ክፍል ፳
ስለቤተክርስቲያን አደረጃጀት እና አስተዳደር፣ በፈየት፣ ኒው ዮርክ ወይም በዚያ አካባቢ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። የዚህ ራዕይ ክፍሎች የተሰጡት በበጋ ፲፰፻፳፱ (እ.አ.አ.) አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። በዚያ ጊዜ አንቀጾች እና ቃል ኪዳኖች ተብሎ የሚታወቀው ሙሉ ራዕዩ የተመዘገበው በሚያዝያ ፮፣ ፲፰፻፴ (ቤተክርስቲያኗ በተደራጀችበት ቀን) ሳይሆን አይቀርም። ነቢዩ እንደጻፈው፥ “በትንቢት እና ራዕይ መንፈስ ከእርሱ [ከኢየሱስ ክርስቶስ] የሚከተለውን ተቀበልን፤ ይህም ብዙ መረጃዎችን ብቻ ሳይሆን የሰጠን፣ ነገር ግን እንደ እርሱ ፈቃድ እና ትእዛዝ መቼ የእርሱን ቤተክርስቲያን ዳግም በምድር ላይ ማቋቋም እንደሚገባን ጠቁሞናል።”
፩–፲፮፣ መፅሐፈ ሞርሞን የኋለኛው ቀን ስራን መለኮታዊነት ያረጋግጣል፤ ፲፯–፳፰፣ የፍጥረት፣ የውድቀት፣ የኃጢአት ክፍያ፣ እናም የጥምቀት ትምህርቶች ተረጋግጠዋል፤ ፳፱–፴፯፣ ንስሀ፣ መፅደቅን፣ ቅድስናን፣ እና ጥምቀትን የሚያስተዳድሩ ህጎች ተገልጸዋል፤ ፴፰–፷፯፣ የሽማግሌዎች፣ የካህናት፣ የመምህራን፣ እናም የዲያቆናት ሀላፊነቶች በአጭር ተጠቃለዋል። ፷፰–፸፬፣ የአባላት ሀላፊነቶች፣ ልጆችን መባረክ፣ እና ጥምቀት የሚከናወንበትም ዘዴዎች ተገልጠዋል፤ ፸፭–፹፬፣ የቅዱስ ቁርባን ጸሎቶች እና የቤተክርስቲያን አባልነትን ማስተዳደሪያ ደንቦች ተሰጥተዋል።
፩ በእነዚህ በኋለኞቹ ቀናት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን መነሳት፣ ጌታችንና አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ አንድ ሺ ስምንት መቶ ሰላሳ አመት ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኗም በእግዚአብሔር ፈቃድ እና ትእዛዝ ሚያዝያ በሚባለው በአራተኛው ወር በስድስተኛው ቀን ለአገራችን ህግ ዘወትር ተስማሚ በሚሆን ሁኔታ ተደራጅታ ተመስርታለች—
፪ እነዚህም ትእዛዛት የተሰጡት በእግዚአብሔር ለተጠራው፣ እና የዚህች ቤተክርስቲያን መጀመሪያ ሽማግሌ በመሆን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ እንዲሆን ለተሾመው ለጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ ነበር፤
፫ እናም በእግዚአብሔር፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሀዋሪያ፣ የዚህች ቤተክርስቲያን ሁለተኛ ሽማግሌ እንዲሆን ለተጠራው እና በእርሱ እጅ ለተሾመው ለኦሊቨር ካውድሪ ነው፤
፬ ይህም እንደጌታችን እና አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ነው፣ ለእርሱም አሁንም ለዘለዓለምም ክብር ይሁን። አሜን።
፭ ይህ የመጀመሪያው ሽማግሌ የኃጢአት ስርየት እንደተቀበለ በእውነት ከተገለጸለት በኋላ፣ በአለም ከንቱነት ውስጥ ደግሞም ተጠላለፈ፤
፮ ነገር ግን ንስሀ ከገባ፣ እናም በእምነት እራሱን በቅንነት ትሑት ካደረገ በኋላ፣ መልኩ እንደ መብረቅ ብሩህ፣ እናም ልብሱ ከንጣቶች ሁሉ በላይ ንጹ እና ነጭ በነበረው ቅዱስ መልአክ በኩል እግዚአብሔርም አገለገለው፤
፯ እና ያነሳሱትን ትዕዛዛትንም ሰጠው፤
፰ እናም መፅሐፈ ሞርሞንን ለመተርጎም ቀደም ብሎ በተዘጋጁት መንገዶች በኩል ከላይ ሀይልን ሰጠው፤
፱ ይህም የወደቁትን ሰዎች መዝገብ፣ እናም ለአህዛብና ለአይሁድ ሁሉ ሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የያዘ ነው፤
፲ በሚያነሳሳ መንፈስ የተሰጠ፣ እናም በመላእክት አገልግሎት ለሌሎችም የተረጋገጠ፣ እና በእነርሱም ለአለምም የተገለጸ ነው—
፲፩ ይህ ቅዱሳን መጻህፍት እውነት እንደሆነ እናም በዚህ እድሜና ዘመን እንደ ቀደሙት ትውልዶችም እግዚአብሔር የእርሱን ቅዱስ ስራ እንዲያከናውኑ ሰዎችን እንደሚያነሳሳ እና እንደሚጠራ በማረጋገጥ ነው።
፲፪ በዚህም እርሱ ትላንትናም ዛሬም እናም ለዘለአለም አንድ አይነት አምላክ እንደሆነ በማሳየት ነው። አሜን።
፲፫ ስለዚህም፣ በጣም ታላቅ ምስክርነቶች ስላሏቸው፣ ዓለም ሁሉ፣ እንዲሁም ከዚህ በኋላ ወደዚህ እውቀት የሚመጡት ሁሉ፣ በእነርሱ ይፈረድባቸዋል።
፲፬ እናም በእምነት የሚቀበሉት ሁሉ፣ እናም ፅድቅን የሚሰሩ፣ የዘለአለማዊ ህይወት አክሊልን ይቀበላሉ፤
፲፭ ነገር ግን ባለማመን ልባቸውን የሚያደነድኑ፣ እናም ለሚያስወግዱት፣ ወደ ኩነኔያቸው ይለወጣል—
፲፮ ጌታ እግዚአብሔር ተናግሮታልና፣ እናም እኛ የቤተክርስቲያኗ ሽማግሌዎች፣ በላይ ያለውን የከበረ ግርማዊ ቃላቶቹን ሰምተናል እናም ምስክርነታችንን እንሰጣለን፣ ለእርሱም ክብር ከዘለአለም እስከ ዘለአለም ይሁን። አሜን።
፲፯ በእነዚህ ነገሮች መጨረሻ የሌለውና ዘለአለማዊ የሆነው፣ ሰማይና ምድርን እናም በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረ ከዘለአለም እስከዘለአለም ያው የሆነ የማይቀየር አምላክ እግዚአብሔር በሰማይ ውስጥ እንደሚገኝ እናውቃለን፤
፲፰ እርሱም ሰውን፣ ወንድና ሴትን፣ በመልኩ እና በአምሳሉ ፈጠራቸው፤
፲፱ እናም እውነተኛውን እና ህያው የሆነውን እግዚአብሔርን ብቻ እንዲወዱና እንዲያገለግሉ እናም የሚያመልኩት እርሱን ብቻ እንዲሆንም ትእዛዛትን ሰጣቸው።
፳ ነገር ግን እነዚህን ቅዱስ ህጎችን በመተላለፍ ሰው ስጋዊና አጋንንታዊ ሆነ፣ እናም የወደቀ ሆኑ።
፳፩ ስለዚህ፣ ለእርሱ በሰጠው በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ስለእርሱ እንደተጻፈው፣ ሁሉን የሚገዛው እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ሰጠ።
፳፪ እርሱም በፈተናዎች ተሰቃየ ነገር ግን እራሱን አሳልፎ አልሰጠም።
፳፫ እርሱም ተሰቀለ፣ ሞተ፣ እናም በሶስተኛውም ቀን ዳግም ከሞት ተነሳ፤
፳፬ እናም በአብ ቀኝ በኩል ለመቀመጥ፣ እና እንደአብ ፈቃድ በፍጹም ሀይል ለመንገስ ወደሰማይ አረገ፤
፳፭ ይህም በእርሱ ቅዱስ ስም አምነው እና ተጠምቀው፣ እናም እስከመጨረሻም ድረስ በእምነት የጸኑት ሁሉ ይድኑ ዘንድ ነው—
፳፮ በስጋ ከመጣበት ከመካከለኛው ዘመን በኋላ የሚያምኑት ብቻ ሳይሆን፣ ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ፣ እንዲሁም ከመምጣቱ አስቀድሞ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተነሳስተው ቅዱሳን ነቢያት ስለእርሱ በሁሉም ነገሮች በመመስከር በተናገሯቸው ቃላት ያመኑት ሁሉ ዘለአለማዊ ህይወትን ያገኛሉ፣
፳፯ ስለአብና ወልድ በሚመሰክረው መንፈስ ቅዱስ በኩል በሚመጡት በእግዚአብሔር ስጦታዎች እና ጥሪዎች የሚያምኑት ከእርሱ በኋላ የሚመጡትም እንዲሁም ይሆንላቸዋል፤
፳፰ አብ፣ ወልድ፣ እና መንፈስ ቅዱስ መጨረሻ የሌላቸውና ዘለአለማዊ አንድ አምላክ ናቸው። አሜን።
፳፱ እናም ሁሉም ሰው ንስሀ መግባትና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ማመን፣ እናም አብን በእርሱ ስም ማምለክ፣ እናም በስሙ እስከፍጻሜው መጽናት እንዳለባቸው እናውቃለን፣ ወይም በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መዳን አይችሉም።
፴ እናም በጌታችንና አዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በኩል የምናገኘው ፅድቅ ፍትሀዊ እና እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለን፤
፴፩ እናም በጌታችንና አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በኩል የሚገኘው ቅድስና በሙሉ ሀይላቸው፣ አዕምሮአቸው፣ እናም ጉልበታቸው እግዚአብሔርን ወድደው ለሚያገለግሉት ሁሉ ትክክል እና እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለን።
፴፪ ነገር ግን ሰው ከጸጋ ወድቆ ከህያው እግዚአብሔር ለመለየት የሚያስችለው ሁኔታም አለ፤
፴፫ ስለዚህ በፈተና እንዳይወድቁ፣ ቤተክርስቲያኗ ትጠንቀቅ እና በየጊዜውም ትጸልይ፤
፴፬ አዎን፣ እንዲሁም የተቀደሱትም ቢሆኑም እንኳን ይጠንቀቁ።
፴፭ እናም እነዚህ ነገሮች እውነተኛ እና ከዮሐንስ ራዕይ ጋር የሚግባቡ፣ ከቅዱስ መጻህፍቶችም፣ ወይም በመንፈስ ቅዱስ ስጦታና ሀይል፣ በእግዚአብሔር ድምጽ፣ ወይም በመላእክት አገልግሎት በኩል በሚመጡት የእግዚአብሔር ራዕዮች ላይም የማይጨምሩ እና የማይቀንሱ እንደሆኑ እናውቃለን።
፴፮ እናም ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሯል፤ እናም ክብር፣ ሀይል፣ እናም ግርማ ለቅዱስ ስሙ አሁን እናም ለዘለአለም ይሁን። አሜን።
፴፯ ደግሞም፣ የጥምቀትን ስርዓት በተመለከተ ለቤተክርስቲያኗ በትእዛዝ መልክ የተሰጠ—ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ትሁት የሚያደርጉ፣ እናም ለመጠመቅ ከፈለጉ እናም በተሰበረ ልብ እና በተዋረደ መንፈስ ከመጡ፣ እናም ከቤተክርስቲያኗ ፊት በእውነት ለኃጢአታቸው ሁሉ ንስሀ እንደገቡ ምስክር ካደረጉ፣ እናም እርሱን እስከመጨረሻ ድረስ ለማገልገል ፈቃድ ኖሯቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳቸው ለመውሰድ ፈቃደኛ ከሆኑ፣ እናም የኢየሱስ ክርስቶስን መንፈስ ለኃጢአት ስርየት እንደተቀበሉ በስራቸው በእውነት ካሳዩ፣ ወደ እርሱም ቤተክርስቲያን በጥምቀት ይወሰዳሉ።
፴፰ የሽማግሌዎች፣ የካህናት፣ የመምህራን፣ የዲያቆናት፣ እናም የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት ሀላፊነት። ሐዋርያ ሽማግሌ ነው፣ እናም ማጥመቅም ለእርሱ የተሰጠ ጥሪ ነው፤
፴፱ እናም ሌሎች ሽማግሌዎችን፣ ካህናትን፣ መምህራንን፣ እናም ዲያቆናትን ለመሾም፤
፵ እናም የክርስቶስ ስጋና ደም ምልክቶች የሆኑትን ወይንን እና ዳቦን መባረክ—
፵፩ እና ቅዱሳት መጻህፍቱ እንደሚሉትም፣ ለእሳትና ለመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እጆቻቸውን በመጫን ወደ ቤተክርስቲያኗ የተጠመቁትን ማጽናት፤
፵፪ እናም ማስተማር፣ ማብራራት፣ አጥብቆ መምከር፣ ማጥመቅ፣ እናም ቤተክርስቲያኗን መጠበቅ፤
፵፫ እናም እጆችን በመጫን ቤተክርስቲያኗንም ማጽናት፣ እናም መንፈስ ቅዱስንም መስጠት፤
፵፬ እናም በስብሰባዎች ሁሉ መሪነትን መያዝ ነው።
፵፭ ሽማግሌዎችም እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝና ራዕይ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ስብሰባዎችን ማስተዳደር አለባቸው።
፵፮ የካህን ሀላፊነት መስበክ፣ ማስተማር፣ ማብራራት፣ አጥብቆ መምከር፣ እናም ማጥመቅ፣ እናም ቅዱስ ቁርባንን መባረክ ነው፣
፵፯ እናም የእያንዳንዱን አባል ቤትን መጎብኘት፣ እናም በሚስጥር እና በድምፅ እንዲጸልዩ እና የቤተሰብ ሀላፊነታቸውን እንዲያከናውኑ በጥብቅ ማበረታት ነው።
፵፰ ሌሎች ካህናትን፣ መምህራንን፣ እናም ዲያቆናትን መሾምም ይችላል።
፵፱ እናም ሽማግሌ በሌለበትም ጊዜ ስብሰባዎችን ይመራል።
፶ ሽማግሌ ባለበት ጊዜ ግን፣ የእርሱ ተግባር መስበክ፣ ማስተምር፣ ማብራራት፣ አጥብቆ መምከር፣ እናም ማጥምቅ፣
፶፩ እናም የእያንዳንዱን አባል ቤት መጎብኘት፣ እናም በሚስጥር እና ድምጻቸውን አውጥተው እንዲጸልዩ እና የቤተሰብ ሀላፊነታቸውን እንዲያከናውኑ ማበርታት ብቻ ነው።
፶፪ አስፈላጊ ሲሆን ካህን በእነዚህ ሀላፊነቶቹ ሁሉ ሽማግሌውን ይረዳል።
፶፫ የመምህሩ ሀላፊነትም ቤተክርስቲያኗን ዘወትር መጠበቅ፣ እና እነርሱን መርዳትና ማጠንከር ነው፤
፶፬ እናም ምንም ጥፋት በቤተክርስቲያኗ እንዳይኖር፣ እንዲሁም አባላቶቿ እርስ በራሳቸው እንዳይከፋፉ፣ እንዳይዋሹ፣ እንዳይተማሙ፣ ወይም ክፉ እንዳይነጋገሩ መጠበቅ፤
፶፭ እናም ቤተክርስቲያንም በየጊዜው እንዲሰበሰቡ ማድረግ፣ እናም አባላቶቿ ሀላፊነታቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ ነው።
፶፮ ሽማግሌ ወይም ካህን በማይኖሩበት ጊዜም የስብሰባውን መሪነት ይወስዳል—
፶፯ እናም አስፈላጊ በሚሆንም ጊዜ፣ በቤተክርስቲያኗ ሀላፊነቶቹ ሁሉ ዲያቆናት ይረዱታል።
፶፰ ነገር ግን መምህራንም ሆኑ ዲያቆናት የማጥመቅ፣ ቅዱስ ቁርባንን የመባረክ፣ ወይም እጆችን የመጫን ስልጣን የላቸውም፤
፶፱ ነገር ግን እነርሱ ማስጠንቀቅ፣ ማብራራት፣ ማበረታታት፣ እናም ማስተማር፣ እናም ሁሉንም ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ መጋበዝ አለባቸው።
፷ እያንዳንዱም ሽማግሌ፣ ካህን፣ መምህር፣ ወይም ዲያቆን ከእግዚአብሔር በተሰጠው ስጦታዎች እና ጥሪዎች መሰረት ይሾም፤ እናም እርሱን በሚሾመው ውስጥ በሚገኝ መንፈስ ቅዱስ ሀይልም ይሾማል።
፷፩ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙት ሽማግሌዎችም በሶስት ወር አንድ ጊዜ፣ ወይም ጉባኤው እንደሚመራውና እንደሚቀጥረው በጉባኤ ይሰብሰቡ፤
፷፪ እናም ይህም ጉባዔ በወቅቱ መሰራት ያለባቸውን ማንኛውም የቤተክርስቲያኗን ስራ መስራት አለበት።
፷፫ ሽማግሌዎች አባል ከሆኑበት ቤተክርስቲያን ወይም ከጉባዔው በምርጫ አማካይነት ከሌሎች ሽማግሌዎች ፈቃዳቸውን ይቀበሉ።
፷፬ በካህን የተሾመው እያንዳንዱም ካህን፣ መምህር፣ ወይም ዲያቆንም የምስክር ወረቀት በተሾመበት ጊዜ ከካህኑ መውሰድ ይችላል፣ ይህም የምስክር ወረቀት ለሽማግሌው በሚያቀርብ የጥሪውን ሀላፊነት ለማከናወን የሚያስችለው ስልጣን ይሰጠዋል፣ ወይም ይህን ከጉባኤ ሊቀበለው ይችላል።
፷፭ የዚህ ቤተክርስቲያን ቅርንጫፍ በተደራጀበት ስፍራ፣ ያለቤተክርስቲያኗ ምርጫ ማንም ሰው በቤተክርስቲያን ሀላፊነት አይሾምም፤
፷፮ ነገር ግን የቤተክርስቲያኗ ቅርንጫፍ ባለመኖሩ ምርጫ ሊጠራ በማይቻልበት ስፍራ፣ የሽማግሌዎች አመራር፣ ተጓዥ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ከፍተኛ አማካሪዎች፣ ሊቀ ካህናት፣ እና ሽማግሌዎች የመሾም መብት ሊኖራቸው ይችላል።
፷፯ እያንዳንዱ የታላቅ ክህነት ፕሬዘደንት (ወይም የካህናት አመራር)፣ ኤጲስ ቆጶስ፣ ከፍተኛ አማካሪ፣ እናም ሊቀ ካህናት በከፍተኛ ሸንጎ ወይም በአጠቃላይ ጉባኤ አመራር መሾም አለበት።
፷፰ አባላት ከተጠመቁ በኋላ ያለባቸው ሀላፊነት—ቅዱስ ቁርባኑን ከመውሰዳቸውና ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በመጫን ከሚያጸኗቸው በፊት፣ ሽማግሌዎች ወይም ካህናት ሰዎቹ እስኪገባቸው ድረስ ስለ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን እንዲያብራሩላቸው ብቁ ጊዜን ማግኘት አለባቸው፣ ይህም ሁሉም ነገሮች በዕቅድ ይደረጉ ዘንድ ነው።
፷፱ እናም አባላቶቿ በቤተክርስቲያኗ ፊት እናም በሽማግሌዎች ፊት በአምላካዊ አካሄድ እና ንግግር ብቁ መሆናቸውን ያሳዩ፣ በጌታ ፊት በቅድስና በመሄድ ከቅዱስ መፅሀፍቶች ጋር የሚጣጣሙ ስራዎች እና እምነት ይኑራቸው።
፸ ልጆች ያሏቸው እያንዳንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላትም ልጆቻቸውን በቤተክርስቲያኗ ፊት ወደ ሽማግሌዎች ያምጡ፣ እነርሱም እጆቻቸውን በክርስቶስ ስም ልጆቹ ላይ ይጫኑ፣ እናም በእርሱ ስም ይባርኳቸው።
፸፩ በተጠያቂነት እድሜ ላይ ካልደረሰ፣ እናም ንስሀ ለመግባት ችሎታ ከሌለው፣ ማንም ሰው በክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል መሆን አይችልም።
፸፪ ንስሀ ለገቡት ጥምቀት ከእዚህ በሚከተለው ስነስርዓት ሁኔታ መሰጠት አለበት፥
፸፫ በእግዚአብሔር ተጠርቶ ለማጥመቅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣን ያለው ሰው፣ እራሱን ወይም እራሷን ለጥምቀት ካቀረበው ወይም ካቀረበች ሰው ጋር ወደ ውሀው አብሮ ይገባል፣ እናም እርሱን ወይም እርሷን በስም በመጥራት ይህን ይላል፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠኝ ስልጣን መሰረት፣ በአብ፣ በወልድ፣ እናም በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠምቅሀለሁ (አጠምቅሻለሁ)። አሜን።
፸፬ ከዚያም እርሱን ወይም እርሷን ውሀ ውስጥ ያጥልቅ፣ እና ከውሀ ውስጥም በድጋሚ ያውጣ።
፸፭ ቤተክርስቲያኑም ዘወትር በአንድነት በመገናኘት ጌታ ኢየሱስን ማስታወስ ዳቦና ወይንን መካፈላቸው አስፈላጊ ነው፤
፸፮ እናም ሽማግሌ ወይም ካህን ይህንንም ያድርግ፤ እና በዚህ መንገድም ይህን ያደርጋል—ከቤተክርስቲያኑ ጋር ተንበርክኮና በተረጋጋ ጸሎት ይህን በማለት አብን ይጥራ፥
፸፯ አቤቱ ዘለአለማዊ አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ ይህንን ዳቦ ለሚቋደሱት ነፍሳት ሁሉ የልጅህን አካል በማሰብ እንዲበሉት እና፣ አቤቱ ዘለአለማዊ አባት እግዚብሔር ሆይ፣ እነርሱ የልጅህን ስም በላያቸው ላይ ለመውሰድ ፈቃደኞች መሆናቸውን፣ እና ሁልጊዜ እርሱን እንደሚያስታውሱና እርሱ የሰጣቸውን ትእዛዛት እንደሚጠብቁ ለአንተም ይመሰክሩ ዘንድ፣ በዚህም የእርሱ መንፈስ ሁልጊዜ እንዲኖራቸው ትባርከውና ትቀድሰው ዘንድ በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንጠይቅሀለን። አሜን።
፸፰ ወይኑን የሚያስተላልፉበት መንገድም ይህ ነው—ኩባያውን ወስዶ እንዲህ ይላል፥
፸፱ አቤቱ ዘለዓለማዊ አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ ይህንን ወይን የሚጠጡት ነፍሳት ሁሉ ለእነርሱ የፈሰሰውን የልጅህን ደም በማስታወስ ያደርጉት ዘንድ፣ ሁልጊዜ እርሱን እንደሚያስታውሱ ለአንተም፣ አቤቱ ዘለዓለማዊ አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ ይመሰክሩ ዘንድ፣ በዚህም የእርሱ መንፈስ ሁልጊዜ እንዲኖራቸው፣ ትባርከውና ትቀድሰው ዘንድ በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንጠይቅሀለን። አሜን።
፹ በኃጢአት የሚወድቅ ወይም በጥፋት የሚወሰዱ ማንም የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል፣ ቅዱሳት መጻሀፍቱ እንደሚመሩት ይቀጣሉ።
፹፩ አንድ ወይም ብዙ መምህራንን በቤተክርስቲያኗ ሽማግሌዎች ወደሚደረገው ብዙ ጉባኤዎች ላይ እንዲገኙ መላክም የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ክፍል የሆኑ ቤተክርስቲያናት ሀላፊነትም ነው፣
፹፪ በየወቅቱ የቤተክርስቲያኗ አባላት ስም ዝርዝር ሌሎች ሽማግሌዎች በየጊዜው በሚሾሟቸው በአንዱ ሽማግሌ በመዝገብ ይጠበቅ ዘንድ ሲመጡም ካለፈው ጉባኤ በኋላ ራሳቸውን የቤተክርስቲያኗ አባላት ጋር አንድ ያደረጉትን ሰዎች ስም ይዘው ይምጡ፤ ወይም በአንዳንድ ካህናት እጅም ይላኩ፤
፹፫ ደግሞም፣ ማናቸውም ከቤተክርስቲያኑ እንዲወጡ ቢደረጉም፣ ስማቸው ከቤተክርስቲያኑ ስም ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዙ ለማድረግ ነው።
፹፬ ወደ ማይታወቁበት ስፍራ አባላት ከሚኖሩበት ቤተክርስቲያን አካባቢ ሲሄዱም፣ ጥሩ የቤተክርስቲያን አባል እንደሆኑ የሚዘረዝር የምስክር ወረቀት በደብዳቤ ይዘው መሄድ ይችላሉ፣ ይህ የምስክር ወረቀት ደብዳቤውን የሚወስደው ሰው ከሽማግሌው ወይም ከካህኑ ጋር የሚተዋወቅ ከሆነ፣ ማንኛውም ሽማግሌ ወይም ካህን ሊፈርም ይችላል፣ ወይም ይህም በመምህራን ወይም በዲያቆናት መፈረም ይችላል።