዎቻቸው ሁሉ፣ በቤተክርስቲያኗ ጉዳዮች እኩል ስልጣን ያለው ቡድን ያቋቁማሉ።
፴፰ ለመስበክ እና ወንጌሉን ለማስተዳደር እርዳታ ሲያስፈልጋቸው፣ በማንም ሌሎች ምትክ፣ ሰባዎችን መጥራት የሚጓዙት ከፍተኛ ሸንጎ ሀላፊነት ነው።
፴፱ በትልቁ የቤተክርስቲያኗ ቅርንጫፎች ውስጥ ሁሉ፣ በራዕይ እንደሚመደቡላቸው፣ ወንጌል ሰባኪዎችን መሾም የአስራ ሁለቱ ሀላፊነት ነው—
፵ የዚህ ክህነት ስርዓት የሚረጋገጠው ከአባት ወደ ወንድ ልጅ በሚተላለፍ፣ እና ቃል ኪዳን ለተገባላቸው ለእውነተኛ ተወላጆች ምርጥ ዘርም የሚገባ ነበር።
፵፩ ይህ ስርዓት በአዳም ዘመን የተቋቋመ፣ እና እንደዚህም በዝርያ የተላለፈም ነበር።
፵፪ በስልሳ ዘጠኝ አመቱ በአዳም ወደ ተሾመውና (ከአዳም) ከመሞቱ ሶስት አመት በፊት ወደተባረከው፣ እና ትውልዶቹ በጌታ ምርጥ እንዲሆኑና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንዲጠበቁ በአባቱ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ወደ ተቀበለው ወደ ሴት ከአዳም ሄደ፤
፵፫ እርሱ (ሴት) ፍጹም ሰው ስለነበር፣ እና በአምሳያነቱም እንደ አባቱ መልክ ስለነበር፣ በዚህም ምክንያት በሁሉም ነገሮች አባቱን ይመስል ነበር፣ እና ከእርሱም የሚለየው በእድሜ ብቻ ነበር።
፵፬ ኢኖስም በአንድ መቶ ሰላሳ አራት አመት እና አራት ወር እድሜው በአዳም እጅ ተሾመ።
፵፭ እግዚአብሔር ቃይናን በአርባ አመቱ በዱር ውስጥ ጠራው፤ በሸዶላማቅ ስፍራ በመጓዝም ከአዳም ጋር ተገናኘ። ሹመቱን ሲቀበል እድሜው ሰማንያ ሰባት ነበር።
፵፮ መለልኤል ደግሞም በባረከው በአዳም እጅ ሲሾም እድሜው አራት መቶ ዘጣና ስድስት አመትና ሰባት ቀን ነበር።
፵፯ ያሬድም ደግሞ በባረከው በአዳም እጅ ሲሾም እድሜው ሁለት መቶ አመት ነበር።
፵፰ ሔኖሕ በአዳም እጅ ሲሾም ሀያ አምስት አመቱ ነበር፤ እና በስልሳ አምስት አመቱም አዳም ባረከው።
፵፱ እና ጌታን አየ፣ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፣ እና ሁልጊዜ በጌታ ፊት ነበር፤ እና ለሶስት መቶ ስልሳ አምስት አመታት አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፣ በሚቀየርበት ጊዜ እድሜው አራት መቶ ሰላሳ ነበር።
፶ ማቱሳላ በአዳም እጅ ሲሾም አንድ መቶ አመቱ ነበር።
፶፩ ላሜህ በሴት እጅ ሲሾም እድሜው ሰላሳ ሁለት ነበር።
፶፪ ኖህ በማቱሳላ እጅ ሲሾም አስር አመቱ ነበር።
፶፫ ከአዳም ሞት ሶስት አመት በፊት፣ ሊቀ ካህናት የነበሩትን ሴትን፣ ኢኖስን፣ ቃይና፣ መለልኤልን፣ ያሬድን፣ ሄኖህን፣ እና ማቱሳላን ጻድቅ ከነበሩ ትውልዶቻቸው ጋር ወደ አዳም-ኦንዳይ-አማን ሸለቆ ጠራቸው፣ እና በዚያም በረከቱን ሰጣቸው።
፶፬ እና ጌታን አዩት፣ እና ተነስተውም አዳምን ባረኩ፣ እና ሚካኤል፣ ልኡል፣ የመላእክት አለቃ ብለው ጠሩት።
፶፭ እና ጌታ አዳምን አፅናናው፣ እንዲህም አለው፥ መሪ አድርጌሀለሁ፤ የአህዛብ ሙላትም ከአንተ ይመጣሉ፣ እና በእነርሱም ላይ ለዘለአለም ልዑል ነህ።
፶፮ እና አዳም በተሰበሰቡት መካከል ቆመ፤ እና ምንም እንኳን በእድሜው ያጎነበሰ ቢሆንም፣ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ፣ እስከመጨረሻ ትውልዱ ድረስ ለዘሩ ምን እንደሚደርስባቸው ተነበየ።
፶፯ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በሔኖህ መፅሐፎች ውስጥ ተፅፈው ነበር፣ እና በጊዜአቸውም ይመሰከሩባቸዋል።
፶፰ የቤተክርስቲያኗን ሌሎች ሀላፊዎች መሾም እና ማደራጀትም የአስራ ሁለቱ ሀላፊነት ነው፣ እንዲህም በሚል ራዕይ በመስማማት፥
፶፱ በፅዮን ምድር ውስጥ ለክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ የቤተክርስቲያኗን ጉዳይ በሚመለከት ከቤተክርስቲያኗ ህግጋት ተጨማሪ—
፷ እውነት እላችኋለሁ ይላል የሰራዊት ጌታ፣ የሽማግሌ ሀላፊነት ያላቸውን የሚመራ የሽማግሌዎች አመራር ያስፈልጋል፤
፷፩ እና ደግሞም የካህን ሀላፊነት ያላቸውን የሚመራ ካህን ያስፈልጋል፤
፷፪ እና ደግሞም፣ በዚህም አይነት፣ የመምህራን ሀላፊነት ያላቸውን የሚመራ መምህር፣ ደግሞም ዲያቆናት—
፷፫ ስለዚህ፣ ከዲያቆን እስከ መምህር፣ እና ከመምህር እስከ ካህን፣ እና ከካህን እስከ ሽማግሌ፣ በቤተክርስቲያኗ ቃል ኪዳኖች እና ትእዛዛት መሰረት በተለያዩ ሀላፊነቶች እንዲመደቡ ያስፈልጋል።
፷፬ ከዚያም ከሁሉም በላይ የሆነው፣ የታላቅ ክህነት ይመጣል።
፷፭ ስለዚህ፣ ከታላቅ ክህነት ፕሬዘደንት አንዱ የክህነት ባለስልጣናትን ለመምራት መመደብ አለበት፣ እና እርሱም የቤተክርስቲያኗ የታላቅ ክህነት ፕሬዘደንት ተብሎ ይጠራል፤
፷፮ ወይም፣ በሌላ ቃላትም፣ በቤተክርስቲያኗ ታላቅ ክህነት በበላይነት የሚመራ ሊቀ ካህን ይጠራል።
፷፯ ከዚህም እጆችን በመጫን በቤተክርስቲያኗ ላይ ስርዓቶች እና በረከቶች የሚከናወኑበት ይመጣሉ።
፷፰ ስለዚህ፣ የኤጲስ ቆጶስ ሀለፊነት ከዚህ ጋር እኩል አይደለም፤ የኤጲስ ቆጶስ ሀለፊነት የስጋዊ ነገሮችን ለማስተዳደር ነውና፤
፷፱ ይህም ቢሆን፣ የአሮን እውነተኛ ተወላጅ ካልሆነ በስተቀር፣ ኤጲስ ቆጶስ ከታላቅ ክህነት መመረጥ አለበት፤
፸ የአሮን እውነተኛ ተወላጅ ካልሆነ በስተቀር የዚህን ክህነት ቁልፍ ለመያዝ አይችልምና።
፸፩ ይህም ቢሆን፣ ሊቀ ካህን፣ ወይም እንደ መልከ ጼዴቅ አይነት ስርዓት፣ በእውነት መንፈስ እያወቃቸው፣ በስጋዊ ነገሮች ለማስተዳደር መለያየት ይቻላል፤
፸፪ ዳግሞም ከቤተክርስቲያኗ ሽማግሌዎች መካከል በመረጣቸው ወይም በሚመርጣቸው አማካሪዎቹ እርዳታ፣ የእስራኤል ዳኛ እንዲሆን፣ የቤተክርስቲያኗን ጉዳይ እንዲያከናውን፣ በሚተላለፉት ላይ በፊቱ በሚቀርበው ምስክር በህግጋት መሰረት ለፍርድ ይቀመጣል።
፸፫ ይህም የአሮን እውነተኛ ተወላጅ ባይሆንም እንደ መልከ ጼዴቅ ክህነት ወደ ታላቅ ክህነት የተሾመው ኤጲስ ቆጶስ ሀላፊነት ነው።
፸፬ የፅዮን ድንበር አድጋ እና ሌላ ኤጲስ ቆጶስ ወይም ዳኛ በፅዮን ወይም በሌላ ቦታ ውስጥ እንዲኖር አስፈላጊ እስኪሆን ድረስ፣ እንደዚህም ዳኛ እንዲሁም በፅዮን ነዋሪዎች ወይም በፅዮን ካስማዎች ወይም ለአገልግሎት በሚመደብበት በማንኛውም በቤተክርስቲያኗ ቅርንጫፍ ውስጥ መካከል ዋና ዳኛ ይሆናል።
፸፭ እና ሌሎች ኤጲስ ቆጶሳት እስከተመደቡም ድረስ በዚህ ሀላፊነት ውስጥ ይሰራሉ።
፸፮ ነገር ግን የአሮን እውነተኛ ተወላጅ ለዚህ ክህነት አመራር፣ ለዚህ አገልግሎት ቁልፎች፣ እንደ መልከ ጼዴቅ ክህነት ስርዓት የታላቅ ክህነት ፕሬዘደንት ለፍርድ ከሚመጣበት ጊዜ በስተቀር ያለአማካሪዎች በራሱ ሀሳብ በኤጲስ ቆጶስ ሀላፊነት ለመስራት፣ በእስራኤል ውስጥም በፍርድ ለመቀመጥ ህጋዊ መብት አለው።
፸፯ እና የእነዚህ ሸንጎዎች ውሳኔም እንዲህ ከሚለው ትእዛዝ ጋርም የሚስማማ ይሆናል፥
፸፰ ዳግሞም እውነት እላችኋለሁ፣ ለቤተክርስቲያኗ በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች፣ እና ለቤተክርስቲያኗ በጣም አስቸጋሪ የህግ ጉዳዮች በኤጲስ ቆጶስ ወይም በዳኛ ውሳኔ በቂ ሆኖ ካልተገኘ፣ ወደ ቤተክርስቲያኗ ሸንጎ፣ በታላቅ ክህነት አመራር ፊት ይተላለፋል እና ይወሰዳልም።
፸፱ እና የታላቅ ክህነት ሸንጎ አመራር ሌሎች ሊቀ ካህናትን፣ እንዲሁም አስራ ሁለትን፣ እንደ አማካሪዎች እንዲረዱ ለመጥራት ሀይል አለው፣ እና እንደዚህም የታላቅ ክህነት ሸንጎ አመራር እና አማካሪዎቹ በምስክሮቹ ላይ በቤተክርስቲያኗ ህግጋት መሰረት ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሀይል አላቸው።
፹ እና ከዚህ ውሳኔ በኋላ በጌታ ፊት ይህ ደግሞም አይታሰብም፤ ይህም የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ሸንጎ ነውና፣ እና በመንፈሳዊ ጉዳዮች ውዝግብ ላይም የመጨረሻ ውሳኔን ይሰጣሉና።
፹፩ በቤተክርስቲያኗ አባል ሆኖ ከቤተክርስቲያኗ ሸንጎ ውጪ የሆነ ማንም የለም።
፹፪ እና የታላቅ ክህነት ፕሬዘደንት እስከተላለፈ ድረስ፣ በታላቅ ክህነት ፕሬዘደንት አስራ ሁለት አማካሪዎች በሚረዱት በቤተክርስቲያኗ ዋና ሸንጎ ፊት ይቀርባል፤
፹፫ እና በእርሱ ላይ የሚደረጉት ውሳኔዎች እርሱን በሚመለከት ላለው ውዝግብ መጨረሻ ይሆናል።
፹፬ እንደዚህም፣ በእውነት እና በፅድቅ መሰረት ሁሉም ነገሮች በስርዓትና በክብር በፊቱ ይደረጉ ዘንድ፣ ከእግዚአብሔር ፍትህና ህግጋት ውጪ የሚሆን ማንም የለም።
፹፭ ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ የዲያቆንነት ስልጣን ፕሬዘደንት ሀላፊነት አስራ ሁለት ዲያቆናትን ለመምራት፣ ከእነርሱም ጋር በሸንጎ ለመቀመጥ፣ እና፣ በተሰጡት ቃል ኪዳኖች መሰረት እርስ በራስ በመተናነጸት ሀላፊነታቸውን ለማስተማር ነው።
፹፮ ደግሞም የመምህርነት ስልጣን ፕሬዘደንት ሀላፊነት ሀያ አራት መምህራንን ለመምራት፣ ከእነርሱም ጋር በሸንጎ ለመቀመጥ፣ በቃል ኪዳኖች እንደተሰጠው የስልጣናቸውን ሀላፊነት ለማስተማር ነው።
፹፯ ደግሞም የአሮናዊ ክህነት ፕሬዘደንት ሀላፊነት አርባ ስምንት ካህናትን ለመምራት፣ እና ከእነርሱም ጋር በሸንጎ ለመቀመጥ፣ በቃል ኪዳኖች እንደተሰጠም የስልጣናቸውን ሀላፊነቶች ለማስተማር ነው—
፹፰ ይህም ፕሬዘደንት ኤጲስ ቆጶሱ ይሁን፤ ከዚህ ክህነት ሀላፊነቶች አንዱ ይህ ነውና።
፹፱ ዳግም፣ የሽማግሌዎች ስልጣን ፕሬዘደንት ሀላፊነት ዘጠና ስድስት ሽማግሌዎችን ለመምራት፣ እና ከእነርሱም ጋር በሸንጎ ለመቀመጥ፣ እና በቃል ኪዳናት መሰረት ለማስተማር ነው።
፺ ይህ አመራር ከሰባው ልዩ የሆነ ነው፣ እና በአለም ሁሉ ለማይጓዙት የታቀደ ነው።
፺፩ ደግሞም፣ የታላቅ ክህነት ፕሬዘደንት ሀላፊነት ቤተክርስቲያኗን ሁሉ ለመምራት፣ እና እንደ ሙሴ አይነት ለመሆን ነው—
፺፪ እነሆ፣ አዎን፣ የቤተክርስቲያኗ የበላይ ለሚሆን የሚሰጡትን የእግዚአብሔርን ስጦታዎች ሁሉ የያዘ ባለራዕይ፣ ገላጭ፣ ተርጓሚ፣ እና ነቢይ ይሆን ዘንድይህም ጥበብ ነው።
፺፫ እና ከሰባዎቹ መካከል ተመርጠው በሰባት ፕሬዘደንቶች ይመሩ ዘንድ፣ ይህም ስለሰባዎች ስርዓት በተሰጠው ራዕይ መሰረት ነው፤
፺፬ እና ከእነዚህ ፕሬዘደንቶች መካከል ሰባተኛው ፕሬዘደንት ስድስቱን የሚመራ ይሁን፤
፺፭ እና እነዚህ ሰባት ፕሬዘደንቶችም አባል ከሆኑባቸው ከመጀመሪያዎቹ ሰባዎች ተጨማሪ ሌሎች ሰባዎችን ይምረጡ፣ እና እነርሱንም የሚመሩ ይሁኑ፤
፺፮ እና ደግሞ በአስፈላጊው የወይን ስፍራ አገልግሎት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ ሌሎች ሰባዎችም፣ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት ይመረጡ።
፺፯ እና እነዚህ ሰባዎች፣ መጀመሪያ ለአህዛብ እና ደግሞም ለአይሁዶች፣ ተጓዥ አገልጋዮች ናቸው።
፺፰ በአስራ ሁለቱ ወይም በሰባዎች አባል ያልሆኑት፣ የቤተክርስቲያኗ ሌሎች ሀላፊዎች ግን፣ ምንም እንኳን እንደዚህ አይነት ከፍተኛ ሀላፊነትና ስልጣናት በቤተክርስቲያኗ ቢኖራቸውም፣ በህዝብ ሁሉ መካከል ለመጓዝ ሀላፊነት የላቸውም፣ ነገር ግን ጉዳዮቻቸው እንደሚፈቅድላቸው ይጓዙ።
፺፱ ስለዚህ፣ አሁን እያንዳንዱም ሰው ተግባሩን፣ በተመደበበት ሀላፊነትም በሙሉ ትጋት መስራትን ይማር።
፻ ሰነፍ የሆነው እርሱ ለመቆም ብቁ ሆኖ አይቆጠርም፣ እና ሀላፊነቱን የማይማር እና እራሱን ተቀባይ አድርጎ የማያሳይ ለመቆም ብቁ ሆኖ አይቆጠርም። እንዲህም ይሁን። አሜን።